“አንድ ሰው በተመደበበት ሙያ ስኬታማና ውጤታማ ባለመሆኑ ከኃላፊነቱ ከተነሳ ምኑ ጋር ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የሚሆነው?”

Wednesday, 07 September 2016 14:05

አንድ ሰው በተመደበበት ሙያ ስኬታማና ውጤታማ ባለመሆኑ ከኃላፊነቱ ከተነሳ

ምኑ ጋር ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የሚሆነው?”

አቶ ሙሼ ሰሙ

የቀድሞ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት

 

ለሁለት ቀናት የተካሄደው አራተኛው ዙር ሀገር አቀፍ የወጣቶች ኮንፍረንስ ባለፈው ዕረቡ ነሀሴ 25 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት  ተጠናቋል። ወጣቶቹ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ፤ እንደዚሁም የተለያዩ አደረጃጀቶችን ወክለው የተገኙ ናቸው። ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ መስተዳደሮች የወጣት ወኪሎች በተጨማሪ የጎዳና ተዳዳሪ ወጣት ተወካዮች፣የአካል ጉዳተኛ ወጣት ተወካዮች፣ የወጣቶች ፌደሬሽን እና ሌሎች ተወካዮች ተገኝተዋል። በጊዜው በርከት ያሉ ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጥያቄዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርበዋል።

ኢትዮጵያና መሰል ታዳጊ ሀገራት ከፍተኛ የወጣት ቁጥር የሚገኝባቸው ሀገራት ናቸው። ባደጉት ሀገራት የህዝቡ በህይወት የመኖር እድሜ ረዥም በመሆኑ ከባዱ ፈተና በኢኮኖሚ ውስጥ ታትፎ የሌላቸው አዛውንቶች ቁጥር ከፍ እያለ መሄድ ነው። ኢትዮጵያ የወጣቱ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ እንደ አንድ የሰው ሀብት ቢታይም፤ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ይህንን ኃይል ወደ ስራ ማሰማራት ካልተቻለ ሌላ አገር አቀፍ ፈተና ነው።

በዚህና በሌሎች ጉዳዮች የራሳቸውን አስተያየት እንዲሰጡን የቀድሞ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙን አነጋግረናል። አቶ ሙሼን ከወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ፈተና ጋር በተያያዘ ጥያቄዎችን ብናነሳላቸውም ጉዳዩን ከወቅታዊው አጠቃላይ ሁኔታ ጋር አያይዘው ሰፋ አድርገው መመልከትን በመፈለጋቸው ሌሎች ተጨማሪ ተዛማጅ ወቅታዊ ጥያቄዎችንም አንሰተንላቸዋል። የሰጡትንም ምላሽ እንደሚከተለው አዘጋጅተን አቅርበነዋል።

ሰንደቅ፡- በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገር አቀፍ የወጣቶች ኮንፍረንስ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የወጣት ስራ አጦች ቁጥር የሚመለከተው ይገኝበታል። አሁን ኢኮኖሚው እያሰተናገደው የሰው ኃይልና የስራ ፈላጊው ቁጥር እየተራራቀ ባለበት ሁኔታ የወጣት ስራ አጦች መበራከት ሌላው ከባድ የሀገሪቱ መጻኢ ፈተና ሆኖ ሊታይ አይችልም?

አቶ ሙሼ፡-  ስራ አጥነት በራሱ አንድ ፈተና ነው።  ይሁንና በዚች ሀገር ሰርቶ ከማግኘትና ከስራ አጥነት ባሻገር አንድ በስጋትነት የሚታይ ወሳኝ ጉዳይ አለ። በበርካታ ዜጎች አዕምሮ ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የፌደራሊዝም አደረጃጀት ምክንያት ሀገሪቱ ልትበታተን ትችላለች የሚል ስጋት አለ።

ይህ ደግሞ በቀጥታ ከህልውና ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ነው። ስራ አጥቶም ተስፋ ማድረግ አንድ ነገር ነውይህች ሀገር እንደ ሀገር የመቀጠሏ ጉዳይ ለብዙ ወጣቶች አሳሳቢ ጉዳይ ነው። በጊዜው የሚታዩት አዝማሚያዎች ተስፋን የሚያሰንቁ አይደሉም።

