የአመጽ መንገዱ የት ያደርሰናል?

Wednesday, 10 August 2016 14:09

እየተገባደደ ያለው 2008 ለኢትዮጵያዊያን የሠላምና የመረጋጋት ዓመት አልነበረም። ቀደም ሲል ጀምሮ እዚህም እዚያም ብልጭ ድርግም የሚሉ አለመግባባቶች ወደአመጽና ግጭት ተቀይረው፣ ገዝፈው የታዩበት ዓመት ነበር ማለት ይቻላል።

እንዲህ ዓይነት ግጭቶችና አለመግባባቶች ባለፉት አራት ዓመታት ጠንከር ብለው ታይተዋል። ጥቂቶቹን ለትውስታ ያህል እናንሳቸው።

 

ደቡብ ክልል- ጉራፈርዳ

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጉራፈርዳ ቀበሌ በ2004 ዓ.ም “አካባቢያችንን ለቃችሁ ውጡ” በሚሉ ሹማምንትና ተወላጆች ግፊት በአንድ ጀምበር በሺ የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ተፈናቀሉ። በወቅቱ ችግሩ አሳፋሪና አስደንጋጭ ቢሆንም በችግሩ ስፋት ልክ የፌዴራል መንግሥት ትኩረት መስጠት አለመቻሉ ሌላው ችግር ነበር። በዚህ ችግር ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉ የበታች ሹምማንት የተከሰሱ ቢሆንም ክስተቱ በተለይ በአማራ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ጠባሳን አሳርፎ አልፏል።

 

ደቡብ ክልል - ኮንሶ

በደቡብ ክልል ሰገን አካባቢ ዞን አንዱ የሆነው የኮንሶ ወረዳ ሕዝብ በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ በዞን ደረጃ ተዋቅሮ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ያቀረበው ጥያቄ በክልሉ መንግሥትና በፌዴሬሽን ም/ቤት አዎንታዊ ምላሽ አላገኘም፡፡ ይህን ተከትሎ በሕዝብ የተመረጡ የኮምቴ አባላትን ማሰር፣ መደብደብ፣ ማሳደድ፣ ማስፈራራትና ማዋከብ እንዲሁም ከስራ የማፈናቀል ድርጊቶች በስፋት መካሄዳቸውን የኮምቴው አባላት በወቅቱ ለመገናኛ ብዙሃን ከሰጡት መግለጫ ለመረዳት ይቻላል፡፡

 

 

ጋምቤላ

በ2006 እና በ2007 ዓ.ም በተለያዩ ጊዜያት በጋምቤላ ክልል መዥንገር፣ ጎደሬ፣ ሜጢ ዞኖች በተመሳሳይ ሁኔታ የአማራ ተወላጆች (በእነሱ አጠራር ደገኞች) “አካባቢያችንን ለቃችሁ ውጡ” በሚል በተነሳ ሁከት 126 ሰዎች ሲገደሉ ወደ 7 ሺ የሚደርሱ የአማራ ተወላጆች ከቤት ንብረታቸው እንደዋዛ ተፈናቅለዋል። ይህ ዓይነቱ ኢ-ሰብኣዊ እና ኢ-ሕገመንግሥታዊ ድርጊት ጥሎት ያለፈው ጠባሳ በቀላሉ የሚሽር አልነበረም።

 

በሙስሊሙ ወገን የተነሱ ጥያቄዎች ያስከተለው  ምስቅልቅሎሽ

በሕዝበ ሙስሊሙ ወክሎ የተቋቋመው ኮምቴ በ2004 ዓ.ም ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል “የኢትዮጵያ እስልምና ጉባዔ ምክርቤት (መጅሊስ) ይፍረስና ፍትሐዊ ምርጫ ይደረግ፣ አወሊያ/ቤት በቦርድ ይተዳደር፣ በመጅሊሱ የሚሰጠው የሃይማኖት አስተምህሮ ይቀየር” የሚሉ ነበሩ። ይህ ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ በሰኔ ወር 2004 .ም የመጅሊስ ምርጫ በየቀበሌው እንደሚካሄድ ይፋ መሆኑና ምርጫው በኮሚቴው ዘንድ ተቀባይነት ማጣቱ ውጥረቱን ጨምሮታል።

