ከ10 ሺ 850 በላይ የመከላከያ ኃይል በሠላም ማስከበር ተልዕኮ

Thursday, 07 July 2016 15:18

የኢፊዲሪ መከላከያ ሚኒስቴር በሠላም ማስከበር ተልዕኮ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሰሞኑን አቀርቧል።

ሠራዊቱ በሽግግር መንግሥቱ ወቅትም ሆነ በአዋጅ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በተሌዩ የአፍሪካ ሀገራት ማለትም በዳርፉር፣ በደቡብ ሱዳን፣ በአብዩና በሶማሊያ የተከሰቱ ግጭቶችን ለማርገብና ሠላም ለመፍጠር የተሰጠውን ግዳጅ በብቃት እየተወጣ መሆኑን ሪፖርቱ ይጠቅሳል። የሀገር መከላከያ ሚኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ካቀረቡት ሪፖርት መካከል በሰላም ማስከበር ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራትን ብቻ እንደሚከተለው ቀርቧል።

…………………….

 

የአብዬ ግዛት

­­­የአብዬ የሰላም ማስከበር ስራችን በተመለከተ፤ ሀገራችንን ሁለት ተቀናቃኝ ጎረቤት ሃገሮች ማለትም ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያ በብቸኝነት ተመርጣ የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን በብቃት፣ በታማኝነት፣ በገለልተኝነት እንደምትወጣ በመተማመን ሠራዊቷን ወደ አብዬ ግዛት በማዝመት ሰላም እንድታስከብር መርጠዋታል። ይህ ብቻ ሳይሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ያለምንም ልዩነት ሙሉ በሙሉ በመቀበል ተገቢ ምርጫ መሆኑንና ተልዕኮዋንም ከዚህ ቀደም ያከናወነችውን አኩሪ ተግባር መሠረት በማድረግ መሆኑን በመቀበል ያለምንም ማመንታት ይህንን ተልዕኮ እንደምትፈፅም መርጠዋታል።

 

አብዬ በሁለቱ ሱዳኖች መካከል የምትገኝ አዋሳኝ ግዛት ናት። ይህች ቦታ በብዙዎች ዘንድ ቦታውን አስቸጋሪነትና ያለውን የግጭት ትኩረት ሳቢነት ከግምት በማስገባት በብዙዎች ዘንድ አብዬን የዓለማችን አንዱ ከፍተኛና መፍትሔ የማይገኝለት የግጭት ቦታ ይሉታል። ሆኖም የኢትዮጵያ ሠራዊት ተልዕኮውን በአብዬ ለመፈፀም ጥያቄውን ተቀብሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመሰማራት ግዳጁን በቁርጠኝነት በመፈፀም ላይ ይገኛል።

 

በተጨባጭ በአሁኑ ሰዓት በአብዬ ያለው የተልዕኮ ሃላፊነት እየሰፋ በመምጣቱ ምክንያት ኢትዮጵያ የሠራዊቷን ቁጥር ከፍ እንድታደርግና የድንበር ጥበቃ ዩኒት እንድታሰማራ እየተደረገ ይገኛል። በዚህም መሠረት በአብዬ ያለው የሰው ሃይል ቁጥርም ከአምስት ሺህ በላይ ይሆናል። በአብዬ ተሰማርቶ የሚገኘውም የኢትዮጵያ ሠራዊትም የአቭዬሽን ዩኒት፣ የሁለገብ ሎጀስቲክስ ዩኒት፣ የመድፈኛ ባትሪዎችን፣ የታንከኛ ሻምበሎችን፣ የሞተራይዝድ ሻለቆችንና የቀላል የመስክ መሐንዲስ ሻምበል፣ ተወርዋሪ ሻምበል፣ የስታፍና የመገናኛ ዩኒት፣ የደረጃ ሁለት ሆስፒታል እንደዚሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስታፍና ወታደራዊ ታዛቢዎችን በጥንቅር የያዘ ተልዕኮ ነው። ይህ ደግሞ በአገራችን ስምሪት በወታደራዊ የሰው ሃይል ብቻ ሳይሆን እያሰማራ በሚገኘውም የአሀድ (Unit) ዓይነትም በጥንቅሩ ሁሉን አቀፍ የሆነ እና የሎጀስቲካዊ አቅሙንም ሙሉ ለሙሉ ከሀገራችን የተውጣጣና የተሰማራ በመሆኑ ሀገራችን በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያላትን አቅም ከማሳየቱም በተጨማሪም ለአሀገራችንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተልዕኮ መሳካት እያበረከተች ያለውን አስተዋፅኦ በግልፅ የሚያሳይ ነው።

