የጉዞ ማስታወሻ፡ ከአፍዴራ እስከ ኤርታኤሌ

Wednesday, 15 February 2017 13:33

ሄኖክ ስዩም

አፋር በሰሜናዊ ምስራቅ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኝ ክልል ነው። ክልሉ 96 ሺ 256 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት አለው። በአምስት ዞኖች የተከፋፈለ ሲሆን በኢትዮጵያ አስደናቂ የሚባሉ የቱሪስት መስህቦች መገኛም ነው። በሀገራችን ከሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች ውስጥ ሁለቱ በአፋር ክልል የሚገኙ ናቸው። አዋሽ ብሔራዊ ፓርክን ከኦሮሚያ ጋር ሲጋራ ያንጉዲራሳ ብሔራዊ ፓርክ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በአፋር ክልል ይገኛል። የክልሉ ዋና ከተማ ሰመራ ከአዲስ አበባ 600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።

በየዓመቱ የቤተሰባዊ ትውውቅ ጉዞ ለጋዜጠኞች በማዘጋጀት የሚታወቀው የአፋር ባህልና ቱሪዝም ክልል ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ከአፍዴራ እስከ ዳሉል ጉብኝት እንዲያደርጉ ባዘጋጀው መርሐ ግብር ታድሜአለሁ። መነሻችን ሰመራ ከተማ ናት። ቀኑ ጥር 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ጠዋት ነው። ጸሐይ ሳትወጣ ከሰመራ ተነስተን ወደ አፍዴራ ጉዞ ጀመርን።

ይህ ጉብኝት በዋናነት ብዙ ያልተነገረላቸው እና ከኢትዮጵያውያን ጎብኚዎች ርቀው ወደ ኖሩ ተፈጥሯዊ መስህቦች የተደረገ ጉዞ ነው። ኪልባቲ ረሱ ወይም ዞን ሁለት ወደሚባለው የአፋር ክልል ገብተናል።

ከሰመራ ሰሜናዊ አቅጣጫውን ይዘን በምቹው አስፋልት ጎዳና በመጓዝ 226 ኪሎ ሜትር ላይ የአፍዴራ ሐይቅን ደቡባዊ ክፍል አገኘንው። አፍዴራ በአፋር ከሚገኙ በርካታ ሐይቆች አንዱ ነው። አፋር ውስጥ ከሚገኙት አምስት ምርጥ የተፈጥሮ ሐይቆች ደግሞ በስፋቱም ትልቁ አፍዴራ ነው።

ኢትዮጵያ ለዘመናት የአሰብን ጨው ስትጠቀም ኖራ ከአሰብ ጋር ስትቆራረጥ የደረሰው የጨው ሐይቅ አፍዴራ ነበር። ገና በጠዋት ደርሰን ሙቀቱ ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል። አፍዴራ እጅግ ከሚሞቁ የሀገራችን አካባቢዎች አንዱ ነው። ምናልባትም ከዳሎል ቀጥሎ፤

11300 ሄክታር ስፋት ያለው የአፍዴራ ሐይቅ በጨው ምርቱ ይታወቃል። የአፍዴራ ከተማ ራሷ ጨው ለማምረት የተሰበሰቡ የቀን ሰራተኞች የፈጠሯትና ያደመቋት ከተማ ናት። የመገናኛ ብዙሃኑ ቡድን አፍዴራ እንደ ደረሰ እንደ እኛው አፋርን ለመጎብኘት ጉዞ የጀመሩት የክልሉ ባለስልጣናት በርዕሰ መስተዳድሩ እየተመሩ አፍዴራ ደረሱ።

በአፋር ከክልሉ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 82 140 ሄክታሩ በውሃ የተሸፈነ ነው። ይህ በመቶኛ ሲሰላ 17.14 በመቶው የአፋር ምድር አፍዴራን ጨምሮ እንደ አቢና ገመሪ ባሉ ሐይቆችና እንደ አዋሽና ደናክል ባሉ ወንዞች የተሸፈነ ነው።