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ሕዝበ ሙስሊሙን ከሚወክሉ ኮምቴዎች ጋር ተከታታይ ውይይቶችን በወቅቱ ያደረገ ቢሆንም መግባባት ሊያስገኝ ሳይችል ቀርቷል። ውጥረቱ እየተባባሰ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ መንግሥት ዕውቅና ሰጥቶ በጠረጼዛ ዙሪያ ሲያወያያቸው የነበሩትን የሙስሊም ማህበረሰብ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች ተባባሪዎች አስሮ በጸረ ሽብር አዋጁ መሠረት ክስ መሰረተባቸው። በዚህ መሠረት የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር የነበሩት በኋላም ከሀገር የኮበለሉት የአቶ ጂነዲን ሳዶ ሚስት ጨምሮ 29 ተከሳሾች እና ሁለት ድርጅቶች ላይ ጥቅምት 19 ቀን 2005 ዓ.ም ተከስሰው ፍ/ቤት ቀርበዋል። ይህ የመንግሥት እርምጃ ግን የበርካታ ሙስሊም ወገኖች ድጋፍን አላስገኘለትም።፡ እንዲያውም በተቃራኒው እርምጃው ቅሬታ በማስከተሉ ላለፉት አራት ዓመታት በየመስጊዱ ሞቅ በረድ የሚል ተከታታይ የጸረ መንግሥት ተቃውሞዎችን ሲታዩ ቆይተዋል።

 

ጋምቤላ

ቅዳሜ ሚያዚያ 8 ቀን 2008 ዓ.ም ከወደ ጋምቤላ የተሰማው ዜና ለጆሮ የሚከብድ እጅግ መራር ነበር። መነሻቸውን ጎረቤት ሀገር (ደቡብ ሱዳን) ያደረጉ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ወደጋምቤላ በኑዌር ዞን ሶስት ወረዳዎች ዘልቀው በመግባት ባደረሱት ጥቃት ከ208 በላይ ንጹሐን ዜጎችን በግፍ ገድለዋል። ከ100 በላይ  የሚቆጠሩ የቆሰሉ ሲሆን በርካታ ሴቶችና ሕጻናትም አግተው ወስደዋል። ታጣቂዎቹ በተጨማሪም ከ2000 በላይ የቀንድ ከብቶችንም እየነዱ ወደመጡበት መመለሳቸውም እጅግ አሳዛኝ ዜና ሆኖ አልፏል።

 

ኦሮሚያ

በኦሮሚያ ክልል የአዲስ አበባና የፌንፊኔ ማስተር ፕላን ዕቅድን በመቃወም የተነሳ ህዝባዊ ቁጣ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሶ እነሆ መቋጫ ወደሌለው አለመረጋጋት እየመራን ይገኛል።

በጥር ወር 2008 መጀመሪያ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮምቴ ተሰብስቦ የማስተር ፕላኑ ተቃውሞ የሕዝብ ጥያቄ መሆኑን ማረጋገጡን አስቀምጦ ለግጭቱ መነሻ የሆነው የአዲስአበባና የፊኒፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ተግባራዊ እንዳይሆን፣ በጨፌ ኦሮሚያ በዚህ ዓመት የጸደቀው የከተሞች አዋጅ አንዳንድ ድንጋጌዎች በድጋሚ እንዲታይ ወስኗል። 