 

ሠላም አስከባሪ ሠራዊታችን ወደ አብዬ ግዛት የገባው በሁለቱም ጎዳዎች (ሜሴርያና ንጎክ ዲንካ) መካከል ያለው ግጭት ፈጽሞ ባልቆመበት ወቅት በመሆኑ ሰራዊታችን ወድያውኑ ግጭቱ በተሰማራባቸው ቀጠናዎች በሙሉ እንዲቆሙ የማድረግ ስራውን ቁርጠኝነት በተሞላበት መልኩ አስቸጋሪ በሆነው የአየር ሁኔታ መፈፀም ችሏል። ከዚህም በተጨማሪ ግጭቱን ተከትሎ የነበረውን ሰፊ ዘረፋና ግድያ ሌት ተቀን በመሰማራት ማስቆም ተችሏል። ለረዥም ጊዜ የሁለቱም ጎሳዎች የግጭት መንስኤ ሆኖ ደም አፋሳሽ የሆነው የግጦሽ እና የእርሻ መሬት በመሆኑ ይህም ፍልሰት ሠራዊታችን ወደ ቦታው ከተሰማራበት ጊዜ ጀምሮ ያለ ምንም ደም መፋሰስ እንዲከናወን የማድረግ ስራ ተሰርቷል እየተሰራም ይገኛል።

 

በሌላ በኩል የአካባቢውን ህብረተሰብ የሚደግፍ በርካታ የልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን መንገድ በመጥረግ፣ ት/ቤቶች በማደስ፣ የውሃ ጉድጓድ በመቆፈር፣ ከቀለቡ እየቀነሰ በመስጠት እገዛ በማድረግ ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ በመስራት የተለመደውን ህዝባዊነቱን እያስመሰከረ ይገኛል። ሠራዊታችን ከሁለቱም ህዝቦች ጋር በመቀራረብ ያለምንም አድልዎና ወገንተኝነት በእኩል አይን በማየት ተልኮውን እየተወጣ ይገኛል። በዚህም መሠረት በአብዬ ሰራዊቱ ከገባ በኋላ በተፈጠረው መልካም የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ተፈናቅለው የነበሩ የአብዬ ግዛት ነዋሪዎች ወደ ነበሩበት አካባቢ እንዲመለሱ የማበረታታትና የመመለስ ስራ በሰፊው እያከናወነ ሲሆን አብዛኛውን የዲንካ ጎሳ በታቀደው መንገድ ተመልሶ በሰላም እየኖረ ነው።

 

በአብዬ ሰላም አስከባሪ ኃይላችን በሁለቱም ቡድኖች ዲንካና ምሰሪያ አዋሳኝ ድንበር አዲስ ገበያ በመፍጠር ሁለቱም ህዝቦች ተቀራርበው የሚገበያዩበት በሠላም የሚነጋገሩበት የማቀራረብ ከፍተኛ ስራ በመስራቱ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲገበያዩ ማድረግ ተችሏል። የአብዬን የአስተዳደር እና የፀጥታ ስራን በጋራ (በጥምር) ኮሚቴ በየደረጃው ባለው አመራር በመምራት ችግሮችን በውይይት፣ በድርድርና በማግባባት የመፍታት ባህል እንዲጎለብት የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እየተሰራ ይገኛል። የተባበሩት መንግስታት እና የአካባቢ መስተዳደር ጋር በመሆን መጠበቅ የሚገባቸው ቦታዎችን በአስተማማኝ በመጠበቅ ብዛት ባላቸው የታጠቁ ኃይሎች ዙሪያ የምትገኘዋን አብዬ የሰላም ደሴት እንድትባል አስችሏል። ተቋማትን ከመጠበቅ በተጨማሪ ህዝቦችን የማቀራረብ ግጭት እንዳይፈጠር ከጎሳ መሪዎች ጋር እየተወያየ አስተዳደር ባልተቋቋመበት የፖሊስ ስራ ደርቦ በመስራት በአካባቢው መረጋጋት ከፍተኛ ስራ በመስራት ላይ ይገኛል። በተጨማሪም ሠራዊታችን በአብዬ ግዛት ፀጥታ ከማስከበር በተጨማሪ ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማት ጥገናና ግንባታ ስራዎችን ማለትም ድልድይ፣ ህክምና፣ መንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ የመጠጥ ውሃ፣  መብራት ወዘተ. . . ስራዎችን አከናውኗል። ከዚህም በተጨማሪ እንደ ት/ቤት እና የህክምና ተቋሞችን በትምህርት መረጃና በቁሳቁስ የመደገፍ ተግባር በማከናወን ህዝባዊ ወገንተኝነቱን እያሳየ ይገኛል።

