በክልል ግጭቶች ዙሪያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ

Wednesday, 15 November 2017 12:59

ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከረዥም ጊዜ ዝምታ በኋላ ባሳለፍነው ሐሙስ ዕለት በጽ/ቤታቸው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ በዚሁ መግለጫቸው በመንግሥት በኩል በየወቅቱ መግለጫ አለመሰጠቱን እንደአንድ ድክመት ተቀብለዋል፡፡ አቶ ኃይለማርያም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ዘርፎች ያተኮሩ ጥያቄዎች በጋዜጠኞች ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ዕትም ከሀገሪቱ ሠላምና ጸጥታ ጋር በተገናኘ የሰጡትን ምላሽ አስተናግደናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

 

ለኦሮሚያ እና ለሶማሌ ግጭት የኮንትሮባንድ እና የጫት ንግድ መነሻ እንደምክንያት፣


በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አጎራባች ዞኖች አካባቢ በተከሰተው ግጭት በርካታ የሰው ሕይወት ጠፍቷል። ከፍተኛ ንብረት ወድሟል። ሕዝቡም በተረጋጋ ሁኔታ ሥራውን እንዳይቀጥል የሚያደርግ ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር ይታወቃል። ይሄን ተከትሎ በመላው ኦሮሚያ የተለያዩ ቦታዎች ላይ አለመረጋጋቶች እንደነበሩ የሚታወቅ ነው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ዋናው ምክንያቱንና መነሻውን ማወቅና መረዳት የሚጠቅም ይሆናል።


ከዚህ በፊት በክልሎቹ ወሰን አካባቢ የነበሩ አለመግባባቶችን ለማስቆምና ወሰን ለማካለል መንግሥት የዛሬ 13 ዓመት አካባቢ ሕዝበ ውሳኔ ማካሄዱ ይታወቃል። በዚህ ሕዝበ ውሳኔ መሠረት ወሰኑን ማካለል ይገባ ነበር። ነገር ግን ይሄ ጉዳይ ለብዙ ዓመታት የዘገየ በመሆኑ በመጨረሻ መንግሥት በጥልቅ የተሃድሶ እንቅስቃሴ ወቅት እንደዚህ ዓይነት የተጓተቱ የሕዝብ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተገንዝቦ፤ የሁለቱን ክልሎች አመራሮች ከፌዴራል መንግሥት የሚመለከታቸው አካላት ጋር በከፍተኛ ሁኔታ ተንቀሳቅሰን የወሰኑን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ በርካታ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ተቀምጠው ሕዝቡን በማወያየት ወሰኑ ሊፈታ እንደሚችል፤ ችግሩንም በተወሰነው የሕዝበ ውሳኔው መሰረት ማስተካከል እንደሚቻል ግንዛቤ ተወስዶ ተሠርቷል።


ሕዝቡ ተወያይቶበት የወሰንን ጉዳይ ወደ ማጠቃለሉ ቀርቦ ነበር። ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮች ቢኖሩም በዋናነት የችግሩ መንስኤ የሆነው ግን አካባቢው የተለያዩ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችና ከፍተኛ የጫት ንግድ የሚካሄድበት ነው። ከእነዚህ ንግዶች ሕገወጥነት ጋር ተያይዞ ያልፈታናቸው ችግሮች ነበሩ።


እነዚህ ችግሮች አመርቅዘው፤ የሁለቱን ብሔረሰቦች አጋጭተው አለአግባብ የሚጠቀሙ ኃይሎች የተጠቀሙበት እንደሆነ አይተናል። ስለዚህ ይህንን መሠረታዊ ችግር መፍታት ተገቢ ይሆናል በሚል እምነት እየሠራን እንገኛለን።
በዚህ ሂደት በጣም አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ዜጎቻችን የሞቱበትና የተፈናቀሉበት ሁኔታ አለ። ይህን ችግር በወሳኝ መልኩ ለመፍታት መንግሥት የጀመራቸው ሥራዎች አሉ። የመጀመሪያው ጉዳይ ሠላሙንና ጸጥታውን ማረጋጋት ነው። አሁን አካባቢው በአብዛኛው የመረጋጋት፣ ሠላምና ጸጥታውን የመቆጣጠር ሁኔታ ተፈጽሟል። በዚህና በሌሎች በአገራችን ባሉ አጠቃላይ አካባቢዎች አሁን በደረስንበት ደረጃ አብዛኛው የተረጋጋና ሠላሙ የተረጋገጠበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል።