ይህም ሆኖ ግን በኦሮሚያ የተነሳው ተቃውሞ ሊቆም አልቻለም። ለምን ቢባል በሕዝቡ ውስጥ የተጠራቀሙ ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች በመኖራቸው እንደሆነ ይታመናል። ይህ ተቃውሞ ደም አፋሳሽ በሆነ መልኩ መቀጠሉ ሠላም ወዳድ ኃይሎችን ሁሉ ያሳሰበ፣ የሀገሪትዋንም መጻኢ ዕድል እንዳያበላሽ ብዙዎችን ያሰጋ ክስተት እንደሆነ ቀጥሏል።

 

አማራ ክልል

በጎንደር የቅማንት የማንነት ጥያቄ፣ በኋላም በወልቃይት ጠገዴ “በአማራ ክልል ልንካለል ይገባል” የሚሉ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ በወቅቱ ማግኘት አለመቻላቸው ለደም መፋሰስ ምክንያት ሆነዋል።

በተለይ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በባህርዳር ከተማ የተካሄደው ሰልፍ ሞትን ማስተናገዱ አሳዛኝ ነበር። መንግሥት “ሕገወጥ” ነው ባለው በእነዚህ ሰልፎች በርካታ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ጸረ መንግሥት አቋም ያላቸው ጥያቄዎች አቅርቧል።

 

ከሰልፎቹ ጀርባ ማን አለ?

በመንግሥት በኩል የሰልፉ አስተባባሪ አካል ማን ነው የሚለው ጥያቄ የተደበላለቀ መልስን አስከትሏል። መንግሥት ከሰልፉ ጀርባ “የውስጥና የውጪ ኃይሎች እጅ አለበት” የሚለው አንዱና ተደጋጋሚ ክስ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ “ችግሩ የራሳችን ግልጽነት ማጣት ነው፣ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው” የሚሉ አስተያየቶችንም ሲያቀርብ ቆይቷል።

ኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ሰሞኑን ከፋና ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ በሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን የተሞከሩት የአመፅ እንቅስቃሴዎች ዋና ተልእኮ ህገ መግስታዊ ስርአቱን በኃይል ማፍረስ ነው ብለዋል።

የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስትር እና የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ምክትል ሊቀመንበር ወይዘሮ አስቴር ማሞ በበኩላቸው ግጭቱን የቀሰቀሱት የሻዕቢያ ተላላኪዎችና አሸባሪው ኦነግ ናቸው ሲሉ ከሰዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሰልጣናት በየከተማው እየተካሄደ ያለውን ሕዝባዊ አመጽ ሶስት ዓይነት ባለቤት ይሰጡታል። አንዱ እንደሻዕቢያ ግንቦት ሰባት፣ ኦነግ… ያሉ እንዲሁም አንዳንድ በሀገር ውስጥ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ አካላት ኢንተርኔትን ጭምር በመጠቀም የቀሰቀሱት መሆኑን የሚያስረዳ ነው። ሌላኛው ደግሞ የመልካም አስተዳዳር ችግር የወለደው መሆኑን የሚያመለክተው ነው። በተለይ ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚቀርበው ችግሩን ወደውስጥ ለማሳየት የሚሞክር ነው።

ሶስተኛው የኢህአዴግ ዕይታ “ሰልፉ ባለቤት የለውም” የሚል ነው። ሶስቱንም ዘርዘር እያደረግን እንያቸው።

 

 

