የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ በዋና ኦዲተር ዓይን

Wednesday, 24 January 2018 14:29

 

· በሀይል መቆራረጥ ችግር ብቻ ሁለት ፋብሪካዎች ከ38 ሚሊየን ብር በላይ ከስረዋል
· በአንድ ዓመት 1 ሺ 029 ትራንስፎርመሮች ተቃጥለዋል፣
· ለዓመት የሚጠጋ ጊዜ ሀይል የማያገኙ አካባቢዎች አሉ፣

 

 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚታዩትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመፍታት የህዝቡን ጥያቄ የሚመልስና ቅሬታ እንዳይፈጠር የሚያደርግ ስራ መስራት እንደሚጠበቅበት በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ። ቋሚ ኮሚቴው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከ2006 እስከ 2008 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋነትንና ውጤታማትን ለመገምገም ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት ላይ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ አድርጓል።
በይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባው ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በአገልግሎቱ ላይ ባካሄደው ክዋኔ ኦዲት የተገኙ ግኝቶች በዝርዝር ቀርበው የአገልግሎቱ የስራ ሀላፊዎች ማብራሪያ እንዲሰጡባቸው መደረጉን ከሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያገኘነው ዘገባ ይጠቁማል።


በዚህም ኦዲቱ አዳዲስ የሀይል ፈላጊ ደንበኞች ክፍያ በፈፀሙበት ቀን ቅደም ተከተል ተራቸው ተጠብቆ የማይስተናገዱበት፣ የደንበኞችን ዝርዝር መረጃ በአግባቡ አደራጅቶ ባለመያዝ የደንበኞች አድራሻ የማይታወቅበት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ፕሮሲጀር መሠረት ለደንበኞች የቆጣሪ፣ የትራንስፎርመር ተከላ እና ማሻሻያ ቀልጣፋ አገልግሎት የማይሰጥበትና ለዓመታት የሚጠብቁበት ሁኔታ እንዳለ አሳይቷል።


እንዲሁም የቆጣሪ አንባቢዎችን በተጠናከረ መልኩ ለመቆጣጠርና ለመከታተል የተዘረጋ ሥርዓትና የአሰራር መመሪያ እንደሌለና የቆጣሪ አንባቢያንና የደንበኖች ብዛት እንደማይመጣጠን ያሳየ ሲሆን ለአብነትም በሰሜን ሪጅን ደንበኞች አገልግሎት ማዕከል አንድ ቆጣሪ አንባቢ እስከ 2 ሺ ቆጣሪ የሚያነብበትና በሰሜን አዲስ አበባ ሪጅን 6 የኢንዱስትሪ ደንበኞች ከ2004 ጀምሮ የቆጣሪ ንባብ ባለመነበቡ ብር 53 ብቻ ለቆጣሪ ግብር ቢል እየወጣ ያለበት ሁኔታ እንዳለ ጠቅሷል።


በተጨማሪም ከተለያዩ መንግስታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች ደንበኞች ከ10 ዓመት በፊት ጀምሮ ያልተከፈለና ሲንከባለል የመጣ 133 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር መኖሩና 97 የተለያዩ የአገልግሎቱ ደንበኞች ከ1999 - 2008 በጀት ዓመት ለተጠቀሙበት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ወደ 81 ሚሊዮን ብር ለመክፈል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው በተቋሙ ምንም ዓይነት እርምጃ ያልተወሰደባቸው መሆኑ እንዲሁም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያን የመሰብሰብ አገልግሎት በሚሰጠው በለሁሉ የክፍያ ማዕከል ክፍያ የከፈሉ ደንበኞች፤ አልከፈላችሁም በሚል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማቋረጥ ከሚሠሩ ባለሙያዎች ጋር ውዝግብ የሚገቡበት ሁኔታ መኖሩ እና ሀይል ያገኙ አዲስ ደንበኞች በ2 ወራት ውስጥ ወደ ክፍያ ስርዓት የማይገቡበት ሁኔታ መኖሩ በኦዲቱ ተመልክቷል።


