የጋምቤላ ክራሞት

Wednesday, 20 April 2016 13:18

ዓርብ ሚያዚያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም ለሊት ለጋምቤላ አስከፊ ነበር። ከለሊቱ 11፡00 ሰዓት ግድም አኙዋሃ ዞን ሰርገው የገቡ ታጣቂዎች የከፈቱት ድንገተኛ ጥቃት በመቶ የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን አገር አማን ብለው በተኙበት አስቀርል።  መነሻቸውን ጎረቤት ሀገር (ደቡብ ሱዳን) ያደረጉ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ወደጋምቤላ በኑዌር ዞን ሶስት ወረዳዎች ዘልቀው በመግባት በድንገት ባደረሱት ጥቃት ከ208 በላይ ንጹሐን ዜጎች በግፍ ሲገደሉ ከ100 በላይ  የሚቆጠሩ ቆስለዋል። በርካታ ሴቶችና ሕጻናትም ታግተው ተወስደዋል። ታጣቂዎቹ በተጨማሪም ከ2000 በላይ የቀንድ ከብቶችንም እየነዱ ወደመጡበት መመሳቸውም ተነግሯል።

ከደቡብ ሱዳን ግሬት ፒቡር ግዛት ተነስተው የኢትዮጵያን ሉአላዊ ድንበር አቋርጠው ወደ ጋምቤላ ኑዌር ዞን በመግባት በላሬ፣ በጅካዋ እና በመኮይ ወረዳዎች ስር በሚገኙ 13 ቀበሌዎች ላይ ጥቃት የፈጸሙት ሚያዚያ 7 ቀን ለሊት 11 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ባለው ሰዓታት ውስጥ ነበር ተብሏል። ጥቃቱ መፈጸሙ የታወቀው  ሚያዚያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም ይሁን እንጂ የታጣቂዎቹ ጥቃት ከ15 ቀናት በላይ የወሰደ ነው የመባሉ ጉዳይ እጅግ አሳዛኝና ‘መንግሥት የለም ወይ’ ያስባለ ክስተት ነበር። ይህን ያህል ቀናት ጥቃትና ዝርፊያ ሲካሄድ የመከላከያ ሠራዊት፣ የአካባቢው ሚሊሺያና የፖሊስ ኃይል ምን ሲሰሩ ነበር ለሚለው የበርካታ ኢትዮጵዊያን ጥያቄ እስካሁን በመንግስት በኩል የተሰጠ ይፋዊ ምላሽ የለም።

 

ጥቃቱ መፈጸሙ ከተሰማ በኋላ መንግስት በድርጊቱ ሐዘን እንደተሰማው በጠ/ሚኒስትር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ በኩል ገልጷል። ታፍነው የተወሰዱ እናቶችና ሕጻናትን ለማስመለስ የመከላከያ ሠራዊት ጥረት እያደረገ መሆኑንም ጠ/ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ መንግስት በጋምቤላ ጥቃቱ በተፈጸመ 48 ሰዓታት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ከጥቃቱ ጀርባ የደቡብ ሱዳን መንግስትም ሆነ ተቃዋሚ ኃይሉ እንደሌሉበት አረጋግጫለሁ ቢልም ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለመደና ተራ የከብት ዘረፋ ጥቃት እጅግ በተለየ መልኩ የተሰነዘረው የከበደ ጥቃት የደቡብ ሱዳን ቀውስ ነጸብራቅ ሊሆን ይችላል የሚሉ ወገኖች ድምጽ አስከትሏል፡፡ በደቡብ ሱዳን የእርስበርስ ጦርነት ምክንያት ቀዬአቸውን ለቀው የተሰደዱ በሺ የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናዊያን በጋምቤላ ምድር በስደተኝነት ተመዝግበው እየተረዱ ባሉበት በዚህ ወቅት ይህ ጥቃት መፈጸሙ ምናልባትም የኢትዮጵያ መንግስትን የሸምጋይነት ሚና የሚቃወሙ ወገኖች ሴራ ሊሆን ይችላል የሚል ትንታኔም የሚያክሉ የፖለቲካ ልሂቃን አልጠፉም፡፡

