የእንስሳትን ጉዳት ለመቀነስ ያግዛል የተባለው የመኖ ማምረቻ ማሽን

Wednesday, 13 April 2016 12:18

በሀገራችን በዝናብ እጥረት ሳቢያ በአንዳንድ ቦታዎች በተከሰተው ድርቅ በእንስሳት ላይ ሞትን አስከትሏል። በድርቁ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚሆን ደራሽ የተቀናጀ ግብርናና ሁለገብ የልማት ሥራ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ከስኳር ፋብሪካ ተረፈ ምርቶች የተቀናበረ የእንስሳት መኖ ሊያመርት መሆኑ ተገለፀ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ለምግብ እጥረትና ለከፋ ችግር መዳረጋቸው ይታወሳል። በዚህም ሳቢያ ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚገኙ እንስሳትም ላይ እጅግ የከፋ ችግር በመከሰቱም ከደጋማዎቹ አካባቢዎቻችን አልፎ ተርፎም ከውጭ ሀገራት የእንስሳት መኖ በማስመጣት ችግሩን ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑም ይታወቃል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍና ከደጋማዎቹ አካባቢዎቻችንና ከውጭ ይመጣ የነበረውን የእንስሳት መኖ ለመተካትና አምርቶ ለማቅረብ የድርጅቱ የሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር በሆኑት በካፒቴን መኮንን ካብትህይመር እዚሁ ሀገራችን የመጀመሪያ በሆነ የፈጠራ ባለቤትነት የተሰሩ ማሽኖች የተቀናበሩ የሙከራ ምርቶች በእንስሳትና አሳ ሐብት ሚኒስቴር የእንስሳት እርባታና መኖ ልማት ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር ገ/እግዚአብሔር ገ/ዮሀንስ የክብር እንግድነት፣ በአቶ አታክልቲ ተስፋዬ በስኳር ኮርፖሬሽን ኮርፖሬት ፕላኒንግ ሥራ አስፈፃሚና በአቶ ተክላይ ገ/አምላክ በስኳር ኮርፖሬሽን የተጓዳኝ ምርቶች ሥራ አስፈፃሚ በተገኙበት የመጨረሻው የሙከራ ምርት ተመርቷል። ለዚህ ተግባር የሚሆኑ 4 ማቀናበሪያና 1 መከረታተፊያ ማሽን ተሰርተው ለድርቁ አካባቢዎች ለሚገኙ እንስሶች አስተማማኝ መኖ ለማቅረብ ዝግጅቱ መጠናቀቁን የደራሽ የተቀናጀ ግብርናና ሁለገብ የልማት ሥራ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወሰንሰገድ መሸሻ በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ ገለፀዋል።

ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ የቆየ ሲሆን ወደፊትም ከፍተኛ ድርሻ ይዞ እንደሚቀጥል ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግርም ላይ የተተከለው የስትራቴጂ እቅድ አንፃር መገመት አያስቸግርም። 85 በመቶ የሚሆነው የሀገራችን ሕዝብ በግብርናና ግብርና ጋር ተዛማጅ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ላይ መሰማራቱና 80 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ገቢ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ከዘርፉ የሚገኝ ሲሆን ዘርፉ የኢትዮጵያን 45 በመቶ አመታዊ ገቢ /GDP/ንና ኤክስፖርት ከሚደረገው 80 በመቶውን የሚሸፍን ነው።

