ከግጭቱ ጀርባ ያሉ አካላትን ፍለጋ

Thursday, 28 September 2017 14:36

- ግጭቱን በማቀጣጠል የኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች፣ በጥቅም የተሳሰሩ ብሎገሮች፣ የውጭ ኃይሎች ተጠርጥረዋል፤

- የክልሎቹ ከፍተኛ አመራሮች ራሳቸውን ንፁህ አድርገዋል፤

 

 

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ድንበሮች መካከል ባለፉት ሳምንታት የተፈጠረው ደም አፋሳሽ ግጭት አሁንም ድረስ መነጋገሪያነቱ እንደቀጠለ ነው። ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅና እጅግ ጭካኔና ኢ- ሰብዓዊነት በጎደለው መልኩ ሰዎች ብሔርና ዘር ለይተው እንዲጨፋጨፉ የሆነበት ትዕይንት እጅግ አስደንጋጭና መጪውን ጊዜ አስፈሪ የሚያደርግ ክስተት ነበር። ይህንን ተከትሎ የሁለቱ ክልሎች በኮምኒኬሽን ጽ/ቤቶቻቸው በኩል ፀብ ጫሪና ወንጃይ ንግግሮች ከማሰማት አልፈው ለእልቂቱ አንዳቸው ሌላኛውን ተጠያቂ እስከማድረግ፣ አንዳቸው ሌላኛውን የውጭ ሀይሎች ተልዕኮ አስፈጻሚ አድርጎ እስከመፈረጅ የደረሰ እንካሰላንቲያዎችን ሲለዋወጡ ታዝበናል።


የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልል ፕሬዚደንቶች አዲስ አበባ መጥተው ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ካነጋገሩና ከተገማገሙ በኋላ ግን ድንጋጤያቸው ከገጽታቸው ላይ ሳይጠፋ መግለጫ ሰጥተዋል። በዚሁ መግለጫቸው «ግጭቱ የአመራሩ እና የሕዝቡ ፍላጎት አይደለም» በማለት እንደተለመደው ውጫዊ ምክንያት ሰጥተው ለማለፍ ሞክረዋል። የሆኖ ሆኖ በዚህ ጠንካራ መንግሥትና ሠላም ወዳድ ሕዝብ አለ በሚባልበት ሀገር ስለፈሰሰው ደም፣ ስለደረሰው መፈናቀልና ሰብዓዊ ቀውስ እስካሁን በግልጽ ተጠይቆ ለፍርድ የቀረበ አካል (ግለሰብ) አልተገኘም። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኮምኒኬሽን ቢሮ ሰሞኑን ያወጣው ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ ከችግሩ ጀርባ ያሉ አካላት ኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች ናቸው የሚል አንደምታ ያለው ነው።


የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው የመንግሥትን ሥልጣን ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ አመራሮች መጠየቅ መጀመራቸውን በመጥቀስ መነሻ ጉዳዩን ውስጣዊ መሆኑን ጠቆም አድርገዋል። ይህ የሚኒስትሩ አባባል የሁለቱ ክልል ፕሬዚደንቶች «እኛ የለንበትም» ዓይነት መግለጫ የሚቃረን ነው።


የኦሮሚያ ክልልዊ መንግሥት ሰሰሞኑን ባወጣው መግለጫ የክልል ከፍተኛ አመራር በኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች የተቀነባበረ የስም ማጥፋት ዘመቻ እየተካሄደበት ነው ከማለቱም በተጨማሪ የጥቅም ትስስር አላቸው ያላቸውን ብሎገሮች አስጠንቅቋል።


በክልሉ ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት በኩል ሰሞኑን የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው ኪራይ ሰብሳቢ አካላት ላይ እየተወሰደ ያለዉ እርምጃ የክልሉን ሕዝብ የማስደሰቱን ያህል ጥቅማቸዉ የተነካባቸዉን ግለሰቦችን አስደንግጧል። እነዚህ ጥቅማቸዉ የተነካባቸዉ ግለሰቦች ያለ የሌለ ኃይላቸውን አሰባስበዉ የክልሉን አመራር ከዚያም አልፎ የክልሉን ሕዝብ እና መንግስት መልካም ስም ጥላሸት ለመቀባት ዘመቻ ከፍተዋል።


መግለጫው እንዲህ ይላል። «የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄዉ ከተጀመረ ጊዜ ወዲህ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ጠንካራ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሆነ ይታወቃል። የክልሉን ህዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲባል በክልሉ ሲስተዋሉ የነበሩ ህገ ወጥ የመሬት ዘረፋ፣ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ ህገወጥ የዶላር ዝዉውር፣ ህገ ወጥ የማዕድን ዘረፋ እና በመሳሰሉት የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት ላይ ጥብቅ እርምጃ በመዉሰድ ለህዝብ ጥቅም እንዲዉል በማድረግ ላይ ይገኛል። የክልላችንን ህዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በክልሉ እየተካሄደ ያለዉ የጸረ- ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል በህዝቡ ንቁ ተሳትፎ እና ድጋፍ እየተከናወነ ነዉ። በሌላ በኩል ያለአግባብ ጥቅም ሲያግበሰብሱ የነበሩ ግለሰቦች ይህን የጸረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ለማደናቀፍ የቻሉትን ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የጸረ- ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ የፈለገዉን መስዋዕትነነት ቢያስከፍልም የህዝቡን ጥቅም እስካረጋገጠ ድረስ በማይቀለበስ ደረጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ለማረጋገጥ እንወዳለን።»


