የሰሜን ፓርክ የባለሃብቶች ትኩረት እና የሕዝቡ ቁጣ

Wednesday, 11 May 2016 12:38

ሚያዚያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም ከምሽቱ 1፡30 ገደማ። በሰሜን ጎንደር ደባርቅ ከተማ በሚገኘው ሶና ሆቴል ደጃፍ ያልተለመደ ግርግር ታየ። ሆቴሉ ከአዲስ አበባ ከተማ የሰሜን ፓርክን ለመጎብኘት በሄዱ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተይዞ ነበር። ግርግርና ሁከቱን አየት አድርገው የተመለሱ ጋዜጠኞች ሰላማዊ ሰልፍ መሰል ነገር እየተካሄደ መሆኑን ውስጥ ላሉት ጓደኞቻቸው ሹክ አሉ። ጋዜጠኞቹም በሁኔታው በመደናገጥ የተፈጠረውን ለማየት ወደደጅ ወጡ። በርግጥም በርካታ ሕዝብ እንደተቆጣ አገኙት። ሁኔታው እንዲረጋጋ ከተደረገ በኋላ እንደተሰማው ሕዝቡን ያስቆጣው የሰሜን ፓርክ ውስጥ ለባለሃብቶች የሚሰጡ ቦታዎችን በተመለከተ ግልጽነት ያለው አካሄድ አለመኖሩ ነው። ሕዝቡ ያቀረበው የማብራሪያ ጥያቄ በቂ መልስ ባለማግኘቱ ነው። ከጋዜጠኞቹ ጋር በስፍራው የነበሩት ኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎች ሁኔታውን በማረጋጋት በአጭር ጊዜ መልስ እንደሚሰጡ ቃል ባይገቡ ኖሮ ተቃውሞው ሌላ መልክ በያዘ ነበር።

 

ተቃውሞው ምንድነው?

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም አቀፉ የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ዕውቅና ከተሰጣቸው ቅርሶች አንዱ ነው። በዋንኛነት ፓርኩ ውስጥ ሰፋሪዎች በመኖራቸው ምክንያት የዱር እንስሳቱ አደጋ ላይ መሆናቸው ዩኔስኮ በመግለጽ የኢትዮጽያ መንግስት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰፋሪዎቹን ከፓርኩ ውስጥ ማስወጣት ካልቻለ ከመዝገቡ እንደሚሰረዝው የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ ሕዝቡን በማሳመን ወደደባርቅ ከተማ መልሶ የማስፈር ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ። ይህ ስራ ፓርኩንም የማዳን ተልዕኮ ያዘለ በመሆኑ ሕዝቡ አምኖበት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ብዙዎች የሚስማሙበት ነው። በፓርኩ ውስጥ የሰፈረውን ሕብረሰብ በአንድ በኩል የማስወጣቱ ስራ እየተፋጠነ ባለበት ሂደት በሌላ በኩል ደግሞ አዳዲስ ባለሀብቶች በፓርኩ ውስጥ ሎጆችን ለመስራት ፈቃድ ጠይቀው መሬት ለመረከብ ጫፍ መድረሳቸው መሰማቱ ነው ለቁጣው መቀስቀስ አንድ መንስኤ የሆነው። ያነጋገርናቸው ወገኖች እንዳሉት እኛ የመንግስትን ጥያቄ በማክበር እትብታችን ከተቀበረበት፣ ከኖርንበት፣ ከወለድንበት፣ ከተዳርንበትና ከዳርንበት አካባቢ ለቀን ስንወጣ እኛ የለቀቅነውን መሬት ለባለሃብት መስጠት ማለት ምን ማለት ነው የሚል ጥያቄን ያቀርባሉ። አንዳንዶቹም ጥያቄውን ለጠጥ በማድረግ “መሬቱን ከእኛ ቀምተው ለባለሃብቶች ሸጡት” ሲሉ ተደምጠዋል።

“አንተ ፓርክ ውስጥ መኖርህ አልጠቀመም፣ ውጣ፤ ዋልያ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ ይቀመጥበት” ሲባል እሺ ብለን ከብቶቻችንን በርካሽ ዋጋ ጭምር እየሸጥን ተነሳን። እኛ ይህን ስናድርግ  ግለሰቦች መሬት ወስደው እንዲገነቡ መፍቀድ ምን ማለት ነው? ለዚህ ለዚህ እኛ ለምን ተነሳን? በማለት ጠይቀው ድርጊቱ አምርረው ያወግዛሉ።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ሰሜን ፓርክን መሰረት አድርገው በአካባቢው የተደራጁ አምስት ማህበራት መኖራቸውን ያስታውሳሉ። ዕቃ አከራይ አለ፣ ድንኳን አከራይ አለ፣ የጫኝ ማህበራት አሉ፣ አስጎብኚዎች አሉ፣ ምግብ አብሳዮች አሉ። እነዚህ በሺ የሚቆጠሩ አባላት ያላቸው ማህበራት ህይወታቸው የተሳሰረው ከሰሜን ፓርክ ከሚገኝ የቱሪስት ገቢ ጋር ተያይዞ ነው። እናም የአዳዲስ ሎጆች መምጣት እንጀራችንን ጭምር የሚያሳጣ ነው ብሏል።

 

ምን ያህል ኢንቨስትመንት ታስቧል?

በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳዊድ ሙሜ ዓሊ ተፈርሞ ሰኔ 4 ቀን 2007 ዓ.ም ለዱር እንስሳት አጠቃቀምና ገበያ ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት የተጻፈ መመሪያ አዘል ደብዳቤ እንዲህ ይላል። “የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ እ.ኤ.አ በ1969 ተመስርቶ በ1978 በዓለም ተፈጥሮ ቅርስነት በዩኔስኮ ከተመዘገበ በኃላ በሰው ሰራሽ ጫና ችግሮች የተነሳ እ.አ.አ በ1996 በዓለም የተፈጥሮ ቅርሶች መዝገብ ዝርዝር ውስጥ እንዲካተት መደረጉ ይታወሳል።…..

ነገርግን በብሔራዊ ፓርኩ እየቀረቡ ያሉ የሎጅ ኢንቨስትመንቶች ስለተበራከቱና አንድ አንድ የተፈቀዱ የሎጅ ኢንቨስትመንት ጉዳዮችም እያወዛገቡ ስለሚገኝ ጉዳዩ እልባት እስኪያገኝ ድረስ በሰሜን ተራራዎች የሚቀርቡ የሎጅ ግንባታ ጥያቄዎች እንዳይስተናገዱና ቀደም ሲል ቀርቦ በሂደት ላይ የሚገኙትም ቢሆኑ ከሰኔ 3 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ ባሉበት እንዲቆሙ እንዲደረግ” በማለት ስድስት ፕሮጀክቶችን ይዘረዝራል። እነሱም ውልክፊት ሪዞርት፣ ጃካራንዳ፣ ዋይልድ ኢትዮጵያ፣ ሙለር ማውንቴን፣ ሎንግቪዩ፣ አይናመዳ ናቸው።

“በተጨማሪም ደብዳቤው ሎጅም ቢሆን የስራ እንቅስቃሴና አሰራሩ ሁሉ የፓርኩን ሕልውና የተከተለና ከአካባቢ ጋር የተስማማ መሆኑን ክትትል ተደርጎ ማረጋገጫ ሪፖርት እንዲቀርብ እየገለጽኩኝ ያለዋና ዳይሬክተሩ ዕውቅና ምንም ዓይነት ደብዳቤ እንዳይጻፍና ውሳኔም እንዳይሰጥ በጥብቅ አስታውቃለሁ።”  ይላል።

ይህ የዋና ዳይሬክተሩ የእገዳ ደብዳቤ ከስድስት ወር ቆይታ በኃላ ህዳር 24/2008 በተጻፈ ደብዳቤ እገዳው መነሳቱን በራሳቸው ፊርማ ለዳይሬክቶሬቱ አሳውቀዋል። ይህን ተከትሎ የመሬት ርክክብ እንቅስቃሴ መታየቱ ለአሁኑ የአካባቢውን ህብረተሰብ ተቃውሞ መነሻ ሳይሆን እንደማይቀር የሚናገሩ ወገኖች አሉ።

የመንግሥት ምላሽ ምንድነው?

አቶ ግርማ ቲመር በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ፣ የጥበቃ ቦታዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው። ከሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ሰፋሪዎችን የማስወጣቱ ሒደት ረዥም ታሪክ የነበረው መሆኑን በማስታወስ በአሁን ሰዓት ሰፋሪዎች በራሳቸው ፈቃድ ከፓርኩ ለቀው እየወጡ መሆኑን ያረጋግጣሉ። “ሁለት ዓይነት ሰፋሪዎች የማስነሳት ሕጋዊ አካሄድ አለ። አንዱ በፈቃደኝነት (Voluntary) ሲሆን ሌላኛው በአስገዳጅ ወይንም ያለፈቃድ (In Voluntary) የሚደረግ የማስነሳት ተግባር ነው። ቦታው ሲፈለግ ህብረተሰቡ ዓላማውን ተረድቶ በራሱ ፈቃድ ሊነሳ ይችላል። በሌላ በኩል ፓርኩ ለልማት ሲፈለግ መንግስት ለሰፋሪዎች ተገቢውን ካሳና ጥቅም ሰጥቶ እንዲነሱ የሚያደርግበት ሕጋዊ አካሄድ አለ። በሰሜን ተራሮች ፓርክ የተደረገው ግን ሕብረተሰቡ በፈቃዱ እንዲነሳ ነው። የተሟላ መሰረተ ልማት (መንገድ፣ ትራንስፖርት፣ ውሃ፣ ኤሌክትሪክና የመሳሰሉትን በቅርብ ለማግኘት)፣ እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ሲል ወድዶና ፈቅዶ ያደረገው ሰፈራ ነው።

