የኢህአዴግ ግምገማ እና ተጨባጩ እውነታ

Wednesday, 13 September 2017 12:19

የኢህአዴግ ምክርቤት ባለፈው ሳምንት ስብሰባውን ካካሄደ በኃላ ያወጣው መግለጫ አነጋጋሪ ጉዳዮች አጭሯል። የግንባሩን መግለጫ እናስቀድም።

………

 

የኢህአዴግ ም/ቤት ጳጉሜ 3 እና 4 ቀን 2009 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የ2009 ዓ.ም የድርጅትና የመንግስት ስራዎች ዕቅድ አፈፃፀምን በጥልቀት በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎች በማስቀመጥ መደበኛ ስብሰባውን አጠናቀቀ።


ምክር ቤቱ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ባለፈው ዓመት በነሐሴ ወር የተጀመረው በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ የሚገኝበት ሁኔታ፤ በተሃድሶው የተገኙ ውጤቶችና በቀጣይ ሊተኮርባቸው የሚገቡ ጉዳዮች በዝርዝር በመገምገም በሁሉም ደረጃዎች በተካሄዱ መድረኮች በተዛቡ አመለካከቶች ላይ ነጻ፣ ግልጽ ትግል መደረጉን ፈትሿል። በተለይም ስልጣንን ለግል ጥቅም ከማዋል ጋር ተያይዞ የሚታይ የስልጣን አተያይ ችግር የወለዳቸው የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካ መገለጫ የሆኑት ትምክህተኝነት፣ ጠባብነት፣ የሐይማኖት አክራሪነት፣ ብልሹ አሰራርና ሙስና እንዲሁም በፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ላይ የሚታዩ የተዛቡ አመለካከቶች ላይ ጠንካራ ትግል መደረጉንም ተመልክቷል።


የኢህአዴግ ምክር ቤት የተሃድሶ ሂደቱ በአባላት ዘንድ ተቀዛቅዞ የነበረውን የእርስበርስ መተጋገል ከማጠናከሩም በላይ የውስጠ ድርጅት ትግልና ዴሞክረሲያዊነት እንዲጠናከር ያደረገ ሲሆን በኢህአዴግ አባላትና ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አላስፈላጊ መጠራጠር በማስወገድ የትግል አንድነት እንዲፈጠር ማስቻሉንም ገምግሟል።


ጥልቅ ተሃድሶው ተቀዛቅዞ የነበረውንና ድርጅቱ ጥንካሬውን ይዞ እንዲዘልቅ የአንበሳውን ድርሻ የሚጫወተውን የውስጠ ድርጅት ትግል እንዲቀጣጠል በዚህም ፀረ ዲሞክራሲያዊነትና አድርባይነት እየቀነሰ እንዲሄድ ማድረግ መቻሉን የተመለከተው የኢህአዴግ ም/ቤት ጥልቅ ተሃድሶውን ተከትሎ ከማዕከል እስከ ታች መሰረታዊ ድርጅትና ህዋስ ድረስ የማጥራትና በሰው ኃይል፣ በአደረጃጀትና በአሰራር መልሶ ለማደራጀት በትግል ላይ የተመሰረቱ ስራዎች መከናውቸውንም አይቷል። በመንግስትም በተመሳሳይ መልኩ መንግስታዊ አሰራሩን ጠብቆ ከላይ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ህዝብን ባሳተፈ አገባብ መልሶ የማደራጀት ስራ መከናወኑን ምክር ቤቱ ገምግሟል።


የኢህአዴግ ም/ቤት ላለፉት ተከታታይ ወራት በየደረጃው ያለውን አመራር ፖለቲካዊና ርዕዮተ ዓለማዊ አቅም ለማጎልበት የተሰጡ ስልጠናዎችና በግንባሩና ብሄራዊ ድርጅቶች በሚዘጋጁ ልሳናት በተዘጋጁ የመታገያ ጽሁፎች በበርካታ ጉዳዮች ላይ የተሟላ ግልፅነት እንዲያዝ ከማድረግ ጀምሮ በአባላት ዘንድ መተጋገል፣ መተራረምና ጓደዊ መተማመንና የህዳሴውን ጉዞ ለመምራት የሚያስችል የአመራር ቁመና እንዲፈጠር እያስቻለ መሆኑንም ተመልክቷል።


