የሙስና ዱካ

Wednesday, 07 December 2016 15:07

“ሙስናና ብልሹ አሠራር፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደር ችግር (የአፈጻጸም ችግር)…” የተሰኙ ቃላቶች በተለይ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በሚገኙ መገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ ሰምተናቸዋል፣ እየሰማናቸውም ነው። ሥጋቶቹና ችግሮቹ ግን የሚነገረውን ሲሶ ያህል የመቅረፍ ዕድል ያገኙ አይመስሉም። በቅርቡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተነሱ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን ተከትሎ “የመንግሥትን ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል..” የሚሉ ንግግሮች ከከፍተኛ አመራሩ እየተሰማ ነው።

ሙስና (Corruption) ሥርወ ቃሉ ላቲን ነው። ሙስና ሥልጣንን አማክሎ መያዝ፣ ሥልጣንን ያለገደብ መጠቀም እና ተጠያቂነት አለማስፈንን ይመለከታል። (corruption= Monopoly power + Discreation + Accountability) በሥልጣን አለአግባብ መገልገልን፣ አለአግባብ ሐብት ማፍራትን፣ የሚመለከት ነው። በሀገራችን የሙስና ጽንሰ ሃሳቡ ገንዘብ ከመስጠትና ከመቀበል ጋር ጠበብ ብሎ የሚታይ ነው። ነገርግን ጽንሰ ሃሳቡ ሰፋ ያለ ነው። ሙስና የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ በማለት የሚከፍሉትም አሉ።

የፖለቲካ ሙስና የፖለቲካ ሥልጣንን ተጠቅሞ አለአግባብ መበልጸግን ወይንም ሌሎች እንዲበለጽጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸትን ይመለከታል። ለአብነት ያህል በአዲስአበባ ከተማ ሙስናና ብልሹ አሠራር ከሰፈነባቸው መካከል መሬት ቀዳሚው ነው። መሬት ውድ ሐብት በመሆኑ ሥልጣኑ ያለው ሰው በሕገወጥ መንገድ ለራሱና ለፈቀዳቸው ሰዎች “ኪስ” ቦታዎችን እንዲያገኙ በማድረግ አለአግባብ እንዲበለጽጉ የሚደረግበት አሠራር ሰፍኖ መቆየቱ ጸሐይ የሞቀው ሐቅ ነው። በዚህ መንገድ በአንድ ጀምበር ሚሊየነር መሆን የቻሉ፣ ትልልቅ ሐብትም ያፈሩ ሙሰኞች እዚህም እዚያም መታየታቸው አልቀረም።

የኢኮኖሚ ሙስና የሚባለው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት ተብሎ የሚከናወን ነው። ለምሳሌ አንድ የጉምሩክ  ኦፊሰር የግል ጥቅም ለማግኘት ብሎ መፈተሽ ያለበትን ተሽከርካሪ ሳይፈትሽ ወይም ለይስሙላ ያህል አየት አደርጎ እንዲያልፍ ሊተባበርና ለዚህም ሥራው በጉቦ መልክ ገንዘብ ሊቀበል ይችላል። አንዳንዶች ይህን ሕገወጥ ሥራ ቢዝነስ ይሉታል። ጋዜጠኞች ደግሞ ከስራቸው ጋር በተገናኘ የሚቀበሉት ማባበያ “ቡጢ” ሲሉ ይጠሩታል። አንድ የፍ/ቤት መዝገብ ቤት ሠራተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ብቻ በተከሳሽ ጥያቄ የከሳሽ ፋይል እንዲጠፋ ወይንም ከፋይሉ ውስጥ የተወሰኑ ጠቃሚ መረጃዎች እንዲጠፋ ሊተባበርና ገንዘብ ሊቀበል ይችላል። የትራንስፖርት ቢሮ ሠራተኛው አንድ ተገልጋይ በፍጥነት ወይንም ያለወረፋ በማገልገል ገንዘብ ሊቀበል ይችላል። ነጋዴው የተለያዩ ሸቀጦችን በማከማቸት ወይንም በመደበቅ ሰው ሰራሽ እጥረት ከፈጠረ በኃላ ትንሽ ትንሽ ሸቀጦችን እየለቀቀ እጥፍ ድርብ ትርፍ ሊያካብት ይችላል። ይህ አድራጎት የመልካም አስተዳደር ችግርን የሚያስከትል ቢሆንም በቦታው የተቀመጡ ሰዎች በዚህ አድራጎት ውስጥ የተገኙት በአብዛኛው የኢኮኖሚ ጥቅም ከማግኘት ጋር በተያያዘ ነው።