 

በአብዬ ሠላም ማስከበር ስራችን ሠራዊታችን እየተጫወተ ያለው ሚና እጅግ ከፍተኛ ቢሆን መስራት ያለበት የፖለቲካ ስራ በተገቢው ባለመስራቱ የሠራዊታችንን ተልዕኮ ረጅም እንዲሆንና ሠራዊታችንንም ከሰላም መጠበቅ በተጨማሪ ሌሎች ስራዎችንም ደርቦ እንዲሰራ ተገዷል።

 

የኢፊዲሪ መከላከያ ኃይል ወደ ሶማሊያ የገባው በሁለት መሰረታዊ ነገሮች ነው። አንደኛው “በሀገራችን ተጨባጭ አደጋ ስለተቃጣ” ማለትም አልሸባብ (እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት) ከፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት (ጅሃድ) ማወጃቸው ሲሆን ሁለተኛው የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ድጋፍ ጥሪ ነው። የመንግስታችን አቋም በጎረቤቶቻችን ሰላም ከሌለ በእኛም ሀገር ሰላም አይኖም የሚል ሲሆን ጎረቤት አገሮችም ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿን ሰላም የራሷ ሰላም አድርጋ ከማየት በስተቀር የተለየ ፍላጎት እንደሌላት እና በገለልተኝነት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዋን ብቻ የምታረጋግጥ መሆኑን በተጨባጭ ስላረጋገጡና ስላመኑበት ነው።

 

ይህ በአፍሪካውያን ህዝቦች ዘንድ ያተረፍነው ታማኝነት በተባበሩት መንግስታት ይሁን በአፍሪካ ህብረትም ሙሉ ተቀባይነትን እያገኘና ከጊዜ ወደ ጊዜ የኢትዮጵያን ተመራጭነት እያሳደገ በመሄድ ላይ ይገኛል። ለዚህም ነው ሠራዊታችን የአፍሪካ ህብረትና የሶማሊያ መንግስትን ጥሪ ተቀብሎ በሶማሊያ በአፍሪካ ህብረት አርማ ስር ለሰላም ማስከበር ግዳጅ እ.ኤ.አ. ከ2014 ጀምሮ አሚሶምን ተቀላቀለው። በአሁኑ ሰዓት በሶማሊያ 4 ሺ 600 በላይ የኮንቲንጀንት ሠራዊት አባላትና ከ20 በላይ የኃይል ማዘዣ ስታፍ መኮንኖች ሠላም አስከባሪ ኃይል አሰማርተናል።

 

