የመንግሥታዊው የሰብዓዊ መብት ኮምሽን ሪፖርት ሲቃኝ

Wednesday, 15 June 2016 12:43

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮምሽን ከኦሮሚያና ፊንፊኔ ዙሪያ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በአንዳንድ አካባቢዎች እንዲሁም በሰሜን ጎንደር ዞን የቅማንት ብሄረሰብ የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የተከሰቱ ግጭቶችን መርምሮ ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ሪፖርት አቅርቧል።

ኮምሽነር ዶ/ር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር ባለፈው ሳምንት ዓርብ ዕለት ለፓርላማው በንባብ ያቀረቡት ሪፖርት እንደሚለው ምርመራው የተካሄደው መርማሪ ቡድን ችግሮቹ ወደተከሰቱባቸው አካባቢዎች በመላክ ተጎጂ ወገኖችን፣ ሕብረተሰቡን፣ የፖሊስና መከላከያ ኃይል፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና እንዲሁም የሆስፒታል ምንጮችን በማግኘት የተከናወነ ነው። ሪፖርቱ የችግሩን መንስኤ፣ ያስከተለው ጉዳት እና የኮምሽኑን ምክረሃሳብ የያዘ መሆኑን ጠቅሰዋል።

 

 

የኦሮሚያ ክልል ግጭትን በተመለከተ

የኮምሽኑ ሪፖርት በጥቅሉ የኦሮሚያ ግጭት መነሻ ከዚህ ቀደም መንግሥት ከሚለው ጋር በተዛመደ መልኩ የመልካም አስተዳደር ችግር መሆኑን ያስቀምጣል። ሕዝቡ በተለይ የጋራ ማስተር ፕላኑን እና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ማንሳቱ ሕገመንግሥታዊ መብቱ እንደነበረ ማረጋገጫ ይሰጥና ይህን አጋጣሚ ግን ሌሎች ጸረ ልማት ኃይሎች ባልተገባ መንገድ ስላቀጣጠሉት ለሁከትና ብጥብጥ ብሎም ለሰው ሕይወትና ለንብረት መውደም መንስኤ መሆን እንደቻለ ያትታል።

በኦሮሚያ ክልል በ10 ዞኖች በመልካም አስተዳደር ረገድ ሕዝቡ ካነሳቸው ችግሮች መካከል የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ በእኩልነትና በፍትሐዊነት እየተሰጠ አለመሆኑ፣ ፍትሕ የማግኘት መብት አለመከበሩ፣ የግብር አከፋፈል ከመመሪያ ውጪ መተግበሩ፣ የመሬት ወረራ መስፋፋቱ፣ የመንግሥት ዕቅዶችና ፖሊሲዎች ለሕዝቡ በተብራራ መልኩ በወቅቱ መቅረብ አለመቻሉ ወይንም አሳታፊነት መጓደሉ፣ የመሠረተ ልማት (መብራት፣ ውሃ..) የመሳሰሉ ጉድለቶች መባባስ፣ ጥቂት የአመራር አባላትና ተባባሪዎቻቸው በመሬት ዘረፋ ላይ መሰማራት፣ የመብት ጥሰት ፣ ሙስናና በብልሹ አሠራር መባባሱ፣ በዚህም የሚገመገሙ አመራሮች ሕጋዊ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ከቦታ ቦታ የማዘዋወር ሥራ መከናወኑ ቅሬታ ማስከተሉ፣  ለልማት ተነሺ የሆኑ እርሶአደሮች በበቂ ሁኔታ የሚቋቋሙበትና ካሳ የሚያገኙበት ሁኔታ ችግሮች መኖራቸው፣ ከህገመንግስቱ ድንጋጌ ውጪ የአርሶአደሩ መሬት የሚሸጥበት አሰራር መኖሩ፣ ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ ወጣቶች በአጠቃላይ ስራአጥ ወጣቶችን ለማገዝና ወደስራ ለማስገባት እንዲሁም በአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፎች ተደራጅተው ለመስራት የሚያደርጉት ጥረት በተገቢው መንገድ እገዛ አለመደረጉ እና የመሳሰሉ ችግሮች በኮምሽኑ ተዘርዝረዋል።

