“ሕዝብ ካልተሳተፈበት ተቃዋሚም ሆነ ኢህአዴግ…ሊጀምረው የሚፈልገው አመፅ የሻይ ስኒ ማዕበል ከመሆን አይዘልም”

Wednesday, 17 August 2016 13:23

“ሕዝብ ካልተሳተፈበት ተቃዋሚም ሆነ ኢህአዴግ…ሊጀምረው የሚፈልገው አመፅ የሻይ ስኒ ማዕበል ከመሆን አይዘልም”

የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ

 

የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን በሞት ካጣናቸው አራት ዓመታት አለፉ።  የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ባደረባቸው ህመም በውጪ ሀገር በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሰኞ ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጋቸውን በታላቅ ሐዘን የምናስታውሰው ነው። በያዝነው ሳምንት መጨረሻ ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና የትግል አጋሮቻቸው የሞቱበትን ዕለት በጸሎት አስበውት እንደሚውሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች መረጃ ይጠቁማል። በሕይወት የሚገኙት የትግል አጋሮቻቸው የእሳቸውን ራዕይ ለማስፈጸም ቃል ገብተዋል፣ የጠ/ሚኒስትር አስተሳሰብና ራዕይ መገለጫ ናቸው ተብሎ የሚገመቱት ሕያው ንግግሮቻቸው፣ ጹሑፎቻቸው፣ የሰጧቸው አመራሮች ናቸው። ከንግግሮቻቸው መካከል የሚከተሉትን  ለትውስታ አቅርበነዋል።

 

***          ***          ***

 

ጥያቄ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን የሚተካ ሰው አይገኝም በሚለው አስተያየት ይስማማሉ?

አቶ መለስ-እንግዲህ በየትኛውም የስራ መስክ ቢሆን የማይተካ ሰው የለም፤ በተለይ ደግሞ በፖለቲካ መስክ። የፖለቲካ ስራ የቡድን ስራ ነው። አፈፃፀምን በሚመለከት የሚከናወነው ተግባር ደግሞ የመላ ሕዝብ ስራ ነው። መሪዎች በቡድን መምራት መቻል አለባቸው። የሚፈጽመው ደግሞ ዞሮ ዞሮ ህዝቡ ነው። ስለዚህ በአመራር ደረጃም ካየነው የቡድን ስራ ስለሆነ አንድ ግለሰብ የማይተካ ነው የሚያስብል አይደለም። ግለሰቦች የየራሳቸው ሚና ይኖራቸዋል። አንዱ በአንድ መልኩ ሊልቅ፣ በሌላ መልኩ ሊያንስ ይችላል። ነገር ግን ጠንካራ ቡድን በግለሰብ ላይ የተመሰረተ አይደለም። በቡድን ላይ የተመሰረተ ነው። ጠንካራ ቡድን ከሆነ ደግሞ አንድ ግለሰብ ስለቀረ ቡድኑ ወዲያውኑ አይልፈሰፈስም። ደካማ ቡድን ከሆነ ግን ምንም ያህል ጠንካራ ተጫዋች ቢመደብም ለውጥ ሊያመጣ አይችልም። ስለዚህ ዞሮ ዞሮ የማይተካ ሰው አለ የሚባለው አባባል ብዙውን ጊዜ ግብዞች የራሳቸውን ሚና ለማግዘፍ የሚጠቀሙበት እንጂ አንዳችም ሳይንሳዊ መሠረት ያለው አይደለም።

ጥያቄ፡- በእርስዎ እድሜ ኢህአዴግ ተሸንፎ ተቃዋሚ ፓርቲ የሚሆን ይመስልዎታል?

አቶ መለስ፡- እንደ ሁኔታው ነው። ‘‘ስንት ዓመት እንደምቆይ አላውቅም። የአሁኑ ተርም ይህ (አምስት ዓመት) ሳያልቅም ማለፍ ይኖራል።’’ የአሁኑ ተርም ካለቀ በኋላም ማለፍ ይኖራል። እርግጠኛ መሆን አልችልም፣ ግን እንደምገምተው በሚቀጥለው አምስት አመት ስራችንን ካላጨማለቅን፣ ስራዬን በምለቅበትም ወቅት ከአምስት አመት በኋላ በሚካሄደው ምርጫም ቢሆን፣ ኢሕአዴግ ሊያሸንፍ ይችላል የሚል ግምት አለኝ። ስራችንን ካጨማለቅነው ግን በሚቀጥለው አምስት አመት እንደምንዘረር ምንም ጥርጥር የለውም። ስለዚህ ዞሮ ዞሮ የሚወስነው ጥሩ ስራ መስራታችን ላይ ነው። ጥሩ ስራ ከሰራን አሁን ያገኘነውን ውጤት የማንደግምበት ምክንያት የለም። ባለፈው ምርጫ ሕዝቡ ቢጫ ካርድ ሲሰጠን በግልፅ አስተምሮናል። ካላስተካከልን በቀላሉ በዝረራ ሊጥለን እንደሚችል እናውቃለን።

