ለከፍተኛ ትምህርት ፈላጊዎች፣ እንደማስጠንቀቂያ

Wednesday, 24 August 2016 14:37

አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱ 2009 ልንቀበል ቀናቶች ብቻ ይቀሩናል። ወቅቱ የትምህርት መክፈቻ ነው። ይህ ወቅት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አዳዲስ ተማሪዎችን የሚቀበሉበትም ነው። እናም ተማሪዎች ማሟላት የሚገባቸውን፣ ተቋማትም መከተል ያለባቸው የትምህርት ቅበላ መስፈርቶች ለማስታወስ ትክክለኛ ጊዜው አሁን ነው።

በትምህርት ዘርፍ ሕግና ሥርዓትን ሲጓደል ትውልድን ጭምር ሊጎዳ የሚችል የጥራት እና የብቃት ችግርን ያስከትላል። እርግጥ ነው፤ በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት የጥራት ችግር ዘርፈ ብዙና የተወሳሰበ መሆኑን በርካታ ምሁራን በየጊዜው የሚገልጹት ጉዳይ ነው። መሠረታዊ ከሆኑትና በባለሙያዎች ከተለዩት ችግሮች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ።

-    ተማሪው በቂ ትምህርት ሳያገኝ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግባት፣

-    ካሪኩለሙ ተግባራዊ ክህሎትን የማስጨበጥ አቅም ማነስ፣

-    የሰለጠኑ መምህራን በሚፈለገው ደረጃ በብዛት ያለመኖር፣

-    የከፍተኛ ትምህርት ግብዓቶች እጥረትና በአግባቡ ያለመጠቀም ችግር፣

-    የተመራቂውን ዕውቀትና ክህሎት የሚመዝን ብቁ የመገምገሚያ ሥርዓት አለመኖር፣

-    ለምርምር አመቺ የሆነ የዩኒቨርሲቲና የኢንዱስትሪ ግንኙነት ያለመኖር ይጠቀሳሉ።

በተጨማሪም በከፍተኛ የትምህርቱ ዘርፍ የተሰማሩ አንዳንድ ተዋንያን ሕግና ሥርዓትን ተከትለው መሥራት አለመቻላቸው በትምህርት ጥራቱ ላይ እያስከተለ ካለው ጉዳት በተጨማሪ ተማሪዎች የትምህርት ማረጋገጫ ዲግሪ እና ዲፕሎማዎች ውድቅ (ዋጋ አልባ) እንዲሆኑ መንስኤ እየሆነ ነው። በተለይ በግሉ ዘርፍ ከፍተኛ የትምህርት ዘርፍ የተሰማሩ አንዳንድ ተቋማት ከቅበላ መስፈርት ውጪ ተማሪዎችን መቀበል፣ ባልተፈቀደላቸው ዘርፍ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር፣ ተገቢውን የሰው ኃይልና ቁሳቁስ እና አደረጃጀት አለመያዝ ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው። በዚህም ምክንያት ተቋማት የተቀበሏቸውን ተማሪዎች እንኳን ማስመረቅ ሳይችሉ ችግር ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ታይቷል።

 

የተቋማቱ ቁመና በ2008 በጀት ዓመት

በ2008 በጀት ዓመት 119 የትምህርት መስኮች የእውቅና ፈቃድ እና የእውቅና ፈቃድ እድሳት መከልከላቸው፣ የከፍተኛ ትምህርትና አግባብነት ኤጀንሲ በ2008 የመጀመሪያው 6 ወራት ውስጥ ከ110 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለያዩ 261 የትምህርት መስኮች ለቀረቡለት የእውቅና ፈቃድ እና የእውቅና ፈቃድ እድሳት ጥያቄ ምላሽ መስጠቱን ገልጿል። 

የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ከሰኔ 2007 እስከ ታህሳስ 2008 ዓ.ም. ድረስ ከቀረቡት 261 የትምህርት መስኮች ውስጥ የእውቅና ፈቃድ እንዲሰጥባቸው የቀረቡባቸው የትምህርት መስኮች 192 ሲሆኑ ሲሆኑ የተቀሩት 69 የትምህርት መስኮች የእውቅና ፈቃድ እድሳት ናቸው። በቀረበው ጥያቄ መሰረት ፕሮግራሞቹን ለመክፈት ወይም ለመቀጠል የሚያስችል መመዘኛ መስፈርት ማሟላታቸውን ለማረጋገጥ ያካሄደውን የዶክመንት ምርመራና የመስክ ግምገማ ውጤትን ማዕከል በማድረግ ለ106 የትምህርት መስኮች እውቅና ፈቃድ መስጠቱን እና ለ86 መከልከሉን፤ እንዲሁም ለ36 ፕሮግራሞች የእውቅና ፈቃድ ፈቅድ እድሳት እንደሰጠና ለ33 ፕሮግራሞች እንደከለከለ ገልጿል። በአጠቃላይ በመጀመሪያው 6 ወራት ውስጥ ያቀረቡለትን ጥያቄ መነሻ በማድረግ የዶክመንትና የመስክ ግምገማ አካሂዶ ባገኘው ውጤት መሰረት ለ142 ፕሮግራሞች ሲፈቅድ ለ119 ፕሮግራሞች ከልክሏል። 45 ነጥብ 6 በመቶ ለሚሆኑ (119 ፕሮግራሞች) የእውቅና ፈቃድና የእውቅና ፈቃድ እድሳት ከልክሏል።

ጥያቄ ባቀረቡበት የትምህርት መስኮች የተፈቀደላቸው ተቋማት በመመዘኛው መሰረት ስልጠና ለመጀመር ወይም ለመቀጠል የሚያስችሉ መስፈርቶችን ማለትም የቋሚ መምህራን ብዛትና ስብጥር፤ የተሟላ ቤተ-መጻህፍት፤ የተደራጀ ቤተ-ሙከራና የኮምፒዩተር ማዕከል ደረጃውን የጠበቀ ስርዓተ-ትምህርት እና ሌሎች ግብዓቶችን አሟልተው በመገኘታቸው ሲሆን እውቅና ፈቃድ እና እድሳት የተከለከሉት እኝህን የመሳሰሉ መመዘኛዎችን ሳያሟሉ በመገኘታቸው መሆኑን ኤጀንሲው አሳውቋል።

በግልከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለመማር ከመወስንዎ በፊት

መከተል ያለብዎ ቅድመ-ጥንቃቄዎች

     አንድ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የእውቅና ፈቃድ ጥያቄ ለኤጀንሲው ስላቀረበ ብቻ “በሂደት ላይ ነኝ፤ ይፈቀድልኛል” በሚል አስቀድሞ እራሱን ማስተዋወቅ፣ ተማሪ መመዝገብና ማሰልጠን አይችልም። ምክንያቱም የእውቅና ፈቃድ ጥያቄ አቅርቦ ተገምግሞ መስፈርቱን አሟልቷል ወይም አላሟላም የሚለው ውሳኔ የሚረጋገጠው ኤጀንሲው በደብዳቤ ሲገልጽለት ብቻ ነው። ተማሪ መቀበል የሚችለው በተጠየቀው የትምህርት መስክ መመዘኛውን ያሟላ ስለሆነ ተማሪ ተቀብሎ ማሰልጠን ይችላል የሚል ደብዳቤ/ፈቃድ ከተሰጠበት ዕለት አንስቶ ነው። ፈቃዱ ከተሰጠበት ዕለት በፊት ተመዝግበው የሚማሩ ተማሪዎች ካሉ የተማሩት ትምህርት የሚያዝላቸውና ህጋዊ ሊሆኑ የሚችሉት ፈቃድ ከተሰጠበት እለት ጀምሮ ነው። ከዚያ በፊት ያሳለፉት ጊዜና ያወጡት ገንዘብ ከንቱ ሆኖ ስለሚቀር ከመመዝገባቸው በፊት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። ለምሳሌ በአካውንቲንግ የትምህርት መስክ ዲግሪውን ለመማር የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በቅድሚያ ተቋሙ በአካውንቲንግ አውቅና ፈቃድ ተሰቶታል? በየትኛው ካምፓስ ነው የተፈቀደለት? የተፈቀደለት እስከ መች ድረስ ነው? ፈቃዱ ታድሷል? ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሆነውን መረጃ ማግኘት አለበት። መረጃውን በቀላሉ የሚያገኘው ተቋሙ የተሰጠውን ፈቃድ እንዲያሳየው መጠየቅ፤ የማሳየት ግዴታ አለበት። ከኤጀንሲው የተሰጠውን ፈቃድ ካላሳየ ገንዘብ አውጥቶ መመዝገብ ለብክነት ስለሚዳርግ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። እውቅና ፈቃድህን አሳየኝ ማለትና በተጨባጭ ማረጋገጥ ብቻ በቂ ነው። እውቅና ፈቃድ ባላገኘበት ወይም ባልታደሰ ፈቃድ እየመዘገበ ከሆነ ተጨባጭ መረጃ በመያዝ ለኤጀንሲው ጥቆማ እንዲሰጡ አሳስቧል።

