የመንግሥት በጀት አፈጻጸም በፌዴራል ዋና ኦዲተር ዓይን

Wednesday, 18 May 2016 13:56

 

-    24 መ/ቤቶች ከ221 ሚሊየን ብር በላይ ላወጡት ገንዘብ የተሟላ ማስረጃ አላቀረቡም፣

-    56 መ/ቤቶች ደንብና መመሪያን ሳይከተሉ ከ61 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ ፈጽመዋል፣

-    77 መ/ቤቶች ከ546 ሚሊየን ብር በላይ የግዥ አዋጅ ደንብና መመሪያ በመጣስ ግዥ ፈጽመዋል

 

 

የፌዴራል ዋና ኢዲተር የፌዴራል መንግሥት መ/ቤቶች የ2007 በጀት ዓመት ሂሳብ ኦዲት ትላንት ግንቦት 9 ቀን 2008 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አቅርቧል። ዋና ኢዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በዚሁ ሪፖርታቸው 153 ሂሳብ አቅራቢ ከነበሩ የመንግሥት መ/ቤቶች መካከል 145 መ/ቤቶችን ከ24 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የተቀሩትን ስምንቱን በኢዲት ሰርቪስ ኮርፖሬሽን ኦዲት መደረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በዋናው ኢዲተር መ/ቤት 145 ያህል የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶችና በ294 የወረዳና ከተማ አስተዳደር የፋይናንስ ጽ/ቤቶች ላይ ኦዲት በማድረግ የኦዲት ሪፖርት ማዘጋጀቱን ጠቅሰዋል። በዚህ መሠረት የዋና ኦዲተር ግኝት ከ55 ገጾች በላይ ሪፖርት የያዘ በመሆኑ በጥቂት ርዕሰጉዳዮች ላይ ብቻ የተጠቀሰውን የዋና ኢዲተር ሪፖርት እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

 

የጥሬ ገንዘብ ጉድለት በተመለከተ፣

የጥሬ ገንዘብ ሂሳብ አያያዝና አጠባበቅ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ2 በ3 መ/ቤቶች ብር 196,544.65 የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ተገኝቷል። የጥሬ ገንዘብ ጉድለት የተገኘባቸውም የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ፣ ጅማ ዩኒቨርስቲ እና የፌዴራል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤጀንሲ ናቸው።

 

በተጨማሪም በበጀት ዓመቱመጨረሻ በሂሳብ መግለጫ ሪፖርት የተደረገውና በቆጠራ የተገኘው ጥሬ ገንዘብ መካከል በ6 መ/ቤቶች (ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ አሶሳ ዩኒቨርስቲ፣ ሐሮማያ ዩኒቨርስቲ፣ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ፤ በፌዴራል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤጀንሲ እና በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር-በስልጠና ዋና መምሪያ) ቆጠራው በብር 284,971.53 በማነስ ልዩነት ያታየ ሲሆን፤ በ6 መስሪያቤቶች (ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ፣ ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ፣ ሚዛን ቴፒ፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ እና በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር - በሎጅስቲክ ዋና መምሪያ) ደግሞ ብር 2,034,074.93 ቆጠራው ከመዝገብ በመብለጥ ታይቷል። እንዲሁም በ208 መስሪያቤቶችና በ5 ቅ/ጽ/ቤቶች የተለያዩ የጥሬ ገንዘብና የባንክ ሂሳብ አያያዝ ድክመቶች መኖራቸው በኦዲቱ ተረጋግጧል።

 

የጥሬ ገንዘብና የባንክ ሂሳቦች ላይ ተገቢ ቁጥጥር አለማድረግ ለገንዘብ ብክነት፤ ጉድለትና ምዝበራ የሚያጋልጥ በመሆኑ፤ የጥሬ ገንዘብ ሂሣብ በየወቅቱ ተቆጥሮ ከመዝገብ ጋር እንዲመሳከር፤ በሂሣብ መግለጫ ሪፖርት ላይ የተመለከተው የጥሬ ገንዘብ ሂሣብ በቆጠራ ከተገኘው ጋር ሊመዛዘንና ትክክለኛነቱ ሊረጋገጥ እንደሚገባ፤ በጉድለት የታየው የጥሬ ገንዘብ ሂሳብ ተገቢው እርምጃ ተወስዶ እንዲተካ፣ በማነስ/በመብለጥ የታየው ልዩነትም ተጣርቶ እንዲተካ ወይም ተገቢው ማስተካከያ እንዲደረግ እና የታዩት የጥሬ ገንዘብና ባንክ ሂሳብ አያያዝ ድክመቶች አንዲስተካከሉ አሳስበናል።

 

የውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሣብ

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፋይናንስ አስተዳደር ደንብ ቁጥር 190/2002 አንቀጽ 32 እስከ 35 በተደነገገው መሠረት የሰነድ ሂሳብ በወቅቱ መወራረዱ ሲጣራ በ94 መስሪያቤቶችና በ11 ቅ/ጽ/ቤቶች ብር 2,078,949,440.60 በደንቡ መሠረት በወቅቱ ሳይወራረድ ተገኝቷል።

