የ2008 በጀት እና አፈጻጸሙ

Thursday, 14 July 2016 15:31

 

የ2009 ዓ.ም (ከሐምሌ 1 ቀን 2008 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም) የፌዴራል መንግሥት በጀት 274 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ሆኖ በቅርቡ ጸድቋል። ይህ በጀት ከ2008 በጀት ዓመት ከጸደቀው በጀት በ21 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ያለው ሲሆን በ2008 የጸደቀውን ተጨማሪ በጀት ጨምሮ በጠቅላላው ከጸደቀው በጀት ጋር ሲነጻጸር በ13 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት ያሳያል። የዘንድሮው በጀት ሲታሰብ ያለፈው በጀት ዓመት አፈጻጸም ምን ይመስል ነበር፣ ምን ተግዳሮቶች ነበሩ የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም።

 

የ2008 በጀት ዓመት የማክሮ ኢኮኖሚና

የፊስካል ፖሊሲ አፈጻጸም

በ2008 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ በተገኙ መረጃዎች ላይ በመመስረት የበጀት ዓመቱን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች አፈጻጸም እና የመንግሥት ገቢ ግመታ ላይ ያለውን አንደምታ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ለመገምገም ሞክሯል። በመገባደድ ላይ በሚገኘው በ2008 በጀት ዓመት ኢኮኖሚው 11 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ ተተንብዮ ነበር። ለዚህ ዕድገት ከፍተኛ ምንጭ ከሆኑት ዘርፎች አንዱ የግብርናው ዘርፍ ሲሆን ከባለፈው በጀት ዓመት ጀምሮ በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች በተከሰተው አልኒኖ በግብርናና በሰብል ምርት ላይ ጉዳት መድረሱ የሚታወቅ ነው። ሆኖም በያዝነው በጀት ዓመት ትርፍ አምራች አካባቢዎች ላይ ተጽዕኖ እንዳልነበረው ለማየት ተችሏል። ምንም እንኳን ተጽዕኖው ባረፈባቸው የአገራችን አካባቢዎች የሰብልና የእንስሳት ምርት ላይ የተወሰነ ተጽዕኖ ሊያሳድር ቢችልም በመስኖና በበልግ ወራት በሚኖረው ዝናብ የተጠናከረ የግብርና ተግባር በማካሄድ እንዲሁም ችግሩ ባልተከሰተባቸው አካባቢዎች በሚገኘው ትርፍ ምርት ተጽዕኖውን በማካካስ ለበጀት ዓመቱ የተያዘውን ኢኮኖሚ ግብ ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት መደረጉን የኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር ሪፖርት ያሳያል።

በሌላ በኩል በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች በበጀት ዓመቱ የተያዘውን ዕድገት ለማሳካት የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዳሉ ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ለመረዳት ይቻላል። በአጠቃላይ በኤልኒኖ ምክንያት በግብርናው ዘርፍ ሊኖር የሚችለውን ተጽዕኖ ከላይ እንደተገለጸው በመቋቋም እና በ2008 በጀት ዓመት የታቀደውን የ11 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ለማሳካት ብርቱ ጥረትን እንደሚጠይቅ ግምት ተወስዷል።

በሌላ በኩል የኤክስፖርት ንግድ መቀዛቀዝ በያዝነው በጀት ዓመት ቀጥሎ የታየ ጉዳይ ነው። በ2008 በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ከወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን ከ2007 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ከተገኘው 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ጋር ሲነጻጸር በ141 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ወይንም በ6 ነጥብ 5 በመቶ ዝቅ ያለ አፈጻጸም አሳይቷል። በዘጠኝ ወራቱ ከኤክስፖርት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ለዓመቱ ከታቀደው 4 ቢሊየን ዶላር ጋር ሲነጻጸር 51 በመቶ ያህል ብቻ አፈጻጸም አሳይቷል።