 

ይህ የኤጀንሲው እርምጃ በተለይ በግል ተቋማት ለመማር የሚፈልጉ ወገኖች በቅድሚያ ዩኒቨርሲቲው ወይንም ኮሌጁ መማር በሚፈልጉበት የትምህርት ዘርፍ ዕውቅና ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ይገባቸዋል። አብዛኛው የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሕግና ሥርዓትን ጠብቀው በመሥራት ላይ መሆናቸው የሚታወቅ ቢሆንም አንዳንድ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተቃራኒው በምዝገባ ወቅት የትምህርት ሚኒስቴር ያስቀመጠውን የቅበላ መስፈርት በመጣስ ከመስፈርት ውጪ ተማሪዎችን የሚቀበሉበት ሕገወጥ አሠራር እየተከተሉ መገኘታቸውን  ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ ይጠቁማል። ይህንንም አስቀድሞ ለመከላከል ሲባል ኤጀንሲው በአጠቃላይ የቅበላ መስፈርቱን ለሕዝቡ ይፋ አድርጓል። ይህን የማያሟሉ ተማሪዎች አንዳንድ ተቋማት እንቀበላለን ብለው ቢያግባቡዋቸው እንኳን እንዳይመዘገቡ ወይንም ከኤጀንሲው ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲጠይቁ መክሯል።

ስለቅበላ መስፈርቶች

     በማንኛውም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም በዲግሪ ፕሮግራም ለመማር የሚፈልጉ ተማሪዎች ቀጥሎ የተቀመጡ መስፈርቶችን ማሟላት ይኖርባቸዋል። እነዚህም፡-
     1ኛ. የመሰናዶ ትምህርት ያጠናቀቁ ትምህርት ሚኒስቴር ለትምህርት ዘመኑ ያስቀመጠውን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ መቁረጫ ነጥብ ያሟሉ ወይም
     2ኛ. ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም በ10+3፣ በደረጃ 4 እና 5 ያጠናቀቁ እንዲሁም በቀድሞ 12+2 ዲፕሎማ ያላቸው ሆነው


• በሙያው የደረጃ አራት የብቃት ምዘና (COC level-4) ያለፉ፣
• በሰለጠኑበት ሙያ ቢያንስ አንድ ዓመት የስራ ልምድ ያላቸው እና 

• ተቀባይ ተቋማት የሚዘጋጁትን የመግቢያ ፈተና ያለፉ ሆነው እነዚህን መረጃዎች ሙሉ ለሙሉ በምዝገባው እለት የሚያቀርቡ ወይም


    3ኛ. በውጭ ሀገር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አጠናቀው ወደ ከፍተኛ ትምህርት መግባት የሚያስችላቸው የአቻ ግመታ በኤጀንሲው የተሰጣቸው ወይም
    4ኛ. ተቀባይነቱ የተረጋገጠ ሌላ ዲግሪ ያላቸው መሆን አለባቸው።
    ከቅበላ መስፈርት ውጪ የዲግሪ መርሃ-ግብር ተመዝግቦ መማር ትርፉ የገንዘብና የጊዜ ብክነት ብቻ መሆኑን ኤጀንሲው አሳስቦ ወላጆች፣ ተማሪዎች፣ ስፖንሰር የሚያደርጉ አካላት፣ በአጠቃላይ ትምህርት ፈላጊዎች አስቀድመው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኤጀንሲው ይመክራል።ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
1330 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us