ምክንያት አንድ

ኢህአዴግ እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች መንስኤውን ብዙውን ጊዜ ወደውጭ ሲገፋ ይታያል። ጠ/ሚ ኃ/ማርያም ደሳለኝ በየካቲት ወር 2008 አጋማሽ ከመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ በኦሮሚያ ክልል ከተቀጣጠለው አመጽ ጀርባ የሻዕቢያና የውጭ ኃይሎች እጅ አለበት ብለዋል። በርካታ የመንግስት አካላትም ተመሳሳይ መግለጫዎችን ሰጥተዋል። አንዳንድ ወገኖች ይህን የመንግሥት ባለስልጣናት አቋም ለእነግንቦት ሰባት የቀረበ ገጸበረከት (ሽልማት) አድርገው ይቆጥሩታል። ምክንያቱም እነግንቦት ሰባት እና ኦነግ ያሉ አመራሮችና ደጋፊዎች በሀገር ውስጥ ምንም መሠረት ሳይኖራቸው በአሜሪካና በአውሮፓ ተቀምጠው ባሉበት ሁኔታ ከቀውሱ ጀርባ እነሱ እንዳሉ አድርጎ በኢህአዴግ በኩል የሚሰጠው ተደጋጋሚ መግለጫ የሌላቸውን ጡንቻ እንዲያገኙ ከመርዳቱም በተጨማሪ ጠንካራ አቅም እንዳላቸው በሕዝብ ዘንድ እንዲታይ ትልቅ የህዝብ ግንኙነት ሥራን በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙሃን ሰርቷል በሚል የኢህአዴግን ፖሮፖጋንዳ “ቀሽምነት” የሚተቹ ወገኖች አሉ።

 

ምክንያት ሁለት

ኢህአዴግ በውስጡ የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩን በተደጋጋሚ ያመነውና ችግሩንም ለመፍታት ተደጋጋሚ መሀላ ሲፈጽም መቆየቱ የሚታወቅ ነው። በሌላ በኩል ኢህአዴግ ለራሱ አባሎች ጭምር ያለው ግምገማ ምን ይመስላል? በአባሎቹ ጥራት ይተማመናል ወይ? የሚል ጥያቄም መነሳቱ አይቀሬ ነው። ይህን በተመለከተ ባለፈው ዓመት ነሃሴ ወር በመቀሌ ከተማ በተካሄደው የግንባሩ 10ኛ ጉባዔ ወቅት የቀረበ ሪፖርት እንዲህ ይላል። “ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል ጊዜ በአራት ዙሮች 16 ሺህ 166 ጀማሪና መካከለኛ አመራሮች ሥልጠና ተሰጥቷል። ለመካከለኛና ጀማሪ አመራሩ ከተሰጠው ሥልጠና ሒደት ለመገንዘብ እንደተቻለው በተለይ በጀማሪ አመራር ደረጃ የሚገኙ አባሎችን በፖሊሲዎቻችን ላይ ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ የሚያነሱዋቸው ጉዳዮችም አንዳንዶቹ ከኪራይ ስብሳቢ ተቃዋሚ ኃይሎች አጀንዳዎች ብዙም ያልተለዩ ናቸው። ይህን በመገንዘብ በተደረገው ክትትል፣ ድጋፍና ግምገማ በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተሻለ ግንዛቤ ፈጥረው መውጣታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥርዓት ከመዘርጋቱም በላይ ሥልጠና አጠናቀው ወደመደበኛ ሥራቸው የተመለሱ አመራሮች በተግባራዊ እንቅስቃሴ ያመጡትን ለውጥና ያልተሻገሩዋቸውን ጉዳዮች ለመለየት የሚያስችል የመስክ ምልከታ ግብኣት በማሰባሰብ የሥልጠና አሰጣጡን የማጎልበትና ለሚመለከታቸው አካላት ግብረ መልስ በመስጠት ፕሮግራሙን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል” በሚል ያስቀምጣል።

የጉባዔው ሪፖርት ኢህአዴግ በአባላት ምልመላ ወቅት ተገቢው ጥንቃቄ ባለመደረጉ የጥራት ችግር ማስከተሉን ይጠቅሳል። “አባላት ሲመለመሉ ስለድርጅቱ ታሪክ፣ ፕሮግራም፣ እሴቶችና ሕገደንብ ዝርዝር ግንዛቤ ሳይዙ የሚመለመሉበት ሁኔታ እንዳለ ያመለክታል። ይህ ችግር የጎራ መደበላለቅን ሁሉ አስከትሏል። ጠባብነትን፣ ትምክህትን እንዲሁም በሃይማኖት ሽፋን የሚደረግ አክራሪነትን ለመታገል አላስቻለም” ይላል።