የሰብል እርሻ 29 በመቶ አመታዊ ገቢ/GDP/፣ የእንስሳት ተዋፅኦ 12 በመቶ እና ደን ደግሞ 4 በመቶውን የሚሸፍኑ መሆናቸውን ጥናታዊ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የኢትዮጵያ አመታዊ ገቢ /GDP/ በ2005 ዓ.ም በ20 ቢሊዮን ዶላር ይጨምራል ተብሎ እንደሚታሰብና ይህ ሁኔታም የሀገራችንን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድርሻ የተሸከመውን ግብርናን ለከፋ አደጋ መዳረጉ ከህዝብ ቁጥር በፍጥነት መጨመር፣ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ በሚፈጠረው የመሬት መራቆትና በተለዋዋጭ የአየር ንብረት ክስተት ሳቢያ ሊፈጠር የሚችለውን ያልተጠበቀ ሐገራዊ አደጋ ግምት ውስጥ በማስገባት በካፒቴን መኮንን ካብትህይመር ሃሳብ አመንጪነት፣ ገንዘብ አቅራቢነትና የእንስሳት መኖ መከትከቻና ማቀነባበሪያ ማሽኖች በአእምሮአዊ ንብረት ፅ/ቤት ተመዝግቧል። በሀገራችን የመጀመሪያ የሆኑ የቴክኖሎጂ ስራዎች አቶ ወዳጄ እምሩ፣ ዶ/ር አበረ ተበጄና አቶ ወሰንሰገድ መሸሻ ሆነው በጋራ በባለቤትነት ያቋቋሙት ደራሽ የተቀናጀ ግብርና እና ሁለገብ የልማት ሥራ ኃ/የተ/የግል ማኅበር የሚባል ኩባንያ ከስኳር ተረፈ ምርቶች የእንስሳት መኖ በማምረት በድርቁ ለተጎዱ አካባቢዎች ለሚገኙ እንስሳትን ለመታደግ ተነሳስተዋል።

ይህ ድርጅት በ8 ሰዓት 126 ኩንታል ማምረት የሚችሉ 4 ማቀናበሪያ ማሽኖች በመስራት ባለፈው ሳምንት መጋቢት 27/2008 ዓ.ም የመጀመሪያውን ይፋ የሆነ የሙከራ ምርት አምርተው ለሚመለከታቸው አስፈትሸዋል።

ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የተለመደውን የእንስሳት መኖ ለማቅረብ የማይቻልበት ሁኔታ እንደሚፈጠር የተገነዘቡት እነዚህ 4 ቴክኖሎጅስቶችና ተመራማሪዎች ከስኳር ፋብሪካ የሚገኙ ባጋስንና ሞላሰስን ባካሄዱት ምርምር ያገኙትን ስሌተ ምጣኔ በመጠቀም ለመጀመሪያ ጊዜ ለሌሎች ተግባራት ብቻ ጥቅም ይሰጥ የነበረውንና ለቀለብነት አገልግሎት ላይ ያልዋለውን ባጋስን በድርቅ ለተጎዱ አካባቢ ለእንስሳት በመኖነት በማቅረብ የሀገሪቱን 12 በመቶ አመታዊ ገቢ /GDP/ የሚሸፍነውን የእንስሳት ሐብታችን በመታደግ ለወገን ደራሽ መሆናቸውንና ለኢኮኖሚውም አጋርነታቸውን የሚያስመሰክሩበት ሁኔታን ፈጥረዋል።

እስካሁን ሞላሰስን ከገፈራ፣ ከዩሪያ፣ ከውሃ፣ ከማእድን ጥንቅር፣ ከጨው፣ ከስሚንቶ፣ ከስንዴ ፉርሽካ፣ ኖራ፣ ድርቆሽ፣ ፋጉሎ፣ የሸክላ አፈር፣ የእፅዋትና ከአገዳ ሰብሎች ተረፈ ምርት ጋር እየመረጡ እንደየሁኔታው በአንዱ ወይም በሁለቱ በማደባለቅና የእንስሳት መኖነት ማዘጋጀት የተለመደ ሲሆን ከላይ የተጠቀሱት አብዛኞቹ ከውሃና ከዝናብ ጋር በተለይም ከጥሩ አየር ንብረት ጋር የሚገኙ ናቸው። ይህ መሆኑ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ለሚገኙ እንስሶች በመኖነት ለማቅረብ ከሎጅስቲክ አንፃርም በትራንስፖርት ችግርና ከደጋማው አካባቢዎች ካሉ እንስሶች አፍ እየመነገጉ መንጠቅ የሚመከር ባለመሆኑ ደራሽ የተባለው ኩባንያ ባጋስንና ሞላሰስን በማደባለቅ እጅግ ተመራጭ የሆነ የእንስሳት መኖ በማምረት እንስሶችን ለመታደግ መዘጋጀቱንና መንግስትም አስፈላጊነቱን በማመን ለአፈፃፀሙ አጋዥ ሆኖ መገኘቱን ዋና ሥራ አስኪያጁ ለሰንደቅ ጋዜጣ አክለው ገልፀዋል።