የኢህአዴግ ወጣቶችና ሴቶች ሊግ የጥልቅ ተሀድሶ አፈፃፀምን በጥልቀት የተመለከተው የኢህአዴግ ም/ቤት ሊጎቹ ሀገራዊ፣ ክልላዊ እና አካባቢያዊ ነባራዊ ሁኔታውን ያገነዘበ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን የገመገመ ሲሆን ሊጎቹ ከተሃድሶው በኋላ የወጣቶችንና የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት ማድረጋቸውንም አይቷል። ምክር ቤቱ ሊጎቹን ለተልዕኮአቸው ለማብቃት ሁለንተናዊ ድጋፍ መስጠት እንደሚገባም ተመልክቷል።


በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ በተካሄዱ የጥልቅ ተሃድሶ መድረኮች የሰቪል ሰርቫንቱ የአገልጋይነት መነፈስ ማነስና ውጤታማ አገልግሎት አለመስጠት በዚህም ተገልጋዩን ህዝብ ለምሬት የሚዳርጉ ችግሮች መኖራቸው በመለየት ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችሉ ጥረቶችን እየተደረጉ መሆናቸውን የተመለከተው ምክር ቤቱ አሁንም ግን በሚፈለገው ደረጃ የህዝብን እርካታ ያለረጋገጠ በመሆኑ ቀጣይ ትግል የሚጠይቅ መሆኑን አስምሮበታል።


ምክር ቤቱ በጥልቅ ተሃድሶው የተለዩ ችግሮችና አፈታታቸው ላይ ከመላው ህዝብ ጋር በመግባባት በህዝቡ ዘንድ ድርጅታችን አሁንም ችግሮቹን ሊያስተካክል በሚችልበት ቁመናና አቅም ላይ ይገኛል የሚል አስተሳሰብና እምነት እየጠነከረ መምጣቱን የገመገመ ሲሆን የተከናወነው በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴም የነበሩ ጉድለቶችን በዝርዝር ከመፈተሽ ጀምሮ የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ ውጤቶችን መመዝገባቸውንም አይቷል።


በተዛባ የስልጣን አተያይ ምክንያት ትክክለኛው መስመር በትክክለኛ አገባብ እንዳይፈጸምና ከመስመሩ ተጠቃሚ መሆን የጀመረው ህዝብ የሚያስከፉ የመልካም አስተስዳደር ችግሮችን መከሰታቸውን የተመለከተው የኢህአዴግ ምክር ቤት አንገብጋቢ የነበሩትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች፤ በተለይም በገጠርና በከተማ የስራ ዕድል ፈጠራ በሚመለከት ስራ ፈላጊዎችን የመለየት፣ የማደራጀት የማሰልጠንና መሰል ተግባራትን በመፈፀም በርካታ ስራዎችን ተከናውነዋል። በዚህም አበረታች ውጤት ተመዝግቧል። ካለው የስራ ፈላጊዎች ቁጥርና ከችግሩ ስፋት አኳያ በቀጣይም የርብርብ ማዕከል እንደሚሆን አጽንኦት ሰጥቶታል።


ከአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት አኳያ በየዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች በዝርዝር በመለየት መፍታት የተጀመረ ቢሆንም ህዝቡን በሚያረካ ደረጃ ባለመሆኑ ቀጣይ ትኩረት የሚፈልግ መሆኑን አጽንኦት አስምሮበታል። ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በተለይም በፍትህ አካላት የተካሄደው ተሃድሶና የተጀማመሩ ስራዎች እንደተጠበቁ ሆነው አሁንም ቀጣይ ስራዎች እንደሚጠይቁ ምክር ቤቱ ገምግሟል።