በጥቅሉ እስከዛሬ ለሙስና የተሰጠው ትርጓሜ የተሟላና በግልጽ የተቀመጠ ሆኖ አልተገኘም። ሙስና ማለት ሥልጣንን በመጠቀም የህዝብን ሐብት ለግል ጥቅም ማዋል ነው የሚለው ትርጉም ኢኮኖሚዊ ጠቀሜታ ላይ ተኮረ ነው። በተጨማሪም ይህ ትርጓሜ በግለሰቦችና በግል ተቋማት የሚፈጸመውን ሙስና አያካትትም። ለአብነት ያህል ቁማርተኛው የእግርኳስ ዳኛውን በገንዘብ ቢገዛው የመንግሥት ኃላፊውን ላይመለከት ይችላል። የአንድን ግለሰብ ወይም ተቋም የጥናትና ምርምር ውጤት መሰረቅ ሙስና ነው። ግን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት የተፈጸመ አይደለም። አንድ የፖሊስ መኮንን ወንጀል ያልፈጸመን ግለሰብ በሀሰት ወንጅሎ ለማስቀጣት የሚያርገው ጥረት ሙስና ቢሆንም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት የተደረገ፤ ላይሆን ይችላል።

በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉም የሙስና ዓይነቶች እንደወንጀል የማይቆጠሩባቸው ሁኔታዎች ነበሩ። አ.ኤ.አ ለ1977 ዓ.ም በፊት የአሜሪካ ኩባንያዎች ከአገር ውጪ የሥራ ኮንትራት ለማሸነፍ የሚሰጡት ጉቦ እንደወንጀል አይቆጠርም ነበር። በመሆኑም ሙስና በአብዛኛው የሕግ ጉዳይ ሳይሆን የሥነምግባር ጥያቄ ሆኖ ይታያል።

ስለዚህ ሙስና ከኢኮኖሚ ጥቅም አንጻር ብቻ ታይቶ “አለአግባብ የሕዝብ ሐብት ለግል ጥቅም ማዋል ነው” በሚለው ትርጓሜ ብቻ ሊታጠር አይገባውም። ምክንያቱም ሙስና በኢኮኖሚያዊ ጥቅም ብቻ የተንጠለጠለ ባለመሆኑ ነው። ሙስና ለመፈጸም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አንዱ ቢሆንም ክብርን ለማስጠበቅ፣ በሥልጣን ኮርቻ ላይ ለመፈናጠጥ፣ ወሲባዊ እርካታን ለማግኘት የሚሰጡት ጉቦዎች ወይም ጥቅማጥቅሞች ሊሆኑ ይችላሉ። አደገኛ ዕጾችና ቁማሮች ሳይቀር የሙስና ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

የሙስናን ትርጉም ከሕግና ከሥነምግባር አንጻር ብቻ ማየትም አዳጋች ነው። አንድ ጨዋ ባል ሚስቱ ስትባልግ አግኝቶ ቢገድላት ወንጀል ነው ሊባል ይችላል። ግድያው ከሥነምግባር አንጻር የሚደገፍ አይደለም። ግን ሰውየው ስትማግጥ ያገኛት ሚስቱን መግደሉ በምንም መልኩ ሙስና ነው ሊባል አይችልም ሲሉ የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ክቡር ገና በአንድ መድረክ ላይ ያቀረቡት ጥናታዊ ወረቀት ያስረዳሉ

