የሰሜን ጎንደር ክራሞት

Wednesday, 20 July 2016 14:16

 

«አማራ ነን፣ በትግራይ ክልል ልንካለል አይገባም» የሚሉ የወልቃይት ተወላጆች ጥያቄያቸውን ማቅረብ ከጀመሩ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ እንዳስቆጠሩ ይናገራሉ፣ ጥያቄያቸው ግን ምላሽ ከማግኘት ይልቅ ማፈን፣ ማሳደድ፣ ማዋከብና ማሰር መቀጠሉን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል። የወልቃይት የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ አቅራቢ ኮምቴ አባላት እንደሆኑ የሚናገሩ ግለሰቦች ጥያቄዎቻቸውንም በአዲስ አበባ በመገኘት ለፌዴሬሽን ም/ቤት፣ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን፣ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እና ለሚዲያዎች ሲያደርሱ ቢቆዩም ተገቢውን ምላሽ እንዳላገኙ በቅሬታ መልክ አቅርበዋል። ሰሞኑን ይህ ጥያቄ በድንገት ወደ ግጭት አምርቶ ለበርካታ ሰዎች ሞትና መቁሰል እንዲሁም ለንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል።

 

ስለግጭቱ መነሻ


ሐምሌ አራት ለሐምሌ አምስት አጥቢያ የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማነንት ጥያቄ ኮሚቴ አራት አባላት በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውና አንዱን የኮሚቴ አባል ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን በግዳጅ ለመውሰድ በተደረገ ግብግብ በጎንደር ከተማ ግጭት መቀስቀሱን የኮሚቴው ፀሐፊ አቶ አደራጀው ናኘው ለአሜሪካ ድምጽ አማርኛ ፕሮግራም ተናግረዋል።


የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎትና የፌደራል ፖሊስ የጋራ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል በሰሜን ጎንደር የሽብር ተግባር ላይ ተሳታፊ ነበሩ ያላቸውን ተጠርጣሪዎችን እንቅስቃሴ ይፋ አድርጓል። በመግለጫው መሠረት የፀጥታ ኃይሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ሲሞክሩ በነበረው የተኩስ ልውውጥ ዘጠኝ የፌዴራል ፖሊስ አባላት፣ አንድ የመከላከያና አንድ የአማራ ክልል ፖሊስ አባል በድምሩ 11 የፀጥታ ኃይሎችና የአምስት ሠላማዊ ዜጎች ህይወት ማለፉን ግብረ ኃይሉ አስታውቋል። 11 የፌዴራል እንዲሁም 5 የክልሉ ፖሊስ አባላት ከባድ ጉዳት አጋጥሟቸዋል፤ ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረትም ወድሟል።


ግብረ ኃይሉ ባወጣው መግለጫ እንደተገለጸው፤ በፀረ ሠላም ኃይሎቹ ላይ ረዘም ላለ ጊዜ ክትትል ሲደርግ ቆይቷል። ቡድኑ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እያደረሰ በመሆኑ ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም አባላቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል እርምጃ ተወስዷል።


ይኸው ቡድን በሰኔ አካባቢም አንድ ሰላማዊ ግለሰብን በማፈንና በማገት ገንዘብ ለመዝረፍ ሙከራ ያደረገ ሲሆን፤ ጨለማን ተገን በማድረግ ደግሞ በሌላ አንድ ግለሰብ ላይ የግድያ ወንጀል ፈጽሟል። ባለፈው ሰኔ በተለያየ ጊዜ በጠገዴ ወረዳ ኩርቢና ሰሮቃ በተባሉ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ በመንግሥትና በህዝብ ተሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል።


በተጠርጣሪዎች ላይ ተገቢውን መረጃ ያሰባሰበው የፌዴራል ፖሊስ ጥቃቶቹ ከመፈፀማቸው በፊት ባደረገው ክትትል የቡድኑ አባላት ከኤርትራ መንግሥት ጋር በቀጥታ እየተገናኙ የሽብር ጥቃታቸውን በተደራጀ ሁኔታ ለመፈፀም ልዩ ልዩ ስምምነቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።