የጉዞአችን መጀመሪያ በሆነው የአፍዴራ ሐይቅ፣ በአስደናቂዎቹ የሐይቁ ዳር ዳርቻ የፍል ውሐ ምንጮች ሙቀቱን የሚያስረሳ ቆይታ አደረግን። አብዲ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም የቱሪዝም ፕሮሞሽን ባለሙያ ነው። አፍዴራን በሚመለከት ለጋዜጠኞች የማስተዋወቅ ገለጻ አደረገ። የአብዲ ቁጭት ይህንን መሳይ ፍል ውሐ መድሃኒት ነው ተብሎ በውጪ ጎብኚዎች ሲጎበኝ በየገበታችን የሚቀርበው ጨው መገኛ ጭምር ሆኖ በሀገር ውስጥ ጎብኚዎች አለመታወቁ እንደሚከነክነው እግረ መንገዱን የጎብኙ ግብዣውን ሲያቀርብ ገለጸልን።

አፍዴራ ምሳችንን በልተን ወደ ኤርታኤሌ ጉዞአችንን ቀጠልን።

ከአፍዴራ ዓበአላ በርሐሌ የሚወስደውን ዋና መንገድ ጥለን ወደ ቀኝ ታጥፈን የአሸዋ ላይ መንገዱን ተያያዝነው። ይህ መንገድ ሙያ ለሌለው ሹፌር ፈተና ነው። መኪናችን የመስክ በመሆኑ ልነቅ የሚለውን አሸዋ ጥሶ ለማለፍ ችግር አልገጠመንም። ከሩቅ ወደሚታየው የእሳት ባህር ተራራ ስንጠጋ ጸሐይ ወደ ደመናው እየገባች ነበር።

ከአፍዴራ 170 ኪሎ ሜትር ያክል ተጉዘን መጥተናል። ይህቺ መንደር አስኮሚ ባህሪ ትባላለች። ወደ ኤርታኤሌ የሚጓዘ ጎብኚዎች አየር ስበው ቀሪውን የእግር ጉዞ የሚያስቡባት የእረፍት ቦታ ናት። ከመላው ዓለም የእሳቱን ባህር ብለው የሚመጡ ጎብኚዎችን ስትቀበል የኖረች፤ አፋሮች የእንግዳ ተቀባይነት ባህል ሙዚየም ናት። ሲመሽ ከቀይ ባህር የሚመጣው ንፋስ አየሯን ይፈውሰዋል።

ከአስኮሚ ባህሪ ኤርታኤሌ ለመጓዝ ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን ደስ የሚልና እሳተ ገሞራ የፈጠረው የዐለት ጌጣጌጥ እየተመለከቱ ሽቅብ ይወጣሉ። በርከት ያልን ተጓዦች ስለሆንን የምሽቱን ጉዞ ያለ ስጋት ነበር የጀመርነው። አፋር ልዩ ሓይሎች ውለታ ደግሞ ምትክ የለውም። በሾሉ ድንጋዮች ላይ ስንራመድ የአፋር ልዩ ሃይሎች ክንድ ላይ ሆነን ነበር።

ደረስን። የሚጤሰው ተራራ ስር፤ ይህ የሲኦል ደጃፍ የሚባለው የዓለማችን ልዩ ስፍራ ነው። ደመናው በእሳቱ ቀለም ሌላ ውብ መልክ ይዟል። ታይቶ የማይጠገብ መልክ። ይሄ በተለምዶ ኤርታኤሌ የሚባለው ስፍራ አይደለም። በቅርቡ የፈነዳው እሳተ ገሞራ ነው። ከቀድሞው ኤርታኤሌ የእሳት ባህር አጠገብ የሚገኝ አዲስ ክስተት። ዓለም ወደ እዚህ ስፍራ እየሮጠ ነው። የውጪው ጎብኚ ቁጥር ጨምሯል። በምሽቱ የባትሪያቸው ወጋገን ከርቀት የሚታየው ጎብኚዎች ማንም ሰው ኤርታኤሌ መድረስ አለበት የተባለ አስመስለውታል።

ወደ ኤርታኤሌ የሚመጣ ጎብኚ የእግር ጉዞውን ምሽት ማድረግ ይኖርበታል። የእጅ ባትሪ የግድ ነው። ምናልባት እሳት እንደ ውሃ በሚንቦጫረቅበት ዳርቻ ሙቀቱ አይጣል ነው ብሎ ራቁቱን የሚመጣ ካለ ብርዱ ሲጠብሰው ያድራል። የሚደረብ ልብስ የግድ ነው።