 

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ እና ሰማያዊ ፓርቲ  ሰኞ ዕለት በጋራ ባወጡት መግለጫ ዜጎቻችንን ለዚህ ዓይነቱ የከፋ ጥቃት ሊዳረጉ የቻሉት መንግስት ቀደም ሲል ራሳቸውን የሚከላከሉበትን ትጥቅ በማስፈታቱ ነው በማለት የተጠያቂነቱን አፈሙዝ ወደመንግስት አዙረውታል፡፡

 

ፓርቲዎቹ አያይዘውም ከዚህ ቀደም ባሉት መንግስታት በየጠረፉ አካባቢዎች ይመደብ የነበረው ጠረፍ ጠባቂ ኃይል እንዳይኖር በመደረጉ የውጭ ሀገር ታጣቂዎች እንደፈለጉ ድንበር ጥሰው የሚገቡበትና ወገኖቻችን ላይ ጥቃት የሚያደርሱበት ሁኔታ የተፈጠረ መሆኑንም ለመረዳት ችለናል ብለዋል፡፡

 

የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ትላንት ሚያዚያ 11 ቀን 2008 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ ከዛሬ ረቡዕ እስከነገ ሐሙስ ድረስ የሚቆይ የሁለት ቀናት ብሔራዊ የሀዘን ቀን ያወጀ ሲሆን በነዚህ ቀናት በመላ ኢትዮጵያ እና በውጭ ኢምባሲዎች፣ ቆንስላ ጽ/ቤቶች እና መርከቦች የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ወስኗል፡፡

 

ጥቂት ስለጋምቤላ

የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከኢትዮጵያ በስተደቡብ ምዕራብ ይገኛል። በሰሜን በቤንሻንጉልና ኦሮሚያ ክልሎች፣ በምስራቅ ከኦሮሚያና ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ በደቡብ ምዕራብ ከደቡብ ሱዳን ጋር ይዋሰናል። ክልሉ 765 ነጥብ 10 ሄክታር የቆዳ ስፋት አለው። አማካኝ የሙቀት መጠኑ 28 ነጥብ 3 ዲግሪ ሴልሺየስ (ቆላማ አየር ያለው) ቢሆንም ዓመቱን ሙሉ በአረንጓዴ የተሸፈነች ናት። የክልሉ መካከለኛና ምስራቃዊ ክፍሎች ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነ ነው።

 

ክልሉ ከሚመረቱ ዋና ዋና ሰብሎች መካከል ከአገዳ እህሎች በቆሎና ማሽላ፣ ከጥራጥሬ እህሎች አኩሪ አተር፣ አደንጓሬና የመሳሰሉት ከቅባት እህሎች ሰሊጥና ለውዝ፣ ከብዕር እህሎች ሩዝና ዳጉሳ፣ ከጭረት ተክሎች ጥጥ እንዲሁም የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎች ናቸው።

 

ጋምቤላ ዓመቱን ሙሉ ያለማቋረጥ የሚፈሱ አራት ታላላቅ ሀይቆች ማለትም ባሮ፣ አልዌሮ፣ ጊሎና አኮቦ ባለቤት ናት። ውብና ድንቅ የዱር እንስሳትም መናኸሪያ ናት።

 

