አዲስ አበባን ለማደስ!....

Wednesday, 14 December 2016 14:05

ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ባስቀመጠው ጥልቅ ተሀድሶ መሰረት ሰሞኑን የተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ስብሰባ የተለያዩ ሹመቶችን በማፅደቅ መጠናቀቁ ተሰምቷል።

ምክር ቤቱ ምክትል አፈጉባኤ የነበሩትን አቶ ወልደገብርኤል አብርሃን በማንሳት አቶ ተስፋዬ ተርፋሳ ተክቷቸዋል። ከዚህ ባለፈም በከንቲባ ድሪባ ኩማ የቀረቡለትን ስምንት የስራ አስፈጻሚ አመራሮችን ሹመት ተቀብሎ አፅድቋል።

በዚህም መሰረት፡-

1. ዶክተር ጀማል አደም ዑመር የጤና ቢሮ ኃላፊ፣
2. አቶ ማቲዎስ አስፋው የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር፣
3. ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ የመንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ፣
4. አቶ መሃመድ አህመዲን የትምህርት ቢሮ ኃላፊ፣
5. አቶ ዘርዑ ሱሙር የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ፣ 
6. አቶ ልዑልሰገድ ይፍሩ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ፣
7. አቶ ለዓለም ተሰራ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ፣
8. አቶ ዲላሞ ኦቶሬ የንግድ ቢሮ ሃላፊ ሆነው ተሸመዋል።


በተጨማሪም ምክር ቤቱ የ14 ዳኞችና የሶስት ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሰብሳቢ ሹመትንም ተቀብሎ ማጽደቁ ታውቋል።


ከተማዋ ከንቲባ ድሪባ ኩማ፤ በ2008 ዓ.ም ከተቋቋሙት ዘጠኝ የስራ አስፈጻሚ አመራሮች ውስጥ ሰባቱ የቢሮ ኃላፊዎች እንዲቀጥሉ መወሰኑን ተናግረዋል።


የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ፣ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ነባር ኃላፊዎች ባሉበት እንዲቀጥሉ ተወስኗል።


አዲስ የከተማ ማስተር ፕላን ተጠንቶ በመጠናቀቁ ምክንያት አራት የማስተር ፕላን ማስፈፀሚያ ተቋሞች እንደሚቋቋሙ፣ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አደረጃጀትና አሰራር ላይ እየተደረገ ያለው ጥናት ሲጠናቀቅም አደረጃጀቱ በአዲስ መልክ እንደሚሰራ ከንቲባ ድሪባ አስታውቀዋል።

 

የአመራር ለውጡ ምን ይፈይድ ይሆን?

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፌዴራል መንግሥቱን የሚኒስትሮች ም/ቤት ፈለግ በመከተል ኃላፊዎችን የማንሳትና የማዘዋወር እርምጃ ወስዷል። አዎ! አዲስ አበባ ለውጥ ያስፈልጋታል። ካሪዝማቲክ (በሕዝብ የሚወደድ፣ ሰርቶ የሚያሰራ) መሪዎችን ትሻለች። ሰሞኑን  የተደረገው ሹም ሽር የከተማዋን ተግባራት በብቃት ለመፈጸም የሚችሉ መሪዎችን መደፊት ለማምጣት ያለመ እንደሆነ ይታመናል። በመሆኑም አስተዳደሩ ውዝፍ ችግሮቹን በአዲሱ ካቢኔ ብቃት ያለው አመራር ለመቅረፍ ይችላል ተብሎ ይገመታል።

አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ፣ የዲፕሎማሲና የዓለም አቀፍ ተቋማት መናኽሪያ እንደመሆንዋ ስምዋን የሚመጥን ደረጃ ላይ እንድትገኝ የሁሉም ነዋሪዎችዋ ምኞት ነው። በአሁኑ ሰዓት በከተማዋ የሚታዩት መኖሪያ ቤት ችግር፣ የትራንስፖርት፣ የደረቅና የፈሳሽ ቆሻሻ ማኔጅመንት፣ የመብራት፣ የመጠጥ ውሃ እና የመሳሰሉት ችግሮች በመፍታት ረገድ አዲሱ ካቢኔ የተሻለ አመራር እንዲሰጥ ይጠበቃል።

 

