ማህበራዊ ድረገጾች እና ፖለቲከኞቻችንን

Wednesday, 04 May 2016 13:01

ዘመኑ የመረጃና የቴክኖሎጂ ነው። የቴሌኮም፣ የኮምፒውተር፣ የተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ የኢንተርኔት…. ቴክኖሎጂዎች መስፋፋትና መዘመን ዓለምን ወደአንድ ጠባብ መንደርነት እየሰበሰባት ይገኛል። ዛሬ አዲስአበባ ቁጭ ብሎ በአንዲት አነስተኛ ተንቀሳቃሽ ስልክ የድምጽ፣ የምስል መልዕክቶችን ከየትኛው የዓለም ጫፍ መለዋወጥ ቀላል ሆኗል። የቴክኖሎጂውን መስፋፋት ተከትሎ እያበቡ የሚገኙት የማህበራዊ ድረገጾች ሰዎችን እንዲሁ በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ሃሳብ እንዲለዋወጡ ከመርዳት ባለፈ በአረቡ ዓለም እንደታየው ዓይነት አብዮት እንዲቀጣጠልና አምባገነኖች ከስልጣን እንዲለቁም የማይናቅ ሚና ተጫውተዋል። እንዲህ ዓይነቱ ክስተትም የመረጃን ኃያልነት በገሃድ አሳይቷል።

 

በአሁኑ ወቅት ፌስቡክ የተባለው በማርክ ዙከንበርግ የ32 ዓመት ወጣትና አራት ጓደኞቹ እ.አ.አ በ2004 የተመሰረተው ማህበራዊ ድረገጽ በአሁኑ ወቅት 1 ነጥብ 65 ቢሊየን ሰዎች ተጠቃሚ አድርጓል። ዓመታዊ ገቢውም 17 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር የደረሰ ሲሆን ወጣቱ ዙከንበርግም የቴክኖሎጂ ፈጠራ ዕውቀቱ ባስገኘለት ሐብት ከዓለም ቢሊየነሮች ተርታ መሰለፍ ከቻለ ዋል አደር ብሏል።


የምስረታውን መቀመጫ አሜሪካ ሳንፍራንስሲስኮ ደረገው ትዊተር እ.አ.አ በ2006 የተመሠረተ ሲሆን 332 ሚሊየን የሚደርሱ ተጠቃሚዎችን አሉት። ትዊተር ከፌስቡክ የሚለይበት አንዱና ዋናው ጉዳይ አጫጭር ሃሳቦችን ብቻ ለማስፈር የሚያስገድድ መሆኑ ነው። ከ140 ቃላትን (ካራክተር) በላይ ለመጻፍ አያስችልም። በዚህ ምክንያት ሃሳብን በስፋት ይገድባል የሚሉ ወገኖች ትዊተርን አይመርጡትም። በአሁኑ ወቅት ዓመታዊ ገቢውም 2 ነጥብ 21 ቢሊየን ዶላር ደርሷል።


የእነዚህ ማህበራዊ ድረገጾች እያደጉ መምጣትና በሕዝቦች በአጭር ዓመታት ተቀባይነትን ማግኘት የፖለቲካ መሪዎች፣ መንግስታትና ተቋማት ቀልብ ለመሳብ ችሏል። በዚህም ምክንያት ባለስልጣናቱ በዚህ መረብ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለሕዝባቸው በቂ መረጃን እንዲያቀርቡ እያስገደዳቸው ነው። በመሆኑም የዓለማችን ታላላቅ መሪዎች ሳይቀር የፌስቡክ ገጽ ከፍተው የግል፣ የመንግስታቸውንና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ በማስፈር ከህዝባቸው ጋር በቀላሉና በቀጥታ መገናኘት ችለዋል።


በአሁኑ ሰዓት ከዓለማችን ፖለቲከኞች መካከል የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ፕሬዚደንት የሆኑት ሁሴን ባራክ ኦባማ የፌስቡክ ገጻቸው 48 ሚሊየን 426 ሺ 241 ተከታዮችን በመያዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ፖለቲከኞች በመጀመሪያዎቹ ረድፍ ይገኛሉ። ባለቤታቸው ሚሼል ኦባማ 15 ሚሊየን 349 ሺ 059 ተከታይ አላቸው። የእንግሊዙ ዲቪድ ካሜሮን 1 ሚሊየን 66 ሺ 941 ያህል ተከታይ ያላቸው ሲሆን የጀርመንዋ ቻንስለር አንጄላ ሜርክል 2 ሚሊየን 11 ሺ 904፣ የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ፍራንኮ ሆላንዴ 876 ሺ 889 ተከታዮችን አፍርተዋል።


