የኢትዮ የትራፊክ ደህንነት ኮንፈረንስ ሰሞኑን ይካሄዳል

Wednesday, 28 December 2016 14:28

 

ይና ቢዝነስ ፕሮሞሽን ሥራዎች ከፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ እና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በአሁኑ ወቅት በአሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰውን የትራፊክ አደጋ አስመልክቶ ሁሉን ዓቀፍ ግንዛቤ የሚፈጥር በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን አገር ዐቀፍ “የኢትዮ የትራፊክ ደህንነት ኮንፈረንስ” አዘጋጀ። ኮንፈረንሱ በዋነኛነት በመላው ዓለም የሚከበረውን የዓለም አቀፍ የመንገድ ትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች መታሰቢያ ቀን አስመልክቶ “የትራፊክ ደህንነት ለሁሉም በሁሉም!” በሚል መሪ ቃል ታህሳስ 26 ቀን በኤሊያና ሆቴል ይካሄዳል።

እንደዓለም ጤና ድርጅት መረጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚከሰት የመንገድ ትራፊክ አደጋ ሳቢያ በየዓመቱ ቁጥራቸው 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ የዓለማችን ሰዎች ህይወታቸውን ያጣሉ። 50 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ለቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ይዳረጋሉ። በየዕለቱም ከ3 ሺ 400 ያላነሱ የምድራችን ነዋሪዎች ከቤታቸው ወጥተው ሳይመለሱ ይቀራሉ። ባደጉት አገራት በመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ ከ60 ከመቶ የሚለቀው ጉዳት በአሽከርካሪዎች ላይ ሲደርስ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ግን ከ80 በመቶ በላይ አደጋ ሚደርሰው በእግረኞች እና በተሳፋሪዎች ላይ ነው። በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከትራፊክ አደጋ ጋ ተያይዞ ከሚከሰተው ሞት ውስጥ 70 ከመቶ የሚሆነው የሚከሰተው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገራት ውስጥ ነው። ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት ያላቸው የመኪና ብዛት ከ4 በመቶ ባይበልጥም ከ10 በመቶ ያላነሰ ሞትን በትራፊክ አደጋ በማስተናገድ ከፍተኛ የመንገድ ትራፊክ አደጋ ከሚከሰትባቸው አካባቢዎች መካከል ዋንኛው መሆናቸው አልቀረም። በታዳጊ አገራት ከኤችአይቪ በመቀጠል ወጣቱን የሕብረተሰብ ክፍል በመግደል አቻ የሌለው የትራፊክ አደጋ እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ይፋዊ መረጃ ከሆነ በአሁኑ ወቅት በዓለም በገዳይነቱ 9ነኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ይሄው የተሸከርካሪ አደጋ ተገቢውን ጥንቃቄ አገራት ካልወሰዱ በቀር ከሶስት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሶስተኛው ዓለም አቀፍ ገዳይ የጤና እክል ሊሆን ስለመቻሉ ይፋ አድርጓል። በአገራችንም ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ በመጣው የትራፊክ አደጋ በአማካይ በዓመት ከ3000 ሺህ ያላነሱ ዜጎች ሕይወታቸውን እያጡ ነው። ምንም እንኳ በመዲናችን በነዋሪዎቿ ከሚከናወነው እንቅስቃሴ ውስጥ 70 ከመቶ የሚደርሰው በእግር ቢሆንም በአዲስ አበባ ብቻ በየቀኑ በአማካይ ከ20 ያላነሱ የትራፊክ ግጭቶች ሲከሰቱ በየዓመቱ ደግሞ በአማካይ ከ7000 ያላነሱ ግጭቶች ሪፖርት ይደረጋሉ። በአገር አቀፍ ደረጃም ከአንድ ዓመት በፊት (በ2007 ዓ.ም.) ተከስቶ በነበረው የመንገድ ትራፊክ አደጋ ሳቢያ ቁጥራቸው 3ሺህ 847 ያክል ሰዎች ለሞት ሲዳረጉ ከ11ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ለቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል፣ እንዲሁም ከ668 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል።