 

ከዚህ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት፤ የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገለግሎት ብር 342,235,704.80፣ የትምህርት ሚኒስቴር ብር 315,133,460.41፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት ብር 172,191,236.99፣ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ብር 139,258,386.16፣ ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ብር 138,482,895.82፣ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ብር 85,982,359,92፣ የግብርና ቴክኒክ ሙያና ትምህርት ስልጠና ማስተባበሪያ ብር 75,882,513.81፤ ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ብር 69,010,479.00፤ እና በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የአዲስ አበባ ኤርፖርት ብር   67,228,586.69 ይገኙበታል።

 

ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሣቡ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት በወቅቱ ካልተወራረደ ወይመ ካልተሰበሰበ በቆየ ቁጥር የመሰብሰብና ወደ ሀብትነት የመለወጥ እድሉ ተዳክሞ ባክኖ የሚቀር በመሆኑ መ/ቤቶቹ የፋይናንስ ደንብና መመሪያዎችን ተከትለው ገንዘቡን እንዲሰበስቡ ወይም እንዲያወራርዱ አሳስበናል።

 

የተሟላ የወጪ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ ተመዝግቦ የተገኘ ሂሣብ

በወጪ ለተመዘገቡ ሂሣቦች የተሟላ ማስረጃ መቅረቡን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፣ በ24 መ/ቤቶች የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ ብር 221,879,238.59 በወጪ ተመዝግቦ ተገኝቷል።

 

የተሟላ የወጪ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ ከመዘገቡት መስሪያቤቶች ትምህርት ሚኒስቴር ብር 95,526,864.83፣ ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ብር 26,417,436.86፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብር 10,000,000.00፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ብር 8,601,445.18 ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ብር 5,100,434.00፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ብር 4,646,850.00 ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

 

ተሟልተው ካልቀረቡት ማስረጃዎች መካከል ከዕቃ አቅራቢው የተሰጠ ተገቢ ማስረጃ ሳይቀርብ፣ በቀረበው የክፍያ ጥያቄ መሠረት የተፈፀመ እንጂ የተከናወነውን ሥራ በሚያሳይ ዝርዝር ማስረጃ ሳይደገፍ፤ የመንግሥት ሰራተኞች የውሎ አበል መጠየቂያና መፍቀጃ ቅፅ አንድ ሳይዘጋጅ፣ የዱቤ ሽያጭ እንጂ የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ ያልቀረበ መሆኑ፣ የቀረቡት ተራ ደረሰኞች ማለትም የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር የሌላቸው እና በባንክ በኩል ገንዘቡ ተልኮ ሥራ ላይ ስለመዋሉ ወይም ለተቀባዩ ስለመድረሱ የሚገልጽ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ የተመዘገቡ ሂሳቦች ጐላ ያሉት ናቸው።

 

ማንኛውም ሂሣብ በወጪ ከመመዝገቡ በፊት በፋይናንስ አስተዳደር አዋጁ፣ ደንቡና መመሪያ መሠረት ማስረጃዎች መሟላታቸው እንዲረጋገጥ፣ ያልተሟሉት ማስረጃዎች እንዲሟሉና ለወደፊቱም ተገቢው ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አሳስበናል።

 

ደንብና መመሪያን ሳይከተሉ ያለአግባብ የተፈፀሙ ክፍያዎች

ኦዲት በተደረጉት መ/ቤቶች ደንብና መመሪያ ተጠብቆ ክፍያ መፈጸሙ ሲጣራ በ56 መስሪያቤቶችና 4 ቅ/ጽ/ቤቶች ብር 61,397,293.70 ከደንብና መመሪያ ውጭ አለአግባብ ተከፍሎ ተገኝቷል።

 

ከደንብና መመሪያ ውጪ አለአግባብ ክፍያ ከፈፀሙ መስሪያቤቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ፣ ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ብር 15,062,986.00፣ ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ብር 9,980,512.35፣ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ብር 6,837,046.79 ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ብር 5,329,915.35፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት ብር 2,261,095.55፣ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ብር 3,798,720.53 እና የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ብር 2,087,760.45 ሲሆኑ፤ ከምክንያቶቹም ከሚመለከተው አካል ሳይፈቀድ የትርፍ ሰዓት ክፍያ መፈጸም፣ ለሠራተኞች አበል፣ ደመወዝና ማበረታቻ ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ በመፈጸም፤ ሰራተኞች መስክ ሳይወጡ የውሎ አበል በመክፈል፣ የምግብና መኝታ አገልግሎት ተከፍሎ እያለ በተጨማሪ የውሎ አበል በመክፈል፣ የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ሳይፈቅድ የኃላፊነት አበልና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ክፍያ መፈጸም እና መስሪያቤቱን ለለቀቁና ለትምህርት ውጪ ሄደው በዚያው ለቀሩ ሰራተኞች ለበርካታ ወራት የደመወዝ ክፍያ መፈጸምና በመሳሰሉት ምከንያቶች ወጪ የተደረጉ መሆናቸው በኦዲቱ ተረጋግጧል።