በክልሉ በ13 ወረዳዎች፣ በአንድ ልዩ ወረዳ፣ በአንድ ከተማና በሶስት የብሔረሰቦች ዞኖች የተከፋፈለ ሲሆን አምስት ብሔረሰቦች ማለትም አኙዋሃ፣ ኑዌር፣ ማጃንግ፣ ኮሞ እና ኦፓ ብሔረሰቦች በመከባበርና ይኖሩበታል። ከክልሉ አስተዳደር ባገኘነው መረጃ መሰረት የማዕከላዊ ስታስቲክስ ባለስልጣን በ1999 ዓ.ም ባደረገው ቆጠራ መሠረት በጋምቤላ 306 ሺ 919 ሕዝብ የያዘ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አምስቱ ነባር ብሔረሰቦች ማለትም ኑዌር 46 ነጥብ 65 በመቶ፣ አኙዋሃ 21 በመቶ፣ ማጃንግ 4 በመቶ፣ ኦፓ 0 ነጥብ 32 በመቶ፣ ኮሞ 0ነጥብ 02 በመቶ ድርሻ ሲይዙ የተቀረው 26 በመቶ የሌሎች ብሔርብሔረሰቦች ተወላጆችን የሚያሳይ ነው። በጋምቤላ የሚገኙት አምስት ብሔረሰቦች የናይሎ ሰሐራዊ ልሳን ቤተሰብ የሆኑ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ናቸው።

 

የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልል ነባር ብሔረሰቦች በጥቂቱ  እናስተዋውቃችሁ።

 

ኑዌር

 

የኑዌር ብሔረሰብ አባላት በኢትዮጵያና በሱዳን ይገኛሉ። አሠፋፈራቸው በዋናነት የዓባይ ሸለቆን ዳርቻ ተከትሎ በተፋሰሱ ሥር በሚገኘው ለጥ ያለ ሜዳ ላይና በጋምቤላ ክልል በሰፊው የሚገኘውን የባሮ ወንዝን ዳርቻ ተከትሎ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ኑዌሮች በዚህ ለጥ ባለ ሜዳማ መሬት ላይ ከብቶቻቸውን እያረቡና ወንዞች ትተውት የሚሄዱት ረግረግ ውሃ ጠፈፍ ሲል በሚፈጥረው ርጥብ መሬት ላይ መጠነኛ የግብርና ተግባር በማከናወን ሕይወታቸውን ይመራሉ።

 

ኑዌሮች በጋምቤላ ክልል ውስጥ ትልቁን የሕዝብ ቁጥር ሲይዙ በክልሉ አምስት ወረዳዎች ውስጥ ይገኛሉ። ኑዌሮች በዋናነት በከብት እርባታ ይታወቃሉ። ለብሔረሰቡ አባላት የከበት ርባታ የመኖር ዋስትና ብቻ ሳይሆን በርከት ያሉ ምሳሌያዊ፣ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ እሴቶች ያሉት ተግባር ነው። በብሔረሰቡ ውስጥ የከበት ርባታ ለማኅበራዊ ትስስር፣ ለቤተሰብ ምሥረታ፣ ለራስ ከበሬታና ለባህል ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ከዚህም አልፎ በኑዌር ብሔረሰብ የቤተሰብ አባቶች ከሞቱም በኋላ ቢሆን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ትስስራቸው እንደሚቀጥል ስለሚታመን ከብቶች ከቅድመ አያቶች መንፈስ ጋር ለሚኖረው ትስስር ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው ተብሎ ይታመናል። በኑዌር ባለው ማኅበራዊ አደረጃጀት ሥርዓት ውስጥ ይህ ነው የሚባል ሁሉን አቀፍ ገዥና አለቃ ብዙም የማይታወቅ ሲሆን፤ ይህም በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት አለው። ስለዚህም በመካከላቸው ልዩ የሆነ መከፋፈልና የበላይነትና የበታችነት የሌለባቸው፣ ልዩ በሆነ ፍትሐዊ እኩልነት የሚያምኑ፣ በሁሉም ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በአንድነትና በትብብር መንፈስ በእኩልነት የሚኖሩ ሕዝቦች ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም ኑዌሮች ለተፈጥሮ ያላቸው ትልቅ አክብሮት ዋና መገለጫቸው ነው። ቁመታቸው ረጃጅም የሆኑትና በጠንካራ ማኅበራዊ አደረጃጀታቸው የሚታወቁት ኑዌሮች ለሚያረቧቸው ከብቶቻቸውና የሚኖሩባት መሬት ልዩ ከበሬታ አላቸው። በሚኖሩበት አካባቢ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና አረንጓዴ ገጽታ ለዚህ ምስክሮች ናቸው። ኑዌሮች ለሽማግሌዎችና ለቤተሰብ ኃላፊዎች ከበሬታ አላቸው። የብሔረሰቡ አባላት ከፊል አርሶአደሮችና አርብቶ አደሮች ሲሆኑ ለኑሮአቸው ፍጆታ ስድሳ በመቶ የሚሆነውን ከእርሻ ምርት ይሸፍናሉ። በዚህም በቆሎ፣ ማሽላና መጠነኛ የጓሮ አትክልት ሲያመርቱ በተጨማሪም በአካባቢያቸው ካሉት ወንዞች ጋር ባላቸው ትስስር ዓሣ በማምረት ይተዳደራሉ።

