የፈተና መሰረቅ እና የማህበራዊ ሚዲያዎች መንታ ዕይታ

Wednesday, 01 June 2016 12:19

ጃዋር መሐመድ የሚባል የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ፖለቲከኛ በሳምንት በፊት በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በቅርቡ ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ የብሔራዊ ፈተና እንዲራዘምላቸው የጠየቁ ወገኖች ተገቢ ምላሽ አላገኙም በሚል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ለሰረቀ ሰው የ100 ሺ ብር ሽልማት ማዘጋጀቱን ሲያውጅ ማንም ከቁብ የቆጠረው አልነበረም። ባለፈው ሳምንት እሁድ ለሊት ለሰኞ አጥቢያ ፈተናው ተሰርቆ በእነጃዋር አማካይነት ከእነመልሱ በማህበራዊ ድረገጾች ሲረጭ ግን በሁሉም ወገኖች ዘንድ ድንጋጤን ፈጥሯል። ይህ ጉዳይ መንግስትን አጥብቆ የሚቃወመው የጃዋር ጉዳይ ብቻ አድርጎ መመልከት አይቻልም። በመላ ሀገሪቱ ከ254 ሺ በላይ ተማሪዎች የ12ኛ መልቀቂያ (የዩኒቨርሲቱ መግቢያ) ፈተና ለመቀመጥ ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርጉ ከርመው ለፈተናው እየተዘጋጁ ያሉበት ወቅት ላይ አቅሙ፣ ሥልጣኑ ባላቸው ሰዎች አማካይነት ፈተናው ተሰርቆ የተማሪዎችን ድካም መና ማስቀረት በቀጥታ መንግስትንም የሚመለከት ጉዳይ ነው። በፈተና ድርጅት ውስጥ ምን ዓይነት አሰራር አለ? የፈተና ሕትመት የቱን ያህል ሚስጢራዊነቱ የተጠበቀ ነው? የቱ ጋ ነው ብልሽቱ ያለው? በመንግሥት ገንዘብ፣ ጊዜ እንዲሁም በተማሪዎችና በወላጆች ሞራል ላይ ለደረሱ ጉዳቶች ተጠያቂው ማንነው? የሚለው በቂ መልስ ማግኘት ይኖርበታል።

ጉዳዩ መከሰቱ ከታወቀ በኋላ የትምህርት ሚኒስትር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ሰኞ ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል። ፈተናው እንዲቋረጥ በመደረጉ ወላጆችና ተማሪዎችንም በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል።

ሚኒስትሩ በዚሁ መግለጫቸው ኮድ 14 የሚባለው የእንግሊዝኛ ፈተና ከነመልሱ ተሰርቆ በተለያዩ ድረገጾች መሰራጨቱን አምነዋል። ለዚህም ተጠያቂ ያደረጉት «ሞራል የጎደላቸው» ያሏቸውን ያልታወቁ ሰዎችን ነው። ምትክ ፈተናም በአጭር ጊዜ ተዘጋጅቶ እንደሚቀርብም አስታውቀዋል።

ባለፉት ሁለት ቀናት ጉዳዩ በማህበራዊ ድረገጾች በከፍተኛ ደረጃ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። አብዛኛዎቹ ጦማሪዎች /ብሎገሮች (ኢህአዴግን ይደግፋሉ) የሚባሉት ጭምር ከጥፋቱ ጋር ተያይዞ መንግስትን  ተችተዋል። እስቲ አንዳንዶቹን አለፍ አለፍ ብለን እንመልከታቸው።

በፍቃዱ ዘሓይሉ የተባለ ጸሐፊ በፌስቡክ ገጹ ላይ የሚከተለውን አስፍሯል።

«ጉዳዩ ትግሉን የመቀበል ወይም ያለመቀበል ነው። ስርቆት ነውር ነው። ግድያ ደግሞ ጭራሽኙ ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው። የሰው ነፍስ ለማትረፍ የተፈጸመ ስርቆት ለእኔ ቅዱስ ስርቆት ነው» ብሏል።