ሞላሰስ በስኳር ይዘቱ ከፍተኛ የሆነ ከሸንኮራ አገዳ ጭማቂ የሚገኝ ተረፈ ምርት ሲሆን በእንስሳት እርባታ ውስጥ እንደዋነኛ የኃይል ምንጭ ከሚያገለግሉት መኖዎች አንዱና ዋነኛው ነው።

ባጋስ ደግሞ የስኳሩ ጁስ ከወጣ በኋላ ቀሪው ቃጫማ የሆነ ቅሪት ወይም ተረፈ ምርት ሲሆን ከፍተኛ የቃጫ ይዘት ስላለው የመኖ ጥራቱ እጅግ ዝቅተኛ ቢሆንም ከሞላሰስ ጋር በምጣኔ በመቀላቀል የመበላት ደረጃውን ማሳደግ መቻሉን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልፀው በብዛት በተቋቋሙት የስኳር ፋብሪካዎች የሚገኘው ባጋስ የተባለው ተረፈ ምርት በየፋብሪካዎቹ በፈርነስነት የኃይል ምንጭ ሆኖ ተቃጥሎ የሚያቀጣጥል ከመሆኑ ባለፈ እንደተራራ ተከምሮ በከንቱ እየባከነ ያለ በመሆኑና ሞላሰሱም በየፋብሪካዎቹ ውስጥ ለውስጥ ላሉት ለጥርጊያ መንገዶቻቸው እንደሬንጅ /ካትራሜ/ በማገልገል አስፋልትነት ባሕሪ እንዲይዙ እያደረገ ነው። በተጨማሪም፣ ለአልኮል ፋብሪካዎች በጥሬ እቃነት፣ ለውጭ ሀገራት በወጪ ንግድ እየተጓዘ የሚገኝ ከመሆን ለገበሬው በክረምትና በእርጥበት ወቅት የሚበቅሉትን የተፈጥሮ ሳርና ቅጠላቅጠሎችን በድርቆሽ መልክ የሚዘጋጁትንና ከመሳሰሉት የዱቄትና የዘይት ፋብሪካ ተረፈ ምርቶች ጋር በማደባለቅ መጠቀም የተጀመረ ቢሆንም ከተዛባው የአየር ንብረት ችግር አንፃር ብዙ ሊያስኬዱን የማይችሉ መሆናቸው ለደራሽ መቋቋም አይነተኛ ምክንያት መሆኑም ተገልጧል።

ሀገራችን ከአለም 10ኛ ከአፍሪካ አንደኛ እንደሆነች የሚነገርለት የእንስሳት ምርት ሊያመነጭ የሚገባውን የኢኮኖሚ ጥቅም እየሰጠ አለመሆኑ ይታወቃል። የእንስሳት ምርትና ምርታማነቱን ከሚወስኑት ሁኔታዎች መካከል ዋናዋናዎቹ የእንስሳት የመኖ አቅርቦትና ጥራት የእንስሳት ዝርያና የእንስሳት በሽታዎች መሆናቸው ይታወቃል።