ያልተፈቀደ የሀይል አጠቃቀምን ወይም ብክነትን ያለመቆጣጠር እና ለመቆጣጠር የተሰራው ስራ ሽፋንም አነስተኛ መሆኑ፣ የተቋሙ የሀይል ብክነት ቁጥጥር ሥራ ስለመሰራቱ የሚያሳይ መረጃ ማቅረብ ያልተቻለና የሀይል ስርቆትና የትርፍ ሀይል ጭነት ኢንስፔክሽን አፈፃፀም ሪፖርት ግልፅነት የጎደለው መሆኑ፣ የደንበኞችን ቅሬታ በመቀበል ረገድ በአገልግሎት መስጫ ተቋማት የቅሬታ መቀበያ ፎርም ከማዕከል ማዕከል የሚለያይ መሆኑ፣ ማዕከላቱ የቀረበን ቅሬታ ስለመፍታታቸው መረጃ በሌለበት ሁኔታ በየወሩ የተፈታ ቅሬታ ሪፖርት ለሪጅኖች የሚላክበትና የተፈቱ ቅሬታዎችን ብዛት በትክክል የማይገልጹ ሪፖርቶች የሚወጡበት ሁኔታ መታየቱ በኦዲት ግኝትነት ተጠቅሰዋል።


ከዚህም ሌላ ኦዲቱ በሀይል ማሰራጫ መስመር መበጠስ የአገልግሎት መቋረጥ ሲኖር በአሰራር በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ከመጋቢ መስመሮች አገልግሎት እንዲቀጥል ለማድረግና ያለ ፕሮግራም የሀይል መቆራረጥ ካለና ከ 4 ሰዓት በላይ የሚቆይ ከሆነ በሬዲዮና በቴሌቭዥን መግለጽ ሲገባው የማይገለጽበት፣ ጥገናውም በወቅቱ የማይደረግበት፣ የአስቸኳይ ጊዜ ጥገና ክፍል ስልኮች በሰራተኞች የማይነሱበት፣ ከአስቸኳይ ጊዜ ጥሪ ማዕከል ከአስቸኳይ ጊዜ ጥገና ክፍል የሚገናኙበት የመረጃ ማስተላለፊያ ስርዓት ፈጣንና ቀልጣፋ ያልሆነበት፣ ፈጣን ምላሽ ባለመሰጠቱም ለአብነት በምርት ወቅት ሀይል በመቋረጡ የድሬዳዋ የምግብ ኮምፕሌክስ ከ36 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ፣ የድሬደዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ደግሞ ከ2 ነጥብ 2 ሚልዮን ብር በላይ ለኪሳራ የተዳረጉበት ሁኔታ እንዳለ አሳይቷል።


የማስፋፊያ መስመሮችና ትራንስፎርመሮች ላይ የአገልግሎት ዘመናቸውን ጠብቆ የማሻሻያ ስራ እንደማይሰራና የማከፋፈያ ጣቢያዎች ከደንበኞች ፍላጎት ጋር በተናበበ ሁኔታ አስቀድመው እንዲሻሻሉ እንደማይደረጉ፣ በአገልግሎቱ ካሉት ትራንስፎርመሮች ውስጥ 40 በመቶ ያህሉ የአደጋ መከላከያ መሳሪያዎች (አሬስተርና ድሮፕ አውት ፊውዝ) የሌላቸው በመሆኑ በ2007 በጀት ዓመት 1 ሺ 029 ትራንስፎርመሮች በጭነት ምክንያት መቃጠላቸውን ኦዲቱ አሳይቷል። እንደዚሁም መስመሮች የአገልግሎት ዘመናቸው ተጠብቆ ባለመታደሳቸው፣ በትራንስፎርመር ብልሽትና የኤሌክትሪክ ገመድ ተሸካሚ የእንጨት ምሰሶዎች በአፈር ፀባይና በምስጥ በመበላት በመውደቃቸው በተለያዩ አካባቢዎች በመብራት መቆራረጥ የሚቸገሩበት፣ መብራት ለአመት ያህል የማያገኙበትና ከፍተኛ የሀይል ተጠቃሚ ደንበኞችም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ለጀነሬተር ወጪ የሚያወጡበት ሁኔታ መኖሩም ማስረጃዎችን ለአብነት በማቅረብ ኦዲቱ አመልክቷል።