ስለመኖሪያ ቤት ችግሮች

በከተማዋ ካሉት ችግሮች መካከል የመኖሪያ ቤት ችግር የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ ነው። በ2005 በጀት ዓመት በተካሄደው ድጋሚ ምዝገባ በጠቅላላው 994 ሺ788 ሕዝብ የመኖሪያ ቤት ፈላጊነት አመልክቷል። አብዛኛው ሕዝብም በ20/80፣ በ40/በ60 እና በ10/90 የቤት ልማት መርሃግብሮች ቁጠባውን እያከናወነ ነው። ከእነዚህ የቤት ልማት መርሃግብሮች መካከል ከፍተኛ ተመዝጋቢ የያዘው (ከ860 ሺ በላይ ሰዎች ያመለከቱበት) 20/80 መርሃግብር ነው። ወደ 160 ሺ ገደማ ነዋሪዎች በ40/60 መርሃግብር አመልክተው ቁጠባ ላይ ናቸው። ወደ 23 ሺ ገደማ ያመለከቱበት የ10 በ90 የቤት ፈላጊዎች ሙሉ በሙሉ የቤት ባለቤት ማድረግ መቻሉ እንደ አንድ አዎንታ የሚወሰድ ነው።

መንግሥት የመኖሪያ ቤት ችግሩን ተገንዝቦ ከ1996 ዓ.ም ወዲህ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት በማቋቋም የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ የሄደበት ርቀት ምንም እንኳን አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ጋር  ባይመጣጠንም እርምጃው በራሱ የሚደነቅ ነው። በጋራ የመኖሪያ ቤቶች ፕሮግራም በ40/60 እና 10/90 ሳይጨምር በ20/80 በተለምዶ ኮንዶሚኒየም በሚባለው ፕሮግራም ብቻ ከ860 ሺህ በላይ የሚጠጋ ነዋሪ በቤት ፈላጊነት ተመዝግቦ እየተጠባበቀ ሲሆን ባለፉት 12 ዓመታት ብቻ ወደ 175 ሺህ ገደማ ነዋሪዎች የቤት ባለቤት ሆነዋል። ይህ የአሁኑ እጅግ ዘገምተኛ የሆነ አካሄድ በዓመት 15ሺ ቤቶችን እንኳን ለመገንባት ያስቻለ አይደለም። በዓመት 15 ሺ ቤቶች ቢገነባ ተብሎ ቢወሰድ እንኳን ሌላ ዙር ምዝገባ ሳይካሄድ የተመዘገቡትን ከ860ሺ በላይ ሕዝብ የቤት ባለቤት ለማድረግ ከ50 ዓመታት በላይ ጊዜን የሚወስድ መሆኑ ሲታሰብ ፕሮግራሙ የህዝብን አጣዳፊ የመኖሪያ ቤቶች ችግር ከመቅረፍ አንጻር ያለው አቅም ዋጋቢስ ያደርገዋል። እናም የቤት ልማት ፕሮግራሙ አካሄድና አዋጪነት ከሁሉም አቅጣጫ መርምሮ ተጨማሪ የመኖሪያ ቤቶችን ችግርን የሚቀርፉ አፋጣኝ እርምጃዎችን አስተዳደሩ መውሰድ ይጠበቅበታል። በኮንደማኒየም ቤቶች ግንባታ የውጪ ሀገር ልምድ ያላቸው አልሚዎች እንዲሳተፉ ማድረግ፣ ዜጎች በማህበር ተደራጅተውና የባንክ ብድር ተመቻችቶላቸው የራሳቸውን ቤት የሚሰሩበት፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ቤት ማልማት የሚችሉ ባለሃብቶች ወደዘርፉ ገብተው ቤቶች እንዲሸጡ፣ እንዲያከራዩ የሚደረግበት እንዲሁም በዘርፉ ፈጣን ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ሌሎችም አማራጮችን የማየቱ ጉዳይ ፈጣን ምላሽን የሚሻ ነው።

 

የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ጉዳይ፣

የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ቁጥሮች ላይ ተንጠልጥሎ የሚታይ ነው። አንዳንዴ የከተማዋ 70 በመቶ፣73 በመቶ፣ ሌላ ጊዜ 90 በመቶ የመጠጥ ውሃ ፍላጎት ተሟልቷል የሚል እርስ በርስ የሚላተሙ መረጃዎች በመገናኛ ብዙሃን ፍጆታነት ውለው ተሰምተዋል። እውነታው ግን ይህንን አያረጋግጥም። በመሀል ከተማ ያሉ አካባቢዎች ጭምር ከውሃ እጦት ጋር ተያይዞ ውሃ በቦቴ እስከማደል የተደረሰበት ተጨባጭ ሁኔታ እየታየ መሆኑ የቁጥሩን ጨዋታ ፉርሽ ያደርገዋል።