የፌዴራል ፖሊስ በቡድኑ ላይ በርካታ ማስረጃዎችን አሰባስቧል። የቡድኑ አባላት ሲያደርጉት የነበረውን የስልክ ምልልስም በማስረጃነት ይዟል።


እነዚህ መረጃዎች እንዲሁም በግለሰቦች ላይ የደረሰው ጥቃት ቡድኑ ወደ ሽብር ጥቃት መሸጋገሩን የሚያሳዩ በመሆናቸው የፌዴራል ፖሊስ የፍርድ ቤት ማዘዣ በመያዝ ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም የቡድኑን አባላት በቁጥጥር ስር ለማዋል ተንቀሳቅሷል።


ሆኖም ግን እንዲያዙ ከተወሰነባቸው የቡድኑ አባላት መካከል አራቱ በሰላም እጃቸውን ሲሰጡ ሁለቱ ተኩስ ከፍተዋል።


በተመሳሳይ ወቅት ለጊዜው እንዲያዙ ያልተወሰነባቸው የቡድኑ አባላት ደግሞ በፀጥታ ኃይሎች ላይ ከኋላ በከፈቱት ተጨማሪ ተኩስ በፖሊስ አባላትና ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሞትና የመቁሰል አደጋ ደርሷል።


ህግን በመተላለፍ ላለመያዝ ተኩስ የከፈቱት ግለሰቦች ቀደም ሲል ባካሄዱት ቅስቀሳና በአካባቢው የነበረውን ውጥረት ተከትሎ በጎንደር ከተማና በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎች ሰፋ ያለ የዝርፊያና ሁከት ተግባር ተከስቷል።

 

ይህንንም ተከትሎ በአካባቢው በሰላም ይኖሩ የነበሩ የተወሰኑ የትግራይ ተወላጆችና የማህበረሰቡ አባላት የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል።


በተፈጠረው ሁከት የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችና ሌሎች ተሽከርካሪዎች በእሳት ጋይተዋል። የንብና የወጋገን ባንኮችን ለመዝረፍም አጥሮቻቸውን፣ በሮቻቸውንና መስኮቶቻቸውን ሰባብረዋል።


የተለያዩ ሆቴሎችም የዝርፊያና ንብረት የማውደም ተግባራት ተፈፅሞባቸዋል፤ ሁለት የፌዴራል ፖሊስ መኪናዎችም ተቃጥለዋል።


በኤርትራና በአንዳንድ የውጭ አገራት የመሸጉ የሽብር ሃይሎች አጋጣሚውን በመጠቀም ሁከቱን ለማባባስ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሃሰት ወሬዎችን በማሰራጨት ላይ መሆናቸውንም የግብረ ኃይሉ መግለጫ አመልክቷል።


እነዚህ አካላት የአማራ ተወላጆች በአንዳንድ የትግራይ አካባቢዎች ጥቃት የደረሰባቸው በማስመሰልና መሰረተ ቢስ ወሬዎችን በማሰራጨት ላይ መሆናቸውንም ገልጿል።


የፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉ የጎንደር ህዝብ፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የክልሉ መንግሥት የአጥፊዎችን ጥቃት በማደናቀፍ ላደረጉት ትብብር ምስጋና አቅርቧል።


ግብረ ሃይሉ የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያን ሠላም ለማተራመስ የሚያደርገው ተግባር እንደማይሳካለት ተገንዝቦ ከዕኩይ ተግባሩ እንዲታቀብ አስጠንቅቋል።

ድጋፍም ተቃውሞም ያስተናገደው የዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም አስተያየት በማህባራዊ ሚዲያ ተሳትፎአቸው የሚታወቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በፌስቡክ ገጻቸው የሚከተለውን አስተያየት አስፍረዋል። አስተያየታቸው ከፍተኛ ድጋፍና የተቃውሞ ንግግርን ያስከተለ ነው።
…….