ይህ ብቻ ሳይሆን “በዚች አገር ላይ ስራ ሰርቼ በምፈልገው ደረጃ ህይወቴን አለውጥም” የሚል ስጋት አለ። ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልም ሌላኛው በዚች ሀገር ያለ መሠረታዊ ጥያቄ ነው። ሰራ ማግኘቱ ብቻ ሳይሆን ከስራ ጋር ተያይዘው የሚነሱ በርካታ ጉዳዮች አሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ወጣቱ ዛሬ የሚጠይቀው ሀሳቡን በነፃነት የመግለፅ መብቱ እንዲከበርለት ነው። ዲሞክራሲያዊ መብቶቹ እንዲጠበቁለት ነው።

አንድ ሰው ስራ አገኘ ሲባል የሚለካው ከምን አንፃር ነው?ስራ ማግኘቱ ብቻ በራሱ የመጨረሻ ግብ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል? በስራ ውስጥ እኮ ብዙ ሊተነተኑ የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች አሉ። አንዱ ጉዳይ፤ ተቀጣሪው በስራው የሚያገኘው የክፍያ ሁኔታ ነው። ሰራተኛው ሰርቶ በሚያገኘው ገቢ እነደየደረጃው ራሱን ማስተዳደር መቻል አለበት። ለተቀጠሩበት ስራ የስራ ዋስትና  ማግኘት ያስፈልጋል። አንድ ዜጋ አሁን የሚሰራው ስራ ቀጣይ ኑሮን ለማሻሻል ተስፋ የሚያሰንቀው መሆን መቻል አለበት። በደመወዝ ቤተሰብ መመስረት፣ለኑሮ አመቺ የሆነ መኖሪያ ቤትን መከራየት መቻልና የመሳሰሉት ሁሉ፤ አንድ ሰው ስራ ከማግኘቱ ባሻገር ያሉ ጥያቄዎች ናቸው። ስለዚህ እነዚህ ጥያቄዎች ከስራ አጥነቱ ባሻገር ስራ ባለው ዜጋም ውስጥ እየተጠየቁ ያሉና መልስም የሚያሻቸው ጉዳዮች ናቸው። 

 አግባብ ያልሆነ ኢኮኖሚያዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖር ሌላኛው ጥያቄ ነው በአግባቡ ከተያዘና በአግባቡ ከተመራ ሀገሪቱ ውስጥ ያለው እምቅና የለማ ሀብት ለዜጎች በቂ ነው። ይሁንና ዘረፋ፣ ሙስና እና የሀብት ብክነቱ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል እንዳይኖር ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው።

  

ሰንደቅ፡- አሁን የተፈጠረውን ግጭትና የፖለቲካ ውጥረት ተከትሎ ኢህአዴግ የውስጡን ችግር በመፍታት መፍትሄ ለማምጣት ያሰበ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልፅ ይታያልጠቅላይ ሚኒስትሩ  የወጣቱ ችግር በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ የሚታይ መሆኑን ገልፀዋል። በእርስዎ አተያይ አሁን የሚታየውን የወጣቱን ስራ አጥነት፣ስደት፣ለግጭቶች ተጋላጭ መሆን በዚህ ገዢው ፓርቲ አቅጣጫ መፍታት ይቻላል?

አቶ ሙሼ፡- አይመስለኝም። ስራው ከሁሉም በፊት ወጣቱም ሆነ ሌለው ህዝብ የሚያናሳቸውን  ጥያቄዎች ከመቀበል ይጀምራል። ወጣቱ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተቀፅላ እየተበጀላቸው “የሌሎች ሀይሎች አጀንዳ ናቸው” ሲባሉ ቆይተዋል። በመጀመሪያ ጥያቄው ምንም ይሁን ምን ዜጎች ሲያነሱት መቀበል ያሻል። ከዚህ ውጪ ምላሹን የመስጠቱ ጉዳይ አቅም የሚፈቅደውና የማይፈቅደው፣ጊዜ የሚጠይቅና አፋጣኝ ምላሽ የሚሻውን ጉዳይ ሊለይ ይችላል። የችግሮቹ መፈጠር እኮ ከመነሻው ጥያቄዎቹን ለመቀበልና ለማስተናገድ ፍላጎትን ማሳየት ባለመቻሉ ነው። ችግሮች ባልተፈቱ ቁጥር እየተጠራቀሙ ሄዱ፤ በመጨረሻ ወደ አደገኛ አዝማሚያ አመራ።