በአብዛኛው የሀገራችን ክፍል በተለይም በአርብቶ አደሩ አካባቢ የእንስሳት መኖ አቅርቦት ወቅታዊ ዝናብን ተከትሎ በሚለመልም የተፈጥሮ ግጦሽ ላይ መመስረቱ እፅዋት በሰው ንክኪ ሳቢያ እንዲጠፉ ምክንያት በመሆኑ ተፈጥሮ የሰጠችንን ለማጥፋት የበኩሉን ድርሻ እያከናወነ ነው። በተፋሰስ ልማት የተጀመረው የተጎሳቆሉ መሬቶችን የማገግም የልማት ተግባር ልቅ ግጦሽን ማኅበረሰቡ በራሱ ተነሳሽነት እየከለከለ ከመምጣቱ አንፃር ሐገሪቱ ደራሽ ኩባንያ ከባጋስና ከሞላሰስ ሊያመርቱት ከተዘጋጁበት ዝግጅት አንፃር የሚበረታታና የሚደገፍ ወቅታዊ ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል። በተለይም ማምረቻ ማሽኖቹ በኛው ልጆችና እዚሁ ሐገር ውስጥ ተመርተው ወድ ስራ መግባታቸው ሌላው የሚያስመሰግን ሥራ መሆኑም አስደሳች ጅምር እንደሆነ ተገንዝበናል።

ደራሽ ኩባንያ ከመንግስት ጋር በመሆን በአጭር ጊዜ እቅዱ ለመነሻ 4 ማደባለቂያና አንድ መከረታተፊያ ማሽን ሰርቶ ወደ ሥራ የገባ ቢሆንም በመካከለኛና በረጅም ጊዜ እቅዱ በእያንዳንዱ የስኳር ፋብሪካ 20 ማደባለቂያና አንድ መከረታተፊያ ማሽኖችን በመስራትና በመትከል  በሁለት ፈረቃ በቀን 1000 ኩንታል በማምረት በወር እስከ 30.000 ኩንታል የእንስሳት መኖ በማምረትና ለማቅረብ አቅዷል። ኩባንያው በድርቁ ሳቢያ የሚከሰተውን የእንስሳት መኖ እጥረት የሚታደግና በሂደትም ለሌሎች አካባቢዎች በሽያጭ በማቅረብ የእንስሳት ሐብታችንን ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በማዋል ለብዙ ወገኖቻችን ሰፊ የሆነ የስራ እድል እንደሚፈጥር ዋናው ስራ አስኪያጅ አስታውቀው መንግስት በተለመው እቅድ መሰረት ቅድሚያ በሚሰጥባቸው አካባቢ በተለይም በአፋር ውስጥ በ15 ቀናት 4ቱን ማሽኖች በማንቀሳቀስ ድርቁ በከፋበት አካባቢ ተክለው ማምረትና ለተጎዱት እንስሶች እንደሚደርሱላቸው አረጋግጠውልናል።  

53 ሚልዮን የሚደርሱ የቀንድከብቶችና ባጠቃላይ የእንስሳት መኖ የሚያስፈልጋቸው ከ80 ሚልዮን በላይ እንደሚገመቱና በአብዛኛው የሀገራችን ክፍል በተለይም በአርብቶ አደሩ ተደራሽ እንደሚሆኑ ተገምቷል።

የዓለም ሙቀት እየጨመረ ከባሕር ጠለል ከፍታ በአማካይ 2 ሚሊ ሜትር የደረሰና በአንዳንድ አካባቢዎች የዝናም መጠን እየጨመረ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ የዝናም መጠን በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መሆኑም ይታወቃል።

የአየር ንብረት መዛባት ከሚያስከትላቸው ክስተቶች ኤልኒኖና ላኒና የሚጠቀሱ ሲሆን ኤልኒኖ የዝናብ ስርጭትና መጠንን በማዛባት የውሃ እጥረትን ስለሚያስከትል የሰብል ምርትን በከፍተኛ ደረጃ በመጉዳት ለኢኮኖሚያዊ መናጋት ይዳርጋል። ላኒና ደግሞ በተቃራኒው መደበኛ ባልሆነ ሁኔታ የዝናብ መጠንን በመጨመር ለጎርፍና መሰል አደጋ የሚያጋልጥ ነው።