በጎንደር የተከሰተውን የማንነት ጥያቄ ሰበብ በማድረግ አንዳንድ ግለሰቦች ብጥብጥ ለማስነሣት ቢሞክሩም መንግሥታችን በሰከነ ዘዴ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ሥር አውሎታል:: የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ከአማራ ተወላጆች ጋር በመወያየትና በማሳመን የወልቃይትን መሬት የትግራይም ሆኖ የአማራ ተወላጆች በጋራ እንዲኖሩበት በማግባባት ላይ ይገኛል። ወልቃይት የአማራ ነው በማለት የሚነዛው ፕሮፓጋንዳም የሐሰት መሆኑና ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የታለመ በመሆኑ ሊወገዝ ይገባዋል:: የትግራይ ሕዝብና የአማራ ሕዝብ ለረዥም ጊዜያት በመቻቻልና በመከባበር አብረው የኖሩ በመሆናቸው በጥቂት ግለሰቦች ፍላጎት የሚጣሉ አይደሉም:: የትኛውም ብሔር በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል በመሄድ የመኖር መብት ያለው በመሆኑ የአማራ ብሔር ተወላጆች ወልቃይት ጠገዴ ሄደው ቢኖሩ አንድም የትግራይ ተወላጅ ቅሬታ እንደማይሰማው ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ:: በዚህ አጋጣሚ የትግራይ ሕዝብ አማራ ወንድሞቹን በፍቅር በማየት የተለመደ እንግዳ ተቀባይነቱን በተግባር ማሳየት እንዳለበት ለማሳሰብ እወዳለሁ:: ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!


……

 

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መግለጫ


የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሕዝብ ለዘመናት ከነበረበት ድህነትና ኋላቀርነት ለመውጣት ባደረጉት ዙሪያ መለስ ርብርብ እነሆ ሁለንተናዊ ለውጥ የጀመረና ብሩህ ተስፋ የታየበት ክልል መፍጠር ችለዋል። የክልላችን ሕዝቦች አስከፊውን ስርዓት ለማስወገድ በከፈሉት መስዋዕትነት፣ ለልማት የተመቸና ማንም በሰላም ወጥቶ መግባት የሚችልበት፤ እንዲሁም ዜጐች ምንም ልዩነት ሳይደረግባቸው በመቻቻልና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት በመመስረት ላይ ይገኛሉ።


በክልላችንም ይሁን በአገራችን እየተፈጠረ ያለው ይህ የሚያጓጓ እና ብሩህ ተስፋ የታየበት ሁኔታ ያልተመቻቸው እና የምንገነባው ስርዓት ጠላቶች በየጊዜው በክልላችን ልማትና ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት ለመሆን ያላሰለሰ ጥረት ቢያደርጉም በአስተዋዩና ሠላም ወዳዱ የክልላችን ሕዝብ ጥረት አልተሳካላቸውም። ይህም በመሆኑ ክልላችን በመለወጥ ላይ ሲሆን በሀገራችን ለሚካሄደው ሁሉን አቀፍ ለውጥ ሁነኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።


ይሁን እንጂ እነዚህ አካላት አሁንም ማንኛውም አጋጣሚ በመጠቀም ክልላችንን ብሎም ሀገራችንን የብጥብጥና የሽብር ዓውድማ ለማድረግ ሌት ከቀን በመስራት ላይ ናቸው።


ሰሞኑን በጐንደር ከተማ የብሔራዊ ፀረ-ሽብር ግብረ-ኃይል በወንጀል የጠረጠራቸውን አካላት በቁጥጥር ስር ለማዋል በተሰማራበት ወቅት በተፈጠረው ግጭት በሀገራችንና በክልላችን ፖሊስ አባላት እንዲሁም በንፁሃን ዜጐች ላይ የሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት ደርሷል። በንፁሃን ዜጐች እና በመንግስት ንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል። በሂደትም በሰላም እና በተረጋጋ ሁኔታ በሚኖሩ ሰላማዊ ዜጐች ላይ አለመረጋጋት ተከስቷል።