በአንዳንድ አካባቢዎች ከወሰን ጋር ተያይዞ ይነሱ የነበሩ ችግሮች የተፈቱና መፈታት መጀመራቸውን የገመገመው ምክር ቤቱ ከዚህ አኳያ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሊ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች፤ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል እንዲሁም በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል ከወሰን ጋር ተያይዞ ተፈጥረው የነበሩትን ችግሮች በመፍታት ረገድ አበረታች ስራዎች መከናወናቸውንም ምክር ቤቱ አይቷል። በበኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልሎች መካከል አሁንም ትኩረት የሚሹ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውንም አመላክቷል። በቀጣይም በዚህ ረገድ የሚታዩ ችግሮች የህዝቡን ዘላቂ ሰላም እንዳያውኩ ለማድረግ ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተመልክቶታል።


በአጠቃላይ የተጀመረው መልካም አስተዳደር የማስፈን ተግባር ዋነኛ የርብርብ ማዕከል ሆነ እንደሚቀጥል አስምሮበታል።


ሙስናና ብልሹ አሰራርን በሚመለከት ከጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴው ጋር ተያይዞ ዋናው ስራ በአመላከት ላይ የሚደረግ ትግል መሆኑን እንደተጠበቀ ሆኖ ችግር ውስጥ የገቡ በፌደራል፣ በክልል፣ በዞን፣ በወረዳና በሌሎች ታችኛው የአስተዳደር ደረጃዎች የሚገኙ በርካታ ቁጥር ያላቸው አመራሮች ላይ ፖለቲካዊና አስተደዳራዊ እርምጃ ከመወሰድ በተጨማሪ ማስረጃ በተገኙባቸው ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በህግ እንዲጠይቁ በማድረግ ተጠያቂነትን ለማስፈን የተደረገውን ጥረት በጥንካሬ በመገምገም በቀጣይም የጸረ ሙስና ትግሉ ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ መሄድ እስከሚገባው ርቀት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አጽንኦት ሰጥቶታል።


የኢህአዴግ ምክር ቤት በአጋር ድርጅቶች የመታደስ እንቅስቃሴንም በዝርዝር ፈትሿል። አጋር ድርጅቶቹ ከሚመርዋቸው ክልሎች ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የተሻለ መተጋገል የተደረገበት እንደነበር ገምግሟል። ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አያይዞው የነበሩትን የኪራይ ሰብሳቢነት፤ ጸረ ዴሞክራሲና ጠባብነት በዝርዝር በመገምገም ለማስተካከል ጥረቶች በማድረግ ላይ መሆናቸውንም አይቷል። ኢህአዴግ አጋሮቹ ነጻነታቸውን ተጠብቆ የአቅም ግንባታ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑንም የተመለከተው ምክርቤቱ አጋር ድርጅቶቹ በጥልቅ ተሃድሶ የተለዩ ችግሮችን ለመፍታትና የህዝብን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ በቀጣይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጻል።


በአጠቃላይ ጥልቅ ተሃድሶው አገሪቱን ከመስቀለኛ መንገድ የታደገ፣ በተቀመጠለት አቅጣጫ በመተግበር ላይ ያለና የህዳሴውን ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በተቀመጠው አቅጣጫ የተፈጸመና ተደማሪ ውጤት ያመጣ ወቅታዊና ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ምክር ቤቱ ገምግሟል። በዚህም በተካሄደው የአባላትና የህዝብ መድረኮች እንዲሁም በድርጅት ልሳናት ላይ በተደረገው ትግል የስርዓቱ አደጋ የሆኑትንና ጫፍ ደርሰው የነበሩትን እንደ ትምክህትና ጠባብነት ያሉ ችግሮች ማፈግፈግ መጀመራቸውን አይተዋል። በዚህም የጥልቅ ተሃድሶው ሂደት አመራሩና አባላቱ ዘንድ ለበለጠ ትግል እንዲነሳሱ ያደረገ ሲሆን በህዝቡ ዘንድም ችግሮቹ ይፈታሉ የሚል ተስፋ የጫረና በሂደቱ ላይም ህዝቡ ንቁ ተዋናይ እንዲሆን መነቃቃትን የፈጠረ መሆኑን አመልክቷል።