ከምንም በላይ ደግሞ እነዚህና መሰል ችግሮች በየጊዜው ከሕዝቡ ቢቀርቡም በየደረጃው ያሉ አካላት ለጥያቄዎቹ ተገቢውን መልስ በወቅቱ መስጠት አለመቻሉ ለግጭቱ መነሳት እንደአንድ ምክንያት ተቀምጧል።

በኮምሽኑ ሪፖርት መሠረት በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው ግጭት በአጠቃላይ 173 ሰዎች ሲሞቱ 956 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሷል። በኦሮሚያ ክልል ከሞቱት ወገኖች መካከል 14 ያህሉ የጸጥታ ኃይል አባላት ሲሆኑ 14 የሚሆኑት የአስተዳደሩ አመራሮች ናቸው።

ኮምሽኑ ባካሄደው ምርመራ ከሕዝቡ የቀረቡትን ጥያቄዎች የተለያየ ዓላማ ያላቸው በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አሸባሪ ተብለው የተፈረጁና እንዲሁም በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግሩን በማቀጣጠል ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው ጠቅሷል። ይህን ከባድ አደጋ ለመቆጣጠር የጸጥታ ኃይሎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን የሚያትተው ይህ ሪፖርት በጸጥታ ኃይሉ በኩል የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝና ሕግን መሠረት ያደረገ ነበር ብሏል።

ኮምሽነር ዶ/ር አዲሱ በዚሁ ሪፖርታቸው የተጎዱ ወገኖች የሚቋቋሙበት፣ የፈረሱ የእምነት ተቋማት የሚገነቡበት፣ በየደረጃው ያሉ አጥፊዎች ለሕግ የሚቀርቡበት ሁኔታ እንዲመቻች በሪፖርታቸው ላይ ጠይቀዋል።

 

የቅማንት ብሄረሰብ የማንነት ጥያቄ ተከትሎ ስለደረሰው ግጭት

በሰሜን ጎንደር ዞን የቅማንት ብሄረሰብ የማንነት ጥያቄ ማቅረቡ ሕገመንግስታዊ እንደነበር የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮምሽን ሪፖርት ይጠቅሳል። ይህ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በክልሉ መንግስት እንዲሁም በፌዴራሉ የፌዴሬሽን ም/ቤት በኩል የተወሰዱት እርምጃዎች ግን ደካማ መሆን ለግጭቱ መፈጠር አይነተኛ ምክንያት መሆኑን አመላክቷል። እንዲሁም አጥኚ ቡድን ተቋቁሞ ጥያቄው የጥቂት ቋንቋውን ተናጋሪ ግለሰቦች አድርጎ ለማሳየት መሞከሩ ትክክል እንዳልነበር፣ ሕገመንግስቱ ቋንቋን መሠረት ቢያደርግም ቋንቋውን አንድም ሰው ተናገረው ወይም ከዚያ በላይ ሕገመንግሥቱ ያስቀመጠው ነገር እንደሌለ ተመላክቷል።

ግጭቱ ከተፈጠረ በኃላ ከሰሜን ጎንደር ዞን የተሠማራው ልዩ ኃይል በተለይ በአይከልና በማወራ ቀበሌዎች በወሰደው እርምጃ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሞትና የመቁሰል አደጋ እንዲከሰት ማድረጉ ተመጣጣኝና ህጋዊ ምክንያት የሌለው ነበር ብሎታል።

በኮምሽኑ ሪፖርት መሠረት ከቅማንት የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በተከሰተ ግጭት በአጠቃላይ 97 ሰዎች ሲሞቱ 86 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላልና ከባድ የመቁሰል አደጋ ደርሷል ብሏል።