አሁን ራሱ ኢህአዴግ ጥያቄዎቹን በጥያቄነት እየተቀበለ ያለውም በከፊል ነው። የሀገሪቱ የውስጥ ችግር ሲንከባለል የቆየው እኮ “የውጭ ኃይሎች እጅ አለበት፣ከጀርባው እነገሌ አሉበት” በሚል ሰበብ አስባብ ነው። አሁንም ቢሆን ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው በዜጎች የተነሱትን ጥያቄዎች አንድ በአንድ ለይቶ መቀበሉ ላይ ነው። ከዚያ በኋላ ነው ስለመፍትሄ ማውራት የሚቻለው። የወጣቱም ችግር መፍትሄ የሚፈለግለት ከዚሁ አቅጣጫ ነው የሚል እምነት አለኝ።

ሰንደቅ፤- ኢህአዴግ በዳግም ህዳሴ ለውጦችን የሚያመጣ መሆኑን በመግለጫና በተለያዩ የመንግስት ኃላፊዎች በኩል ሲገልፅ ቆይቷል። ስህተቶችንም ማመኑን አመልክቷል። እነዚህ ጥያቄዎቹን መቀበሉን አያሳዩም?

አቶ ሙሼ፡- 25 ዓመት ሙሉ “እታረማለሁ፣ ተሳስቻለሁ” ማለት ምን ማለት ነው? ሁሉም ሰው የተሰጠው በጊዜ ተገድቦ ነው። ምንም ነገር የሚሰራው በጊዜ ተለይቶ በተቀመጠ ገደብ ነው። ሰዎች ተፈጥሮ ባስቀመጠልን ገደብ በህይወታችን አንድ ቀን አንዘልም፤ አንድ ቀንም አንጨምርም። ይህ ከሆነ ለምንድን ነው የኢህአዴግን ስህተት እድሜ ልካችንን የምንሸከመው? እኔ ይሄ የሚገባኝ ነገር አይደለም። ሁልጊዜ ተሳስቻለሁ ከማለት፤መፍትሄ የማምጣቱ ጉዳይ ከአቅማቸው በላይ ከሆነ የሌሎችን እገዛ መጠየቅ ነው። በሙያ መመራት የሚገባቸው ሥራዎችና ኃላፊነቶች ካሉ በባለሙያ እንዲመሩ ማድረግ ነው

 ያላቸው የፖለቲካ አመለካከት እንደተጠበቀ ሆኖ በሙያቸው ሀገራቸውን ማገልገል የሚችሉና ፍላጎት ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን አሉ። እነዚህ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች የመፍትሄ አካል መሆን የሚችሉ ናቸው። ሀገሪቱ የሁሉም ናት። ህዝቡንና አገሪቱን ለማገልገል የግድ በአንድ የፖለቲካ አስተሳሰብ ውስጥ ግቡ የሚለው አካሄድ አያዋጣም። የትም አገር እድገት የሚመጣው ስራው በተገቢው ባለሙያ ሲሰራ ብቻ ነው። አንድ ችግር ሲፈጠር  የፖለቲካ ሹመኞችን ከአንዱ መስሪያ ቤት ወደ ሌላ በማዛወር መፍትሄ ማምጣት  አይቻልም። ይህ ለዓመታት ያየነውና ምንም ለውጥ ያላመጣ ጉዳይ ነው።

ሰንደቅ፡- የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ማንም ሰው የኢህአዴግን አላማ እስካስፈፀመ ድረስ ከሙያው ይልቅ የፖለቲካ ታማኝነቱ ቅድሚያ ተስጥቶት በመንግስት የስራ ኃላፊነት ላይ የሚመደብ መሆኑን በአንድ ወቅት የገለፁበት ሁኔታ ነበር። በቅርቡ ደግሞ ዜጎች ማናቸውምን የፖለቲካ አመለካከት ይዘው በሙያቸው ሀገራቸውን ማገልገል የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ተመልክቷል። በቅርቡም የሚኒስትሮች የካቢኔ ለውጥም ይጠበቃል። በዚህ ሂደት የተሻለ ለውጥ ይጠበቅ ይሆን? እንደ አንድ የፓርቲ አቋም ለውጥስ ተደርጎ መወሰድ ይችላል?