አገልግሎቱ ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከክልል መስተዳድሮች፣ ከኢትዮጵያ መንገድ ባለሥልጣን እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር ስራዎች በሚሰሩበት ወቅት ለመደጋገፍ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ የሚሰራበት ሁኔታ ያልተፈጠረ መሆኑ እንዲሁም የውስጥ ኦዲት የሥራ ክፍል በተለያዩ ማዕከላትና ሪጅኖች ላይ ከ2006 እስከ 2008 ዓ.ም ያገኛቸው የኦዲት ግኝቶች ላይ በሚሰጠው የማሻሻያ ሀሳብ መሠረት ወቅታዊና አስተማሪ እርምጃዎችን ወይም እርምቶችን የማይወሰድ መሆኑም በኦዲቱ ተገልጿል።


በአጠቃላይ እነዚህ ችግሮች ደንበኞችን ለአገልግሎትና ለመልካም አስተዳደር እጦት እንዲሁም ተቋሙን ለኪራይ ሰብሳቢነት የሚዳርጉ በመሆናቸው የተከሰቱበትን ምክንያትና በችግሮቹ ላይ ከኦዲቱ በኋላ የተወሰዱ የማሻሻያ ስራዎችን የአገልግሎቱ ኃላፊዎች እንዲገልጹ ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጎሳዬ መንግስቱና ሌሎች የአገልግሎቱ የስራ ኃላፊዎች በጉዳዮቹ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።


ለአዲስ ሀይል ፈላጊ ደንበኞች ቅደም ተከተልን የጠበቀ አገልግሎት አለመስጠትን በተመለከተ በናሙና በታየው ዲስትሪክት ላይ ደንበኞችን ካለወረፋ ባስተናገደ የስራ ኃላፊ ላይ እርምጃ እንደተወሰደ፣ ደንበኖችን በቅደም ተከተል ማስተናገድ በአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያው ላይ እንዲካተት እንደተደረገ፣ ከ140 ሺ በላይ ወረፋ ከሚጠብቁ ተገልጋዮችን ወደ 25ሺ ያህል መቀነስ እንደተቻለና ለነዚህ ምላሽ ከተሰጠ በኋላ በቀጣይ ደንበኛው በመጣበት ቅደም ተከተል መሰረት እንደሚስተናገድ ከዚህ ውጭ ግን ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ኤክስፖርት ኢንዱስትሪዎችና ማህበራዊ አገልግሎቶች አሁንም ካለወረፋ እየተሰጠ ያለው አገልግሎት በዚሁ አግባብ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።


በደንበኞች መረጃ አያያዝ በኩልም የመረጃ ማደራጀት ስራ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።


ከቆጣሪ አንባቢዎች ጋር በተያያዘ የቆጣሪ አንባቢዎች ላይ የሚታይ የአመለካከት ችግር እንዳለ፣ ስህተት ሲፈጽሙ እርምጃ የሚወሰድበት ሁኔታ እንደነበረ፣ ከኦዲቱ በኋላም መተዳደሪያ ደንብ እንደተዘጋጀላቸው፣ አንድ ቆጣሪ አንባቢ 2 ሺ 200 ደንበኛ በወር መሸፈን የሚጠበቅበት ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ከዚያም በላይ የሚሸፍኑበት ሁኔታ እንዳለና ይህንን ለማካካስም የማትጊያ ስርአት እንደተበጀ ከዚህ ሌላም ተጨማሪ ቆጣሪ አንባቢዎች እንደተቀጠሩ አስረድተው ዋነኛው የችግሩ መፍትሄ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎችን መጠቀም በመሆኑ ይህንን ለማከናወን እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። ከዚህም ሌላ ለቆጣሪ ግብር 53 ብር ብቻ ይከፍሉ የነበሩት የኢንደስትሪ ደንበኞች ጉዳይ መስተካከሉን አስረድተዋል።