 

ትራንስፖርት

ጥናቶች እንደሚሳዩት በአዲስአበባ ከተማ ከሚኖረው ሕዝብ 60 በመቶ ያህሉ የሚጓጓዘው በእግሩ ነው። ቀሪው 11 በመቶ በአውቶብስ፣ 20 በመቶ በታክሲ፣ 5 በመቶ በግል መኪና፣ 3 በመቶ በመንግስትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሸከርካሪዎች የሚጠቀም ነው። 60 በመቶ እግረኛ በሆነበት በዚህች ከተማ የትራንስፖርት ችግር የዕለት ተዕለት አጀንዳ ነው። ችግሩ የነዋሪውም የአስተዳደሩም ራስ ምታት እንደሆነ አሁን ድረስ የዘለቀ ችግር ነው። ችግሩን ለመቅረፍ በፌዴራልም በአስተዳደሩም የተለያዩ እርምጃዎች የተወሰደ መሆኑ የሚካድ ባይሆንም አሁንም ፍላጎቱን የሚመጥን እርምጃ መውሰድ ባለመቻሉ ዜጎች በጠራራ ጸሐይ ጭምር ታክሲና አውቶቡስ ጥበቃ በየጎዳው ተሰልፈው የሚታዩበት ታሪክ ቀጥሏል።

 

መልካም አስተዳደር ማስፈን - እንደነጠላ ዜማ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የበላይ ኃላፊዎች በየጊዜው፣ በየመድረኩ የሚነገሩና በተጨባጭ ግን ሲፈቱ የማይታዩ ችግሮች መካከል የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የሙስናና ብልሹ አሰራር ችግሮች በተግባር መፍትሔ የሚሹ አንገብጋቢ ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ዛሬም በየክፍለከተማውና ወረዳዎች ነዋሪዎች የሚፈልጉትን መንግሥታዊ አገልግሎት በፍጥነትና በጥራት አያገኙም። ዛሬም የመንግሥት ሹመኞችና አንዳንድ የሲቪል ሰርቪስ ተቀጣሪ ሠራተኞች በደመወዝ ለተቀጠሩበት ሙያ አገልግሎት ለመስጠት ጉቦ መቀበላቸው ነውርነቱ ቀርቷል። ሙስናና ብልሹ አሠራርም በበርካታ መ/ቤቶች ሕጋዊ መስሏል። የከተማዋ ከፍተኛ አመራር ጭምር ይህን መሰል ችግር በየመድረኩ ከማውገዝ ያለፈና እዚህም እዚያም የተበጣጠሰ እርምጃ (ሰዎችን የማባረር) ከመውሰድ ሌላ ምንም ማድረግ አልቻለም።

 

የፅዳት ጉዳይ

የከተማዋ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ማኔጅመንትም ከሰፈር ጀምሮ እስከ አደባባይ ድረስ በችግሮች የተሞላ ነው። በከተማዋ ዝናብ ጠብ ሲል በብዙ ሚሊየን ብር ወጥቶባቸው የተገነቡ መንገዶች በጎርፍ ተሞልተው የሚታዩበት ትዕይንት የተለመደ ሆኗል። መንገዶቹ እንዴት በቂ የፍሳሽ ማስወገጃ ሳይኖራቸው እንዴት ተገነቡ የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ ያሉትንም ፍሳሽ ማስወገጃዎች በወቅቱ በማደስና በማጽዳት ረገድ ወስንነቶች መኖራቸው ተጨማሪ ምክንያት መሆኑ አልቀረም። ከቤትና ከተቋማት ወደአደባባይ የሚጣሉና የሚለቀቁ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎች በወቅቱ ያለመነሳት፣ ሥራውም ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚከናወን አለመሆኑ ከተማዋን ደረጃና ተመራጭነት ያሳነስ ተግባር ሆኖ እየታየ ነው። እናም አዲሱ ካቢኔ እነዚህን መሰል ችግሮችን አጥንቶ፣ ነዋሪዎች ጋር ተቀራርቦ በመወያየት ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችሉ ተከታታይ እርምጃዎችን የመውሰድ ከባድ ሥራ ይጠብቀዋል። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
604 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us