አቶ ሙሼ፡- 25 ዓመት ሙሉ ከአንዱ ሚኒስቴር ቦታ ወደ ሌላው እየተዘዋወሩ የምናውቃቸው 15 ወይም 20 የሚሆኑ ሰዎች ናቸው። እነዚህ የሚሾሙት ሰዎች በዚያ ዘርፍ ልምድ አላቸው? ሙያ አላቸው?፣ እውቀት አላቸው? የሚለው ጉዳይ አይታይም። በዘርፉ ችሎታ እንደሌላቸውና ውጤታማ እንዳልሆኑ እየታወቀ፤ ከሀገር ጥቅም ይልቅ እነሱን ላለማስከፋት ሲባል ከአንዱ መስሪያ ቤት ወደ ሌላው እየተዘዋወሩ በሹመታቸው እንዲቀጥሉ ሲደረግ ቆይቷል።

 ላለፉት ሁለት አስርት አመታት የተመለከተው እውነታ ቢኖር ይሄንን ነው። መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ካስፈለገ የሙያ ቦታዎች በሙሉ ለባለሙያተኞች ክፍት መሆን አለባቸው። ቀደም ሲል በነበረው አካሄድ ሁሉም ነገር በፖለቲካ አስተሳሰብና በአባልነት እየተቃኘ የሚሄድበት አሰራር የሚቀጥል ከሆነ ለውጥ አይኖርም።

ያላቸውን የፖለቲካ አመለካከት ይዘው ሀገራቸውን በሙያ የሚያገለግሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር እናደርጋለን ብለው ከሆነ፤ በቀጣይ ከመጪው ጥቅምት ጀምሮ የምናየው ጉዳይ ይሆናል። ይህንን ጉዳይ በአቋም ለውጥነቱ የማረጋግጠው በተግባር ሳየው ብቻ ነው። ይሄንን አቋም ከነአሰራሩና ከነአፈፃፀሙ ተብራርቶ ሲቀርብ ካላየሁት በስተቀር አላምንም።

ሰንደቅ፡- ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ሚኒስትሮችና አንዳንድ የመንግስት ኃላፊዎች ከሚኒስትርነት ቦታቸው ከተነሱ በኋላ በሌላ ሹመት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የሚሆኑበት ሁኔታ አለ። በቀጣይ በሚኖረው የካቢኔ ለውጥ መሰል አካሄዶች የሚኖሩ ከሆነ ለውጡ የቱ ጋር ነው?

አቶ ሙሼ፡-እዚህ ጋር የግለሰብ ሰም ማንሳት አልፈልግም።

ሰንደቅ፡- የግለሰብ ስም አላነሳንም። አጠቃላይ ባለው አካሄድ ላይ አስተያየትዎን እንዲሰጡበት ነው።

አቶ ሙሼ፡-አንድ ሰው በተመደበበት ሙያ ስኬታማና ውጤታማ ባለመሆኑ ከኃላፊነቱ ከተነሳ ምኑ ጋር ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የሚሆነው? ይህ ብቻ አይደለም። ትምህርት ሚኒስትር የነበረ ሰው በድንገት  የመንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን ይሆናል። በአንድ ወቅት አንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን የመራ ሰው ከመራው መስሪያ ቤት ጋር በማይገናኝ ሌላ የሚኒስትርነት ቦታ ይመደባል። ለዓመታት በጣት  የሚቆጠሩ ሰዎች  እዚያና እዚህ የሚሽከረከሩት፤ ይህች አገር ሰው ስለሌላት ነው?

በእንዲህ አይነት አካሄድ የሚጠበቅ ለውጥ አይኖርም። የሚሰጡት የፖለቲካ ሹመቶች እንደተጠበቁ ሆነው፤ የዚህን ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የፖለቲካ ውሳኔ ብቻ በቂ አይደለም። በመሆኑም አሁንም የቀደመው አካሄድ በመሰረታዊነት መለወጥ መቻል አለበት።

ሰንደቅ፡- አንድ ሰው በሙያው ቢሾም፤ ያው የሚያገለግለው የመንግስትን የፖለቲካ ፕሮግራም፣ ፖሊሲና መመሪያ ነው። ከዚህ አንፃር አንድ ሰው የፖለቲካ አመለካከቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ሀገሪቱን በሙያው ማገልገል ይችላል ሲባል በምን መልኩ ነው አስታረቆ መሄድ ይቻላል?