ያልተሰበሰበ የአገልግሎት ክፍያን በተመለከተ አፈጻጸምን በማሻሻል ከኦዲቱ በኋላ ውዝፍ ተሰብሳቢ የአገልግሎት ሂሳቦችን ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከባቡር ፕሮጀክትና ሌሎች አካላት የመሰብሰብ ስራ መሰራቱንና በቀጣይም እንደሚሰራ አስረድተዋል። ከለሁሉ የክፍያ ማእከል ጋር በተያያዘም ችግሩ የተፈጠረው ከተገልጋዮች የአገልግሎት ክፍያ መክፈያ ጊዜ ውጪ ክፍያ ማእከሉ የሚቀበል በመሆኑና ይህ መረጃ ለአገልግሎቱ ባለሙያዎች በወቅቱ ባለመድረሱ መሆኑን በመግለጽ ችግሩ እንደተስተካከለ አስረድተዋል።


ወደ ክፍያ ያልገቡ ደንበኞችን በተመለከተም ክፍያን መክፈል ያልጀመሩ ደንበኞችን የማጣራት ስራ በኮሚቴ እየተሰራ እንዳለ ተናግረዋል።


ከሀይል ስርቆትና ብክነት ጋር በተያያዘም የተወሰነው ብክነት በቴክኒካል ችግሮች እንደሚከሰትና የተቀረው ግን በህገወጦች የሚፈጸም መሆኑን ጠቅሰው ህገወጥ ተጠቃሚዎችን ለማጣራት አጣሪ ቡድን ተቋቁሞ እንደተሰራ፣ ስለተሰራውም ስራ ሪፖርት ባለማድረግ ችግር እንጂ የተሟላ መረጃ እንዳለና ደንበኞች ከየትኛው ትራንስፎርመር እንደሚጠቀሙ የሚታወቅበት ከስተመር ኢንዴክስ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ገልጸው በዋናነት ግን መፍትሄው ዘመናዊ ቆጣሪዎችን መጠቀም እንደሆነ አስረድተዋል። በቴክኒካል ችግር የሚመጣውን ብክነት ለመቀነስ ግን የኔትዎርክ ማሻሻያ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግና ለዚህም ጥናት እየተካሄደ እንዳለ አስረድተዋል።


የቅሬታ አቀባበል ስርአቱ ወጥነት ባይኖረውም ቅሬታዎችን ለመፍታት የሚደረግ ጥረት እንዳለና ይበልጥ ችግሮችን ለመፍታት የመረጃ አያያዝ ስርአቱን የማጠናከር ስራ እየተሰራ አንደሆነ የስራ ኃፊዎቹ አስረድተዋል።


የጥገናና የመረጃ መስጫ የስልክ መስመሮች ላይ ያለውን ችግር በመቀበል ባንድ ጊዜ እስከ ሃምሳ ጥሪ ተቀብሎ ማስተላለፍ የሚያስችል 24 ሰዓት የሚሰራ ዘመናዊ ስርአት እንደተዘረጋ፣ ከዚህ ሌላ በክልሎችም በዋና ዋና ከተሞች 24 ሰዓት በዞኖች ደግሞ እስከ ምሽቱ 5 ሰዓት የሚሰሩ የጥገና ማእከሎች አሰራር እንደሚኖር ተናግረዋል። የሀይል መቋረጥን በተመለከተም በተቻለ አቅም በተለያዩ ሚድያዎች ፌስቡክንና ቲዊተርን ጨምሮ መረጃው እንደሚሰራጭና መረጃው በትክክል ህብረተሰቡ ጋር መድረሱን ማረጋገጥ ግን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።


