ሸራተን አዲስ ሆቴል ከቀድሞ ሠራተኞቹ ጋር የነበረውን የፍርድ ቤት ክርክር አሸነፈ

Wednesday, 25 May 2016 12:48


ከሸራተን አዲስ ሆቴል የተሰናበቱ 65 ያህል ሠራተኞች አለአግባብ ከሥራ ተሰናብተናል በሚል በሆቴሉ ላይ መሥርተውት የነበረው ክስ ከፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ጀምሮ እስከሰበር ሰሚ ችሎት ክርክር ሲደረግበት ከቆየ በኋላ በሸራተን ሆቴል አሸናፊነት ተደመደመ። ሠራተኞቹ እንዲከፈላቸው የተወሰነላቸው ካሳ አፈፃፀም በሂደት ላይ የሚገኝ ሲሆን አንዳንድ ሠራተኞች በቀጥታ የካሳ ጥያቄያቸውን ለሆቴሉ በማቅረብ ክፍያቸውን በመውሰድ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

 

የሸራተን አዲስ ሆቴል ሠራተኞች የነበሩት እነ ዳዊት ሳሙኤል 65 ሰዎች በፈፀሙት ጥፋት ምክንያት ድርጅቱ የሥራ ውላቸውን በማቋረጥ ከሥራ እንዲሰናበቱ አድርጓል። ሠራተኞቹም ያላግባብ ሕገወጥ በሆነ መንገድ ከሥራ ተባረናልና ወደሥራችን እንመለስ በማለት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ክስ መስርተው ነበር።

 

የሸራተን ሆቴልም የክስ ማመልከቻ ሲደርሰው በጠበቆቹ አማካኝነት ባቀረበው መልስ ሠራተኞቹ የተባረሩት ባግባቡ ነው ወደስራ ሊመለሱ አይገባም ስለዚህ ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባዋል የሚል ክርክር አቅርቦ ፍ/ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር እና ማስረጃዎች ካዳመጠ በኋላ የካቲት 20 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት በመ. ቁጥር 157/49 በሆነው መዝገብ የሠራተኞችን ወደ ስራ መመለስ ጥያቄ ውድቅ አድርጎ ወደስራ ልትመለሱ አይገባም፣ ካሣ ሊከፈላችሁ ግን ይገባል በማለት ውሳኔ ሰጥቷል።

 

ሠራተኞቹም ይህንን የፍ/ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ይግባኛቸውን በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት አቅርበው ፍ/ቤቱም ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ በመ.ቁጥር 116675 ሐምሌ 27 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ በማድረግ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ውሳኔንን አጽድቆታል።

 

አሁንም ሠራተኞቹ ይህንን የሁለቱን ፍ/ቤቶች ውሳኔ በመቃወም ጉዳያቸውን በይግባኝ በፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበው ይህ ችሎት ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ የበታች ፍ/ቤቶች የሰጡአቸው ውሳኔዎች መሠረታዊ የህግ ስህተት የሌለባቸው ስለሆነ ሠራተኞቹ ያቀረቡት አቤቱታ ተቀባይነት የለውም በማለት በመ.ቁጥር 117178 ጥር 25 ቀን 2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውሳኔ ሰጥቷል።

 

እነኝህም ሠራተኞች ይህንኑ የፍትህ አካላቱ የሰጡአቸውን ውሳኔዎች አምነውና ተቀብለው አንዳንዶቹ ወዲያው በፍ/ቤቱ የተወሰነባቸውን ካሳ ከድርጅቱ ቀርበው ሲወስዱ፣ አብዛኛዎቹ ግን ፍ/ቤቶቹ በሰቱአቸው ውሳኔዎች መሠረት የካሳው ገንዘብ እንዲከፈላቸው የአፈፃፀም ክስ መስርተው ጉዳዩ በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመታየት ላይ ይገኛል በመሠረቱ ወደ ፍ/ቤት ሄደው ክፍያው እንዲሰጣቸው ከመጠየቅ ይልቅ እንደሌሎች ጓደኞቻቸው ቀርበው ቢጠይቁ የሚከለክላቸው አካል ያልነበረ መሆኑን ሆቴሉ ገልጿል።

 

የጉዳዩ አመጣጥና አሁን ያለበት ሁኔታ ይህን የሚመስል ሆኖ ሳለ አንዳንድ ጋዜጦች ሠራተኞቹ ከኢትዮጵያ ውጭ ባለአካል አማካኝነት እንዳሸነፉ እና ሸራተንም እንደተሸነፈ ተደርጎ የሚናፈሰው ወሬ ስህተት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

 

በአንዳንድ ጋዜጦች ላይ እንደተገለጸው ድርድር ተካሂዷል የተባለው በስታርውድና በአለም አቀፍ የሠራተኞች ማህበር ፌዴሬሽን መካከል ሲሆን ሸራተን አዲስ ሆቴል በዚህ ድርድር ወቅት ተሳታፊ አይደለም፣ ተደራዳሪም አልነበረም።

 

ሸራተን አዲስ ሆቴል በሚድሮክ ኃ/የተ/የግ ማህበር ሥር ከተቋቋሙት ድርጅቶች መካከል አንዱ ሲሆን የሚመራውና የሚተዳደረውም በሀገራችን ህግና የፍትህ ሥርዓት አማካኝነት ነው። ከዚህ ውጭ ሌላ የውጭ ሀገር አካል በሚሰጠው ውሳኔ እንዲገዛ ወይም እንዲፈፅም የሚገደድበት አንዳችም አይነት ሥምምነትም ሆነ ህግ የለም። ስታርውድና አለም አቀፍ የሠራተኞች ፌዴሬሽን ሊስማሙ ይችላሉ። ይህ መብታቸው ነው። ይህ ስምምነታችን ግን የሀገራችንን ህግና የፍ/ቤቶችን ውሳኔ የሚሽር አይደለም። ቢሆንም አይገባውም። እነርሱም በስምምነታቸው መሠረት ሸራተን ሆቴል እንዲፈጽም የላኩት አንዳችም ውሳኔ የለም፣ ሊኖርም አይገባም። ለነገሩ የስምምነቱ ይዘት ነው ተብሎ እየተገለፀ ያለው የካሳ ክፍያን በሚመለከት እንጂ ወደሥራ ሊመለሱ ይገባል የሚል እንደሌለበት ግልጽ ነው።

 

የሸራተን አዲስ ሆቴል ከቀድሞ ሠራተኞቹ ጋር በገጠመው የፍ/ቤት ክርክር ዋና አላማ ህግና ሥርዓትን ተከትሎ የተሰናበቱ ሠራተኞች ወደሥራ እንዳይመለሱ ማድረግ ነበር። ይህንን ደግሞ በሀገራችን የፍትህ መድረክ አረጋግጦ በአሸናፊነት ተወጥቷል። ማንኛውም ግለሰብ ሆነ አካል ይህንን የፍ/ቤቶችን ውሳኔና ሕግ ሊያከብር እና ሊቀበል ግድ ይለዋል ሲል ከሸራተን አዲስ ሆቴል የደረሰን መግለጫ አሳስቧል።  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
589 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us