በተለይ በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ 15ሺ ሰዎች በትራፊክ አደጋ መሞታቸው የጉዳዩን አስከፊነት በግልፅ ያሳያል። በመንገድ ትራፊክ አደጋ የተነሳ ከሟቾቹ እና ለከፋ የአካል ጉዳት ከሚዳረጉት ውስጥ 80 ከመቶ የሚሆኑት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው እግረኞች እና ተሳፋሪዎች መሆናቸው ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ እና የጉዳቱን መጠንም በእጅጉ አሳዛኝ ያደርገዋል።

በጤና ተቋማት፣ በማህበራዊ ኑሮ፣ በግለሰብ ሆነ በአገር ምጣኔ ሃብታዊ እና በቤተሰብ ደህንነት ላይ እጅግ የከፋ እና አሳሳቢ ሊባል የሚችልን ጫና እያስከተለ ያለውን የትራፊክ ደህንነት ያለመጠበቅ መሰረታዊ ችግርን መቅረፍ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው አይሆንም። በመሆኑም በሰው ሰራሽ ስህተት እየተከሰተ ያለውን መተኪያ የሌለውን የሰው ሕይወት ለመታደግ የሁሉንም ተሳትፎ ይጠይቃል። በዚሁ መሰረትም በአንደኛው “የኢትዮ የትራፊክ ደህንነት አገር ዓቀፍ ኮንፈረንስ” ከፌዴራል እስከ ክልል ከፍተኛ ኃላፊዎች እና የመስኩ ባለድርሻ አካላት፣ በርካታ አገር ውስጥ ሚዲያዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራማሪዎች፣ የታላላቅ የግል ተቋማት አመራሮች እና ሌሎችም እንግዶች ተሳታፊ ይሆናሉ። በተለይም በኮንፈረንሱ የመኪና አደጋን ለመቀነስ ብሎም ለማጥፋት ከፍተኛ ተስፋ የተጣለባቸው አገራችን ፈጣሪዎች የምርምር ውጤቶች በስፋት ይቀርባሉ። 

የኮንፈረንሱ ዋና አስተባባሪ አቶ ሲሳይ ኃይሌ የትራፊክ አደጋ እያደረሰ ያለውን ያህል ጉዳት በአገራችን ሆነ በአህጉራችን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተገቢው ትኩረት እንዳልተቸረው ገልፀው በተለይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጭምር የትራፊክ ደህንነት ጉዳይ አንገብጋቢ በመሆኑ ከዘላቂ የልማት ግቦች ውስጥ እንዲካተት ማድረጉን አውስተዋል። አክለውም “በተለይ ቅድሚያ ለደህንነት በመስጠት በአገራችን እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋ በመተባበር የተዘጋጀው በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የትራፊክ ደህንነት ኮንፈረንስ ዋነኛ ባለድርሻ አካላትን በስፋት በማሳተፍ በመንገድ ሁለንተናዊ ደህንነት፣ በትራፊክ አደጋ ዙሪያ እተከሰቱ ያሉ ጉዳቶችን በጥልቀት በማሳየት፣ የትራፊክ ደህንነትን የተመለከተ የዳሰሳ ቅኝት (ጥናት) በማድረግ እንዲሁም ለንግድ፣ ለግል አሽከርካሪዎች ለሕዝብ ሆነ የግል የትራንስፖርት ተቋማት ጠቃሚ የሆነን የመረጃ ግብዓት በቀላሉ እና በነፃ በማቀበሉ ረገድ የውይይት መድረኩ የላቀን ሚና ሊጫወት የሚችል ይሆናል።” ሲሉ የውይይት መድረኩን መሰረታዊ ፋይዳ ገልፀዋል።