የተቃጠሉ ትራንስፎርመሮችን በተለመከተም ትራንስፎርመሮቹ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ሲጠራቀሙ የመጡ ጉዳት የደረሰባቸውና ያልተጠገኑ እንደሆኑ፣ ለትራንስፎርመሮቹ የመብረቅ መከላከያ ከውጭ ሀገር ተገዝቶ የሚመጣ በመሆኑ በፋይናንስ ችግር ምክንያት ባለመገዛቱ ካለመብረቅ መከላከያ እንደተተከሉና አሁንም ለመግዛት በሂደት ላይ እንዳለ ገልጸው የውጭ ምንዛሪና የፋይናንስ ችግሩ እንዲፈታ እንዲሁም የአገልግሎት ታሪፍ ማሻሻያ እንዲደረግ በመንግስት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። በተለያዩ አካባቢዎች ከሀይል እጦትና መቆራረጥ ጋር በተያያዘም በኦዲቱ የተጠቀሱት ችግሮች እንዳሉና ሁኔታውን ለመቀየር የማሻሻያ (የሪሀብቴሽን) ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።


ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ከመስራት አኳያ ከቴሌኮም፣ ከውሃ፣ ከመሬት፣ ከጸጥታ አካላት ወዘተ. ባጠቃላይም ከ 7 ተቋማት ጋር ስምምነት መፈረሙንና ችግሩ ግን ሁሉም ተቋም በጀት ሲኖረው ወደ ስራ ስለሚገባ ስራዎችን በጋራ አንድ ላይ አቀናጅቶ አለመፈጸም መሆኑን አስረድተዋል።


በአጠቃላይ በአገልግሎቱ ላይ የሚታዩት ችግሮች ከአሰራር፣ ከአመለካከት፣ ከአደረጃጀት፣ ከግብአት፣ ከሰው ሀይል እጥረት ወዘተ. ጋር የተገናኙ መሆኑንና እነዚህን ችግሮቸ ለመፍታት ኦዲቱን መሰረት በማድረግ የድርጊት መርሀግብር ተዘጋጅቶ የተሻለ ሽፋንና ጥራት ያለው ቀልጣፋና መልካም አስተዳደርን ያረጋገጠ አገልግሎት ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።


የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ፍሬህይወት ውሃና የኤሌክትሪክ ሀይል ሽፋንን በማሳደግ አብዛኛውን ህብረተሰበ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንዳለ፣ የአገልግሎቱን አደረጃጀት ያልተማከለ ለማድረግ ጥረት መጀመሩንና በአተገባበሩ ላይ ከክልሎች ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝ፣ በየክልሉ ያሉ የኤሌክትሪክ ባለሙያዎች እየተደራጁ የጥገና ስራዎችን ለአገልግሎቱ በክፍያ እንዲሰሩ ለማድረግ እንደታቀደ እንዲሁም ዘመናዊ ቆጣሪዎችን ስራ ላይ ለማዋል እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ከዚሁ ጋር አያይዘው በመንግስት ለዘርፉ በቂ በጀት ካለመመደቡ፣ ከግዥ ስርአቱ ጋር ተያይዞ ጥራት ያላቸው ግብአቶችን መግዛት ካለመቻሉ፣ እየተሰራበት ያለው የአገልግሎት ታሪፍ ከ12 አመታት በላይ ሳይሻሻል ከመቆየቱ እንዲሁም ከሰው ሀይል ፍልሰት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዳሉ ገልጸው ምክር ቤቱና ቋሚ ኮሚቴዎቹ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።


የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በአገልግሎቱ እንደተወሰዱ የተገለጹት እርምጃዎች ጥሩ መሆናቸውንና በርግጥም እርምጃዎቹ ስለመወሰዳቸው በክትትል ኦዲት እንደሚረጋገጥ ጠቅሰው ተቋሙ አገልግሎት አሰጣጡ ውጤታማ እንዳይሆን ያደረጉትን ውስጣዊ ጉዳዮች፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያሉ ግንኙነቶች እንዲሁም ከመንግስት ድጋፍ ጋር ያሉ ችግሮችን ለይቶ ማየት እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል።