 

በመሆኑም ከደንብና መመሪያ ውጪ ያለአግባብ የተከፈለው ሂሣብ ተመላሽ እንዲሆነና ለወደፊቱም ደንብና መመሪያዎች ተከብረው መሰራት እንዳለበት ኦዲት ለተደረጉት መስሪያቤቶች አሳስበናል።

 

የግዢ አዋጅ፤ ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ የተፈጸሙ ግዢዎች

የዕቃና አገልግሎት ግዢ በመንግሥት ደንብና መመሪያ መሠረት የተፈጸመ መሆኑን ለማጣራት ኦዲት ሲደረግ፣ በ77 መስሪያቶችና 5 ቅ/ጽ/ቤቶች ብር 546,059,783.00 የመንግሥትን የግዢ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ያልተከተለ ግዢ ተፈጽሞ ተገኝቷል።

 

ከግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያዎች ውጭ ግዥ ከፈጸሙ መስሪያቤቶች መካከል ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ብር 161,399,723.74፣ አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብር 81,187,004.35፣ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ብር 44,669,141.93፣ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ብር 33,285,467.58፣ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ብር 25,961,711.36፣ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ብር 24,639,473.79፣ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ብር 20,278,574.57፣ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ብር 17,052,194.00፣ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ብር 1,187,734.36 ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

 

ከዚሁ በተጨማሪ በ6 መስሪያቤቶች ያለውል ስምምነት የብር 21,808,781.25 ክፍያ ፈጽመው ተገኝቷል።

 

ካልተከተሏቸው የግዥ ደንብና መመሪያዎች ውስጥ ጨረታ በማውጣት ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ግዥዎች ያለጨረታ በመግዛት፣ በዋጋ ማወዳደሪያ /ፕሮፎርማ/ አማካኝነት መፈጸም ያለበትን ግዥ ፕሮፎርማ ሳይሰበስቡና ውድድር ሳየደረግ ግዥ መፈጸሙ እና የተለያዩ ግዥዎችን ከአንድ አቅራቢ ብቻ መፈጸም የሚሉት ይገኙበታል።

 

የግዢ መመሪያንና የተጨማሪ እሴት ታክስ ደንቦችን ሳይከተሉ ግዢ መፈጸም ለምዝበራና ለጥራት መጓደልና ለግብር ስወራ ጭምር የሚያጋልጥ በመሆኑ፣ የመንግሥት ግዢ ደንብና መመሪያን አክብረው በማይሰሩ መስሪያቤቶች ላይ የተጠናከረ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል።

 

የበጀት አጠቃቀም

ከበጀት በላይ ወጪ የሆነ ሂሣብ

መስሪያቤቶች የተፈቀደላቸውን በጀት በአግባቡ መጠቀማቸውን ለማረጋገጥ በተደረገው ኦዲት በ41 መስሪያቤቶች በልዩ ልዩ የሂሳብ መደቦች ከተፈቀደላቸውና ከተደለደለው በጀት በላይ በደንቡ መሠረት ሳያስፈቅዱና በጀት ሳያዛውሩ ከመደበኛ በጀት ብር 621,319,554.74 እና ከካፒታል በጀት ብር 124,831,405.18 በድምሩ ብር 746,150,959.92 ከተደለደለው በጀት በላይ ወጪ የሆነ ሂሳብ ተገኝቷል።

 

ለልዩ ልዩ የሂሳብ መደቦች ከተፈቀደላቸው በጀት በላይ በደንቡ መሠረት ሳያስፈቅዱና ሳያዛውሩ ሥራ ላይ ካዋሉት መስሪያቤቶች መካከል የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ብር 186,511,080.05፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ብር 123,560,176.47፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ብር 54,131,615.00፣ ሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ብር 43,010,493.00፣ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ብር 39,080,757.06፣ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ብር 35,861,587.36፣ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ብር 35,343,027.00 እና ዲላ ዩኒቨርሲቲ ብር 35,110,366.58 ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

 

ከዚህ በተጨማሪም የመንግሠት ፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ ለስራው ምንም በጀት ሳይያዝ ብር 454,342,50 ወጪ አድርጎ ተገኝቷል።

 

በጀት ሳይፈቀድ ወይም ዝውውር ሳይደረግ ወጪ ማድረግ በፋይንስ አስተዳደር አዋጅ የተከለከለ በመሆኑ መስሪያቤቶች በፋይናንስ አስተዳደር አዋጅና ደንብ እንደዚሁም በበጀት አዋጁ መሠረት የተፈቀደላቸውን በጀት የተቀመጠውን አሠራር በመከተል በተገቢው መንገድ የበጀት ዝውውር በማድረግ አስፈቅደው ሥራ ላይ ማዋል እንዳለባቸው አሳስበናል። ነገር ግን ይህ ጉዳይ እየተሻሻለ ባለመሆኑ ም/ቤቱና የገንዘበና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ተገቢውን አፋጣኝ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል።n

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
876 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us