“የግል ሚዲያዎችን መንግስት እንደሚፈልጋቸው ጥያቄ ውስጥ መግባት የለበትም”

Wednesday, 30 August 2017 13:07

“የግል ሚዲያዎችን መንግስት እንደሚፈልጋቸው ጥያቄ ውስጥ መግባት የለበትም”

አቶ አባዱላ ገመዳ

የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባኤ

ሰኞ ነሐሴ 22 ቀን 2009 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ፤ የግል ሚዲያዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉበት ሁኔታ፣ እያጋጠሟቸው ያሉት ተግዳሮቶች እና ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ የተሰናዳ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በዚህ የምክክር መድረክ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ ከመድረኩ “መንግስትዎ የግል ሚዲያዎችን የልማት እና የዴሞክራሲ አጋር አድርጐ ይወስዳቸዋል ወይ?” ተብለው ለቀረበባቸው ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ በዚህ መልኩ አቅርበነዋል።

 

 

አፈጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ ምላሻቸውን ምሳሌ በመስጠት ነበር የጀመሩት። ይኸውም “ሚዲያ በኒውክለር የሚመሰል ነው። በአንዳንድ ሀገሮች የኤሌትሪክ ኃይል ይሰጣል፤ ሀገር ይገነባል። በሌሎች ሀገሮች ደግሞ የጥፋት መሣሪያ ነው፤ ማንም ሳይለይ ያጠፋል። በጎረቤታችን ሩዋንዳ አንድ የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ሕዝብ አፋጅቷል፤ ለ700ሺ ሰዎች እልቂት ምክንያት ሆኗል። ስለዚህም ሚዲያ ሁለቱንም ተግባራት ሊያከናውን የሚችል ነው።”

ከዚህ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አያይዘውም፤ “በእኛ ሀገር የመንግስት እና የግል ሚዲያዎች የተጫወቷቸው ምርጥ ሥራዎች አሉ ብሎ መውሰድ ይቻላል። በዴሞክራሲያው ሥርዓት ውስጥ ብሔራዊ መግባባቶች እንዲፈጠሩ ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ሕብረሰተቡ ችግሮቹን እንዲረዳ በማድረግ በእያንዳንዱ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲፈጥር የሰሯቸው በጣም ጥሩ ስራዎች አሉ። በእኔ ግምት አንዳንዶቻችን እንደምንገልጸው ሳይሆን፤ ከሚዲያ ያገኘነው ልምድ ውድቀት አይደለም። በጣም ብዙ የተገኙ ልምዶች አሉ። ብዙ ያደጉና ያበቡ ነገሮች አሉ። ብዙዎች በኢንዱስትሪው ውስጥ አልፈዋል፤ ጥቂቶች ግን ቀርተዋል። ሚዲያው ሲፈጠር ብዙ ፍላጎት ያለው ሰው ወደ ሥራው ገብቷል። ነገር ግን ፍላጎት ብቻውን፣ በቂ አይደለም። ሙያው ብቃትን ይጠይቃል፤ ብቃትም ብቻ በራሱ በቂ አይደለም። የሥርዓቱን ባሕሪ መረዳትም ያስፈልጋል፤ የሥርዓቱን ባሕሪ ካልተረዳህ መዋኘት አትችልም። ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ተጣጥመው ተግባራዊ በሚሆኑበት ወቅት የተመዘገበው ኃይል ሁሉ አልቀጠለም። አንዳዶች ምርጥ ሥራዎች ሲሰሩ፤ የተወሰኑት ችግር ውስጥ ገብተዋል፤ በመንግስትም በግሉም ዘርፍ የሚታዩ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ ገና ከጅምሩ ፀረ-ሕገመንግስት አፍራሽ ተግባሮች ውስጥ ገብተው ታይተዋል።” ብለዋል።

