ሼህ አልአሙዲ ማን ናቸው?

Wednesday, 08 November 2017 18:45

 

በሳዑዲ በንጉሳዊያን ቤተሰቦች የፖለቲካ ሥልጣን ሽኩቻ ጋር ተያይዞ ባሳለፍነው እሁድ ዕለት በሪያድ በሚገኘው ዕውቁ ሪትዝ ካርልተን (Ritz-carlton) ሆቴል በቁም እስር ካሉ ባለሃብቶች አንዱ የሚድሮክ ሊቀመንበር የክብር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አል-አሙዲ መሆናቸውን የሳዑዲ እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ይገኛሉ። ሆኖም በሀገር ውስጥ ይህ ዜና ሐተታ እስከተጠናቀረበት ትላንትና ዕለት ድረስ ስለጉዳዩ ይፋዊ መግለጫ የሰጠ አካል የለም።


ሼህ ሙሐመድ ባለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ ብቻ ከ70 በላይ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በማዕድን፣ በሪልስቴት፣ በማኒፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስ በመሳሰሉት የተሰማሩ ኩባንያዎችን በመመስረት ከ110 ሺ በላይ ወገኖች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉ ባለሃብት ናቸው።


ፈጣሪ ከደጉ ሼህ ሙሐመድ ጎን እንዲሆን እንመኛለን። ለመሆኑ ሼህ ሙሐመድ ማን ናቸው የሚለውን በጥቂቱ ምላሽ ለመሥጠት የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ካሳተመው «የልማት አርበኛ» የተሰኘ ልዩ መጽሔት የሚከተለው ተጠናቅሯል።

 

*** *** ***

 

እንደ መነሻ


ነፍሱን ይማረውና የመድረኩ ንጉሥ ድምጻዊ የክብር ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ ስለሼህ ሙሐመድ ሲናገር ሳግ እየተናነቀው “ሙሐመድ ወንድሜ ነው” ይል ነበር:: ጥላሁን ስለሼህ ሙሐመድ አውርቶ የማይጠግበው ሕመም ላይ በነበረበት ወቅት የሕክምና ወጪውን በመሸፈናቸው ብቻም አይደለም:: ልክ ከአንድ አብራክ እንደተገኘ ወንድም ፍቅርና ደግነታቸውን ስለለገሱት እንጂ:: ይህንን የሼህ ሙሐመድን ርህራሄና ደግነት የሚገልጽበት ቃላት ቢያጣ “ወንድም አለኝ” ሲል በመረዋ ድምጹ አንጎራጎረ:: ለነገሩ ገጣሚውስ ቢሆን፡- “ሰው ማለት፣ ሰው የሚሆን ነው፣ ሰው የጠፋ ዕለት” አልነበር ያለው::


ይህ የሼህ ሙሐመድ ኢትዮጵያዊ ደግነት እትብታቸው ከተቀበረበት ደሴ የተቀዳ ነው:: የደሴ ሕዝብ “ደግና ሩህሩህ ነው” ሲባል ከኖረበት ከዚያው ከምንጩ! የዓለማችን ባለጸጎችን ሐብት ተከታትሎ በሚመዘግበውና ይፋ በሚያደርገው “ፎርብስ” መጽሔት መረጃ መሠረት የክቡር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አል-አሙዲ ከየመናዊ አባታቸው እና ከኢትዮጵያዊ እናታቸው እ.ኤ.አ ጁላይ 21 ቀን 1946 ዓ.ም በደሴ ከተማ ተወለዱ፤ አብሮ አደጋቸውና በርካታ ኩባንያዎቻቸውን የሚያስተዳድሩት ጓደኛቸው ዶ/ር አረጋ ይርዳው ሼህ ሙሐመድ ለትንሽ ጊዜ በደሴ ወ/ሮ ስሂን ት/ ቤት መማራቸውን ይገልፃሉ::