በአገራችን መንገድ ትራፊክ አደጋ ምክንያት በየእለቱ ከ10 ያላነሱ ንፁሀን ዜጎች ህይወት ይቀጠፋል፣ የበርካቶች አካል ይጎድላል፣ በርካታ ሚሊዮን ብሮች የሚገመት ሀብት ይወድማል። ከሕይወት ማጥፋቱ እና አካል ማጉደሉ ባሻገርም የትራፊክ አደጋው በኢኮኖሚ ዙሪያ እያደረሰ ያለው አደጋ በጣም አስከፊ ነው። በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ 17 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ ከአንድ ኣመት በፊት በነበረው በጀት ዓመት ለጉዳት ካሳ ከ2.4 ቢሊዮን ብር በላይ መክፈላቸው ይፋ ሆኗል። የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ የ2007 ዓ.ም. የመጀመርያ ደረጃ የኦዲት ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ በበጀት ዓመቱ ከተከፈለው የጉዳት ካሳ ውስጥ ከ65 በመቶ በላይ የተከፈለው ለሞተር ወይም ከተሽከርካሪዎች አደጋ ጋር ለተያያዘ ጉዳት ነው። ይህንን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን አደጋ ለመቀነስ ደግሞ የሁሉንም ተሳትፎ ይጠይቃል። ይሁን እንጂ የአሽከርካሪዎች ስህተት፣ የተሽከርካሪዎች ቴክኒክ ብቃት ችግር፣ የእግረኞች ተገቢውን ጥንቃቄ አለማድረግ፣ የመንገዶች ምቹ አለመሆን እና ሌሎች ምክንያቶች ተደምረው ለሀገራችን የትራፊክ አደጋ መባባስ በዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሱ ናቸው። ስለሆነም ውድና መተኪያ የሌለውን የሰውን ህይወት እና በርካታ ሀብት የፈሰሰባቸውን ንብረቶች ከመንገድ ትራፊክ አደጋ ለመታደግ ጊዜው ሚሻውን የመፍትሔ ሐሳብ በአፋጣኝ መውሰዱ ተገቢ ይሆናል። በዚሁ መሰረት በአገር አቀፉ የውይይት መድረኩ ለፖሊሲ አውጪዎች ሆነ ለትራፊክ ደህንነት ባለሙያዎች እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦች የሚቀርቡባቸው ይሆናል። በዚሁ አጋጣሚ ከትራፊክ ደህንነት ጋ በተያያዘ ማናቸውም ጥናትን ያደረጉ ተቋማት ሆነ ግለሰቦች በዚህ ኮንፈረንስ ላይ ተሳታፊ ይሆኑ ዘንድ በአዘጋጆቹ ጥሪ ቀርቧል።

በኮንፍረንሱ ላይ በአገራችን ከትራፊክ ደህንነትን ጋ የተያያዙ ዓብይ ጉዳዮች በስፋት ጥናታዊ ወረቀቶች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው እንደመሆኑ በዋንኛነት ዘመናዊ የትራፊክ ደህንነት ማስጠበቂያ መንገዶች፣ ለመኪና አደጋ ሚያጋልጡ ልማዶች እና የመፍትሔ ሐሳቦች፣ መኪና እያሽከረከሩ እንደ ጫት ያሉ አነቃቂ ነገሮችን መውሰድ ያላቸው አሉታዊ ጫና፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ለመጣው የትራፊክ አደጋ መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ የቴክኖሎጂ እና የሌሎች አገራት ተሞክሮ በስፋት ይቀርባል።

በዚሁ አጋጣሚም ለዚህ ሁለገብ ፋይዳ ላለው ኮንፈረንስ መሳካት የሚዲያ ተቋማት አጋርነት ወሳኝ በመሆኑ ለሚሰጡን የዜና ሽፋን ይና ቢዝነስ ፕሮሞሽን ምስጋናውን ከወዲሁ በማቅረብ የሚዲያ ተቋማችሁ ታህሳስ 26 ቀን በኤሊያና ሆቴል በመገኘትም ኮንፈረንሱ ላይ በመገኘት አስፈላጊውን የሚዲያ ሽፋን ለሕብረተሰቡ ያደርስ ዘንድ በክብር ጋብዟል። አዘጋጆቹ ሰንደቅ ጋዜጣ ለፕሮግራሙ የሚዲያ አጋር በመሆኑም ምስጋናቸውን ገልፀዋል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
435 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us