ዳንኤል ብርሃነ የተባለ ብሎገር በበኩሉ «የ12ኛ ክፍል ፈተና ላይ የተፈጸመው ጥቃት ለምን እንደምቃወም» በሚል ርዕስ ይህን አስነብቧል።

1. በኦሮሚያ በነበረው ተቃውሞ ምክንያት በጣም ሊጎዱ የሚችሉ አካባቢዎችን ከደርዘን በላይ ወረዳዎች አስከሐምሌ እንዲራዘምላቸው ተደርጎ ነበር። ስለዚህ ያ ሰበብ አያስኬድም።

2. ሊራዘምለት ሲገባ የቀረ ወረዳ አለ ቢባል እንኳን ከመንግስት ወይንም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ሂሳብ የምታወራርድበት መንገድ ትፈልጋለህ እንጂ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ልጆችን አታጠቃም። እኛ ሰፈር ወረርሽኝ ገብቶ መንግስት ችላ ቢለው፣ መንግስት ላይ ግፊት ለማድረግ በሚል ሰበብ በሀገሪቱ በሚሉ አንትራክስ አላሰራጭም።

3. በሺዎች የሚቆጠሩ ፈታኞችና ት/ቤቶች በሚሳተፉበት ሀገራዊ ፍጻሜ ውስጥ ሁሌም ቢሆን ሌባ አይጠፋም። ነገርግን ኃላፊነት የሚሰማን ሰዎች ፊት ስለምንሰጣቸው ጥፋታቸው ውስን ይሆናል። የዛሬው ክስተት ልዩ የሚያደርገው ሌብነቱን ሊያበረታቱ የሚፈልጉ ግለሰቦች መፈጠራቸው ነው።

4. ለ12ኛ ክፍል ፈተና ስዘጋጅ ምን ያህል የስሜት ውትረት ውስጥ እንደነበርኩኝ አስታውሳለሁ። የፈተና ዋዜማ የት እንደነበርኩ የትኛውን ክፍል ሳነብ እንደነበር የትኛው ክፍል ደግሞ ላንብብ አላንብብ ብዩ ሳመነታ እንደነበር አስታውሳለሁ። በማግስቱ ፈተናው ቢሰረዝ ኖሮ ተመልሼ ተመሳሳይ ዝግጅት ለማድረግ ሞራል እንደሚያንሰኝ እርግጥ ነው። እንዲያውም ውጤቴ ይጎዳ ነበር። ከመጀመሪያው እንዲህ ዓይነት ውጥረት ውስጥ ያልገባ ተማሪ ደግሞ ጊዜ ስለጨመርክለት የሚያደርገው ዝግጅት አይኖርም። ስለዚህ በፈተናው ስረዛ ሚጠቀም ይኖራል ማለት አንድም የኢትዮጵያን ፈተና ባህርይና ውጥረት አለማወቅ አልያም ራስን ማታለል ነው።

5. በዚህ ፈተና የሚሳተፉ ልጆች ሁሉም የተመቻቸው ወይንም የመካከለኛው መደብ ቤተሰብ አባላት አይደሉም። ለዚህ ፈተና ዝግጅት ተብሎ አባቱ ሥራ ከማገዝ ፋታ የተሰጠው ልጅ፣ የጓዳ ስራ የቀነሰላት ልጅት፣ ወዘተ እንደገና ለሳምንታት ፋታ ገኛሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። «የእናንተ ፈተና ደግሞ አይልቅም ወይ» ነው የሚባሉት።

ለማንኘውም በዚህ አጋጣሚ የፈተናውን ሚሲጢራዊነት አጠባበቅ ሥርዓት ላይ ሙሉ ፍተሻ ሊደረግ ይገባል።

አብዱራህማን አህመዲን የተባሉ ኢዴፓን በመወከል የቀድሞ የፓርላማ አባል የነበሩ እንዲህ ይላሉ። «የፈተናው መጥፋት ቶም እና ጄሪን አስታወሰኝ። ቶም አንዳንድ ጊዜ ጄሪን የሚፈልገው ራሷን በእጁ ብድግ እያደረገ ነው። ፈተናው የተፋው ኢህአዴግ ጉያ ውስጥ ነው። ኢህአዴግ ወደሌላ አቅጣጫ ከመሄዱ በፊት ውስጡን ይፈትሽ!»

መንግሥታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰኞ ዕለት ዕትሙ «ፈተናው እንዴት ተሰረቀ? ተጠያቂነት ይኑር!» በሚል ርዕስ ጠንከር ያለ መልዕክት ጽፏል። «…ድርጊቱ ጥራትና ብቃት ያለው ትውልድ ለመገንባት የሚደረገውን ጉዞ የሚያደናቅፍ አንድ ፈተና ነው» ካለ በኃላ ፈተናው የትና እንዴት ተሰረቀ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መስጠትና ተጠያቂውን መለየት እንደሚያስፈልግ ጽፏል።

ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ በበኩሉ «ምክንያት (Cause) አልባየ "ነጻነት" ትግል ሁሌም በዚህ መልኩ ነው የሚገለጸው:: ጃዋር ነገሩን እንደ አንድ አመርቂ "የነጻነት ትግል ግኝት" ቆጥሮ የኔ የትግል ውጤት ነው ብሎ ፌስቡክ ላይ እየፎከረ ነው:: ጃዋር ሆይ! ከስታንፎርድ እስከ ኮሎምቢያ ድረስ ተምረህ ያገኘኸው "እውቀት"፣ በተወለድክበት ቀዬ ያሉ ታናናሾችህን ኮሌጅ የመግባት ህልም ለማጨናገፍ ካዋልከው:: "ትግልህ" በእርግጥም cause አልባ ለመሆኑ ከዚህ በላይ ማስረጃ የለም»።

የኦሮሚያ ክልል ኮምኒኬሽን ቢሮ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ በየአመቱ ሚሊየን የኦሮሞ ልጆች የትምህርት ዕድል እንደሚያገኙ ጠቁሞ «አስነዋሪ» ያለው ድርጊት እንደ ሌሎች የአገሪቱ ህዝቦች ልጆች ሁሉ የኦሮሞ ልጆችም ተጠቃሚ እንዳይሆኑ የተፈፀመ ወንጀል ነው ካለ በኃላ አጥፊዎቹ ለፍርድ ቀርበው አስፈላጊውን ቅጣት ሊያገኙ ይገባል ሲል ይደመድማል።

ማስረሻ ማሞ የተባለ ብሎገር ስሜቱን እንዲህ በስነግጥም ይገልጸዋል።

«ከፈተና አድነን ነበረ ጸሎቴ ዘወትር ጠዋት ማታ

እንደበቆሎ እሸት አገር ተሸልቅቃ ከንፈሬ ላይ ሟሙታ

ከፈተና ሽሽት ስሮጥ እየዋልኩ ስሮጥ እየነጋ

በጠራራ ጸሀይ ፈተና ተሰርቆ ፈተና ፍለጋ»

በመጨረሻም የተቋረጠው ፈተና ከሰኔ 27 እስከ 30/2008 ዓ.ም እንደሚሰጥ ትምህርት ሚኒስቴር በራዲዮ ፋና በኩል ትላንት ይፋ ያደረገ ቢሆንም በመካከሉ የሚከበረው የረመዳን በዓል ጉዳይ ሌላ ጥያቄ ይዞ ብቅ ብሏል። ምናልባትም በዚህ ምክንያት ትምህርት ሚኒስቴር የፈተና ቀን ለውጥ ሊያደርግ እንደሚችል የብዙዎች ግምት ሆኗል።n

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
1845 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us