 

አኙዋሃ

አኙዋሃዎች ስያሜያቸውን ያገኙት አብሮነትን ከሚገልጹ ማኅበራዊ እሴቶቻቸው እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። የብሔረሰቡ አባላት “አኙዋሃ” ማለት “አብሮ ሆነ ማለት ነው” ይላሉ። የአኙዋሃ ብሔረሰብ ጆር፣ ጎግ፣ አበቦ፣ ጋምቤላ፣ ኢታንግና በከፊል ጂካዎና ዲማ በሚባሉ ወረዳዎች ስር ይገኛሉ። አኙዋሃዎች የክልሉን መሬት አቋርጠው የሚፈሱትን ወንዞች ተከትለው በመጡ አባቶቻቸው አማካይነት ከጥንት ጀምሮ አሁን ሰፍረው በሚገኙባቸው ቦታዎች መኖር እንደጀመሩ ይነገራል። የብሔረሰቡ አባላት ከውሃ ጋር ያላቸው መስተጋብር ጠንካራ በመሆኑ በአራቱ ታላላቅ ወንዞች አኮቦ፣ ጊሎ፣ አልዌሮ (ባሮ) ዳርቻዎች ሰፍረው ይገኛሉ። የወንዞቹ ስምም ቀደም ብለው በመጡ አኙዋሃዎች አያት ቅድመ አያቶች እንደተሰየሙ ይነገራል። አኙዋሃዎች በአብዛኛው በግብርና የሚተዳደሩ ሲሆን ማሽላ፣ በቆሎ፣ ትንባሆና ዱባ፣ ያመርታሉ። ከላይ እንደተገለፀው ከመጀመሪያ አሠፋፈራቸው ወንዞችን የተከተለ በመሆኑ የተለያዩ የዓሣ ዝርያዎችን በማምረትና በመጠቀም ይታወቃሉ።

 