ሼህ ሙሐመድ የትውልድ ቦታቸው “ደሴ ነው፤ አንዳንዴም ወልዲያ ነው” የሚል ጉንጭ አልፋ ክርክሮች በተለይም ከወሎ ሰዎች ተደጋግሞ ይሰማ ነበር:: እሳቸው ግን የትም ሆነ የትም ያው ወሎ ውስጥ መወለዳቸውን በመጥቀስ ነገሩን በቀልድ መልክ ሲያልፉት ኖረዋል:: በአንድ ወቅት ግን “ትውልዳቸው ደሴ፤ ያደጉት ደግሞ ወልዲያ” መሆኑን በአንደበታቸው በመናገራቸው ለክርክሩ የመጨረሻ እልባት ሰጥተውታል:: በዚህ ንግግራቸው የተማረኩ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ሼህ ሙሐመድ “ደሴና ወልዲያን አስታረቁ” ሲሉ ክስተቱን ዘግበዋል::


የሼህ ሙሐመድ እናት የወ/ሮ ሩቅያ ሙሐመድ ወላጅ አባትና የደሴ ታላቁ መስጂድ ኢማም በነበሩት በሐጂ ሙሐመድ ያሲን ስም የሚጠራ ባለ ስምንት ፎቅ ታላቅ የንግድ ማዕከል ሕንጻ በደሴ መሀል ፒያሳ በአንድ ወቅት በተመረቀበት ሥነሥርዓት ላይ ሼህ ሙሐመድ የማይረሳ ንግግር አድርገዋል:: “የተወለድኩት ደሴ፤ ሸዋበር ነው:: በተወለድኩ በ48 ቀኔ ወደ ወልዲያ ተወሰድኩ:: የልጅነት ጊዜዬን በወልዲያ፤ የወጣትነት ጊዜዬን ደግሞ በደሴ አሳልፌያለሁ:: ደሴም ተወለድኩ ወልዲያ ያው ወሎ ነው” ብለው ተናግረዋል::


ሼህ ሙሐመድ በወጣትነታቸው ወደ ውጪ አገር ባመሩበት ወቅት እናታቸው ወ/ሮ ሩቅያ ሙሐመድ በድንገት ከባድ አደራ ጣሉባቸው:: አደራውም “ሙሐመድ አገርህን እንዳትረሳ!” የሚል ነበር:: ሼህ ሙሐመድ ይህ የእናታቸው ከቋጥኝ የከበደ አደራ በሕሊናቸው ሠሌዳ ላይ እንደታተመ ኖረ:: እናም የደርግ ሥርዓት ተወግዶ ኢህአዴግ አገሪቷን ከተቆጣጠረ በኋላ የእናታቸውን አደራ ለመፈጸም መንፈሳቸው ተነሳሳ:: ዘወትር በሕሊናቸው ውስጥ ጉልህ ሥፍራ ያላት አገራቸው ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ተነሱ::


በእርግጥም ፍላጎታቸው የሚሳካበት አጋጣሚ ተፈጠረ:: እርሳቸው አጋጣሚውን እንደሚከተለው ይተርኩታል:: “የደርግ መንግሥት ከወደቀ በኋላ በሦስተኛው ወር አንድ አብሮ አደግ ጓደኛዬ ወደ ኢትዮጵያ እንድመጣ ጥሪ አቀረበልኝ:: ወደ አገሬ ከመጣሁ በኋላ የአገሪቱ የበላይ አመራሮች በልማት መስክ እንድሳተፍ ያቀረቡልኝን ጥሪ በመቀበል ዕቅድ አውጥቼ ወደ ሥራ ገባሁ” በማለት ወደ ልማት የገቡበትን አጋጣሚ ያስታውሳሉ::


“ፎርብስ” መጽሔት እ.ኤ.አ በመጋቢት 2014 ባወጣው መረጃ መሠረት የሼህ ሙሐመድ ጠቅላላ የሐብት መጠን 15 ነጥብ 3 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር መድረሱን፣ የነበራቸውም ደረጃ ከ65 ኛ ወደ 61 ኛ ከፍ ማለቱን አስታውቋል:: ይሁን እንጂ ሼህ ሙሐመድ ስለ ፎርብስ መረጃዎች በአንድ ወቅት ተጠይቀው “ከየት እያመጡ እንደሚጽፉት አላውቅም፤ እኔን አልጠየቁኝም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል:: አያይዘውም “እነሱ ያሉትን ዝም ብሎ አሜን ብሎ መቀበል ነው:: እኔ ግን እንዲህ ነው ብዬ መናገር አልፈልግም እንጂ የሐብት መጠኔን አውቀዋለሁ” ሲሉ በተዘዋዋሪ የፎርብስን መረጃ ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል አስተያየት ሰጥተዋል::