ከአፍሪካ መሪዎች መካከል የኬንያው ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ 2 ሚሊየን 293 ሺ 302፣ የሩዋንዳው ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ 569 ሺ 297፣ የኢትዮጵያው ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ 31 ሺ 625፣ ባለቤታቸው ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ 18 ሺ 654 ተከታዮችን አፍርተዋል። በኢትዮጵያ ከ22 በላይ የካቢኔ አባላት የሆኑ ከፍተኛ ባለስልጣናት ያሉ ቢሆኑም አብዛኛዎቹ የራሳቸው የፌስቡክና የቲዊተር አድራሻ የላቸውም። አንዳንዶቹ ለስም ያህል አካውንት የከፈቱ ቢሆንም በየዕለቱ አዳዲስ መረጃዎችን በመስጠትና በመቀበል ረገድ ውስንነት የሚታይባቸው ናቸው።


በግል ባደረኩት መጠነኛ ዳሰሳ የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ በፌስቡክና በቲውተር የላቀ ተሳትፎ ከሚያደርጉ ባለስልጣናት መካከል በቀዳሚኒት የሚጠቀሱ ናቸው። ከስማቸው ቀጥሎ «ገቨርንመንት ኦፊሻል» የሚለው የፌስቡክ ገጻቸው እስከትላንት ወዲያ ጠዋት ድረስ ዶ/ር ቴዎድሮስ 740 ሺ 446 ያህል የፌስቡክ ተከታዮችን አፍርቷል።

ባለሥልጣናቱ በድረገጾቻቸው ምን ያወራሉ?

 

የፌስቡክ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆነው ማርክ ዙከንበርግ የፌስቡክ ኦፊሻል ገጹ 61 ሚሊየን 206 ሺ 358 ተከታዮችን አፍርቷል። ዙከንበርግ በዚህ ገጹ ላይ የሚያሰፍራቸው የግልና ቤተሰባዊ ጉዳዮች ነው። ስላገኛቸው ሰዎች፣ ስለጎበኛቸው ሀገራትና ቦታዎች፣ ስለኩባንያው ዕድገት፣ አንዳንድ ለውጦችና የመሳሰሉ ርዕሰ ጉዳዮችን ያካፍላል።


በተመሳሳይ ሁኔታ አብዛኛዎቹ የዓለማችን መሪዎች በግል የፌስቡክና የቲውተር ገጾቻቸውን የሚያሰፍሩት የግል ሃሳባቸውን ነው። አንዳንዴ የቤተሰብ ጉዳዮችንም ያነሳሉ።


በተለይ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ለምርጫ የሚቀርቡ ዕጩዎች ለምርጫ ቅስቀሳና ድጋፍ ይጠቀሙበታል። ከቤተሰቦቻቸው፣ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር የተነሱትን ፎቶግራፎች ያካፍላሉ። እነዚህ የፌስቡክ ገጾች እያንዳንዱ መሪ ከሕዝቡ (ከሚደግፋቸውም ከሚቃወማቸውም) ፊድ ባክ የሚሰበስቡበትም ነው።


ስለዚህ ጉዳይ አብነት ማንሳት ይቻላል። የኢትዮጵያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ሚያዚያ 13 ቀን 2008 ዓ.ም በአማርኛ ቋንቋ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ የሚከተለውን አስፍረው ነበር። “የፖለቲካ አስተሳሰባችን ልዩነት ቢኖረው ችግር የለውም፣ ጤናማ ነው። አንዱ በግራ ብንሄድ እንፈጥናለን፣ ሌላው በቀኝ ያፈጥነናል ሊል ይችላል። አገራችንን ሕዝባችንን መውደድ ግን አማራጭ የለውም። ስለዚህ ፖለቲካችንን ስናራምድ የሀገር የሕዝባችን መውደድ አይለየን። ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!” የሚል የግል ሀሳባቸውን አስፍረዋል። ይህ ጠንካራ መልዕክት እስከትላንት በስቲያ ድረስ 21 ሺ 393 ሰዎች የወደዱት (ላይክ ያደረጉት) ሲሆን 3ሺ 109 ሰዎች ደግሞ የዶክተሩን ሃሳብ ለሌሎች አጋርተዋል። ሌሎች 3ሺ 320 ያህል ሰዎች ደግሞ በድጋፍም በነቀፌታም መልክ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።


