በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የባለሃብቱ ተሳትፎ ሲቃኝ

Wednesday, 31 January 2018 13:01

 

በዳግማዊ.ሕ

ኢትዮጵያውያን ከአመት ልብሳቸውና ከዕለት ጉርሳቸው ቀንሰው የዘመናት ህልምና ቁጭታቸውን እውን ለማድረግ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የአቅማቸውን ሁሉ ድጋፍ አድርገዋል፤እያደረጉም ነው።


ከነዚህ ኢትዮጵውያን መካከል ሃና ጀባን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። ትውልድና እድገቷ በደቡብ ብሄር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጋሞ ጎፋ ዞን ነው። እንደ ሌሎች ሁሉ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለመደገፍና አሻራዋን ለማኖር ምኞቷ ነበር። ሆኖም ይህን እውን ለማድረግ እጅ አጠራት። ግን አንድ ነገር ማድረግ እንደምትችል ደግሞ እርግጠኛ ነበረች። ደሟን በጨረታ በመሸጥ የህዳሴ ግድብ ቦንድ መግዛት።ብዙዎችን ያስደመመ ሀሳብ ነበር። በሃና ተግባር ስሜቱ የተነካው የአካባቢው ነዋሪ በከበረ ደሟ ምትክ ያለውን ለግሷት ቦንድ እንደትገዛና ምኞቷ እውን እንዲሆን አድርጓል።


ልክ እንደ ሀና ሁሉ ከሰል ሸጠው ቦንድ የገዙ እናት፣ ያላትን አንዲት ዶሮ ሸጣ ቦንድ የገዛች ታዳጊ፣ ከዕለት ቀለባቸው ቀንሰው ድጋፍ የሰጡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሁሉም በህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ አሻራቸውን በማኖር ታላቅ ገድል ፈጽመዋል።


የህዳሴው ግድብ እንከን እንዳይገጥመው ከአየርና ከምድር ደህንነቱን ለማረጋገጥ ለሴኮንድ አይኑን ሳይነቅል አስተማማኝ ጥበቃ በማድረግ ላይ የሚገኘው የሀገር መከላከያ ሃይል እስካሁን ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ቦንድ በመግዛት አጋርነቱን አሳይቷል። በተመሳሳይ የፌዴራል ፖሊስ አባላትም እንዲሁ ለሰባተኛ ጊዜ ቦንድ ገዝተዋል።


ለነገሩ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ እንኳን ገንዘባቸውን ህይወታቸውን ለመስጠት ወደኋላ እንደማይሉ የአደባባይ እውነታ ነው።


ለታላቁ የህዳሴ ግድብ በተለይም መካከለኛና አነስተኛ ገቢ ባለው የህብረተሰብ ክፍል በኩል የሚደረገው ድጋፍ ከፍተኛ ቢሆንም በአንጻሩ አንዳንድ ባለሃብቶች ድጋፋቸውን ከመስጠት መቆጠባቸው አሊያም በአደባባይ በህዝብ ፊት የገቡትን ቃል ከመፈጸም ማፈግፈጋቸው ግን የሚያሳዝን ጉዳይ ነው።


ሀገራችን የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲን መከተል ከጀመረች ወዲህ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ተጠቅመው በርካታ የግል ባለሀብቶች ተፈጥረዋል፤ሚሊየነርና ቢሊየነር በመሆን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ተደማሪ አቅም ፈጥረዋል።


በዚሁ ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ወደ ሃብት ማማ የወጡ ባለሃብቶቹም ቢሆኑ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ /ባለፉት ስድስት ዓመታት/ እስካሁን 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በቦንድና በስጦታ ድጋፍ አድርገዋል።


ባለሃብቶቹ ቃል ከገቡት 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር አኳያ ሲታይ አፈጻጸሙ 46 በመቶ ብቻ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ቃላቸውን ጠብቀው ለግድቡ ድጋፋቸውን ያበረከቱ የመኖራቸውን ያህል ቃላቸውን ያላከበሩ እና ምንም ዓይነት ድጋፍ ያላደረጉ በርካታ ባለሀብቶች መኖራቸውን ለመታዘብ ይቻላል።


ቃላቸውን ጠብቀው ህዝብና መንግስት የሚጠብቅባቸውን ግዴታ የተወጡት ግድቡን መደገፍ ሀገራዊ ግዴታችን በመሆኑ በህዝብ ፊት የገባነውን ቃል መፈጸም ይገባናል ሲሉ በግልጽ ቋንቋ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።


ቃላቸውን ከተግባር ካዋደዱት ባለሃብቶች መካከል በወጪ ንግድ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ በላይነህ ክንዴ አንዱ ናቸው። ግድቡ በራስ አቅም የሚገነባ መሆኑ ከተገለፀ በኋላ 27 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ቦንድ ገዝተዋል። አቶ በላይነህ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ኩራት፤ በራስ የመተማመን ስሜትን የሚያሳድግና ቀና ብለን እንድንሄድ የሚያደርግ ፕሮጀክት መሆኑን ይገልፃሉ።
‹‹ኢትዮጵያዊ ነኝ ለማለት፤ ኢትዮጵያን ወደ አንድ ከፍ ያለ ደረጃ የሚያደርሳትን ግድብ መደገፍ ይገባል። የህዳሴ ግድብ ጉዳይ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ ብሎም የሞራል ጉዳይ ነው።›› ነበር ያሉት አቶ በላይነህ።


አነስተኛ ገቢ ካለው የህብረተሰብ ክፍል እስከ ባለሀብቱ ድረስ ለግድቡ ድጋፉን ሲገልፅ መቆየቱን ነገር ግን ፕሮጀክቱ በቀጣይ የሚያመነጨውን የኤሌክትሪክ ሀይል ከመጠቀም አንፃር ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ባለሀብቱ እንደሆነ ነው አቶ በላይነህ የሚናገሩት።


