ደም አፋሳሹ ግጭት ወዴት ይወስደን ይሆን?

Wednesday, 20 September 2017 17:10

 

አዲሱ ዓመት (2010 ዓ.ም) መባቻ ጥሩ ዜና የተሰማበት አልነበረም። በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች አልፎ አልፎ ከድንበር እና ከግጦሽ ጋር የተያያዙ ደም አፋሳሽ ግጭቶች የተለመዱ ቢሆንም ባለፉት ሳምንታት የታየው ግን ከምንግዜውም በላይ የከፋና አሳዛኝ ክስተት የተስተዋለበት ነበር። ሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች እርስበእርስ የተገዳደሉበት፣ ግጭቱም ሠላማዊ ሰዎችን ሕይወት አውኮ ለመፈናቀል የዳረገበት መሆኑ አሳዛኝ ነበር።

 

አጠቃላይ መረጃ


የኦሮምያ የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት እንደሚለው የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል ከኢትዮጵያ ሶማሌ ብሄራዊ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸዉ የቦረና፣ ጉጂ፣ ባሌ፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች የኢትዮጵያ ሶማሌ ልዩ ፖሊስ በሰላማዊ ዜጎች ላይ በሚያደርሰዉ ጥቃት የተነሳ ከአምና ጀምሮ ሠላም አልነበረም ይላል። ከዚህ ጋር ተያይዞም የበርካታ ንጹሃን ዜጎች ህይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን፣ በ2009 የበጀት ከአምስቱ ዞኖች የግጭት አካባቢዎች 416 ሺ 807 የሚሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች ከልዩ ፖሊስ ጥቃት በመሸሽ ህይወታቸዉን ለማትረፍ ሲሉ ቀዬአቸዉን ጥለዉ ለመፈናቀል መገደዳቸውን ያትታል።


ሰሞኑን በተከሰተ ችግርም ከ55,000 በላይ የሚሆኑ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ተፈናቅለዉ በሐረር፣ ጭናክሰን፣ ሚኤሶ እና ባቢሌ ከተሞች በድንኳን ተጠልለዉ ይገኛሉ ብሏል።


የሶማሌ ክልል የመንግሥት ኮምኒኬሽን ቢሮ በበኩሉ "በኦሮሚያ ክልል ነዋሪ በሆኑ የሶማሌ ተወላጆች ላይ የዘረኝነት ጭፍጨፋ የተጀመረ ሲሆን በተለይ በአወዳይ ከተማ በትላንትናው እለት ከ50 በላይ የሆኑ ንጹሀን ዜጎች እስከዛሬ ድረስ በሀገራችን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በአሰቃቂ ሁኔታ የተቀጠፉ ሲሆን ከ300 በላይ የሚሆኑ ደግሞ በመከላከያ ሰራዊት ሀይል ህይወታቸውን በማትረፍ ወደ ሐረር እንዲገቡ ተደርጓል::…ይላል. . ." ለዚህም ድርጊት የኦሮሚያ ክልል መሪዎችን ተጠያቂ ያደርጋል።

 

የሁለቱ ክልል መሪዎች በአዲስአበባ መገኘት
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ለማ መገርሳ እና የሶማሌ ክልል ፕሬዚደንት አቶ አብዲ ኡመር ከግጭቱ በኃላ በአዲስአበባ ተገኝተው ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ከመወያየታቸውም በተጨማሪ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። ሁለቱ መሪዎች በዚሁ መግለጫቸው ግጭቱ የክልል መንግስታቱም፣ የህዝቡም ፍላጎት አለመሆኑን አንጸባርቀዋል። ዜናው እንዲህ ይላል።


«በኦሮሚያ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ሰሞኑን የተፈጠረው ግጭት ሁለቱን ህዝቦች እንደማይወከል የሁለቱ ክልል ርእስ መስተዳድሮች ገለጹ።


የኦሮሚያ ክልል ርእስ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አቻቸው አቶ አብዲ መሃመድ ኡመር….መግለጫ ሰጥተዋል።


ርእሳነ መስተዳድሮቹ በጋራ መግለጫቸው፥ በግጭቱ በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማቸው ተናግረዋል።»


መሪዎቹ በመግለጫቸው ለተከሰተው ችግር በይፋ ኃላፊነትን መውሰድ አልፈለጉም። እንዲያውም የችግሩ መነሻ ውጫዊ ለማድረግ የሄዱት ርቀት “ግጭቱ ሁለቱን መንግሥታትና ሕዝቦች አይወክልም” በሚል ነበር። በእርግጥ የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝብ አብሮ የኖረ፣ የተዋለደ…በመሆኑ በራሱ የሚፈጥረው ግጭት እንደሌለ የሚታመን ነው። ነገርግን በየደረጃው ያሉ ሹማምቶች ትንንሽ አለመግባባቶች እንዲካረሩ በማድረግ ትልቅ ጥፋት ሊያደርሱ የሚችሉበት ዕድል የተዘጋ አይደለም።