ይህ የተፈጠረው ሁኔታ የክልሉን መንግስትና ሕዝብ በእጀጉ አሳዝኗል። በዚህ አጋጣሚ የክልሉ መንግስት በተፈጠረው ሁኔታ እጅግ ያዘነ መሆኑን ሲገልፅ ለተጐጂ ወገኖች መፅናናትንና መረጋጋትን ይመኛል።


በመሠረቱ በሀገራችን እየተገነባ ያለው ስርዓት የሕግ-የበላይነት ያለበት እንጂ ማንም ሰው በምንም ምክንያት ከሕግ በላይ የሚሆንበት ስርዓት አይደለም። በሕጉ መሠረት ስልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው አካል በወንጀል የጠረጠረውንና በቂ መረጃና ማስረጃ ሊያቀርብበት የሚችለውን አካል ሕጉንና አሠራሩን ጠብቆ በቁጥጥር ስር ማዋሉ የሚጠበቅና ለሕዝብና ለሀገር ደህንነት ሲባል የግድ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው። የክልላችንም መንግስትና ሕዝብ በሕግ የበላይነት ላይ መቼም ቢሆን የማያወላዳ አቋም ያላቸው ሲሆን ለሕግ የበላይነት አበክረው እንደሚሰሩ ማንም ሊገነዘብ ይገባል። በመሆኑ ሕግን ለማስከበር የሚደረግ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ለአፍታም ቢሆን ቸል የማንል ሲሆን በማንኛውም ሁኔታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሕግና ስርዓትን ለማስከበር በትብብር የምንሰራ መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን። በመሆኑም ሻብዕያ እና መሰሎቹ በጐንደር እና አካባቢው የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም መላ ክልሉን የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ መራወጣቸውን አቁመው አደብ እዲገዙ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ እንገደዳለን።


በዚህ አጋጣሚ በጐንደር እና አካባቢው የተፈጠረውን ሁኔታ ወደ መላ የክልላችን አካባቢዎች ለማስፋፋት ሕና ግጭቱም መልኩን ቀይሮ የዘር ቅርፅ እንዲይዝ ጥረት የሚያደርጉ ወገኖች ከዚህ እኩይ ተግባራቸው እንዲቆጡ እናሳስባለን።


የእስከ አሁኑም እኩይ እንቅስቃሴያቸው የተገታው በጐንደርና አካባቢው አርቆ አሳቢ እና አስተዋይ ሕዝብ ጥረት ነው። የክልሉ መንግስት ለጐንደርና አካባቢው ሕዝብ በዚህ አጋጣሚ እስከአሁን ላሳየው ጨዋነት እና ታላቅ ኃላፊነት የተሞበላት እንቅስቃሴ የላቀ አክብሮትና ምስጋና ያለው መሆኑን እየገለፅን አሁንም እያንዳንዱን ነገር በአስተዋይነት፣ በአርቆ አሳቢነት እና በሕግ የበላይነት መነፅር እየተመለከተ ማንኛውንም ወንጀል እንዲከላከል ጥሪውን እያስተላለፈ በማንኛውንም ዓይነት የወንጀል ድርጊት ላይ ምህረት የሌለው እርምጃ እንደሚወስድ እንገልፃለን።


የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ሐምሌ 11 ቀን 2ዐዐ8 ዓ.ም
ባህር ዳር
……..

በአሁኑ ሰዓት በሰሜን ጎንደር ዞን ጠንከር ያለ ውጥረት እንደሚታይ ከተለያዩ ወገኖች አስተያየት ለመረዳት ይቻላል። መንግስት ሠላምና መረጋጋት የማስፈን ግዴታ እንዳለበት የሚታወቅ ሲሆን በዚህ ሒደት የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል አጠቃቀም እንዳይከሰት ከመከላከል ጎን ለጎን ችግሩን ለመፍታት ከሕዝብ ጋር የሚያደርገውን ውይይት አጠንክሮ ሊቀጥልበት እንደሚገባ የብዙዎች አስተያየት ነው።

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
1105 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us