መግለጫው አያይዞም «…. ኪራይ ሰብሳቢ አካላት ላይ እየተወሰደ ያለዉ እርምጃ የክልሉን ህዝብ የማስደሰቱን ያህል ጥቅማቸዉ የተነካባቸዉን ግለሰቦች አስደንግጧል። እነዚህ ጥቅማቸዉ የተነካባቸዉ ግለሰቦች ያለ የሌለ ኃይላቸዉን አሰባስበዉ የክልሉን አመራር ከዚያም አልፎ የክልሉን ህዝብ እና መንግስት መልካም ስም ጥላሸት ለመቀባት ዘመቻ ከፍተዋል። በዚህ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻቸዉ በክልሉ መንግስት የጸረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል እርምጃ ከተዋሰደባቸዉ ግለሰቦች ጋር የጥቅም ትስስር ያላቸዉን "ብሎገሮች"፣ "አክቲቪስቶች" እና "ጋዜጠኞች" በማሰማራት የበሬ ወለደ የሀሰት ታሪኮችን በመፈብረክ የክልሉን መንግስት የስራ ኃላፊዎች በ"ፋሺስትነት" የመፈረጅ፣ በክልሉ አንድም ሰዉ ሳይፈናቀል "ሰዎች ተፈናቅለዋል" የሚል አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት፣ ግጭት ሳይፈጠር "ኦሮሞ እና እከሌ የሚባል ብሄረሰብ ተጋጭተዋል "የሚሉ እና የመሳሰሉትን የሀሰት መረጃ በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ። እነዚህ እየተቀነባበሩ የሚሰራጩ የተንኮል እና የሀሰት መረጃዎች ግብ የኦሮሞ ህዝብ እና የክልሉ መንግስት ከአጎራባች ክልሎች እና በክልሉ በሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች ዘንድ በጥርጣሬ እንዲታይ የማድረግ እኩይ አላማ ያለዉ እንደሆነ ግልጽ ነዉ። ከዚያም በላይ የኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎችን የጥቅም ገመድ በመበጣጠስ ላይ የሚገኘዉን የክልሉን የተሀድሶ አመራር "ጠብ አጫሪ" እና "የሀገር አንድነት ስጋት" አስመስሎ በማቅረብ፣ የክልሉን ሚዲያ፣ መሪ ድርጅቱን እና አመራሩን በፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በማዳከም ለኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች የተመቸች ደካማ ክልል እንዲኖር የማድረግ ፍላጎት ያለዉ መሆኑን ለክልላችን ህዝብ እና መላዉ የሀገራችን ህዝቦች ለማስገንዘብ እንወዳለን» ብሏል።


የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የክልሉ ህዝብ እና መንግስት ተረጋግቶ የልማት እና የጸረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉን እንዳያፋፍም እየተደረጉ ያሉ የተንኮል እና የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎችን እና በዚህ እኩይ ተግባር እየተሳተፉ ያሉ ግለሰቦች እና ተቋማት በህዝቡ ዘንድ እንዲጋለጡ ይሰራል።


ከዚያም ባለፈ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረዉን ችግር ለማረጋጋት ከሰጡት አቅጣጫ በተቃራኒ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት በወንድማማች ህዝቦች እና በህዝብና መንግስት መካከል ጥርጣሬ እና ግጭት እንዲፈጠር እያደረጉ ያሉ አካላት የክልሉ መንግስት ለህግ እንዲቀርቡ የሚያደርግ መሆኑን እንገልጻለን ሲል አክሏል።


በተያያዘም የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ከትላንት በስቲያ ተመሳሳይ ይዘት ያለው መግለጫ ሰጥተዋል። ሚኒስትሩ በዚሁ መግለጫቸው በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ ሙያዊ ሥነምግባርን በጣሰ መልኩ ለግጭት የሚያነሳሱ መረጃ የሚያደርሱ አካላት ላይ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።


ዶክተሩ በዚሁ መግለጫቸው ግጭቱ የፌዴራል ሥርዓቱን እና የሕዝቡን ፍላጎት እና የፌዴራል ሥርዓቱ የቆመለት የሕዝቦች አብሮ የመኖር እሴት የጣሰ ነው ብለውታል።


ከፌዴራል ሥርዓቱ ዓላማ በተቃራኒ እጃቸውን በማስገባት ሥልጣናቸውን ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ አመራሮች መጠየቅ መጀመራቸውን ይፋ አድርገዋል። በተጨማሪም የፌዴራል መንግሥት ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የፌዴራል ፖሊስ በማሰማራት ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ እያደረገ መሆኑን ከቀዬያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የመጠለያና የምግብ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
288 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 265 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us