ሼህ ሙሐመድ የሐብት ምንጭ በዋነኛነት የነዳጅ ዘይት ይሁን እንጂ በማዕድን፣ በግብርና፣ በሆቴል፣ በኮንስትራክሽን፣ በሪልስቴት፣ በሆስፒታል፣ በሥልጠናና ምርምር፣ በፋይናንስ፣ በኦፕሬሽን ሜንቴናንስ እና በመሳሰሉት ዘርፎች በተለይ በአሜሪካ፣ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ በመሰማራት ይታወቃሉ:: በአጠቃላይ በዓለማችን ላይ በኩባንያዎቻቸው ውስጥ ከ200 ሺ በላይ ለሆኑ ሠራተኞች ሥራ መፍጠር የቻሉ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኩባንያዎቻቸው ቁጥር ከ70 በላይ መድረሳቸውን፣ ኩባንያዎቹም ከ40ሺ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የሥራ ዕድል ማስገኘታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ::


የክብር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ በአገራቸው ላይ እያፈሰሱ ያሉትን መዋዕለንዋይ ሦስት ቢሊየን ብር እንደሚደርስ በአንድ ወቅት ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ይግለጹ እንጂ በተግባር የሚታየው ለኢንቨስትመንት የወጣው መዋዕለንዋይ እርሳቸው ከጠቀሱትም በብዙ እጥፍ የላቀ መሆኑን መገመት ይቻላል::


ሼህ ሙሐመድ ከሚያነቡዋቸው መጽሐፍት መካከል ቅዱስ ቁርአን ቀዳሚው ነው:: ከውጪ ቋንቋዎች ዓረብኛ፣ እንግሊዝኛና ጣሊያንኛ ይናገራሉ:: ከ40 አገራት በላይ ከሥራ ጋር በተያያዘ ቁርኝት ስላላቸውም ሌሎች ቋንቋዎችንም ይሞክራሉ:: ከአገር ውስጥ ደግሞ አማርኛ እና ትግርኛ ቋንቋን አቀላጥፈው ይናገራሉ::


ሼህ ሙሐመድ መኪና የመሰብሰብ ልማድ (Hobby) እንዳላቸው በአንድ ወቅት ተናግረዋል:: ይህንንም ሲያስረዱ “እኔ በመጀመሪያ በኢትዮጵያ፣ በሳዑዲና በዱባይ መኪና እነዳለሁ:: አሜሪካ ውስጥም አንድ ሰሞን መኪና መንዳት ጀምሬ ነበር:: በኋላ ግን ጓደኞቼ ‘አንተ አሜሪካን ውስጥ መንዳት ያዳግትሃል፤የመንገድ ሥነሥርዓት ሕጉ እንደሌሎች አገራት አይደለም’ ብለው ከለከሉኝ:: በሳዑዲና በኢትዮጵያ መኪና መንዳት ያስደስተኛል:: አሁን ለምሳሌ ሳዑዲ ውስጥ ‘ቡጋቲ’ የሚባል መኪና አለኝ:: አንዳንድ ጊዜ ነሸጥ ሲያደርገኝና ወጣትነት ሲሰማኝ እርሱን አሸከረክራለሁ:: አዲስ አበባ ስመጣ ‘ማይቫክ’ አለኝ፤ አንዳንድ ጊዜ ‘ማርቼዲሱንም፤ ላንድክሩዘርም’ እነዳለሁ፣ ‘ሌክሰስም፤ ፎርዊልድራይቭም’ አለኝ፤ እነርሱንም አሽከረክራለሁ:: የመኪና ሆቢዬ ሰፋ ያለ ነው” ሲሉ ተናግረው ነበር::