አቶ ሙሼ፡-ይሄ ጉዳይ ከተነሳ መሰረታዊው ጥያቄ የሚሆነው ከመንግስት ፖሊሲ ጋር የሚያያዝ ይሆናል። በባለሙያ መፈፀም የማይችል ፖሊሲ ከሆነ፤ የማየሰራ ፖሊሲ ነው ማለት ነው። ፖሊሲውን ሊያስፈፀም የሚችል የሙያ ሰው መሬት ላይ ካልተገኘለት አስቸጋሪ ነው። በትምህርትና በእውቀት ያልተቀረፀ ፖሊሲ ከሆነ አያግባባም ለአሰራርም ያስቸግራል።  ይህ ከሆነ ደግሞ አንድም መንግስት ፖሊሲዎቹን መቀየር ይጠበቅበታል፤ አለበለዚያም ያለው እጣ ፈንታ መውረድ ነው። “የኔን ፖሊሲ የሚያስፈፅሙት የእኔ አባለት ብቻ ናቸው” የሚል አቋም የሚራመድ ከሆነ፤ፖሊሲው በትምህርት ገበታ ላይ የሌለ ነው ማለት ነው። አለም ላይ የማይታወቅ ፖሊሲ ነው ማለት። ይህ ከሆነ ደግሞ፤ እውነት ነው ማንም ሊያስፈፅመው አይችልም። ሊፈፀም የሚችለው በራሱ በፓርቲው የፖለቲካ ተሿሚዎች ብቻ ነው።

ሰንደቅ፡- በኢህአዴግ በኩል በስፋት የሚሰማው ነገር በፓርቲው ውስጥ ለውጥን በማምጣት ሰፊ ሀገራዊ ለውጥ ማምጣት የሚቻል መሆኑን ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ ፓርቲው በራሱ የሚያካሂዳቸው ለውጦች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ከዚህ ውጪም ውጫዊውን የፖለቲካ ከባበቢያዊ ሁኔታ በመለወጥና የፖለቲካ ምህደሩን በማስፋት፣ በስራ ላይ ያሉና “አሳሪ ናቸው” የሚባሉትን ህጎች በማሻሻልና አሳታፊ የፖለቲካ ስርዓትን በመፍጠር ነው የሚለው ወገኖች አሉ። እርሰዎ በዚህ ዙሪያ ያለዎት አስተያየት ምንድ ነው?

አቶ ሙሼ፡-እኔም በፓርቲው ውስጥ ብቻ ለውጥን በማምጣት የተሟላ ለውጥ ይመጣል የሚል እምነት የለኝም። መጀመሪያ መጠየቅ ያለበት ጉዳይ ህዝቡ ራሱ በፓርቲው ላይ አለው እምነት አለው ወይ የሚለው ጉዳይ ነው? “ህዝቡ በእኔ ላይ እምነት አለው” ብሎ የሚያምን ከሆነ በመጀመሪያ ከምርጫ በፊት በተወሰነ የህዝብ ድምፅ ይሄንን መፈተሸ መቻል አለበት። ይሄ በሌሎች ሀገራት “Vote of Confidence” ይባላል።

 ይህ አሰራር የግድ የምርጫ ቦርድ አያስፈልገውም። በኢንተርኔትና በሌሎች አሰራሮች ሊከናወን የሚችል ስራ ነው። ይህ አይነቱ አሰራር የሚያገለግለው፤ አሁን ኢህአዴግ በሚለው አካሄድ ህዝቡ ተሳታፊ መሆኑን ለማረጋገጥ በፓርቲው ላይ ያለው እምነት በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማወቅ ያገለግላል። ምርጫ አሸንፌያለሁና ተወደደም ተጠላም  አምስት አመት መቀጠል ያለብኝ እኔ ነኝ  ብሎ ሊቀጥል ይችላል። እርግጥ ነው ህገ መንግስቱም የመንግስት ስልጣን የሚያዘው በምርጫ ነው ስለሚል፤ እኔም ይሄን እቀበላለሁ።