ጥያቄ፡- አንዴ ወደተማሪነት ጊዜዎ ልመልሰዎትና ከሚቀጥሉት ሁለት ነገሮች አንዱን ይምረጡ (ሀ) ዳቦ (ለ) ዴሞክራሲ?

አቶ መለስ፡- ምርጫዬ እንደሁኔታውና ጊዜው ይለያያል። የዴሞክራሲ እጦቱ ከባርነት የማይተናነስ ከሆነ ዳቦ አገኘህም አጣህም መኖር ትርጉም የለሽ ይሆናል። ባርያ ሆነህ ከመኖር ሞት ይሻላል። ይህ አዲስ ነገር አይደለም። ለዚህም ነው የታገልነው። በግፍ ቀንበር ተሰቃይተህና ተማረህ፣ ባሪያ ሆነህ ከመኖር ታግለህ ብታሸንፍ ታሸንፋለህ፤ ባታሸንፍ ደግሞ በሰላም ትገላገላለህ። ስለዚህ የሚያንገሸግሽ ግፍና መከራ ውስጥ ከሆነ ያለኸው ዳቦ ቢኖርም፣ ባይኖርም ትርጉም የለውም።

ሆኖም ግፉ ብዙም የማያንገሸግሽ ከሆነና ዳቦ አጥቼ ተርቤ የምሞት ከሆነ ዳቦን እመርጣለሁ። በቀን ሶስቴ መብላት ከጀመርኩ ግን ያቺን ትንሽ ግፍም ቢሆን ማስወገድ እፈልጋሁ። ስለዚህ ረሃብ ማለት ሞት ከሆነና ከባርነት የተሻለ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ሁኔታካለ እሱን መታገስ እችላለሁ። ነገር ግን ሁኔታው ከባርነት የማይተናነስ ከሆነ የፈለገው ቢመጣ ዳቦ ትርጉም የለውም። ሆዴ ከሞላ ግን ያቺን ውስን በደልም ቢሆን መቀየር እፈልጋለሁ። ስለዚህ ዳቦ ወይም ዴሞክራሲ ብቻ ተብሎ የሚመለስ ሳይሆን እንደየሁኔታው ይለያያል። እንደየደረጃና የመጥገብህ ሁኔታ መታገስ የምትችለው የግፍ መጠን አለ። ሆኖም እኔ እንደ ታጋይ የፈለገው ምክንያት ቢደረደር መሸከም የማልችላቸው ነገሮች አሉ።

ጥያቄ-የተለያዩ ወገኖች ግንቦት 20ን ጨለማ፣ ግንቦት 7ን ብርሃን አድርገው ይስሏቸዋል። እርስዎ በሁለቱ መካከል ያለውን ግንኙነት እንዴት ይገልፁታል?

አቶ መለስ፡- ግንቦት 20 ባይኖር፣ ግንቦት 7 አይታሰብም። ስለዚህ ግንቦት 7፣ የግንቦት 20 ውጤት ነው። የግንቦት ሃያ ዘውድ የዴሞክራሲ ዘውድ ነው። የራሱ እንቁዎች ነበሩት። ግንቦት 7 ተጨማሪ እንቁዎችን በዚያ ዘውድ ላይ አኑሯል። የግንቦት ሃያ ድል ታሪካዊና የምንኮራበት ነው። የግንቦት 7 ድል ይህን ታሪካዊ ድል ያጠናከረና ስር እንዲሰድ ያደረገ ሌላ ታሪካዊ ድል ነው። በዚህ እንኮራለን። እነዚህ ሁለት ድሎች የግንቦት 20ውም ሆነ የግንቦት 7ቱ የኢህአዴግ ብቻ ሳይሆኑ የመላ ኢትዮጵያ ህዝብ ድሎች ናቸው። በነዚህ ድሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ሊኮሩና ሊደሰቱ ይገባል። እንኳን ደስ አላችሁ!