ሌላው ቀርቶ ከስድስት ወራት በፊት በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሸምጋይነት የሁለቱ ክልል መሪዎች ተስማምተው፣ ጥፋተኞችን ለፍርድ ለማቅረብና ተመሳሳይ ጥፋትም እንደማይደገም ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም ምንም የወሰዱት እርምጃ ባለመኖሩ ዳግም ችግሩ ሊከሰት ችሏል።


አንዳንድ በጉዳዩ ላይ በገለልተኛ ወገኖች የተጻፉ መረጃዎች እንደሚሉት በቆዳ ስፋቱ ከአገሪቱ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው የኦሮሚያ ክልል፤ ከሁለተኛው ሰፊ የሶማሌ ክልል ጋር የሚያዋስነው 1410 ኪሜ ድንበር አለው። ይህ ድንበር ግን ክልሎቹ አሁን ያሉበትን ቅርጽ ይዘው ከተመሰረቱበት ጊዜ አንስቶ ውዝግብ አያጣውም። ውዝግቡን ፈትቶ ወሰኖቹን መልክ ለማስያዝ ታስቦም ሕዝበ ውሳኔ ከ400 በሚበልጡ ቀበሌዎች በጥቅምት ወር 1997 ዓ.ም ተደርጓል።


በሕዝበ ውሳኔው መሰረት ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ ቀበሌዎች በኦሮሚያ አስተዳደር ሥር እንዲጠቃለሉ የተወሰነ ቢሆንም የወሰን ማካለል ሥራው ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል። ይህም በየጊዜው ለሚነሱ ግጭቶች አባባሽ ምክንያት መሆኑ አልቀረም።


ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ግን የሁለቱም ክልሎች ፕሬዚዳንቶች ሕዝበ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ ያስችላል የተባለ ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ "ትልቅ ድል" መገኘቱን ሲገልፁ፥ የሶማሌ ክልል አቻቸው አብዲ መሃመድ በበኩላቸው "በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ዳግመኛ ግጭት አይኖርም።'' ብለው ነበረ።


የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋም የችግሩ ምንጭ ''የድንበር ጉዳይ እንዳልሆነ የሚያረጋግጥልን፤ ድንበር በማንጋራባቸው አካባቢዎች ጭምር ጥቃት ሲፈፀም የነበረው። የድንበሩን ጉዳይ በ1997 ሕዝበ-ውሳኔ መሰረት ለመፍታት በተደረሰው ስምምነት መሰረት እየሰራን ነው።ሥራውም ሰባ በመቶ በላይ ተጠናቋል።'' ሲሉ ሌላ ምክንያት ሊኖር እንደሚችል ይጠቁማሉ።


ሆኖም ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ ወንጀለኞች ለፍርድ ሳይቀርቡ፣ ደንበር የማካለል ሥራውም ሳይጠናቀቅ ሌላ ዙር ግጭት ሊከሰት ችሏል፣ ያሳዝናል።

 

የፌዴራል መንግሥቱ አቋም


ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሁለቱ ክልሎች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ሰሞኑን ከተወያዩ በኃላ በደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው መንግሥት በክልሎቹ አንዳንድ አዋሳኝ አካባቢዎች ሰሞኑን የተፈጠረውን ግጭት የማረጋጋትና ሕግን የማስከበር ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።


በዚህ መሠረት የአካባቢዎቹን ሰላምና ፀጥታ ወደነበረበት ለመመለስ በሁለቱ ክልሎች የሚገኙ ዋና ዋና መንገዶች በፌደራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ክትትል ሥር እንዲሆኑ፣ የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች የሕዝቡን ሰላም የመጠበቅና የማረጋጋት ሥራ እንዲሰሩም፣ አካል በማጉደልና የሰው ሕይወት በማጥፋት የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር እንዲያውሉ አቶ ኃይለማሪያም ማዘዛቸው ተዘግቧል።


በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ የትኛውም ግለሰብና የፀጥታ ኃይልም ተጠያቂ እንደሚሆኑ አረጋግጠዋል።

 

እንደማጠቃለያ
በአሁኑ ወቅት የሁለቱ ክልሎች ግጭት ጀርባ መሠረታቸውን በውጭ ሀገር ያደረጉ የመንግሥት ተቃዋሚዎች ናቸው ብሎ ለችግሩ ውጫዊ ምክንያት ለመስጠት የሚደረገው ሙከራ ያረጀ ፕሮፖጋንዳ ነው። እናም መንግሥት ግጭቱን በመለኮስ፣ በማቀጣጠል ሚና ያላቸው በየደረጃው የሚገኙ አካላትን ለፍርድ በማቅረብ የሕግ የበላይነትን በተግባር ሊያረጋግጥ ይገባል።


ለግጭት መነሻ የሆኑ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ከህዝብ ጋር ቀጥታ በመመካከርና በጥናት በመታገዝ ተለይተው ደረጃ በደረጃ መፍትሔ እንዲያገኝ ከፌዴራል መንግሥት ብዙ ይጠበቃል። 

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
303 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 264 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us