በዚህ መሠረት ሠራዊታችን ግዳጁን በሚገባ በማጥናት፣ በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ባይደዋን ማዕከል በማድረግ ከአልሸባብ ጋር በመዋጋት ሰራዊታችን በየዘው ቀጠና የሚገኙ በራሕከበ፣ ደንሱር፣ ሶርዳሉ ቃንሃዛደሬ፣ አወደሊያን የመሳሰሉት/ 15 ቦታዎችን ከአሸባሪው አልሸባብ ነፃ በማድረግ በነዚህ ቦታዎች ሰላም እንዲሰፍንና ህዝቡ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር አድርጓል። በተመሳሳይ በመካከለኛው ሱማሊያ ማዕከሉን በለደዌኒ አድርጎ /መተበጊ፣ ዓሳዒሎ፣ ደስመረብ፣ ጉራእልና ሌሎች/ በድምሩ 29 ቁልፍ የሆኑ የወረዳ ከተማዎችና የገጠር መንደሮችን ነፃ በማውጣት የአልሸባብ አከርካሪን መምታት ተችሏል። በኁሉም ነፃ የወጡ ሶማሊያ አካባቢዎች ህዝብ ራሱን ማስተዳደር እንዲችል ከሶማሊያ ጦር ጋር በመሆን አካባቢውን እንዲቆጣጠር የሚያስችል ስራ ተሰርቷል።

 

በዚህም መሠረት ነፃ በወጡ ቦታዎች የፀጥታና የመስተዳድር አካላት እንዲቋቋሙ ሰራዊታችንን አብሮ በመሆን በሚያከናውነው ድጋፍ አካባቢውን በማረጋጋት ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል። በሶማሊያ የተሰማራው ሰላም አስከባሪ ኃይላችን አልሸባብን ከመደምሰሰና ከማጥፋት ጎን ለጎን የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር ተገቢውን ብቃት እንዲይዝ ሌት ተቀን በማሰልጠን በአንዳንድ አካባቢዎች ራሳቸውን ችለው ግዳጅ በመፈፀም፣ አንዳንድ ጊዜም ከኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ጋር አብረው ግዳጅ በመወጣት ጥሩ ልምድ እያገኙ ራሳቸውን እንዲችሉ እየተደረገ ይገኛል። ስለሆነም የሶማሊያ መደበኛ ሠራዊት ራሱን ችሎ ግዳጅ እንዲፈፅምና ልምድ እንዲወስድ ስልጠና በመስጠት፣ ግዳጅ አብሮ እንዲሰለፍ በማድረግ የልምድ ማስተላለፍና የመጋራት ሥራ በከፍተኛ ደረጃ እየተሰራ ይገኛል። ሰብአዊ እርዳታዎች፣ ወደህዝቡ በወቅቱ እንዲደርሱ እጀባና የፀጥታ ስራ ቀድሞ በማከናወን ድርጅቶች ስራቸውን ያለ ምንም እንቅፋት እንዲሰሩ ማድረግ ተችሏል።

 

ሠራዊታችን በአጠቃላይ መጠበቅ የሚገባቸው አሚሶም/AMISOM/ እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ አስፈላጊው ጥበቃ በማድረግ አገልግሎት ሳይስተጓጎል እንዲሰጥ ማድረግ ተችሏል፣ በጠቅላላ ለAMISOM ከተሰጠው ግዳጅ 12 ሺ ከሚሆን የሰላም አስከባሪ ኃይል የሀገሪቱን 62 በመቶ የቆዳ ስፋት ባለው አካባቢ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ተሰማርቶ ግዳጁን እየተወጣ ይገኛል። በሁሉም አካባቢዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአልሸባብ ኃይል የተደመሰሰ ሲሆን፤ በቅርቡ በሃሰጌን አልሸባብ በአጥፍቶ ጠፊና በታጣቂዎች ያደረገው የማጥቃት ሙከራ በሰላም አስከባሪ ኃይሎችን ከፍተኛ ጀግንነት በተሞላበት ፀረ-ማጥቃት አልሸባብ አጋጥሞት የሚያውቀው ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበታል። አልሸባብ በአሁኑ ጊዜ ከሰራዊታችን ፊት ለፊት ገጥሞ እንደማይሳካለት በማመን አጥፍቶ በማጥፋት፣ በመሸሽና ደፈጣ በማድረግ የመሳሰሉ የአሸባሪ ተግባር ብቻ ታጥሮ የነበረበት አካባቢ ተነጥሎ በወሰን አካባቢ ታጥሮ ይገኛል።

 