በሀገራችን የሙስና ትርጉም ጠበብ ብሎ ይታያል። ብዙውን ጊዜ ከገንዘብ መቀበልና መስጠት ጋር የተቆራኘ ነው። በተለምዶ ጉቦ የሚባለው ዓይነት አድራጎት ብቻ ተደርጎ የሚታይበት ሁኔታም አለ። ነገርግን ጽንሰ ሃሳቡ ሰፊና ውስብስብ ነው። ቀላል ምሳሌ ለማንሳት ያህል በዘመድ አዝማድ የሥራ ቅጥር መፈጸም፣ በቅጥር፣ በሥራ ዕድገት ወቅት በተለይ ሴቶችን ለጾታዊ ፍላጎት ማግባባት ወይንም ማስገደድ ሥልጣንን አለአግባብ መገልገልን ያጠቃልላል። በሥራ አጋጣሚ ያገኙትን መረጃ የተለየ ጥቅም ለማግኘት ሲባል አሳልፎ መስጠት ሙስና ነው። ለምሳሌ በጨረታ ሒደት የተቀናቃኝን መረጃ ለሌላ ተወዳዳሪ አሳልፎ በመስጠት ኢ- ፍትሐዊ ውድድር እንዲኖር ማድረግ፣ ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመታገል በማሰብ ጥቆማ የሰጠን ሰው ማንነት በሚስጢር አሳልፎ መስጠትና በዚህም ጥቅም ማግኘት መጥቀስ ይቻላል። እንዲህ ዓይነት ኢሞራላዊ እና ኢ- ሥነምግባራዊ ተግባራት የሙስና አካላት ናቸው።

የፌዴራሉ የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ኮምሽን በተለይ በሀገራችን በዋነኛነት በሙስና ተንሰራፍቶ የሚገኘው ከግዥ ጋር በተያያዙ ተግባራት ላይ መሆኑን በመረጃ ያነሳል። «የሙስና ተግባር የሚፈጸመው በተወሰኑ ተቋማት ወይንም ሥራ አካባቢዎች ብቻ ነው ብሎ መደምደም ባይቻልም ከተገልጋዮች ጋር የዕለት ተዕለት ግንኙነት የሚያደርጉ ተቋማትና የሥራ አካባቢዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት በጀት የሚመደብላቸውና የመንግሥት ጥቅም (በግዥ፣ ቀረጥና ታክስ በመሰብሰብ ወዘተ) ከማስከበር ጋር የተያያዙ ሥራዎችን የሚሰሩ ተቋማትና የሥራ አካባቢዎች ይበልጥ ለሙስና ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ በመስኩ ላይ የተጻፉ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚህ አንጻር ግዥ ለሙስና ተጋላጭ የሥራ ዘርፍ እንደሆነ መገመት አያዳግትም። በአንዳንድ አገር ውስጥ ለመንግሥት ግዥ የሚመደብ በጀት ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ከ15 በመቶ እስከ 30 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል ይጠቁማል። ይሁን እንጂ ዘርፉ ለሙስና ተጋላጭ ከመሆኑ የተነሳና ግዥዎቹ በውል መሰረት ባለመፈጸማቸው ከ10 እስከ 25 በመቶ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከ40 እስከ 50 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ በሙስና እንደሚመዘበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በአጠቃላይ ለፌዴራል መንግሥት ከሚመደበው ዓመታዊ በጀት ውስጥ ከ60 እስከ 70 በመቶ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ደግሞ ደግሞ እስከ 15 በመቶ የሚሆነው ግዥ ላይ እንደሚውል ጥናቶች ያሳያሉ። በመሆኑም ዘርፉን ከሙስና መታደግ ለነገ የማይባል ተግባር መሆን እንዳለበት የኮምሽኑ መረጃ ያስረዳል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርት እንደሚያሳየው በ2005 በጀት ዓመት ኦዲት ከተደረጉ መንግሥታዊ ተቋማት መካከል 43 በሚሆኑ መ/ቤቶች የግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያን ሳይከተሉ 165 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ግዥ ተፈጽሞ መገኘቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በተመሳሳይ መልኩ በ2004 ኦዲት ከተደረጉ መንግስታዊ ተቋማት መካከል 30 ያህሉ የግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያን ሳይከተሉ 353 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ግዥ ፈጽመው ተገኝተዋል። ይህ ዘርፉ የቱን ያህል ለሙስናና ብልሹ አሠራር ተጋላጭ መሆኑን በተጨባጭ ያሳያል።¾

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
558 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us