ኤልኒኖ አሁን በሀገራችንና በተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ ድርቅን እያስከተለ መምጣቱና እስከ 10 ሚልየን የሚደርሱ ዜጎቻችንን ለምግብ እጥረትና ለከፋ ጉዳት እየዳረገ መሆኑ በገሃድ የሚታይ ሐቅ ሆኗል።

በመደበኛው /climatological/ ክረምት ወቅት የነበረው የኤልኒኖ ክስተት በበጋ ወቅት ዝናብ ሰጪ ለሆኑት ሚትሪዮሎጂካል ስርአቶች ላይ ተፅእኖ ስለሚያሳድር በሀገራችን የበጋ ወቅት ዝናብ ላይም ተፅእኖ እንደሚኖረው ካሁን በፊት በባለሙያዎችና በመንግስትም በትንበያ የተገለፀ ቢሆንም ሰሞኑን በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ በጣለ ድንገተኛና ያልተጠበቀ ዝናም 23 ሰዎች በጎርፍ አደጋ የሞቱና 86 የሚደርሱ ዜጎቻችን መጎዳታቸው ይታወቃል።

ኤልኒኖ በአለማችን ውቅያኖስ በለይም በሰላማዊ ውቅያኖስ/ፓስፊክ/ ያልተለመደና ከሚጠበቀው ከአማካይ በላይ ሙቀት ሲጨምር የሚከሰት ነው።

ኤልኒኖ በተወሰኑ ዓመታት መካከል የሚፈጠርና በአብዝሃኛው ከ12 እስከ 18 ወራት ሊቆይ የሚችልና ረጅም እርቀት ሄዶ ተፅእኖ የማሳደር አቅም ያለው ውስብስብ የአየር ፀባይ ክስተት በመሆኑ በክረምት ወቅት መደበኛው ዝናብ አለመኖርና በበጋ ወቅት ሰሞኑን በሀገራችን የተከሰተው አይነት ያልተጠበቀ ዝናብ በመዝነብ ለጎርፍና ለሌሎች የከፉ ጉዳቶች ይዳርጋል።

ኤልኒኖ በየአምስት ወይም በየሰባት አመቱ የሚከሰትና የአለማችን የውሃ የታችኛው አካል ከመጠን በላይ በመሞቅ የሚፈጠር በመሆኑ የሚከሰተው ሙቀት ወደ መደበኛ የሙቀት ደረጃው እስኪመለስ በትንሹ ከ12 ወራት በላይ ስለሚቆይ በአርሶአደሩና በአርብቶ አደሩ ምርታማነት የሚያስከትለው ተፅእኖ ከአንድ የምርት ዘመን በላይ መሆኑ በተደጋጋሚ በተግባር የታየ በመሆኑ ችግሩ አርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን ለድርቅ አደጋ ተጋላጭ እያደረገ የሃገርን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዳም ነው።

ኤልኒኖ የውቅያኖስ ውሃ ሙቀት በመጨመር የቀዝቃዛና ሞቃታማ የውሃ እንቅስቃሴን እንዲሁም የነፋስ ዥረት አቅጣጫን በመቀየር በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ያለውን የእርጥበትና ደረቃማ የአየር ሁኔታ እንዲዛባ ምክንያትም ነው።

በዚህ ሳቢያም የዝናብ ስርጭትንና መጠኑን በማዛባት የውሃ እጥረት እንዲከሰት፣ የሰብል ምርት እንዲያሽቆለቁል ያደርጋል። ስፋቱና ጉዳቱ የተለያየ በመሆኑ በሀገራችን የተከሰተው ድርቅ የአየር ንብረት መዛባት ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች አንዱ በሆነው ኤልኒኖ ላለፉት 15 ዓመታት የከፋ ሁኔታ ተከስቷል።