ነገር ግን በመሀል የህዝብ እምነት የተሸረሸረበት ሁኔታ ከተፈጠረ ፓርቲው በራሱ ውስጥ ለውጥ በማምጣት እንዲህና እንዲያ አደርጋለሁ ከማለት ይልቅ ህዝቡ በእኔ ላይ ምን ያህል ይተማመናል? የሚለውን ጉዳይ መለየት መቻል አለበት። ይህ በበርካታ ሀገራት ያለ አሰራር ነው። ይህ የህዝብ አመኔታ ተሸርሽሯል ተብሎ ሲታሰብ ከመደበኛው የምርጫ ሰሌዳ ውጪ የሚከናወን አሰራር ነው። እኔ ከፓርቲ የውስጥ ለውጥ ይልቅ ይህ መቅደም አለበት ብዬ አስባለሁ።

ሰንደቅ፡- አሁን እርስዎ ያሉት ሀሳብ እንደተጠበቀ ሆኖ የፖለቲካ ሜዳውን አመቺ ለማድረግ የፕሬስ ህጉን ጨምሮ ቀደም ሲል አጨቃጫቂ የነበሩት ህጎች በማሻሻል የፖለቲካ ተሳትፎው ከፍ የሚልበት ሁኔታ አይኖርም?

አቶ ሙሼ፡- ቅድም ወደ ተናሰሁበት ስመለስ የህብረተሰቡ ጥያቄ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊም ነው። ሰዎች ሀሳባቸውን በነፃነት መንገድ መግለፅ ካልቻሉ፤ ሀሳባቸውን የሚገልፁት ራሳቸው በገባቸው መንገድ ነው። ነፃ ፕሬሱ በመዘጋቱ፣ በመታፈኑና በመዳከሙ እጅግ አስፈሪ የሆነው ፌስቡክ ነው የመጣው። በዚህ የሚተላለፉት መረጃዎች ደግሞ በዘረኝነት የተመረዙ፣ የጉዳዩ ጀማሪ ማን እንደሆነ የማይታወቅ መረጃዎች የሚተላለፉበት ሚዲያ ነው። ይህ ሊሆን የቻለው እኮ የህዝቡ መተንፈሻ ነፃ ሚዲያዎች እንዲጠፉና እንዲዳከሙ በመደረጋቸው ነው። ይሄን ጉዳይ ማስተካከል መሰረታዊው ጉዳይ ነው። ከፕሬስ ህጉም በሻገር ሌሎች የፖለቲካ ምህዳሩን ያጠበቡ ህጎች በሚገባ እየተፈተሹ መስተካከል መቻል አለባቸው።

ሰንደቅ፡- አሁን ህዝቡ እየጠየቀ ያለውን አፋጣኝ ምላሽንና “የኢህአዴግን ፋታ ስጡኝ” አካሄድ በምን መልኩ አጣጥሞ ወደ መፍትሄው መምጣት ይቻል ይሆን?

አቶ ሙሼ፡- ኢህአዴግ እስከ ዛሬ ተቃዋሚዎች የሚሉትን ሰምቶ አያውቅም። ይህም በመሆኑ አሁን ፊት ለፊት ተፋጠው የሚታዩት ኢህአዴግና ህዝቡ ብቻ ናቸው አሁን የጉዳዩ ባለቤቶች ኢህአዴግና ህዝቡ ሆነዋል። ስለዚህ ጥያቄና መልሱም የሚሆነው ከህዝቡ ጋር ነው ማለት ነው። በቀጣይ የሚሰጠውን መልስና ይዟቸው የሚመጣቸውን መፍትሄዎች በጋራ የምናየው ይሆናል። የህዝቡ ቁጣ ገንፍሎ ህይወቱን እስከ መሰዋት አድርሶታል። ከዚህ አንፃር ኢህአዴግ የህዝቡን ጥያቄ በሚያረካ መልኩ መልስ የሚሰጥበት እድል አለ ብዬ አላምንም። ብዙ ጊዜም በከንቱ ጠፍቷል።

ይምረጡ
(11 ሰዎች መርጠዋል)
1821 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us