ይህ ግምገማ ኢህአዴግ በውስጡም ችግሮች እንዳሉበት ጠቋሚ ነው። ችግር መኖሩም ብቻ ሳይሆን እንዲህ ዓይነት አባል ይዞ ሀገራዊ ችግሮችን የመፍታት አቅሙ፣ በየደረጃው የሚታዩና በግንባሩ የታመኑ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮችን ለመፍታት የቱን ያህል ጠንካራ አቅምና ቁርጠኝነት ሊኖረው ይችላል? የሚል ጥያቄንም ማስነሳቱ አይቀሬ ነው።

 

ምክንያት ሶስት

በየአካባቢው እየተነሱ ያሉት ሕዝባዊ አመጾችና ሰልፎች ባለቤት እንደሌላቸው ሲነገርም አድምጠናል። ለዚህ እንደአንድ ምክንያት የሚነሳው በሕገመንግስቱ መሠረት የሰልፉ አስተባባሪ “እኔ ነኝ” ብሎ ሰልፉን የሚያሳውቅ አካል አለመኖሩ አንዱ ምክንያት ነው። ይህም ሆኖ ግን በብዙ አካባቢዎች በአንድ ጊዜ ሕዝባዊ አመጽ መቀጣጠል የቻለው ህዝቡ ፌስቡክና የመሳሰሉ ማህበራዊ ድረገጾች በመመራቱ ነው ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው። አንዳንዶች ይህን ሕዝባዊ ቁጣ በማቀጣጠሉ ረገድ ራሱ የኢህአዴግ አባሉ ሚና አልነበረውም ወይ? በሚልም የሚጠይቁ አሉ።

 

አለመግባባቶች በምን መልኩ እየተፈቱ ነው

ኢህአዴግ በራሱ አባል ጭምር አብዝቶ ከሚተችባቸው ድክመቶች አንዱና ዋንኛው ሕዝባዊ ሰልፎችን ወይንም የአመጽ እንቅስቃሴዎች ደም አልባ በሆነና በሰለጠነ  መንገድ መቆጣጠር ያለመቻሉ ነው። አደባባይ ባዶ እጁን የወጣ ሰልፈኛ በአስለቃሽ ጢስና በውሃ መበተን የሚቻልበት ዘመናዊ መንገድ እያለ ሰዎች ሕይወታቸውን መገበራቸው ብዙዎችን ቅር ያሰኘ፣ ያሳዘነ ክስተት ነው። ይህ በራሱ በኢህአዴግ ታምኖ ሰላማዊ ሰልፍን በዘመናዊ መንገድ ለመቆጣጠር የሚያስችል ስልጠናና አቅሙን ለመገንባት ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸው የሚታወቅ ቢሆንም አሁን ድረስ ከጠመንጃ አስተሳሰብ መላቀቅ እንዳልቻለ በተለይ በተቀናቃኝ ኃይሎች በየጊዜው የሚተችበት ደካማ ጎኑ ነው። በዚህ ምክንያት በቅርቡ በኦሮሚያ እና በአማራ አንዳንድ አካባቢዎች አደባባይ የወጡ ወገኖቻችን በተመሳሳይ የኃይል መንገድ ለመቆጣጠር፣ ለመበተን የተደረገው እርምጃ ብዙዎችን የሕይወት ዋጋ አስከፍሏል። ይህ ዓይነቱ የኃይል እርምጃ ሕዝቡን እልህ ውስጥ ከትቶ ውጥረቱን በማባባስ ሀገሪቱን በዘላቂነት ሠላምና መረጋጋት እንዳያሳጣት፣ ይባስ ሲልም ወደከፋ የእርስ በርስ ግጭት እንዳይከታት የብዙዎች ሥጋት ሆኗል። 

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
746 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us