በቀጣይም አመራሩ፣ አባላትና መላው ህዝብ የህዳሴው ጉዞ ጸር የሆኑትና የስርዓቱ አደጋዎች የሆኑትን እኝህ ችግሮች ለማስወገድ ቀጣይ ትግል ማድረግ እንዳሚገባቸው አጽንኦት ሰጥቶታል።


ምክር ቤቱ ባለፈው ዓመት ተፈጥሮ በነበረው ችግር ምክንያት ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ወደነበረበት በመመለስ ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን የገመገመ ሲሆን አዋጁ መንግስትና ህዝብ በልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ የሚያደርጉትን ርብርብ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን ተመልክቷል። ህዝቡም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ሆነ አዋጁ ከተነሳ በኃላ ዘላቂውን ሰላም ለማረጋገጥ ያሳየው ቁርጠኝነትና ያደረገው አስተዋጽኦ በአድናቆት ተመልክቶታል።


የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በተመለከተ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ከማጎልበትና ምህዳሩን ከማስፋት አኳያ በዓመቱ ከተከናወኑ በርካታ ተግባራት ከሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተጀመረው ድርድርና ክርክር ተጠቃሽ መሆኑን በማመላከት ሂደቱ በመቻቻል፣ በመደማመጥና ሰጥቶ በመቀበል መርህ ላይ በመመስረት ለመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መጠናከር የራሱን ሚና የሚጫወት መሆኑን አመልክቷል።


ከተለያዩ ሲቪክ ማህበራት ጋር የተደረጉ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ውይይቶች ዴሞክራሲያዊ ባህልን ከማጎልበት አንጻር ጠቃሚ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን ያየው ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የተደረጉ ውይይቶች የዴክራሲያዊ ስርዓቱ ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንደለበት ገልጻል። ምክር ቤቱ በየደረጃው ያሉ የህዝብ ምክር ቤቶች እና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት ለማጠናከር የተደረጉ ጥረቶችም አበረታች እንደነበሩም ተመልክቷል።


የሰራዊት ግንባታ አፈጻጸምን የተመለከተው ምክር ቤቱ ከጥልቅ ተሃድሶ ጋር ተያይዞ ድርጅት የመሪነት ሚናውን እንዲጫወት፤ ህዝብ ጠንካራ የሰራዊት ክንፍ ሆኖ ተልዕኮውን በመወጣት የማስፋት ስራቴጂው ተግባራዊ ከማድረግና የህዝብም ተጠቃሚነት ከማስፋት የነበረውን አፈጻጸም በዝርዝር ገምግሟል። በገጠር የሰራዊት ግንባታ በተሻለ ደረጃ የሚገኝ ሲሆን በተለይ በተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ እና የተፋሰስ ልማት የሠራዊት የቁመናውን ይዞ የቀጠለ ሲሆን በሌሎች የገጠር ግንባሮች ተዳክሞ ከነበረው መልሶ የማደረጃት ስራዎች መከናወናቸውን ተመልክቷል። በቀጣይ በከተማ የሰራዊት ግንባታ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አይቷል።