በአፍሪካ፣ በአሜሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ተቋማትን ሳያካትት በኢትዮጵያ ብቻ ከሦስት ቢሊየን ብር በላይ ኢንቨስት የተደረገባቸው ከ70 በላይ ኩባንያዎች በተለያዩ ዘርፎች በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ:: በስዊድንና ሞሮኮ የነዳጅ ማጣሪያዎችን በመግዛትና ቅርንጫፎችን በመክፈት ሥራቸውን ከማስፋፋታቸው በፊት በኮንስትራክሽን (ሪልስቴት) ዘርፍ ተሰማርተው ነበር:: በአሁኑ ወቅት በስዊድን ስመጥር ከሆኑ የውጪ ኢንቬስተሮች ቀዳሚው ናቸው:: በስዊድን ካቋቋሟቸው ድርጅቶች ውስጥ “ፕሪም” የተሰኘው የነዳጅ ኮርፖሬሽን ይጠቀሳል::


“ዊኪፒዲያ” የተሰኘው የኢንተርኔት ኢንሳይክሎፒዲያ ባቀረበው መረጃ መሠረት ሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አል-አሙዲን በስዊዲሽ ነዳጅ ኮርፖሬሽን ከ530 በላይ ነዳጅ ማደያዎች ባለቤት ናቸው:: በኢትዮጵያ የሚገኙ ኩባንያዎቻቸው ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በመሆንም በማገልገል ላይ ይገኛሉ:: በሥራ ፈጠራ፣ በግብር እና በሮያሊቲ ላቅ ያለ ገንዘብ በየዓመቱ የመክፈል ግዴታቸውን በመወጣት ለአገሪቱ ልማትና ዕድገት አዎንታዊ ሚናቸውን እየተወጡ ይገኛሉ:: ከሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አል-አሙዲ በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ኩባንያዎች መካከል ሚድሮክ ወርቅ ላቅ ያለ ግብርና ሮያሊቲ በመክፈል በአንደኝነት ተጠቃሽ ነው::


ኩባንያው በሦስት ዓመታት ማለትም እ.ኤ.አ በ2010፣ በ2011 እና በ2012 በቅደም ተከተል ብር 399 ሚሊየን 328ሺ 068፣ ብር 491 ሚሊየን 327ሺ 233፣ ብር 742 ሚሊየን 496ሺ 823 በድምሩ 1 ቢሊየን 633 ሚሊየን 152ሺ 125 ብር ግብር ከፍሏል:: በተጨማሪም ኩባንያው ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ማስገኘት በመቻሉ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተሸላሚ ሆኗል:: ይህ ኩባንያዎቹ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ያላቸውን የላቀ ድርሻ የቱን ያህል ግዙፍ እንደሆነ የሚጠቁም ነው:: ይህን ያህል ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አስገኘ ሲባል ምን ማለት ነው? ኢንቨስትመንቱ በቀጥታ በሮያሊቲ፣ በትርፍ፣ ግብርና ቀረጥ ከሚያስገባው በተጨማሪ ይህን ግዴታውን በአግባቡ በመወጣቱ አገሪቱ ለመሠረተ ልማት ዝርጋታ የምታወጣውን ወጪ ያግዛል:: ከዚህ ግንባታ ጋር በተያያዘም የሚኖሩ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች ዜጎችን በቀጥታ የሚጠቅሙ ይሆናሉ:: ግንባታዎቹ በመከናወናቸውም የሚመጣው ቀልጣፋ አሠራር በአገሪቱ ኢኮኖሚን በማፋጠን ድህነትን በአጭር ጊዜ ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት ያግዛል::


የመንግሥት ልማት ድርጅቶችና የፕራይቬታይዜሸን ኤጀንሲ በመባል የሚታወቀው መ/ቤት ከ1987 እስከ 2005 ዓ.ም (በኢትዮጵያ አቆጣጠር) ድረስ ብቻ ጨረታ አውጥቶ በድምሩ 260 ድርጅቶችን ወደ ግሉ ዘርፍ ያዛወረ ሲሆን፤ ከነዚህ ድርጅቶች መካከል ሼህ ሙሐመድ 23 ያህል ድርጅቶችን ለመግዛት ችለዋል:: አንዳንድ አትርፈው የማያውቁና ሊዘጉ ጫፍ ላይ ደርሰው የነበሩ የልማት ድርጅቶች ላይ ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ካፒታል በመመደብ ከውድቀት በመታደጋቸው የሠራተኛውን የሥራ ዋስትና ከማረጋገጥ አልፈው ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አስችለዋል። 

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
475 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 834 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us