እንዲሁም የገቢ ንግድን በተመለከተ በ2008 በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ለገቢ ንግድ (ኢምፖርት) 18 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ወጪ የተከፈለ ሲሆን ከ2007 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተከፈለው 16 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ጋር ሲነጻጸር  በ12 ነጥብ 5 በመቶ ያህል ከፍ ያለ ነው። በመሆኑም በወጪ እና በገቢ ንግድ መካከል ያለው የንግድ ሚዛን ጉድለት እየሰፋ መሄዱን ማየት ይቻላል።

 

የዋጋ ግሽበት

የ12 ወራት ተንከባላይ ዋጋ ግሽበት ሁኔታን በተመለከተ ከህዳር ወር 2007 በጀት ዓመት ጀምሮ ጭማሪ አሳይቶ የነበረ ቢሆንም ጭማሪው በጣም አዝጋሚ እንቅስቃሴ ከመሆኑም በላይ ከመጋቢት 2008 የ10 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። እንዲሁም ወርሃዊ የዋጋ ዕድገት ማለትም የመጋቢት 2007 ከመጋቢት 2008 ጋር ሲነጻጸር 7 ነጥብ 5 በመቶ ሆኗል። ይህ የዋጋ ዕድገት በኤልኒኖ ክስተት ምክንያት በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተፈጠረ የዝናብ እጥረት የተነሳ የግብርና እጥረት ይፈጠራል በሚል ግምት በተፈጠረ የገበያ አለመረጋጋት የተከሰተ እንደሆነ የተገመተ ሲሆን በ2008 በጀት ዓመት የተሰበሰበው የግብርና ምርት የጎላ ቅናሽ የታየበት ባለመሆኑ እና በአሁኑ ወቅት በመላው ሀገሪቱ ከፍተኛ ዝናብ እየዘነበ በመሆኑ ገበያው ሙሉ በሙሉ እየተረጋጋ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ ለበጀት ዓመቱ ተግባራዊ ለማድረግ የታቀዱትን የፊስካልና የሞኒተሪ ፖሊሲ እርምጃዎች ትኩረት ሰጥቶ ተግባራዊ ማድረጉ ወሳኝ ይሆናል።

 

የፊስካልና ፖሊሲና የመንግሥት የፋይናንስ አፈጻጸም

በ2008 በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ከታክስ፣ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች፣ የቀጥታ በጀት ድጋፍ ጨምሮ ብር 111 ነጥብ 2 ቢሊየን የተጣራ ገቢ ተሰብስቧል። ይህም ከጸደቀው የዓመቱ በጀት ጋር ሲነጻጸር የ63 ነጥብ 1 በመቶ አፈጻጸም አሳይቷል። በሌላ በኩል በተመሳሳይ ወቅት ውስጥ ብር 145 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ጠቅላላ ወጪ የተደረገ ሲሆን ይህም ከጸደቀው የዓመቱ በጀት ጋር ሲነጻጸር የ65 ነጥብ 7 በመቶ አፈጻጸም አሳይቷል።

 

 

የበጀት ጉድለት አሸፋፈን

በ2008 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት የተሰበሰበው ጠቅላላ የተጣራ የፌዴራል መንግሥት ገቢ (የቀጥታ በጀት ዕርዳታን ጨምሮ) ብር 110 ነጥብ 2 ቢሊየን ሲሆን ጠቅላላ ወጪ ደግሞ 145 ነጥብ 6 ቢሊየን ነበር። በገቢውና በወጪው መካከል ያለው ልዩነት 35 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ነው። ይህን የበጀት ጉድለት ለመሸፈንም ከውጭ ሀገርና ከሀገር ውስጥ በቅደም ተከተል የብር 7 ነጥብ 8 ቢሊየን እና የብር 26 ነጥብ 8 ቢሊየን የተጣራ ብድር ተወስዷል።

በአጠቃላይ በ2008 በጀት ዓመት በተጨማሪ እሴት ታክስ ዝቅተኛ አፈጻጸም በመታየቱና በቀጥታ ታክስ በተለይም በኮርፖሬት ድርጅቶች ንግድ ትርፍ ግብር የተጠበቀውን ያህል አለመሆን እንዲሁም በኤክስፖርት ረገድ የታየው ዝቅተኛ አፈጻጸም ልዩ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ ሚኒስቴሩ መገምገሙ ለማወቅ ተችሏል።¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
597 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us