ለዶክተሩ የተሰጡት አስተያየቶች ሲታዩ ሰዎች ማን ምንይለኛል ሳይሉ፣ ሳይሸማቀቁ፣ ሳይፈሩ ትክክለኛ ሃሳባቸውን ለመስጠት የሚያስችላቸው መድረክ መፈጠሩን ማሳያዎች አድርጎ መውሰድ ይቻላል። ዶ/ር ቴዎድሮስም ይሁኑ የሾማቸው አካል እንዲህ ዓይነት መሰል ሕዝባዊ አስተያየቶችን በመውሰድ ግብረ መልሱን (ፊድባኩን) በአግባቡ ቢጠቀሙበት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሊረዳቸው ይችላል ተብሎም ይገመታል።


ዶ/ር ቴዎድሮስ ባነሱት ሃሳብ ከተሰነዘሩ አስተያየቶች መካከል ሃሳቡን በማወደስና በማጠናከር የተሰጡ አስተያየቶች የመኖራቸውን ያህል የኢትዮጽያ መንግስት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ሕገመንግስታዊ ነጻነትን ያፍናል፣ ጋዜጠኞችን በመጻፋቸው ብቻ ያስራል፣ ፖለቲከኞችን ያሳድዳል፣ ይከሳል፣ ሠላማዊ ሰልፍ የወጡ ወገኖችን ይደበድባል፣ ይገድላል፣ እናም ይህ ድርጊት የህዝብ መውደድ መገለጫ ነው ወይ የሚል ይዘት ያላቸው ጠንካራ ትችቶችና ነቀፌታዎችን ጎርፈውላቸዋል። እንዲህ ዓይነት የሃሳብ ልውውጦች እያደጉ በሄዱ ቁጥር፣ መደማመጥ፣ መከባበር፣ በሃሳብ ነጻነትና የበላይነት የማመን አቅም በየደረጃው ቀስ በቀስ ይጎለብታል። የመንግስት ባለስልጣናትና የሕዝብ ተመራጮች ተጠያቂነት ባደገ ቁጥር በየደረጃው የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ሙስናና ብልሹ አሠራሮች ይቀረፋሉ። በምትኩም ሕዝቡን የሚወዱና የሚያከብሩ፣ ህዝብንም በተግባር ለማገልገል የቆረጡ መሪዎችን በብዛት ማየትና ማግኘት ይቻላል ተብሎ ይገመታል። 

 

ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ የሚያሰፍሩትን አስተያየት ተከትሎ የሚሰጡዋቸው አስተያየቶችን በሙሉ በአዎንታ የሚመለከቷቸው መሆኑን ጠቅሰው በትላንትናው ዕለት በገጻቸው ላይ ይህንን ማስታወሻ አስፍረው ነበር። “በዚህ ገፅ ላይ አስተያየት በመስጠት፣ በማንበብና መልዕክቶቹን ለሌሎች በማድረስ የተሳተፋችሁ ሁሉ እያበረከታችሁት ያላችሁት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። የአገራችን ጉዳይ የማይገባው ዜጋ የለም። አንዳንዶቻችሁ በውስጥ መልዕክት ልካችኋል። ጊዜ ወስዳችሁ ሰፋ ያለና የተተነተኑ ጽሁፎችን አዘጋጅታችሁ የላካችሁም አላችሁ። ሁላችሁም እንደአቅማችሁና እንደፍላጎታችሁ የገለፃችሁት አስተያየት ትልቅ ግብዐት እየሆነልን ነው። ስለሆነም አስተዋፅኦችሁ የበለጠ አጠናክራችሁ እንደምትቀጥሉ ይጠበቃል።”

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1036 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us