“መንግስት የግል ሚዲያዎች ይፈልጋል ወይ?” ለሚለው ጥያቄ መልሱ፤ “አዎ ይፈልጋል የሚል ነው። የሚፈልገው ደግሞ ዴሞክራሲን ስለሚፈልግ ነው፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ እንዲገነባ ስለሚፈልግ ነው። ምንአልባት በጣም ለየት ባለመንገድ ልማታችን እና ዴሞክራሲያችን እኩል ተራምዶ የሕዝባችን ሁለንተናዊ መብት የሚጠበቅበት ሥርዓት በሀገራችን እንዲኖር ነው። ምክንያቱም የልማታችን የሰላማችን እና የአንድነታችን ቀጣይነት የሚረጋገጠው በእሱ ስለሆነ ነው፤ ሌላ ምንም አማራጭ የለንም።” ሲሉ አስቀምጠዋል።

አፈጉባኤው ወደኋላ መለስ ብለው፤ “ቀደም ብሎ “ዴሞክራሲ የምርጫ ሳይሆን፣ የህልውና ጉዳይ ነው” ያለ መንግስት ነው። ዴሞክራሲ አንዱ አስተዳደር ሌላውን አስተዳደር የመምርጥ ጥያቄ ሳይሆን፤ ለእኛ ዴሞክራሲ የሕልውና ጉዳይ ነው። ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አሉ፤ ብዙ ሐይማኖቶች አሉ፤ የተለያየ አስተሳሰብ ያለበት ሀገር ነው፤ በዚህ ላይ ድህነት ተጨምሮ አለ። ስለዚህም በዚህ አይነት ሕብረተሰብ ውስጥ ሀገር በኢኮኖሚ ገንብቶ አስቀጥሎ መሄድ የሚቻለው፣ በዴሞክራሲ ብቻ ነው። ሌሎች መንገዶች ተሞክረው አልተቻለም፤ ወድቀዋል። ሀገራችን ሞክራቸዋለች አላዋጡም፤ ፈርሰዋል። አዋጪው መንገድ ዴሞክራሲ ብቻ ነው። ዴሞክራሲ የሕልውና ጥያቄ ነው ካልን፤ አንዱ የዴሞክራሲ ምሶሶው፤ ሚዲያ ነው።”

“ሚዲያ ማለት ጥቂት የመንግስት፣ ሚድያዎች ማለት አይደለም። ሁሉንም ሃሳቦች ማስተናገድ የሚችሉ ሚዲያዎች በሀገር ውስጥ እንዲፈጠሩ ማድረግ ነው። ስለዚህም የግል ሚዲያዎችን መንግስት ይፈልጋል የሚለው፤ ጥያቄ ውስጥ መግባት የለበትም። አብረን በጋራ መስራት ይፈለጋል ወይ ለሚለው፣ በፍፁም ጥያቄ ውስጥ መግባት የለበትም። ሚዲያ የምርጫ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ በሕገ-መንግስታችን ጥበቃ አግኝቷል። ይህን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ተቋሞች ተቋቁመዋል፤ አዋጆችም ወጥተዋል። ስለዚሀም መንግስት ከዚህ በላይ አይደለም፤ እነዚሁኑ ነው የሚያስከብረው።” ሲሉ የመንግስት ሚና ሕግ ማስከበር መሆኑን ገልፀዋል።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አሉ አቶ አባዱላ ገመዳ፤ “ምንም ይሁን ማንም ሊጠብቃቸው የሚገቡ ጉዳዬች አሉ። ይኸውም፤ የሀገራችን ሕልውና ነው። ምክንያቱም “የሕልውና ጉዳይ ነው” የተባለበት፤ ሀገራችን መቀጠል፣ ከድህንት መውጣት እና አንድነታችንም ማበብ ስላለበት ነው። ይህንን ሕልውናችን የሚነካ ጉዳይ በየትኛውም መንገድ መፈቀድ የለበትም። ስለዚህም ሕልውናችን ከሚነካ ነገር መውጣት ያስፈልጋል ማለት ነው። ከሕልውናችን ውጪ በጣም የሚያሰራበት ብዙ ቦታ አለ። መጫወቻው ቦታ በጣም ሰፊ ነው። ሕብረተሰቡን የምናስተምርበት፤ ያሉንን ችግሮች ነቅሰን የምናወጣበት፣ መፍትሄዎችን የምናሳይበት፣ በጣም ሰፊ ሜዳ አለ። ይህንን ሰፊ ሜዳ በመጠቀም ብሔራዊ መግባባታችን በፈጣን ሁኔታ ማረጋገጥ አለብን። ትውልድን ለመገንባት ያስፈልጋል። እድገታችን ለማፋጠን መስራት ያስፈልጋል።”