በሌሎች ሚሽኖች እንደታየው ሁሉ በሶማሊያ (AMISOM ጥላ ስራ የዘመተው ሰራዊታችንም ጀግንነቱ፣ ህዝባዊ ወገንተኝነቱ ጎልቶ የሚታይበት ተልዕኮ ነው። የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ሥራ ከሌሎች በአይነቱ የሚለየው በአንድ በኩል ሶማሊያ እንደ ሃገር ቀደም ሲል ከነበረው ታሪካዊ ግንኙነት የሚነሳ ኢትዮጵያ በጥርጣሬ መንፈስ ላይ በነበረ ማህበረሰብ የሚፈፀም መሆኑ ሲሆን በሌላ መልኩም ግዳጁ ተመጣጣኝ ሃይል በመጠቀም ተዋግቶ በማፅዳት ሰላም የሚረጋገጥበት መሆኑ ነው። በመሆኑም በአንድ በኩል በአልሸባብ ስራ ገብቶ ይሰቃይ የነበረውን ህዝብ በጀግንነት ተዋግቶና መስዋዕት ከፍሎ ነፃ ማውጣቱ በሌላ መልኩ ከህብረተሰቡ ጎን በመቆም የሰላም ሃይልና የችግሩ ተካፋይ ሰራዊት ሆኖ ሲያገኘው ለሶማሊያ ህዝብ ያልጠበቀውና ከማንም አግኝቶ የማያውቀው ድርጊት በመሆኑ የነበረውን አሉታዊ አስተሳሰብ እንደሰራዊትም እንደሀገርም እንዲቀይርና ይልቁንም የቁርጥ ቀን ደራሹ አድርጎ እንዲመለከተው እየሆነ ይገኛል።

ደቡብ ሱዳን እ.ኤ.አ. በ2013 በደቡብ ሱዳን መንግስት ውስጥ በተፈጠረ እርስ በርስ ልዩነት ወደ ግጭት ሲገቡ የተመድ እና ኢጋድ የሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲሰማራ ሲወስን ከተመረጡ አፍሪካ ሀገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን የኮንቲንጀንት ኃይል እና ስታፍ መኮንኖች የሰላም አስከባሪ ኃይል ከማሰማራቷም በተጨማሪም የተልዕኮው የኃይል አዛዥ ኃላፊነትም ተሰጥቷታል። በዚህ ተልዕኮ በቀጠናው በጥቅሉ 1 ሺ 250 የሰላም አስከባሪ ኃይልና ስታፍ ኦፊሰሮች ተሰማርተዋል። በዚህ ተልዕኮአችንም በሁለት ወገን ይደረግ በነበረው  ግጭት እየተከሰተ የነበረው የህዝብ እልቂት ማስቆም ተችሏል። ሀገራችን ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ ሊፈታ ይገባዋል ብላ የያዘችው አቋምም ተግባራዊ እንዲሆን አግዟል። ከአካባቢው የተፈናቀሉ የአካባቢው ተፈናቃዮች ተብለው የሚጠሩ በሠላም ማስከበር ጉያ እንዲጠለሉ በማድረግ ተመልሰው ወደ አካባቢያቸው እንዲቋቋሙ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ይገኛል።

 

በስምምነቱ መሰረት የሲቪሎችና የተባበሩት መንግስታት ተቋማትን በአስተማማኝ በመጠበቅ አገልግሎት እንዳይቋረጥ ማድረግ የተቻለ ሲሆን የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ከአካባቢው የተፈናቀሉ ህብረተሰብን ከሰለባው መታደግ የጊዜያዊ መጠለያ ካምፕ ደህንነታቸውን የማረጋገጥ ተልዕኮ በመሸከም ተልዕኮውን በመወጣት ላይ ይገኛል። የሰብዓዊ እርዳታ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ወደተፈናቀለው የደቡብ ሱዳን ህብረተሰብ ለመደገፍ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ሳይስተጓጎል እንዲከናወን እየተደገ ሲሆን የተከሰተው ችግርም ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይሸጋገር ሌት ተቀን የመከታተልና የመከላከል ስራዎችን በጀግንነት እየፈፀመ ይገኛል። በተጨማሪም የአካባቢውን መሰረተ ልማትና ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን እየተከላከለና እየጠበቀ ይገኛል። በመሆኑም ደቡብ ሱዳን ህዝብ ተነፃፃሪ የሠላም ተስፋ እንዲገኝ አስችሏል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
545 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us