ይህም ሆኖ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት አስፈላጊ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት በቅርቡ ባደረገው ስብሰባ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል እቅድ አውጥቷል። በእቅዱ መሰረት ዋነኛ ተዋናይ የሆነውን ሕዝባችንን በሙሉ አቅም እንዲሳተፍ ማድረግ ነው። እስከአሁንም ድረስ ችግሩን ለመፍታት ዋነኛውን ሚና የተጫወተው ሠላም ወዳዱ ህዝባችን ነው። ስለዚህ ሠላም ወዳዱ ህዝባችን እንደተለመደው ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ተጨማሪ ትጋትና እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለበት አምነናል። በተከታታይ በተለያዩ አካባቢዎች በምናደርጋቸው የሕዝብ ውይይቶችና ኮንፈረንሶች ህዝቡ በንቃት እንዲሳተፍ ማድረግ የሚገባን ይሆናል።


ሁለተኛው የፖለቲካ አመራሩ ከላይ እስከታች በግጭቱ ውስጥ የተሳተፉ አካላትን ለመቆጣጠር በሚያስችል ደረጃ ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን የመስጠት ሥራ መሥራት ይገባዋል። በዚህም መሠረት በመላው አገራችን በሁሉም አካባቢዎች በተለይም ግጭቱ የተከሰተባቸውን አካባቢዎች ጨምሮ የተለያዩ የአመራር ኮንፈረንሶች እየተካሄዱ ያሉበት ሁኔታ አለ። ይህም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታተ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል።


ከዚያ ባሻገር ግን በሕዝቡና በፖለቲካ አመራሩ ሥራ ላይ የፌዴራልና የክልል ጸጥታ አካላት በተቀናጀ ሁኔታ በተለይም ደግሞ ያለአግባብ ለመጠቀም የሚሞክሩ ኃይሎች፥ ከፀረ ሰላምና ከአሸባሪ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት አለመረጋጋቱ እንዲቀጥል ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ መንግሥት ስለሚገነዘብ ይህንን ጉዳይ በዘላቂነት ለመቆጣጠር የሚያስችል የጸጥታና የሕግ ማስከበር ሥራ ማከናወን እንዳለበት ወስነን እቅድም አውጥተን ከዚህ ሳምንት ጀምሮ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

አብዛኛዎቹ አጥፊዎች በሕግ ቁጥጥር ሥር ስለማዋላቸው፣


በሕገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት በተለይም ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረጉ አብዛኛዎቹ በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርጓል። የቀሩትም በቀጣይ በምንሠራቸው ሥራዎች በቁጥጥር ስር የሚውሉ ይሆናሉ። ወደ ሕግም ቀርበው ተጠያቂ ይደረጋሉ። ከዚያም ባሻገር ጉዳዩ ዘላቂ መፍትሄ የሚጠይቅ በመሆኑ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የችግሩን ሥረ ነገር በማጥናት በሰብአዊ መብትም ሆነ በተለያዩ ጥሰቶች የተሳተፉ አካላትን እስከ አመራር አካላትም ጭምር ቢሆን አጣርተው እንዲያቀርቡ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ሥራ ጀምረዋል። በዚህ የማጣራት ሂደት በሚገኘው ውጤት ላይ ተመስርተን ቀጣይ እርምጃ የምንወስድ ይሆናል። የተጠያቂነቱ ጉዳይ በእነዚህና ሌሎች በምርመራ የሚሳተፉ የፌዴራል አካላት በሚያመጡት መረጃ ላይ ተመስርቶ በቀጣይነትም እርምጃው የሚቀጥል ይሆናል። የህግ ተጠያቂነቱ ጉዳይ በዚህ መሰረት የሚቀጥል ይሆናል።

 

