የፕሮጀክት መዘግየት ዋጋው ምን ያህል ነው?

Wednesday, 21 December 2016 14:36

-    ጊቤ ሦስት ሲታቀድ 18 ቢሊየን ብር፣ ሲጠናቀቅ 35 ቢሊየን ብር

 

የግልገል ጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሰሞኑን የመመረቁ ዜና በተለይ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃንን የአየር ሰዓት አጣብቦ ከርሟል። በእርግጥም 1 ሺ 870 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው እንዲህ ዓይነት ፕሮጀክት ሲመረቅ ደመቅ ያለ ሽፋን ማግኘቱ ሲያንስበት እንጂ አይበዛበትም። ይህም ሆኖ ከምረቃው ዜና ጀርባ ያሉ እውነታዎች እምብዛም ሽፋን የሚያገኙ አይደሉም። ለምሳሌ ፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ከነበረበት ጊዜ ከአምስት ዓመታት በላይ ጊዜ መውሰዱ በገንዘብም፣ በጊዜ ረገድ የሚያስከፍለው ዋጋ የትየለሌ ቢሆንም ይህን አጀንዳ ተከድኖ ይብሰል የተባለ መስሏል።

 

የጊቤ 3 እውነታዎች፣

ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው ቅዳሜ ታህሳስ 8/2009 የተመረቀው የጊቤ ሶስት የኃይል ማመንጫ ግድብ፣ ግንባታው የጀመረው በ1999 ዓ.ም ነው። ፕሮጀክቱ በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት በወላይታና ዳውሮ ዞኖች ድንበር ላይ፤ ከአዲስ አበባ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 450 ኪ.ሜ. ርቀትላይ ይገኛል። ፕሮጀክቱ ከባህር ጠለል በላይ ከ800 ሜትር እስከ 896 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል።

 የግድቡ ርዝመት 630 ሜትር ሲሆን የግድቡ ቁመት/ከፍታ 264 ሜትር ነው። የግድቡ አጠቃላይ ውሃ የመያዝ አቅም 15 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ፣ የኃይል ማመንጫ ዩኒቶች/ተርባይኖች እያንዳንዳቸው 187 ሜጋ ዋት ማመንጨት ይችላሉ። ግድቡ በጠቅላላው የሚያመነጨው 1 ሺ 870 ሜጋዋት ሲሆን ዓመታዊ የኃይል ምርት በአማካኝ 6500 ጊጋዋት ነው። ግንባታውን በጋራ ያከናወኑት የሥራ ተቋራጮች የጣልያኑ ሳሊኒ ኢምፕሬጂሎ እና የቻይናው ዶንግፋንግ ናቸው።

የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ 1 ነጥብ 5 ቢሊዬንዩሮ ሲሆን ገንዘቡ  60 ከመቶ ከቻይናው አይ.ሲ.ቢ.ሲ. ባንክ በተገኘ ብድር፣ ቀሪው 40 ከመቶ በኢትዮጵያ መንግሥት የተሸፈነ ነው። ይህ ፕሮጀክት እስከ አሁን 900 ሜጋ ዋት ያመነጭ ነበር።

የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ወደ 4 ሺ 200 ሜጋ ዋት የሚያሳድገው መሆኑን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የተገኘ መረጃ ያመለክታል። ይህ ኢህአዴግ ሀገሪቱን ሲቆጣጠር 400 ሜጋ ዋት የነበረው ኃይል የማመንጨት አቅም ጋር ሲነጻጸር እጅግ የላቀ ውጤት እንደሆነ ለዘርፉ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ያስረዳሉ። በትግበራ ላይ በሚገኘው የ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ውሃን ጨምሮ ከተለያዩ ምንጮች 17ሺ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማምረት ታቅዷል።

 

በፕሮጀክቱ ላይ የኬንያዊያን የተሳሳተ እይታ

ጊቤ 3 ከኬንያ ጋር በሚያዋስን ቦታ እንደመገኘቱ ፕሮጀክቱ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ያልተደረገበትና በኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር ላይ ለሚኖሩ ኬንያዊያን ወገኖች ሕይወታቸውን የሚያናጋ መዘዝ አለው በሚል ተከታታይና ከፍተኛ ቅስቀሳ ሲያደርጉ መቆየታቸው የሚታወስ ነው። በዚህም ሒደት አበዳሪ ሀገራትና ተቋማት እጃቸውን እንዲሰበስቡም ጥረት አድርገዋል። ይህን የተሳሳተ አቋም ኬንያዊያን በአካል ፕሮጀክቱን እንዲጎበኙ ጭምር በማድረግ በኢትዮጵያ በኩል የተሰሩ ስራዎች ከፍተኛ ውጤት እንደነበራቸው መካድ አይቻልም።

የፕሮጀክቱ መዘግየት ጉዳይ

      ጊቤ 3 እስከምረቃው ድረስ 10 ዓመታትን የፈጀ ሲሆን 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዩሮ (በአሁኑ ምንዛሪ ከ35 ቢሊየን ብር በላይ) ወጥቶበታል። ፕሮጀክቱ ሲጀምር 17 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር እንደሚፈጅ በተደጋጋሚ ይፋዊ መግለጫ ተሰጥቶበት እንደነበር አይዘነጋም። ፕሮጀክቱ ከ17 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ የጠየቀው ፕሮጀክቱ በመዘግየቱ ይሁን ወይንም ሌላ ምክንያት ይኑረው ለጊዜው በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።

     ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተገኘ መረጃ መሠረት ይህ ፕሮጀክት መጠናቀቅ የነበረበት በ2004 ዓ.ም ነበር። የተጠናቀቀው ግን በ2009 ዓ.ም ነው። ለምን? ምን ችግር አጋጠመ? የጊዜው መራዘም ሀገሪቱን ምን ያህል ተጨማሪ ወጪ አስወጣ? የሚሉና መሰል ጥያቄዎች በግልጽ አልተመለሱም። ይህም ሆኖ ግን ጠ/ሚኒስትሩ አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ በምረቃው ሥነሥርዓት ላይ የግድቡ የግንባታ ሒደት ከፍተኛ ፈተናዎችን ማለፉን መናገራቸው አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።  ጠ/ሚኒስትር እንዳሉት ዛሬ በይፋ የተመረቀው የግልገል ጊቤ ፕሮጀክት በቀላሉ እውን የሆነ ሳይሆን በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ ተፈትኖ ያለፈ ታላቅ ሀገራዊ ስኬታችን

ነው። ፕሮጀክቱ ገና ከጅምሩ የተደቀኑበትን የፋይናንስና የመልክዓ ምድራዊ ችግሮች እንዲሁም ከምክንያታዊነት ይልቅ ሃይማኖታዊ በሚመስል መልኩ የአካባቢ ተቆርቋሪ ነን ባዮች ያልተቋረጠ የማጥላላት ዘመቻ በፅናት በመመከት ለስኬት በመብቃቱ ለሁላችንም ወደር የሌለው ብሄራዊ ኩራት ሊሆን ችሏል” ብለዋል። ጠ/ሚኒስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ የፕሮጀክቱ መዘግየት ጉዳይ በፋይናንስና በጊዜ ረገድ ሀገሪቱን ያስከፈለው ዋጋ የትየለሌ ነውና አሁንም ቢሆን ጉዳዩ በቂ ማብራሪያን የሚሻ ነው። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
635 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us