የኢህአዴግ ምክር ቤት የመንግስት ስራዎችን አፈጻጸም በጥልቀት የገመገመ ሲሆን የ2009 ዓ.ም የኢኮኖሚ ዘርፎች የእድገት አዝማሚያ ላይ በመመስረት ሲታይ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በዓመቱ የተተነበየውን የ11ነጥብ1 በመቶ እድገት ሊያሳካ እንደሚችል፤ ይህ የኢኮኖሚው ዕድገት በግብርናው ዘርፍ በ2008 ዓም ካጋጠመው ድርቅ በማገገም ለዘርፉ የተተነበየውን የ8 በመቶ ዕድገት እንደሚያሳካና በኢንዱስትሪውና በአገልግሎት ዘርፎችም ለበጀት አመቱ የተተነበየላቸው የ20 ነጥብ 6 በመቶ እና የ10 ነጥብ 2 በመቶ የተጨማሪ እሴት እድገት በቅደም ተከተል እንደሚያሳካ እንደሚጠበቅ ተመልክቷል። በአጠቃላይ ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገቱ በሁሉም የዕድገት መለኪያዎች ሲታይ ጤናማ ሆኖ መቀጠሉን የገመገመው ምክር ቤቱ በውጭ ንግድ ላይ የሚታየውን ክፍተት ለማስተካከል ልዩ ትኩረት የሚጠይቅ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶበታል።


የአየር መዛባት ያስከተለው ድርቅ ለመቋቋምና በሀገራዊ አቅም ለማቆጣጠር የተደረገው ጥረትና የተገኘው ውጤት አበራታችና ልምድ የተገኘበት መሆኑም የተመለከተው ምክር ቤቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ አደጋን ለመከላከል እንዲሁም የእህል ገበያን ለማረጋጋት እንደመሳርያ የሚያገለግል የስትራቴጂክ መጠባበቅያ የምግብ ክምችት አስተማማኝ መሆኑንም ጠቅሷል።


ምክር ቤቱ የማንፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ በመከናወን ላይ የሚገኙ ስራዎች የገመገመ ሲሆን የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ልማት እንደ አንድ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ መሳርያ አድርጎ እየተጠቀመ ያለ በመሆኑ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን የመሰረተ ልማት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና የገበያ ትስስር ችግሮችን የሚፈታ እንደሆነ ነው የተመለከተው።


ምክር ቤቱ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን አፈጻጸምን የገመገመ ሲሆን የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ሌሎች የሃይል ማመንጫ የመንገድ፣ የባቡር፣ ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች አፈጻጸም የተሻለ ቢሆንም ቀጣይ ትኩረት የሚሻ መሆኑን አስምሮበታል።


በማህበራዊ ልማት የትምህርት እና የጤና መስኮች አፈጻጸም በዝርዝር የገመገመው ምክር ቤቱ በትምህርት መስክ ከቅድመ መደበኛ እስከ የከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነትና ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ የተደረገውን ርብርብ ከፍተኛ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑንም የዩኒቨርሲቲዎች ስርጭትና ተደራሽነት በፍትሃዊነት መከናወኑንና ከነባሮቹ 35 ዩኒቨርሲቲዎችን በመጨመር በአሁኑ ወቅት የዩኒቨርሰቲዎች ቁጥር ወደ 50 ከፍ ማለቱንና ከተደራሽነትና ፍትሃዊነት አኳያ አመርቂ ስኬቶች መመዝገባቸውን የገመገመው ምክር ቤቱ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀማመሩ ስራዎች በቀጣይ ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው መሆኑን አስምሮበታል።


ምክር ቤቱ በጤናው መስክ በተለይም የእናቶችን ጤና አገልግሎት ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱ የእናቶችና ህጻናት ጤንነት ለመጠበቅ ማስቻሉን የገመገመ ሲሆን በአጠቃላይ በጤናው መስክ የተገኙ ስኬቶችን ማስፋትና ማጠናከር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥቶበታል።


በአጠቃላይ ምክር ቤቱ በ2009 ዓም በጥልቅ ተሃድሶው ሂደት የተገኙ መልካም ውጤቶችን በዝርዝር በማየት ያጋጠሙ ችግሮችንም በውል በመለየት በመጪው አዲስ ዓመት የተጀመረው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ይበልጥ እንዲቀጥል፣ የፈጣን ልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱን አጠናክሮ በማስቀጠል የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሶስተኛው ዓመት ማሳካት የ2010 ዓም ቁልፍ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ የድርጅቱ አባላትና አመራር እንዲሁም መላው የሀገራችን ሕዝቦች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ምክር ቤቱ ጥሪውን አስተላልፏል። የኢህአዴግ ምክር ቤት አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የልማትና የብልጽግና በአጠቃላይ የከፍታ ዘመን እንዲሆን ለመላው የሀገራችን ህዝቦች መልካም ምኞቱንም ገልጻል።


…..


