የ2009 ክራሞት

Wednesday, 06 September 2017 13:49

2009 የኢትዮጵያዊያን በጀት ዓመት የአለመረጋጋት እና የፈተና ዓመት ሆኖ ዘልቋል። በዋነኝነት በ2008 ዓ.ም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የተከሰተው ሕዝባዊ አመፅ በሰዎች ህይወት እና ቁስ ላይ ጉዳት ማድረሱን ተከትሎ በ2009 የመጀመሪያው ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ ለ10 ተከታታይ ወራት በሥራ ላይ እንዲውል ግድ ሆኗል። ይህንና መሰል የ2009 ተጨማሪ ሁነቶች በጥቂቱ አለፍ አለፍ ብለን እንቃኛቸዋለን።

 

የኢህአዴግ ‘ጥልቅ’ ተሃድሶ እና ሒደቱ

በ2009 ዓ.ም ዋዜማ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ (ከነሐሴ 10 እስከ ነሐሴ 15/2008) ባካሄደው ስብሰባ ያለፉት 15 ዓመታት ጉዞ ገምግሞ የገጠመውን ችግሮች ለመቅረፍ ጥልቅ ተሀድሶ ለማድረግ መወሰኑን አስታወቀ።

ግንባሩ በዚህ መግለጫው የገጠሙት ችግሮች መነሻዎች አንዱ የመንግሥት ሥልጣንን የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻልና ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ የግል ኑሮ መሠረት አድርጎ የመመልከትና በአንዳንዶችም ዘንድሮ የግል ጥቅምን ከማስቀደም ጋር የተያያዘ እንደሆነ አረጋግጧል።

ለዚህ የኢህአዴግ አቋም መድረክ የተባለው የፓርቲዎች ስብስብ የተቃውሞ ምላሽ የሰጠው ወዲያውኑ ነበር። መድረክ ነሐሴ 23 ቀን 2008 ዓ.ም ያወጣው መግለጫ “የኢህአዴግ የሥራ አስፈፃሚ እና ማዕከላዊ ም/ቤት የሰጡት መግለጫዎች ሕዝቡ ለሚያነሳቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ የሰጡ አይደሉም” የሚል ይዘት የነበረው ነበር።

 

የኦህዴድ - ሥርነቀል እርምጃ

ኦህዴድ በመስከረም ወር 2009 ዓ.ም ለስድስት ተከታታይ ቀናት ባካሄደው የተሀድሶ ግምገማ የድርጅቱን ሊቀመንበር እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ሙክታር ከድር እንዲሁም የድርጅቱን ም/ሊቀመንበርና በምክትል ጠ/ሚ ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትር የነበሩትን ወ/ሮ አስቴር ማሞ ከፓርቲ ኃላፊነት ማንሳቱ በወቅቱ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል። እርምጃው ከጥልቅ ተሀድሶው ጋር የተያያዘ መሆኑ እየታወቀ ኦህዴድ ባለሥልጣናቱን ያነሳበትን ትክክለኛ ምክንያት ለሕዝብ ከመናገር ይልቅ በደፈናው ሰዎቹ የተነሱት “በራሳቸው ጥያቄ መሠረት ነው” ማለቱ በወቅቱ ክፉኛ አስተችቶታል።

መጋቢት 1 ቀን 2009 ዓ.ም ለንባብ የበቃው የኢህአዴግ ልሳን የሆነው አዲስ ራዕይ መጽሔት ከጥልቅ ተሀድሶ ጋር በተያያዘ 90 በመቶ አባላቱ መሳተፋቸውንና 50 ሺ የግንባሩ አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱን አረጋግጧል። የተወሰደው እርምጃም የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መልኩ ከኃላፊነት የማንሳት፣ ዝቅ የማድረግ፣ የማባረር እርምጃ ነው ብሏል።

አሁንም ከጥልቅ ተሀድሶው ጋር ተያይዞ በሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም ከ55 በላይ የመንግሥት የሥራ መሪዎች፣ ባለሃብቶች፣ ደላሎች በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ እየተከናወነ ቢሆንም እርምጃው በሙስናና ብልሹ አሠራር እንዲሁም ከገቢያቸው በላይ ሐብት በማፍራት የሚጠረጠሩ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናትን አልነካም በሚል አካሄዱን የሚተቹ ወገኖች አልጠፉም።