ማህበራዊ ትስስራቸውን በተመለከተ አኙዋሃዎች በመንደር ሲሰባሰቡ በአንድ ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሆነው ይሰፍራሉ፤ በጋራ በመኖርና በጥብቅ ማኅበራዊ ትስስርም ያምናሉ። የአካባቢውን መሪም ይመርጣሉ፤ እሱም “ክዋሮ” ይባላል። ክዋሮ አካባቢውን በማስተዳደር ከፍተኛ ስልጣን ያለው ሲሆን፤ በባህላዊው የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ ከ“ኒያ” ቀጥሎ ከፍተኛው የማስተዳደር ስልጣን ያለው ሰው ነው። ከክዋሮ በላይ ንጉሥ ሆኖ የሁሉም አኙዋሃዎች መንፈሳዊና ማኅበራዊ መሪ በመሆን የሚያገለግለው “ኒያ” ሲሆን በአኙዋሃ ብሔረሰብ ከአንድ ልዑላዊ ቤተሰብ የሚወለድ፣ ሥልጣኑ በትውልድ የሚገኝ የበላይ አስተዳዳሪ ነው። ኒያ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ከአጼ ኃይለሥላሴ ጋር መጠነኛ የሆነ ግንኙነት በመመስረት ትስስር ፈጥረው የነበረ ሲሆን በዘመነ ደርግ ከፍተኛ ስደት ደርሶባቸዋል። በደርግ ዘመን የኒያ ማኅበራዊ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ ፈርሶና ተከልክሎም ነበር። በአሁኑ ሰዓት ይህ ባህላዊ አስተዳደር እንደ ማኅበራዊ እሴት ዕውቅና ተሰጥቶት እየተተገበረ ይገኛል።

 

ማጃንግ

ማጃንግ በጋምቤላ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ነባር ብሔረሰቦች አንዱ ሲሆን፤ የዚህ ብሔረሰብ አባላት ከጋምቤላ ክልል በተጨማሪ በሌሎች አጎራባች ክልሎች ውሰጥ ይኖራሉ። ማጃንጎች በጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአኙዋሃ ብሔረሰብ ዞን አበቦ ወረዳና በማጀንግ ብሔረሰብ ዞን፣ ጎደሬና መንግሽ ወረዳዎች ይገኛሉ። በተጨማሪም በሦስት ክልሎች ማለትም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት በሸካ ዞን የኪ ወረዳ፣ በቤንች ማጂ ዞን ሸኮና ጉራፈርዳ ወረዳዎች እንዲሁም በካፋ ዞን፣ በኢሉአባቦራና በምዕራብ ወለጋ ወረዳዎች ውስጥ ይገኛሉ። ማጀንጎች አሰፋፈራቸውንና አመጣጣቸውን በተመለከተ የራሳቸው አፈታሪክ አላቸው። ይህንንም መሠረት በማድረግ ከደቡብ አቀጣጫ በመነሳት አሁን ሰፍረው ወደሚገኙባቸው ቦታዎች እንደመጡ ይናገራሉ። የብሔረሰቡ አባላት ደቡብ የሚሉት አቀጣጫ አሁን ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በመባል የሚታወቀውን አካባቢ የሚወክል ሊሆን እንደሚችል ቢኖገሩም ቀደም ሲል አያት ቅድመ አያቶቻቸው ይኖሩበት ከነበረውና ከመጀመሪያ ቦታቸው ተነሥተው አሁን ወደሚኖሩበት አካባቢ እንዴት መጡ የሚለውን ታሪክ ለመረዳት ጥናት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

 

በጎደሬ ወረዳ የሚገኙት የብሔረሰቡ አባላት ቀደም ሲል በተለያዩ አካባቢዎች ይኖሩ እንደነበርና (ለምሳሌ በጌለሻ ቀበሌ አሁን የሚኖሩት ማጀንጎች ቀደም ሲል በቴፒ አካባቢ ይኖሩ እንደነበርና) አዲስ መሬት ፍለጋ በባህላዊ መሪዎቻቸው አማካይነት አሁን ወዳሉበት አካባቢ እንደመጡ ይናገራሉ። ከዚህና ከሌሎች መረጃዎች ማለት የሚቻለው የብሔረሰቡ አባላት አያት ቅድመ አያቶቻቸው ይኖሩባቸው ከነበሩ ቦታዎች ተነሥተው አሁን ሰፍረው የሚገኙባቸው ቦታዎችን በመምረጥና በመሞከር በሦስት አጎራባች ክልሎች መስፈራቸውን ነው።

 