ኦዲቱ በናሙና ላይ ተመስርቶ የተደረገ በመሆኑ ሁሉምን የአገልግሎት መስጫ ሪጅኖችን አሰራር መፈተሽ እንደሚያስፈልግ፣ በፋይናንስ በኩልም እየተሰበሰበ ያለውን ገቢ አሁን ካለበት 80 በመቶ ወደ 100 በመቶ ማድረስ እንደሚገባ፣ የወጪ ቁጠባ ስትራቴጂ መቀየስ እንደሚያሻ፣ አሁንም ያሉ አገልግሎት ክፍያ ያልከፈሉ ተቋማትን ሒሳብ ከመሰረዝ ይልቅ እንዲከፍሉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ወደ ህግ የሚሄዱትንም መረጃቸውን በደንብ አደራጅቶ ከጠቅላይ አቃቢ ህግ ጋር በመሆን ማስፈጸም እንደሚጠበቅበትም ክቡር ዋና ኦዲተሩ ገልጻዋል።


ከዚህ በተጨማሪም ከደንበኞች ጥሪ መቀበያ ስልኮች አገልግሎት ጋር በተያያዘ አሁን ያለው ሁኔታ ህዝቡን ቅሬታ ውስጥ የሚጥል በመሆኑ ማሻሻል እንደሚያስፈልግ፣ የመብረቅ መከላከያ የሌላቸው 40% ትራንስፎርመሮች መኖር የሚያመጣውን ችግር በደንብ አይቶ ከአገልግሎት ማስፋፊያው ጎን ለጎን መፍትሄ እየሰጡ መሄድ እንደሚያስፈልግ፣ የሀይል ስርቆት ላይ የሚሰራውን ቁጥጥር ማጠናከር እንደሚገባ፣ አሁን እየባከነ ያለው የኤሌክትሪክ ሀይል ከፍተኛ በመሆኑ የሀይል ብክነት የሚፈጠርባቸውን ሁኔታዎች ለመቀነስ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንደሚያሻ አስገንዝበዋል።


የቋሚ ኮሚቴው አባላትና የተፈጥሮ ሀብት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በአገልግሎቱ አሰጣጥ ላይ ኦዲቱ ባሳያቸው እንዲሁም ህብረተሰቡ በከተሞችም ሆነ በገጠር አካባቢዎች እየተቸገረባቸው ባሉ ጉዳዮች ላይ ድጋሚ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አቅርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።


በወቅቱ በተሰጠው አስተያየት ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያ የመብራት መቆራረጥና የመጥፋት ችግር የሚታይበት፣ ለደንበኞች የተዘበራረቀ የአገልግሎት ክፍያ ጥያቄ የሚቀርብበት፣ ደሀው ህብረተሰብም ከፍተኛ ክፍያ እንዲከፍል የሚጠየቅበት፣ በክልል ያሉ የአገልግሎቱ ወኪሎች በጥቅም እየሰሩ ህዝቡን የሚበድሉበት፣ የኤሌክትሪክ መስመር ተዘርግቶ የአካባቢው ህብረተሰብ ግን ለአመታት የኤሌክትሪክ ሀይል የማያገኝበት፣ አገልግሎቱ መንግስትና ህዝብን እያጣላ ያለበት ሁኔታ እንዳለ ተገልጿል።