 

 

የኢሬቻ የሐዘን ገጠመኝ

መስከረም 22 ቀን 2008 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ የተከበረው ዓመታዊ የኢሬቻ ክብረበዓል ድንገተኛ ክስተትን አስተናግዷል። በዕለቱ በተፈጠረው ተቃውሞ ምክንያት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተከሰተ ግጭት የተፈጠረው ግርግር ሰዎች በመገፋፋት ለሞትና ለመቁሰል አደጋ እንዲጋለጡ ምክንያት ሆኗል። በዚህም ክስተት ብዙ ሰዎች ከቤታቸው እንደወጡ ለመቅረት ተገድደዋል። ሁኔታው አሳዛኝ ሆኖ ያለፈ ሲሆን በቅርቡ ለሟቾች የመታሰቢያ ሐውልት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መቆሙ ተነግሯል። ይህ ሁኔታ በማህበራዊ ድረገጾች ሌላ ዙር የቃላት ጦርነትን አፋፍሞ ከርሟል።

 

የፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ቃልና ተግባር

በመስከረም ወር 2009 የመጨረሻ ሰኞ ዕለት የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ም/ቤቶች መክፈቻ ፕሮግራም ላይ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ተገኝተው በዚህ ዓመት የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን የጠቆመ ንግግር አደርገዋል። ከዚህ ንግግር መካከል የምርጫ ሕጉ እንደሚሻሻል ቃል መግባታቸው የብዙሃንን ትኩረት የሳበ ዓቢይ ርዕስ ጉዳይ ነበር። ፕሬዚዳንቱ በዚሁ ንግግራቸው የምርጫ ሕጉን በማስፋት በሕግ ማዕቀፍ በተደገፈ አኳኋን የሕዝብ ም/ቤቶች የተለያዩ ድምፆች የሚሰሙባቸውና የሚፎካከሩባቸው መድረኮች እንዲሆኑ የምርጫ ሕጉን ማስተካከል እንዲገባ ጠቅሰዋል። አገሪቱ የምትመራበት የምርጫ ሕግ በብዙ ሀገሮች እንዳለ የሚሠራበት ቢሆንም ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የሁሉም የኅብረተሰብ ድምፅ ሊሰማ የሚችልበት አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የሕግ ማሻሻያ ይደረጋል ሲሉ ለሕዝቡ ቃል ገብተዋል። ይህም ሆኖ ይህ ቃል ሳይተገበር ዓመቱ የመጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ መድረሱ ብቻም ሳይሆን ለምን ሳይተገበር እንደቀረም ግልጽ መረጃ ለህዝብ አለመሰጠቱ ወትሮም የተገባው ቃል ለይስሙላ ነው የሚሉ ወገኖችን ሃሳብ ሚዛን የደፋ አድርጎታል።

 

 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መውጣት

     ሕገ መንግስታዊ ስርአቱን ለማስከበርና የሕዝብና የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል። ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተስተዋለውን የጸጥታ መደፍረስ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር አድርጎ የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ ወደ ነበረበት ለመመለስ በየቦታው ለታየው ሁከት፣ ረብሻና ስርዓት አልበኝነት ዋንኛ መገለጫ በሆኑ አውዳሚ ተግባራት ላይ የተጣለውን ክልከላ እንዲሁም ክልከላዎቹ ሲጣሱ በአዋጁ መሰረት የሚወስዱ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን በመለየት አስቀድሞ ለህዝብ ማሳወቅ እንዲሁም አዋጁ ተፈፃሚ ሆኖ በሚቆይበት ጊዜ ክልከላዎቹን ጥሰው በሚገኙ ሰዎችና ድርጅቶች ላይ ተገቢውን የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ መውሰድ ተገቢ ሆኖ ስለተገኘ የህዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር መስከረም 28/2009 አንቀፅ 13/2/ እና በደንቡ አንቀፅ 4 በተፈቀደው መሰረት መመሪያ ወጥቶ ሲሰራበት ከቆየ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በ10 ወሩ በሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም መጨረሻ በዕረፍት ላይ የነበረው ፓርላማ በአስቸኳይ ተጠርቶ እንዲነሳ ሆኗል።