ኮምሽኑ በሪፖርቱ ላይ ባቀረበው ምክረሃሳብ የህዝቡ ጥያቄ አግባብ ባለው ሕግ መሠረት እንዲፈታ፣ ችግሩን በማባባስ ረገድ ሚና የነበራቸው አካላት ጉዳያቸው ተጣርቶ ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል። ሕገመንግሥቱ ለሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች እኩል ቦታ የሚሰጥ ቢሆንም ከዚህ በፊት የተለያዩ በደሎች ለደረሰባቸው ብሄረሰቦች ልዩ ጥበቃና ድጋፍ ሊደረግላቸው አንደሚገባ በሚያዘው መሠረት የአማራ ክልል ልዩ ድጋፋ ባለማድረጉ የቅማንት ማህበረሰብን ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል ብሏል።

በኮምሽኑ ቀረበውን ሪፖርት ላይ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሰኔ 3 ቀን 2008 ዓ.ም ተወያቶ አጽድቆታል።

 

ጥቂት ተጨማሪ ማብራሪያዎች

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮምሽን ኮምሽነር ዶ/ር አዲሱ ገብረእግዚአብሄር፣ ምክትል ኮምሽነር አቶ እሸት ገብሬ፣ የኮምሽኑ የሴቶችና የህጻናት ኮምሽነር ወ/ሮ ኡባህ መሐመድ እና የኢንፎርሜሽን ኮምኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አባዲ ቅዳሜ ዕለት በሒልተን ሆቴል በጋራ በሰጡት መግለጫ ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። በተለይ «ኮምሽኑ ነጻና ገለልተኛነቱ የቱን ያህል ነው?» በሚል ለተነሳው ጥያቄ ዶ/ር አዲሱ በሰጡት መልስ ኮምሽኑ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መሆኑንና ም/ቤቱ ደግሞ የህዝብ መሆኑን ካስረዱ በኋላ ኮምሽኑ ነጻነቱ የተረጋገጠ የህዝብ ተቋም መሆኑን በዝርዝር አስረድተዋል።

በተለይ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ችግር ጋር በተያያዘ የሞቱና የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ሌሎች አካላት ካሰራጩት ጋር ሲነጻጸር አነስ ብሎ ታይቷል በሚል ለቀረበውም ጥያቄ ኮምሽኑ ምርመራውን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በቦታው ተገኝቶ ያከናወነ በመሆኑ መቶ በመቶ እንከን አልባ ነው ባይባልም እንኳን ለእውነታው እጅግ የቀረበ ተአማኒ ሪፖርት አቅርበናል በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

“የጸጥታ ኃይሎች እርምጃ ተመጣጣኝ ነው” የመባሉ ጉዳይም በተመለከተ የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ኃይሉ ወደ ኦሮሚያ ክልል የገባው የክልሉ መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት መሆኑን፣ በማይክራፎን ለማረጋጋት፣ ለመበተን ጥረት ሲደረግ በአንዳንድ አካባቢዎች የተኩስ ምላሽ እንዳጋጠመ፣ የጸጥታ ኃይሎች ባደፈጡ ታጣቂዎች ሲገደሉ መልስ ለመስጠት አለመሞከሩን አብራርተዋል። አያይዘውም አንዳንድ ያነጋገሩዋቸው ወገኖች  “የጸጥታ ኃይሉ በፍጥነት ደርሶ ነገሩን ባያስቆመው ኖሮ እኛንም ዛሬ በህይወት አታገኙንም ነበር” እስከማለት መድረሳቸውን ጠቅሰዋል። በመሆኑም የጸጥታ ኃይሉ እርምጃ ሕግና ስርዓትን መሰረት ያደረገ፣ ተመጣጣኝ እንደነበር በማብራሪያቸውም አረጋግጠዋል።n

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
492 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us