በግጭቶቹ ስለተፈናቀሉ ዜጎች፣


በግጭቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ተፈናቅለዋል። አንዳንዶቹ በጊዜያዊ ጣቢያ ሆነው መንግሥት በሚሰጣቸው ድጋፍ እየታገዙ ነው። ነገር ግን በዘላቂነት ማቋቋም አስፈላጊ ነው። የህዝብ ውይይትና ኮንፈረንሶች በሚቀጥለው ሳምንት ውስጥ እንደጨረስን ዜጎቻችንን በቋሚነት እንዲቋቋሙ ለማድረግ መንግሥት በፌዴራል ደረጃ ግብረ ኃይል አቋቁሞ ከክልል መንግሥታት ጋር በቅንጅት እየሠራበት ያለበት ሁኔታ አለ። አቅም በፈቀደ መጠን ወደነበሩበት ሁኔታ ለመመለስ መንግሥት የተቻለውን ሁሉ የሚያደርግ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እፈልጋለሁ። ዜጎቻችን በዚህ ደረጃ ሲቋቋሙ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ህይወታቸው ወደነበረበት ሁኔታ እንዲመለስ ቅርብ ክትትል እያደረግን የምንሠራ ይሆናል። የዜጎች መፈናቀል ጉዳይ ወደፊትም እንዳይከሰት ማድረግ ይጠይቀናል። ስለዚህ ዘላቂ ሥራው በፖለቲካው መስክ የምናመጣው ለውጥ፥ በተለይም ደግሞ አለአግባብ የመጠቀም፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የሚወገድበትን ሁኔታ በጥናት መሥራት የሚጠበቅብን ይሆናል።


አገራችን ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአስቸጋሪው የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ሠላሟ ተረጋግጦ የራሷ ብቻ ሳይሆን የሌሎችን ሰላም በማስከበር ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገች አገር ናት። የዚህ ዋነኛው ምክንያት ህዝባችን ሰላም ወዳድ በመሆኑ በፀረ ድህነት ትግሉ በሙሉ አቅሙ ለመረባረብ የሚጓጓና የሚፈልግ ነው። ይህ ህዝብ እስካለ ድረስ መቼም ቢሆን የፌዴራል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ባጋጠሙን ተግዳሮቶች ሁሉ አይተናል። ዛሬም ቢሆን እንደዚህ ዓይነት ግጭቶች፣ አለመረጋጋቶች በሚኖሩበት ጊዜ የህዝባችን መሰረት ጽኑ በመሆኑ የፌዴራል ሥርዓታችንም በማይነቃነቅ መሰረት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ቢፈጠሩም አገራችንን ግን ወደከፋ ነገር ሊወስዷት እንደማይችሉ ህዝባችን በሚገባ ተገን ሆኖ የቆመ መሆኑን አረጋግጠናል። ወደፊትም የህዝቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግሥት፣ የፖለቲካ አመራሮች እንደዚሁም ከህዝቡ ጋር በጋራ የሚሠሩ የጸጥታ እና የደኅንነት ተቋማት፣ በጋራ በጽናት የምንሠራበት ይሆናል። ይሄ የተፈጠረው መረጋጋት የበለጠ እንዲጠናከርና ህዝቡም ወደ-ፀረ ድህነት ትግሉ እንዲመለስ እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የጀመርናቸውን ሥራዎች ከመንግሥት ጎን ሆኖ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ማድረግ የሚገባን ይሆናል። ህዝብ ተረጋግቶ ወደቀጣይ ሥራ እንዲገባ ጥሪዬን ለማስተላለፍ እፈልጋለሁ።

 

በኦህዴድና በሶህዴፓ እንዲሁም በኦህዴድ እና በኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች መካከል አለመግባባቶች አሉ?


ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ አባል ድርጅቶቹ ያደረጉት ኮንፍረንስን በማሳያነት በማቅረብ “የተለያየ ፓርቲ እንዴት በተለያየ ኮንፍረንስ ላይ ተመሳሳይ ሀሳብ ያንፀባርቃል?” በሚለው ጥያቄያቸው መልስ ሰጥተዋል።


እየታየ ያለው ችግር በፓርቲዎች መካከል ሳይሆን አመራሩ ላይ ነው፡፡ የትኛውም አካባቢ ያለ ህዝብ የእኔ ህዝብ ነው ብሎ ያለማሰብ የአቋም ችግር አለ። ይህም ችግር የሁሉም የኢህአዴግ አባል እና አጋር ድርጅቶች ችግር ነው ብለዋል፡፡


በኢህአዴግ ውስጥ ይፋ ስለማይደረግ እንጂ ቀድሞም የሀሳብ ትግል መኖሩን በመናገር፥ ሁሌም ግን ያሸነፈው ሀሳብ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል። ሆኖም መረጃን ከመስጠት አንፃር በመንግስት በኩል ያለው ድክመት ሕዝቡን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ለሚናፈስ አሉባልታና የሐሰት ፕሮፖጋንዳ እንዳጋለጠው አምነዋል። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
298 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 827 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us