አያይዘውም፤ “ግራና ቀኝ መርገጥ ውጤቱ፤ ጥፋት ነው። ለሁላችንም አይጠቅም። በርግጥ ብዙዎቹ የተባሉትን ይላሉ። አምነስቲ እና ሌሎቹም ጋዜጠኞች ይታሰራሉ ይላሉ። አንድ ነገር መታወቅ ያለበት፣ ረጋ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ምክንያቱም የእኛን የሚያወግዟቸው ነገሮች በሙሉ፤ በእነሱ ሀገሮች ውስጥ ይተገበራሉ። ለምሳሌ፤ የእኛን ፀረ-ሽብር ሕግ ያወግዛሉ፤ በሀገራቸው ውስጥ ግን በአስደናቂ ሁኔታ ይተገብሩታል። አንድ ጠበንጃ ተገኘ ተብሎ፣ ቤቱን በታንክ ያፈርሳሉ። እኛ አንድ ነገር ስናደርግ ግን ያወግዛሉ። የእኛ ደም ጥቁር አይደለም። የእኛም የእነሱም ደም፤ ቀይ ነው። የእኛ ሀገር፣ ሀገር ነው፣ ደሃ ብንሆንም። የእነሱ ሀገርም፣ ሀገር ነው። ስለዚህም በሀገራችን መኖር አለብን። እንዲሁም የበጎ አድርጐት ሕጎችን በአሜሪካ ይተገበራል። ለምሳሌ በአሜሪካ አንድ በጎ አድራጎት ድርጅት ከተቋቋመበት ዓላማ ወጣ ካለ፤ ግብር ይጥሉበታል። ያስተካክሉታል፤ ከዚያም ወደ መስር ይመልሱታል። በተመሳሳይ መልኩ እኛ ሀገር ሲደረግ ግን መብት ተጣሰ ይላሉ።  ጋዜጠኛም በሽብር ተግባር ውስጥ ከገባ ይጠየቃል። ወይም ካጋጨና ከቀሰቀሰ ይጠየቃል፡፤ እዛም እንደዚሁ ይጠየቃል፤ እዚህም መጠየቅ አለበት። ስለዚህ ብሔራዊ ሕልውናችን የሚነኩ ጉዳዮች ሲታወጁብን እነሱን መመዘኛዎቻችን ማድርግ የለብንም። ይህች ሀገር በሰላም ከዓለም ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበች እንድትቀጥል ያደረጋት፣ ውስጣዊ አንድነቷን እና እነዚህ ለችግር የሚያጋልጧትን ሁኔታዎች መቋቋም በመቻሏ ነው። ስለዚህም ሁሉም እዚህ ላይ መተባበር አለበት። ይህ ማለት ግን የዜጎችን መብት መንካት ማለት አይደለም። ዜጎች የመጠየቅ፣ የመፃፍ፣ የመቃወም፣ የመደገፍ መብታቸው የተረጋገጠ ነው፤ መረጋገጥም አለበት። እነዚህ ሁሉ መብቶች ግን ሕልውናችን በማይነኩ ሕልውናችን በሚያረጋግጡ ድንበሮች ውስጥ መሆን አለባቸው። ስለዚህም የግል ጋዜጦችም እዚህ ላይ አንድነት መፍጠር አለብን። እዚህ ላይ አድነት ከፈጠርን፤ ሁሉም አንድ ጃኬት ይልበስ የሚባል ነገር አይኖርም። ነገር ግን መነሻችን መድረሻን፤ ሀገር መሆን አለበት።  ሕገ መንግስቱ መሆን አለበት። እዚያ ላይ ሆነን ጨዋታችን ልቀጥል ይገባል። ከዚህ መለስ ያለው የአመለካካት ልዩነት ተቀባይነት አለው። እንኳን መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ ቀርቶ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የአመለካከት ልዩነቶች አሉ።” ሲሉ የአመለካከት ልዩነት በጋሬጣነት መነሳት እንዳለበት አስምረውበታል።  