ማጃንጎች አኗኗራቸው ግብርናን መሠረት ያደረገ ሆኖ በቆሎ፣ ማሽላ፣ አገዳ፣ ካላቫ፣ ስኳር ድንች፣ አናናስ፣ ፓፓያ፣ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ሊትረስ፤ ሙዝ፣ ዕርድ፣ ኮረሪማ፣ ዝንጅብል፣ ጥምዝ፣ እንሰትና ትንባሆ ያመርታሉ። ማጃንች በእርሻ ሥራ አፈራርቆ የማምረት ሥርዓት የሚመሩ፣ በአንድ ቦታ ከአምስት በላይ ምርትን የሚያመርቱና መሬትን በየአምስት ዓመቱ የሚለውጡ ናቸው። የዚህ ብሔረሰብ አባላት ከእርሻ ውጭ በከብት ርባታ ያላቸው ተሳትፎ ብዙ የሚባል ባይሆንም በንብና ዓሣ ርባታ ታዋቁ ናቸው።

 

የማጃንግ ብሔረሰብ የቤተሰብ ግንኙነታቸው እጅግ ጠንካራ ሲሆን፤ በትዳር ቢለዩም ከቤተሰባቸው ጋር ያላቸው ቁርኝት ፈጽሞ አይላላም። ማጃንጎች የራሳቸው የሆነ ማኅበራዊ መዋቅርና አደረጃጀት ሲኖራቸው መሪው “ታፓ” ይባል ነበር። ታፓ ከፖለቲካዊ አመራር ይልቅ በሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ከመሆኑም በላይ በማኅበረሰቡ ውስጥ የበረከት አባት፣ የወደፊቱን የሚያውቅና የመፈወስ ሥጦታም ያለው ነው ተብሎ ይታመን ነበር።

 

ኦፖ

 

የኦፖ ብሔረሰብ ራሳቸውን “ኦፖ” በማለት ይጠራሉ፤ የቃሉ ትርጉምም “ሰው” ማለት ነው ይላሉ። የኦፖ ቋንቋ በአብዛኛው የሚነገረው በኢታንግ ልዩ ወረዳ ውስጥ ነው። የቋንቋው ተናጋሪዎች ቁጥር አናሳ ሲሆን፤ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ባቀረበው የቆጠራ ሪፖርት መሠረት የኦፖ ቋንቋ ተናጋሪዎች ቁጥር 999 ያህል ብቻ ነው። በመሆኑም ቋንቋውን ለመደበኛ አገልግሎት የማዋሉ ጉዳይ ገና በጅምር ላይ የሚገኝ ነው። በቅርቡ ቋንቋውን ለጽሑፍ ለማብቃት በተደረገ እንቅስቃሴ የላቲን ፊደል ተመርጦ በባለሙያዎች ተዘጋጅቷል።

 

ኦፖዎች በካልኪስና ጂካዎ ላይ ሰፍረው ሲኖሩ ቆይተው ቀስ በቀስ እየተጓዙ አሁን ወደማገኙባት ኢታንግ አካባቢ በመምጣታቸው ከኮሞ ብሔረሰብና ከኦሮሞ ብሔረሰብ ጋር አብረው መኖር ጀምረዋል። ኦፖዎች በጋምቤላ ክልል ውስጥ ሰፊ ባህላዊ መስሕብ ካላቸው ብሔረሰቦችና በቤተሰብ አመሠራረታቸው ጠንካራ ከሚባሉት ሕዝቦች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።

 

ኦፖዎች በእርሻ ሥራ የሚተዳደሩ ሲሆን፤ እንደ አጋዥ የኢኮኖሚ መስከም ዓሣ ማጥመድን፣ ፍራ ፍሬ ለቀማንና፣ አደንን ይጠቀማሉ። በኢታንግ ልዩ ወረዳ ሰሜናዊ ክፍል የሚኖሩት የኦፖ ቤተሰቦች ዋናኬና መራ ይባላሉ። አፖዎች በጋምቤላ ክልል ውስጥ በቁጥር ብዛት አራተኛ ደረጃን ይይዛሉ።