ጥያቄ፡-ባንድ ወቅት ተቃዋሚዎችን የስኒ ላይ ማዕበል ናቸው ብለው ነበር። ከግንቦት 1997 ምርጫ ውጤት በኋላስ እንዴት አዩዋቸው?

አቶ መለስ፡- አባባሉን በትክክል ለማስታወስ ህዝቡ አመፅና ብጥብጥን ካልፈለገ ተቃዋሚዎች የሚቀሰቅሱት አመፅ የስኒ ላይ ማዕበል ከመሆን አይዘልም ብዬ ነበር። ይህ አባባል ያኔ ትክክል ነበረ፣ አሁንም ትክክል ነው፤ ለዘለቄታውም ትክክል ነው። ህዝብ ካልፈለገውና ህዝብ ካልተሳተፈበት ተቃዋሚም ሆነ ኢህአዴግ አሊያም ሌላ ሰው ሊጀምረው የሚፈልገው አመፅ የሻይ ስኒ ማዕበል ከመሆን አይዘልም፤ የህዝብ ድጋፍ ስለሌለው። የህዝብ ድጋፍ ያለው አመፅ ግን የሻይ ስኒ ማዕበል አይደለም፤ አለምን የሚያናውጥ ማዕበል ነው። ከምርጫው በኋላም ይሄ አቋሜ አልተለወጠም።

ጥያቄ፡-ከአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ግንኙነታችሁ እንዲህ የሻከረው ለምንድነው? በትጥቅ ትግሉ ወቅት ጓደኞች ነበራችሁ። ደርግን ለመጣል አብራችሁ እንዳልታገላችሁ ሁሉ ግንኙነታችሁ ለምን እንዲህ ሻከረ?

አቶ መለስ፡- የችግሩ መንስኤ አስመራ ላይ ያለው መንግስት ከጫካ አስተሳሰብ አለመላቀቅ ነው። ችግሩ ባህሪዩን መተንበይ በማይቻል አንድ አምባገነን መሪ ላይ የተመሰረተ መንግስት መኖሩ ነው።

ጥያቄ-ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ግንባርዎ ላይ ሽጉጥ ደግነን መንግስቱ ኃይለማርያምን ይቅር ይበልዋቸው፤ አሊያ ቃታውን እንስበዋለን ብንልዎ የትኛውን ይመርጣሉ?

አቶ መለስ፡- እኔ ለመንግስቱ ይቅርታ የማድረግና ያለማድረግ መብት የለኝም። ምናልባት ከሌሎች ጋር ሲነፃፀር መንግስቱ በግል ያደረሰብኝ በደል የተጋነነ ላይሆን ይችላል። ቢሆንም የመንግስቱ ጉዳይ የእኔ የግሌ ጉዳይ እንኳን ቢሆን ኖሮ ‘‘እኔ ፈትቼሃለሁ፣ እኔ አስሬሃለሁ’’ ማለቱ ፍትሃዊም፣ ተገቢም አይደለም። እሱ እንዳደረገው ብገድለው ወይም ብምረው ወደመንግስቱ ደረጃ ወርጃለሁ ማለት ነው። ስለዚህ ተበድዬ ከሆነ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ አለብኝ። ስለዚህ እሺ ወይም እምቢ የሚል መልስ መስጠት አልችልም። ባጭሩ አይመለከተኝም ማለት ብቻ ነው የምችለው።

ጥያቄ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የጊዜ አጠቃቀምዎ እንዴት ነው?

አቶ መለስ፡- ጊዜ በሰው ልጅ ቁጥጥር ሥር ያልሆነ የመጨረሻው ውድ ነገር ነው። አንድ ሰው ምን ያህል ጊዜ እንዳው አያውቅም። ስለዚህ ያለውን ጊዜ በአግባቡ መጠቀም አለበት። በእኔ ግምት ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም ሁለት ዋና ዋና ነገሮችን ማጤን ይገባል። አንደኛው አንድ ሰው መስራት የሚችለውን በቅደም ተከተል ለይቶ ማስቀመጡ ነው። የሚፈልገውን ሁሉ መስራት ስለማይችል መስራት የሚገባውን በቅደም ተከተል ለይቶ ማስቀመጡ የመጀመሪያ እርምጃ ይመስለኛል። ሁለተኛው በቅደም ተከተል ተለይቶ የተቀመጠውን በዲሲፕሊን መፈፀም፣ ስራውን በጊዜና በወቅቱ በተቻለ መጠን በጥራት ለመስራት መሞከር ነው። እነዚህን ሁለት ነገሮች ለማሟላት ጥረት አደርጋለሁ።

ጥያቄ፡- መለስ የዓመት ፈቃድ ወስደው ያውቃሉ?