ይህም ቢሆን ግን መንግስት ለተነሺዎቹ ተገቢውን ካሳ እና በሚሄዱበት አካባቢ ለኑሮ አመቺ ነገሮችን በማመቻቸት ከፍተኛ ወጪና እንቅስቃሴ ማድረጉን ያስረዳሉ። 418 ገደማ ለሚሆኑ አባወራዎች (ተነሺዎቹ ) በደባርቅ ከተማ 40 ሚሊየን ብር የሊዝ ግምት ያለው መሬት መሰጠቱን፣ ከ157 ሚሊየን ብር በላይ በካሳ መልክ መከፈሉን አረጋግጠው ህብረሰተቡን የማስነሳቱ ጉዳይ አሁንም መቀጠሉን ተናግረዋል። አይይዘውም ፓርኮችን ለማልማትና ለመጠበቅ ሪሶሰርስ ያስፈልጋል። ሐብቱ የሚመነጨው ደግሞ ከቱሪዝም ከሚገኝ ገቢ ነው። ይህን ገቢ ለማሳደግ ሲታሰብ ቱሪስቶችን አቆይተው በአግባቡ ሊያስተናግዱ የሚችሉ ሎጆች መኖር ወሳኝ ነው። በአሁኑ ሰዓት በሰሜን ፓርክ ውስጥ ያለው አንድ ሰሜን ሎጅ የሚባል ነው። ሌላው አስፈላጊውን ስታንዳርድ ባያሟሉም በሰሜን ፓርክ አቅራቢያ ደባርቅ ከተማ የሚገኙ ሆቴሎች አሉ። ቱሪስት ጥሩ መስህብ ብቻ ስላለ ለጉብኝት አይመጣም። ደረጃውን የጠበቀ ማረፊያ፣ የተሟላ መሰረተ ልማት ይፈልጋል። አንድ ምሳሌ ልስጥህ አሁን ባለው አንድ ሎጅ በዓመት አምስት ሺ ቱሪስት ይመጣ ከሆነ ተመሳሳይ ወይንም ደረጃቸው ከፍ ያሉ ሌሎች ሶሰት ሎጆች ቢጨመሩ የቱሪስት ቁጥሩ እስከ 15 ሺ ከፍ ሊል ይላል ማለት ነው። ቱሪስት ሲመጣ አካባቢው ይጠቀማል ማለት ነው።

አቶ ግርማ ከሶስት ሳምንት በፊት በደባርቅ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ መካሄዱን ያምናሉ። ይም ሆኖ የሰልፉ መነሻ ሎጆች ሲመጡ ቢዝነሳችን ወይንም ጥቅማችን ይነካል በሚሉ ግለሰቦች የቀሰቀሱት እንጂ ከፓርኩ ውስጥ የወጣው ህብረተሰብ ጥያቄ አይደለም፣ “መንግስት ኢንቨስትመንቱን ይፈልገዋል” በማለት የሰዎቹ እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌለው ያስረዳሉ።

በፓርኩ ውስጥ ኢንቨስትመንት የተፈቀደላቸው ባለሃብቶች ጉዳይ የአካባቢው አስተዳደርም ጭምር አላውቅም ያለበት ሁኔታ መኖሩን ያልሸሸጉት አቶ ግርማ በቀጣይ ከክልል ጀምሮ በየደረጃው በጉዳዩ ዙሪያ ተነጋግረው በመተማመን ስራው በጥንቃቄ የሚከናወንበት ሁኔታ እንደሚኖር ጠቁመዋል።

 

ስለሰሜን ተራሮች ፓርክ

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ይገኛል። በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ውስጥ አምስት ወረዳዎችን አካልሎ ያረፈው ይህ ፓርክ በ1959 ዓ.ም በብሔራዊ ፓርክነት ተመዝግቦ ዕውቅናን ያገኘ ሲሆን በሀገራችን ብቻ ከሚገኙ ብርቅዩ ዕጽዋት፣ አእዋፍ እና አጥቢ እንስሳትን በውስጡ ይዞአል። ዋሊያ የተባለው የዱር እንስሳ ብቸኛ መኖሪያም ነው። በሰንሰለታማዎቹ ሰሜን ተራሮች የታጠረው የሰሜን ፓርክ ራስዳሸን ፣ ዋልያ፣ ቀንድና ቧሂት የተባሉ ተራሮችን ጨምሮ በርካታ ተራሮች ይገኙበታል። በሀገራችን ትልቅ ተራራም የሚገኘው በዚሁ የፓርክ ስነምህዳር ነው።

ይህ ፓርክ በዩኔስኮ አደጋ መዝገብ ውስጥ እንዲገባ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል በፓርኩ ግዛት የሰፋሪ ነዋሪዎች መብዛት፣ የዱር እንስሳት ህልውና በቤት እንስሳት አደጋ ውስጥ መግባት፣ (የውሻዎችና የዋሊያ መዳቀል እንዲሁም በእብድ ውሻ በሽታ መለከፍ ይጠቀሳል) እና የፓርኩን የተፈጥሮ ሐብት በልቅ ግጦሽ መጎዳቱ የመሳሰሉት ይገኝበታል። የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ 412 ካሬ ኪሎሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በሀገራችን በቆዳ ስፋታቸው ትንሽ ከሚባሉት ፓርኮችም መካከል አንዱ መሆኑም ይታወቃል።n

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
867 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us