ኤርታኤሌ ዳር መሆን የትም ከመሆን ጋር የሚተካከል አይመስለኝም። በምናባችን የምናስበውን የተለየ ቀለም እና ውበት ፊት ለፊት የምንጋፈጥበት ስፍራ ነው። ከቆምንበት ቢታ ራቅ ብሎ ገና ፈንድቶ ያልበቃለት አዲስ ሌላ የእሳት ተራራ እያየን ነው። ከኤርታኤሌ ስንመለስ ሁላችንም ላይ የሞላው ደስታ ከመንገዱ ድካም ጋር ትግል ውስጥ ገብቶ ነበር።

ከአምስት ወራት በፊት በድንገት የፊነዳው የእሳተ ገሞራ ከቀድሞ ኤርታሌ በግምት አራት ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ የሚገኝ ቦታ ላይ ያረፈ ነው። አዲሱ እሳተ ገሞራ እንደቀድሞው ከጎደጎደ ሥፍራ የሚገኝ አይደለም፤ ይልቁንም ከመሬት ወለል ላይ የተኛ የእሳት ባህር ነው።

በማግስቱ ቁርሳችንን አስኮሚ ባህሪ በልተን ወደ በርሀሌ ጉዞአችንን ቀጠልን። በርሃሌ አድረን በማግስቱ በዓለም ዝቅተኛ ወደሚባለው ምድር ጉዞአችንን ቀጠልን። ቁርሳችንን ከዳሎል ጋር አብራ ዓለም ካወቃት አህመድ ኢላ /አመዴላ/ ጋር በላን።

በጠዋት ዳሉል ስንደርስ በርካታ የውጪ ጎብኚዎችን የጫኑ የአስጎብኚ መኪኖች በጨው ሜዳ ላይ እየጋለቡበት ነበር። ሰዓቱ ጠዋት ቢሆንም ሙቀቱ እኩለ ቀን አስመስሎታል። ይህ የምድር ዝቅተኛው ስፍራ ነው። በአፋር እና በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አህጉራችንን ጭምር የዝቅተኛው እና ሞቃታማው ስፍራ መገኛ ያስባለ ተፈጥሯዊ መስህብ ነው። ዓለም ለዘመናት የምድራችን ሌላኛ ፕላኔት ሲል ሲያወድሰው የኖረ መስህብ ነው።

እንወራረድ ከተባለ ዳሎልን በማወቅ ከእኛ ከኢትዮጵያውያን ዓለም ይበልጠናል። ዳሎልን በመጎብኘትም እንዲሁ ባህር ሰንጥቀው አድማስ አልፈው የመጡ እንግዶቹ ቁጥር የትየለሌ ነው። ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የእኛ ሆኖ ባዕድ፤

አሁን ስለማየው ነገር በቃላት መጻፍ አይሞከርም። ይህንን ለማድረግም አልጀምርም። ዳሎል አይጻፍም። ዳሎል በቃላት አይገለጽም። አፋሮች ዳሎልን መግለጽ ይችሉ ከሆነ ብዬ የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊውን አቶ  መሀመድ ያዮ አናገርኳቸው። በአጭር ቃል "ግሩም ነው፤ ይደንቃል። አይታመንም" ብለው ምላሽ ሰጡኝ።

በጉዞአችን ሁሉ የአፋር ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አብረው አሉ። ለቱሪዝም እና ባህል የሚሰጡትን ትኩረት እንዲህ ሙቀትን መንገድም ሳይበግራቸው አምና የሄዱበትን ዘንድሮም ደግመው በመታደም የማይጠገበውን መስህብ ሲጎበኙ የተመለከተ ይገባዋል። ለጋዜጠኞችም ያሉት ይህንኑ ነበር። "እናንተ የመጣችሁት ሀገራችሁ ነው። ይሄ ሀገራችሁ ነው። ሀገራችሁን መጎብኘት እና ስለ ሀገራችሁ ማስተዋወቅ ኃላፊነታችሁ ነው" አሉ።

በእርግጥ ሀገራችን ነው። ግን የቅርብ ሩቅ ነን። ዳሎልን ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ የናሽናል ጂኦግራፊውን ዘጋቢ ያክል አያውቀውም። ኢትዮጵያዊው ምሁር ለዳሎል ሩቅ ነው። ከዓለም መገናኛ ብዙሃን ዘግይቶ ዳሎል እንዲህ ሆነ፤ ኤርታኤሌ ፈነዳ የሚል ሚዲያ ጋዜጠኞች ነን። እናም ሀገራችን ቢሆንም ስለ ሀገራችን ሩቅ እንደሆንን ያየንበት ድንቅ ጉዞ ነበር።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
643 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us