አቶ መለስ፡- አዲስ አበባ ከገባን ጀምሮ እሁድ እሁድ አልሰራም። ከዚያ በተረፈ እረፍት ኑሮኝ አያውቅም። የ19 ዓመት ወጣት ከሆንኩ ጀምሮ እስካሁን ድረስ እረፍት ኑሮኝ ስለማላውቅ፣ እረፍት ምን እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ፤ ይናፍቀኛል። ጊዜ ባለማግኘቴ ያላነበብኳቸውና ማንበብ የምፈልጋቸው ነገሮች አሉ። ልፅፋቸው ፈልጌ ጊዜ ባለማግኘቴ ያልፃፍኳቸው ነገሮችም አሉ። ጊዜ አግኝቼ እንዚህን ነገሮች መስራት እፈልጋለሁ። ምን ያህል ጊዜ እንደሚገኝ ስለማይታወቅ የተገኘውን ከስር ከስሩ መጠቀምን እመርጣለሁ።

ምንጭ፡- ‘‘መለስ፤ ከልጅነት እስከ ዕውቀት’’፣ በትኩእ ባህታ (ሐምሌ 2002 ዓ.ም) 

***          ***          ***

 

“ሕዝቡ ሌቦችን ያጋልጥ”

የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ

“ሲቪል ሰርቪሱን በተመለከተ ዋናው ችግር ያለው ሥነምግባር ላይ ነው። ህዝብን ለማገልገል የሚያስችል መልካም ሥነምግባር በሌለበት ሁኔታ ሌሎች ሁሉ ይዳከማሉ። ይህንን የሥነምግባር ችግር ለመፍታት በአጭርና በረዥም ጊዜ የሚሳኩ የለውጥ አካሄዶች እየተተገበሩ ነው። በአጭር ጊዜ በሙስና፣ አድልኦ እና በመሰል ተግባራት የተሰማሩ ሰዎችን አጋልጦ፣ በቁጥጥር ሥር አውሎ ለፍርድ በማቅረብ የማስቀጣት ሥራ እየተካሄደ ነው። ነገርግን ሙስና፣ አድልኦ እና የመሳሰሉት የሥነምግባር ችግሮች ምንጮች ካልደረቁ በስተቀር ውጤቱ አመርቂ አይሆንም። ጭቃው ውስጥ የገባው ሰው ጭቃ ሲለቀለቅ፣ ጭቃ ተለቅልቀሃል ብለን ስናስር፣ ሌላ አዲስ ሲገባ እሱም አረንቋ ውስጥ ገብቶ ጭቃ ሲለቀለቅ እሱንም ስናስር…ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ነው የሚሆነው።

ከአጭር ጊዜ አኳያ የሥነምግባር ብልሹነት ያለባቸውን ተከታትሎ ለፍርድ ማቅረብ አስፈላጊ ቢሆንም ከረዥም ጊዜ አኳያ ወሳኙ አረንቋውን ማድረቅ ነው። እናም መንግሥት የችግሩን ምንጭ ለማድረቅና በአጭር ጊዜም የሚተገበሩትን በማከናወን ሙስናን ለመዋጋትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ይሰራል።

ሙሰኞችን በአድልኦ ሥራ ላይ የተሰማሩትን ሰዎች አጋልጠን ለፍርድ ለማቅረብ ጥረት እየተረደገ ነው። ይህንንም በጸረ ሙስና ኮምሽን፣ በፖሊስና በሌሎችም አካላት በኩል እየተተገበረ ነው። ነግር ግን ይህ ሒደት የራሱ ውስንነት አለበት። እናም ህብረተሰቡ ሙስና፣ አድልኦ አለ ብሎ ባሰበ ጊዜ መረጃውን እንዲሰጥ፣ ሌቦችን እንዲያጋልጥ የተለያዩ መድረኮች ተመቻችተዋል። የህብረተሰቡን ጥቆማ መሰረት በማደረግም በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩትን በቁጥጥር ሥር አውሎ ለማስቀጣት ጥረት እየተረደገ ነው።…”

 

ሚያዚያ 9 ቀን 2004፤ በፓርላማ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ 

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
848 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us