 

ኮሞ

ኮሞዎች በጋምቤላ ክልል ሰሜን ምዕራብ የሚኖሩ ሲሆን፤ ተራራማ በሆነው የክልሉ አቅጣጫ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ይዋሰናሉ። አንዳንድ የኮሞ ብሔረሰብ ተወላጆች በክልሉ ከሚገኙት አኙዋሃዎች ጋር ተቀራርበው ይኖራሉ፣ በዚህም የተነሣ በርከት ያሉ የኮሞ ቋንቃ ተናጋሪዎች የአኙዋሃ ቀንቋንም ይናገራሉ። ከቁጥር አንፃር ኮሞዎች በጋምቤላ ክልል ከሚኖሩት አምስት ብሔረሰቦች አነስተኛውን ቁጥር የያዙ ቢሆኑም በሱደንና በአጎራባች ክልሎች ውስጥ በርከት ያሉ የብሔረሰቡ አባላት ይገኛሉ።

 

ኮሞዎች ከዑዱክ፣ ማኦ እና ሙዋማ ብሔረሰቦች ጋር በመሆን በአንድ ላይ በባህልና በታሪክ የሚቀራረቡ ሲሆን፤ በጥቅል ስም ኮማ ይባላሉ። በኢትዮጵያ የሚኖሩት ኮሞዎች ቁጥር በአጠቃላይ 3 ሺህ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። ከዚህ ቁጥር ውስጥ 300 የሚሆኑት በጋምቤላ ክልል ውስጥ ይገኛሉ። ኮሞዎች የሚኖሩት በኢታንግ ልዩ ወረዳ አካባቢ ነው። ኮሞዎች በአባዊ ሥርዓተ ማኅበር የሚተዳደሩ ሲሆን የዘር ቁጥራቸውንም የሚሠፍሩት በአባቶች ትውልድ ነው።

 

ኮሞዎች ማሽላ፣ ለውዝ፣ ትምባሆ፣ ጣፋጭ ፍሬ፣ ስኳር ድንች፣ ቀይ በርበሬና ጥጥ በማምረትና በአነስተኛ ደረጃ በፍየልና ዓሣ እርባታ በማከናወን ይታወቃሉ። በኮሞዎች አስተሳሰብ ማንኛውም ኮሞ የሜኖርበትን አካባቢ ማክበርና መንከባከብ አለበት፤ ከእሱም በፊት ከነበሩት ቅድመ አያቶቹ የወረሰውን ቅርስ ከእሱ በኋላ ለሚመጣው ትውለድ የማውረስ ኃላፊነት እንዳለበት ይሰማዋል፤ ይህንንም “ዋታዊት” ይሉታል። የኮሞዎች ማኅበራዊ አደረጃጀት በጎሣዎችና በቤተሰቦች የተከፈለ ሲሆን፤ በዕድሜ ደረጃ ልዩ ልዩ ኃላፊነቶችን ይወጣሉ፤ በዚህም በዕድሜ ገፋ ያሉት ከፍተኛ የሚባሉ የማኅበራዊ አደረጃጀቶችን ይመራሉ። የኮሞ ሽማግሌዎች ስለ እርሻ ምርት ማማር፣ ስለ እንስሳት ጤንነት፣ ስለ ዝናብ፣ ስለ መሬት ምርታማነትና ስለ ጦርነት መጥፋት ፀሎትና ምልጃ በማድረግ አገልግሎት ይሰጣሉ።

 

እነዚህ ሕዝቦች ተከባብረው የሚኖሩባት ጋምቤላ ለወሮበሎች ጥቃት መጋለጧ፣ መንግስትም ችግሩን አስቀድሞ በመቆጣጠርና በመከላከል ረገድ አቅም የለሽ ሆኖ መታየቱ ብዙዎችን ያሳዘነ ክስተት ሆኗል።     

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
955 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us