እንደዚሁም በገጠር ያሉ እንደ ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ ያሉ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በሀይል እጦት በተገቢው ሁኔታ የማይሰሩበት፣ የመንገድ መብራቶች የማይሰሩበት፣ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች በማሳ ላይ እየወደቁ አደጋ የሚያደርሱበት፣ ባልተመጣጠነ ኤሌክትሪክ ሀይል የተነሳ የግለሰቦችና የመንግስት ንብረቶች የሚቃጠሉበት፣ ህብረተሰቡና ከአነስተኛ ንግድ እስከ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ያሉ የሀይል ተጠቃሚዎች የሀይል መቋረጥን የተመለከተ መረጃ ባለማግኘት ስራ የሚፈቱበት ብሎም በሚልዮኖች የሚቆጠር ሀብት የሚከስሩበትና ለጄኔሬተርና ለነዳጅ ከፍተኛ ሀብት ለማፍሰስ የሚገደዱበት ሁኔታ እንዳለ እንዲሁም በአገልግሎቱ ሰራተኞች ላይ ያለውን የአመለካከት ችግር ከመፍታት ይልቅ በወረዳ ለመብራት ጥገና ተሽከርካሪ እጥረት አለ የሚል አሳማኝ ያልሆነ ምክንያት በመስጠት ወቅታዊ ጥገና የማይደረግበት ሁኔታ እንደሚታይ ተነስቷል።


ባጠቃላይም አገልግሎት አሰጣጡ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር ያለበትና ተቋሙ እውን በመንግስት እየተመራ ነው የሚል ጥያቄ በህዝቡ እንዲነሳ ያደረገ አሰራር ያለበት ተቋም እንደሆነ አስተያየት ተሰጥቷል።


የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ት ወይንሸት ገለሶ በማጠቃለያ አስተያየታቸው አገልግሎቱ ችግሮችን በመለየት ለመፍታትና አሰራርንና አደረጃጀትን በማስተካከል ላይ ትኩረት መስጠቱ በጥንካሬ እንደሚታይ ገልጸዋል።


በሌላ በኩል ግን በመድረክ የተነሱ ጥያቄዎች እስከታች ድረስ ባለው ህብረተሰብ የሚነሱ ጥያቄዎች እንደሆኑና ህብረተሰቡ አገልግሎቱ እኛንና መንግስትን እያጣላን ነው እንዲል ያደረገው በየአካባቢው ያሉ የአገልግሎቱ ተቋማት ለህዝቡ መረጃን በአግባቡ ባለማድረሳቸው፣ ፈጣን አገልግሎትና ምላሽ ባለመስጠታቸው የተነሳ እንደሆነ ገልጸው ለህዝብ ጥያቄ ቀልጣፋ ምላሽ የሚሰጥ ህብረተሰቡ በተቋሙ ላይ እምነት እንዲያሳድር የሚያደርግ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሰራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።


በተጨማሪም ወ/ት ወይንሸት የኤሌክትሪክ ሀይል ሽፋኑን ወደ 70 በመቶ ማድረስ ከመታቀዱ ጋር በተያያዘ ይህንን ለማስፈጸም የሚያስችል የረጅም ጊዜ እቅድን ከወዲሁ ማሰብ እንደሚያስፈልግ፣ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ያሉ የአሰራር ችግሮችን መፍታትና ቅንጅታዊ ስራን የጋራ አቅም አድርጎ መስራት እንደሚገባ፣ ከክልል በየደረጃው ካለው አመራር ጋርም በቅርበት መስራት እንደሚያሻ፣ የተቋሙንና የሰራተኛውን አቅም መገንባት በተለይም በአመለካከት የተገነባ ወጥ አመለካከት ያለው ህብረተሰቡን ማገልገል የሚችል የሰራዊት ግንባታ ላይ መስራት እንደሚገባ፣ የአገልግሎቱ የውስጥ ኦዲት የሚሰጣቸውን አስተያቶች በመውሰድ ቀድሞ መተግበር እንደሚያስፈልግ፣ የውስጥ ኦዲቱን በአቅምና በሰው ኃይል ማጠናከር እንደሚያስፈልግ፣ ተቋሙ አገልግሎቱን በአግባቡ መስጠት ካልቻለ ተጠያቂነት እንደሚኖር አስቦ መስራት እንዳለበት በአጠቃላይም በምክር ቤቱ አባላት እና በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተነሱ ጉዳዮችን ወስዶ የህዝቡን ጥያቄ የሚመልስና ቅሬታ እንዳይፈጠር የሚያደርግ ስራ መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል። 

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
228 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 802 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us