እንደማሳረጊያ


ይህ የኢህአዴግ መግለጫ በውስጡ የያዛቸው ቁምነገሮች በርካታ ናቸው። በተለይ ከጥልቅ ተሀድሶው ጋር በተያያዘ «በአጠቃላይ ጥልቅ ተሃድሶው አገሪቱን ከመስቀለኛ መንገድ የታደገ፣ በተቀመጠለት አቅጣጫ በመተግበር ላይ ያለና የህዳሴውን ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በተቀመጠው አቅጣጫ የተፈጸመና ተደማሪ ውጤት ያመጣ ወቅታዊና ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ምክር ቤቱ ገምግሟል» ሲል ያስቀምጣል። ይህ ምዘና የተከናወነው በራሱ በግንባሩ ወይንስ በሕዝብ የሚል ጥያቄን የሚያስነሳ ነው። ሕዝቡ የግንባሩን ጥረቶች ገምግሞ የደረሰበት ድምዳሜ ከሆነ ትክክለኛና መከበር የሚገባው ሲሆን ግንባሩ በራሱ መዋቅር መረጃ ሰብስቦ የደረሰበት ድምዳሜ ከሆነ ግን መሬት ላይ ካለው እውነታ አንፃር ሲታይ ጉድለት ሊኖርበት እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል። ጥልቅ ተሀድሶው በሥራ ላይ ከዋለ በኋላ በየክልሉ እና በፌዴራል ደረጃ ሰዎች ከሙስናና ብልሹ አሠራር ጋር ተያይዞ መታሰራቸውና አንዳንድ እርምጃዎች መወሰዳቸው እውነት ነው። አንዳንድ ባለስልጣናትንም ከቦታቸው በማንሳት ጭምር የወሰዳቸው እርምጃዎች በጥሩ ጎኑ የሚታዩ ናቸው። ነገርግን የመንግስት ሥልጣንን ለግል ጥቅም ያዋሉ ባለሥልጣናት እነዚህ ብቻ ናቸው ወይ? በከፍተኛ አመራሩ ውስጥ ጭምር ከገቢያቸው በላይ ሐብት ያፈሩ አመራሮች የሉም ወይ ለሚለው ተደጋጋሚ የሆነ የህዝብ ጥያቄ ግንባሩ ቁርጥ ያለ መልስ የሰጠበት ሁኔታ የለም።


በስኳር ኮርፖሬሽን፣ በመንገዶች ባለሥልጣን እና በመሳሰሉት ተቋማት በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ሲመዘበር አንዳንድ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቦርድ ሰብሳቢነት ወይንም አባልነት ጉዳዩን በቅርበት ያውቁ እንደነበር፣ አንዳንዱም ወጪ በቦርዱ ውሳኔ የተፈጸመ ስለመሆኑ በስፋት መነገሩ ከእያንዳንዱ የሙስና ድርጊት ጀርባ ሌሎች ተባባሪ ሰዎች መኖራቸውን ፍንጭ ሰጪ ነው። ይህም የሕዝብ ጥርጣሬ በአግባቡ ሊፈተሽና ምላሽ ሊያገኝ የሚገባ ጥያቄ ነው።


በተጨማሪም በኦሮሚያ፣ በአማራ እና ቤሌች አካባቢዎች በታዩ ግጭቶች ጀርባ የነበሩ ሹማምንት በሰሩት ጥፋት ልክ ስለመጠየቃቸው ሕዝብ በቂ መረጃ የለውም።


እናም የተሀድሶ ሒደቱ ውጤታማ ነው የሚለው ድምዳሜ ጥያቄ የሚነሳበት ከዚህ አንጻር ሲፈተሸ ነው። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
374 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 647 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us