“ሥርዓት ነው የምነገነባው፤ ስለዚሀም ሁላችንም ምን እናድርግ? ከሚለው መነሳት አለብን። መጫወቻ ሜዳችን አንድ ስለሆነ፣ አንዱ ሌላውን እየወቀሰ መሄድ አንችልም። ከዚህ መውጣት አለብን። በመንግስት በኩልም የግሉ ሚዲያ የበለጠ እንዲያብብ ምን እናድርግ? ተብሎ መታሰብ አለበት። መንግስት ምን አድርጓል? ለሚለው ብዙ ነገር አድርጓል። በአመት ሶስት ሺ ተማሪዎች ከሚመረቁባት ሀገር በዓመት ወደ 100ሺ የሚመረቁባትን ሀገር መፍጠር ችሏል። ስለዚህም አስር ጋዜጠኞች ሳይሆኑ 5ሺ ጋዜጠኞች እንዲወጡ አድርጓል። አስር ፀሐፊዎች ሳይሆኑ፤ 100ሺ ፀሐፊዎች እንዲወጡ አድርጓል። ይህ ጋዜጠኝነቱ ላይ ይሰራል፤ ሌላውም ሙያ ላይ ይሰራል። ለእድገት የተከፈቱ በሮዎች ብዙ ናቸው።” ብለዋል።

አፈጉባኤው ቀጠል አድርገውም፤ “ለእያንዳንዱ ገንዘብ አይደጎምም፤ ኪሳራ ነው፤ በር ነው መከፈት ያለበት። እዚህ ውስጥ ሁሉም ሲገባ መክፈል ያለበትን ዋጋ ይከፍላል። የተደላደለና ለስላሳ መንገድ ብቻ አይደለም ያለው። ለምሳሌ ወደ ግብርና የገባው በጣም ተላልጦ ነው ሃብት የሚያፈራው። በሌላው ዘርፍ ተመሳሳይ ነው። በተለይ የጋዜጠኝነት ሥራ ከባድ ነው የሚል ግምት አለኝ። በጣም ጥሩ እውቀት እና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ተግባር ነው። አንዳንዶቹ የላቀ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ሥራ የሚሰሩ አሉ። እንደ ቢቢሲ ሲኤንኤን ጋዜጠኞች ሶሪያ ኢራቅ ውስጥ ጦርነት ሲካሄድ የጥይት መከላከያ አድርገው ጋዜጠኝነት እንደሚዘገቡት በሀገራችን በዚህ ደረጃ ሥራ የሚሰሩ ሚዲያዎች አሉ። ሁልጊዜ ስራቸውን አደንቃለሁ።” ሲሉ እውቅና ሰጥተዋል።

አፈጉባኤው በአስረጅነት ካነሷቸው አንዱ፤ “ለምሳሌ ሕገወጥ ስደትን አብሮ ተጋፍጠው ሞት ከፊታቸው እያሸተቱ በኮንቴነር ተጭነው ከመሐል ሀገር ድንበር ድረስ ተጉዘው ሚስጥሩን ብትንት አድርገው ያወጡ ሚዲያና ጋዜጠኞች በሀገራች አሉ። ግርግር ሳይፈጥሩ በገጠር እንደማንኛውም ስደተኛ ሆነው የገጠሩ ሕዝብ እንዴት እንደሚቸገር እውነታውን ያወጡ ጋዜጠኞች እንዳሉ አውቃለሁ። በጣም ቁርጠኝነትን በሚጠይቅ ሥራ ሞትም ቢሆን እየተጋፈጡ የሚሰሩ ሚዲያዎች እና ጋዜጠኞች እንዳሉ አውቃለሁ። የዚያኑ ያህልም ያገኙትን መረጃ በማጋነን የሚሰሩም አሉ። ስለዚህም ማድረግ ያለብን ሥርዓቱን ለመገንባት መከፈል ያለበት ዋጋ እንዳለ ማወቅ ነው ለዚህ ደግሞ ዋጋ መክፍል አለብን።” ሲሉ ሁሉም አካል መጪውን ለውጥ በፅናት እንዲመለከት አበረታተዋል።¾    

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
283 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 97 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us