እንደ አለምአቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ መረጃ 60 ሚልዮን የሚሆኑ አፍሪካውያን በኤልኒኖ ምክንያት ለከፋ ረሃብ የመጋለጥ አደጋ ተጋርጦባቸዋል። እነዚህ አፍሪካውያን በአሁኑ ጊዜ በጎርፍ በድርቅና መደበኛ ባልሆነ ስርጭት ምክንያት የምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ ጋምቢያ፣ ሞሪታንያ፣ ማላዊ፣ ናሚቢያ፣ ሴኔጋልና ዚምባብዌ የኤልኒኖ ተፅእኖ በከፍተኛ ደረጃ ያረፈባቸው ሃገራት ናቸው።

በኤልኒኖ ክስት በ2015 በበርካታ የምድር ወገብ አካባቢ የሚገኙ አገሮች ውስጥ የዝናብ መጠን ከመደበኛው ከ20 እስከ 30 በመቶ ያህል ቀንሷል። የህ ሁኔታ ከአፍሪካ ባሻገር በሌሎች ሐገሮችም የአየር ንብረታቸው ተዛብቶ ድርቅ ያጋጠማቸው ሲሆን የአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ፣ እንግሊዝ፣ ካናዳ፣ ኮሪያ፣ ብራዚል፣ ኢንዶኔዥያ፣ ሕንድ፣ አውስትራሊያ፣ ኒካራጓ፣ ሆንዱራስ፣ ጓቲማላ፣ ኤልሳልቫዶር፣ ሐይቲና ፓፑዋ ኒውጊኒ ላይ እጅግ የከፋ ጉዳት አድርሶባቸዋል።

በኢትዮጵያም ከ 200 በላይ በሆኑ ወረዳዎች በክረምት ወራት አርሶአደሮቹ መሬታቸውን አለስልሰው ቢያዘጋጁም ዝናብ ባለመጣሉ ማሳቸው በዘር ሊሸፈን ያልቻለና የዘሩ ቢኖሩም በዝናቡ ወቅቱን ጠብቆ አለመጣል ሰብሉ በቡቃያው ቀርቷል። ዝናብ ጣለ ብለው ማሳቸውን ገልብጠው ቢዘሩም መክኖባቸዋል።

በ1965 ዓ.ምና በ1977 ዓ.ም በሀገራችን ተከስቶ የነበረው ድርቅ ወገኖቻችንን ለከፋ የረሀብ እልቂት ዳርጓቸዋል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ከየቀያቸው ተፈናቅለዋል። እንደ መንግስት መረጃ ከሆነ 10 ነጥብ 2 ሚልዮን ዜጎች ለችግሩ ተዳርገዋል። እነዚህ ወገኖች ለከብቶቻቸው ውሃና መኖ ይፈልጋሉ። ከብቶቻቸው ቀለብ ካላገኙ ህልውናቸውን ስለሚያናጋው ቀያቸውን ጥለው ለመሰደድ አይደራደሩም። የተከሰተው ድርቅ ከመቼውም ጊዜ የከፋ ቢሆንም እንደቀድሞዎቹ ድርቅ ጊዜያቶች የከፋ እርሀብ ጎልቶ ባይታይም ሁኔታው ለረጅም ጊዜ የሚቀጥል ከመሆኑ አንፃር ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል ተብሎ ስለሚሰጋ ሁሉም ዜጋ በይገባኛል ስሜት መረባረብ ይገባዋል ተብሎ ይታሰባል።

በመሆኑም ደራሽ የተቀናጀ ግብርና እና ሁለገብ የልማት ሥራ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ለዚህ የከፋ የድርቅ አደጋ የበኩሉን አስተዋፅኦ በማድረግ በድርቅ የተጎዱ እንስሶችን ለመታደግ በማንኛውም ጊዜና ቦታ የትም ሊዘጋጅ የሚችል የስኳር ተረፈ ምርቶችን በማደባለቅ የእንስሳት መኖ በማምረት ሐገራዊ አደራቸውን በሚወጡ ግለሰቦች አማካይነት ወደ ምርት ሊገባ መሆኑ ታውቋል።n 

  

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
708 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us