የካቢኔ ሹም ሹር

ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም የተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ብዙዎቹን ነባር የካቢኔ አባላትን በማሰናበት በአዳዲስ ምሁራን እንዲተኩ አድርገዋል። ከነባር ተሰኗባቾች መካከል ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ዶ/ር ተከስተብርሃን አድማሱ፣ ወ/ሮ አስቴር ማሞ፣ አቶ መኩሪያ ኃይሌ፣ አቶ ያዕቆብ ያላ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ፣ አቶ ቶሎ ሻጊና የመሣሠሉት ተጠቃሾች ነበሩ።

 

የቆሼ አደጋ

ቅዳሜ መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም በኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ስሙ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ ከ75 በላይ ሰዎች ሞት እና ከ300 በላይ መፈናቀል አደጋ መድረሱ፣ ይህን ተከትሎ ከመጋቢት 6 ቀን 2009 ጀምሮ ለሶስት ቀናት ብሔራዊ የሐዘን ቀን መታወጁ የሚታወስ ነው። አደጋውን ተከትሎ ሕዝቡ ባደረገው ርብርብ ከ100 ሚሊየን ብር ያላነሰ መዋጮ መሰብሰብ መቻሉም የሚጠቀስ ነው።

በአዲስአበባ ከተማ ላይ የኦሮሚያ ጥቅም ጉዳይ

በፌዴራል ሕገመንግሥት መሠረት የኦሮሚያ ክልል በአዲስአበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም የሚመለከተው ረቂቅ አዋጅ ከ22 ዓመታት ዝምታ በኋላ የፓርላማን ደጃፍ መርገጥ የቻለው በሰኔ ወር 2009 ዓ.ም ነበር። ረቂቅ አዋጁ በሚኒስትሮች ም/ቤት ጸድቆ ለፓርላማው የቀረበ ሲሆን ስፋት ካለው ይዘቱ መካከል ‘ፊንፊኔ’ የሚለው መጠሪያ ከአዲስአበባ ስያሜ እኩል ዕውቅና እንደሚያገኝ፣ የኦሮምኛ ቋንቋ በተጓዳኝ የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ቋንቋ እንደሚሆን፣ የኦሮሞ ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በአዲስአበባ ከተማ በሚከፈቱ ት/ቤቶች እንደሚማሩ፣ በልማት መስፋፋት ምክንያት ከይዞታቸው ለተፈናቀሉ የኦሮሞ አርሶአደሮች ካሳ እንደሚሰጥ ይደነግጋል።

አዋጁ ከመተግበሩ በፊት በአዲስ አበባ ከአምስት ያላነሱ ደፋን ኦሮሞ ቋንቋ የሚያስተምሩ የትምህርት ተቋማት ተከፍተው ተማሪዎችን በመቀበል በ2010 ዓ.ም ለማስተማር የተዘጋበት ሁኔታ ተስተውሏል።

ረቂቅ አዋጁ በቀጣዩ ዓመት ፓርላማው ያጸድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል።

 

በቅማንት ጉዳይ ሕዝበ ውሳኔ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአማራ እና የቅማንት ሕዝቦች ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው 12 ቀበሌዎች መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ማቀዱን ይፋ ያደረገው በዚሁ በነሐሴ ወር 2009 ዓ.ም ነው።

 የአማራ ክልል ም/ቤትን ቀደም ብሎ መጋቢት 3 ቀን 2007 ዓ.ም የቅማንት ማህበረሰብ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ የቅማንት ማህበረሰብ የራስ አገዝ አስተዳደር 42 ቀበሌዎችን በማቀፍ እንዲመሰረት ማድረጉ የሚዘነጋ አይደለም።

የምርጫ ቦርድ የሚያካሂደው የሕዝበ ውሳኔ የአማራ እና የቅማንት ማህበረሰቦች ተቀላቅለው የሚኖሩባቸውን 12 ቀበሌዎች ብቻ የሚመለከት ነው ተብሏል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
224 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1023 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us