‹‹ግድቡ ችግር ፈቺ እና ከድህነት ለመውጣት በምናደርገው ጥረት ሊያግዝ የሚችል ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው።›› የሚሉት ደግሞ የናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ጥላሁን ናቸው። ግድቡን ለመገንባት የሚያስፈልገው ወጪ የሚሸፈነውም ሆነ ግድቡ የሚገነባው በኢትዮጵያውያን መሆኑን በታላቁ መሪ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አንደበት በተነገረ ማግስት የናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ /ኖክ/ ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ያሉ ሌሎች ኩባንያዎችንም የማስተባበር ስራ መስራታቸውን ይናገራሉ።


‹‹ ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ መስጠት ሀገራዊ ሃላፊነት በመሆኑ ቃላችንን ጠብቀናል።›› ያሉት አቶ ታደሰ ሠራተኞቻቸውን በመሰብሰብ በአንድ ወር ደመወዛቸው ቦንድ እንዲገዙ ያደረጉ ሲሆን ድርጅቱ ደግሞ 15 ሚሊዮን ብር ሰጥቷል። በድጋሚም በሁለተኛ ዙር ድርጅቱ 15 ሚሊዮን ብር ቦንድ ሲገዛ ሠራተኞቹም በተመሳሳይ የወር ደመወዛቸውን በማዋጣት ቦንድ ገዝተዋል። በአጠቃላይ የናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ ኩባንያ ከ38 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዢ በመፈፀም ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ አድርገዋል።


ሀገራችን ከድህነት እንድትወጣ ማገዝ የውዴታ ግዴታ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ታደሰ የኤሌክትሪክ ሀይል ማለት ለሁሉም ዘርፎች በአጠቃላይ ለዕድገታችን መሠረት መሆኑንና ከችግራችን ለመውጣት በምናደርገው ጥረት የግድቡ መገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የተናገሩት።


በአንድ በኩል የገቡትን ቃል አክብረው ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ እያደረጉ ያሉ ባለሀብቶች የመኖራቸውን ያህል የገቡትን ቃል ያልፈፀሙ ወይም ጉትጎታ የሚፈልጉ ባለሀብቶች መኖራቸው ደግሞ ሌላው እውነታ ነው። ይህንን በተመለከተ አቶ ታደሰ ሲናገሩ ‹‹እኛ ባለሀብቶች የግድቡን ግንባታ ለመደገፍ ቃል ገብተናል። በመሆኑም የምንችለውን ማድረግ አለብን።ባለሀብቱ ሰፋፊ የልማት ፕሮጀክቶች በጊዜ እንዲጠናቀቁ የመደገፍ ሀላፊነት አለበት። ፕሮጀክቱ በራስ አቅም የሚገነባ መሆኑን መንግስት አሳውቋል። በመሆኑም ባለሀብቱ ግድቡን በገንዘብ በመደገፍ ረገድ ግንባር ቀደም ሊሆን ይገባል›› ብለዋል።


ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የቤልት ጀነራል ቢዝነስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኢንጅነር ትኳቦ ወልደ ገብርኤል እስካሁን የ5 ሚሊዮን ብር ቦንድ የገዙና የ3 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ቦንድ ለመግዛት ቃል የገቡ ናቸው።


ኢንጅነር ትካቦ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ ደግሞ የመንግስት ሠራተኛው እያደረገ ካለው ከፍተኛ ድጋፍ አንፃር ሲታይ ባለሀብቱ የሚጠበቅበትን ያህል እየተወጣ አለመሆኑን ይናገራሉ።
የህዳሴ ግድብን ግንባታ የመደገፍ ጉዳይ የውዴታ ግዴታ እንደሆነና ግድቡ ምንም እንኳን የኢትዮጵያውያንን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ፕሮጀክት ቢሆንም በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶች ዋነኞቹ ተጠቃሚዎች በመሆናቸው ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉት ድጋፍ ከሌላው ኢትዮጵያዊ በተለየ መልኩ መጠናከር እንደሚኖርበት ያምናሉ።


‹‹የተናገሩት ከሚጠፋ…›› የሚለውን የአበው አባባል ማስታወስ ተገቢ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩት አቶ በላይነህ ማንኛውም ሰው ከተናገረው በላይ እንጂ ከተናገረው በታች መስራት እንደሌለበትም ነው የገለፁት።


መንግስት የፈጠራቸውን የቀረጥ ነፃ መብቶች፣ የሊዝ መሬት፣ የግብር እፎይታ …..ወዘተ የመሳሰሉ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን በመጠቀም ሃብት ያከማቹ ባለሀብቶች እንዲህ ባለው ህዝባዊና አገራዊ ፕሮጀክት ላይ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸው በእጅጉ የሚያስቆጭ ነው።


የህዳሴ ግድብ ‹ስለ ሀገሬ ያገባኛል፤ የሀገሬ ስም ከድህነትና ልመና ጋር ተያይዞ ሲነሳ ያንገበግበኛል› የሚል ማንኛውም ዜጋ ሊደግፈው የሚገባ ፕሮጀክት ሆኖ ሳለ ዳር ቆሞ መመልከት ባስ ሲልም በአደባባይ የገቡትን ቃል መና ማስቀረት እንደ ዜጋ የአገር እና ህዝብ የሚጠበቁትን የዜግነት ግዴታን አለመወጣት መሆኑን ግንዛቤ መያዝ ይገባል። ለመሆኑ በራስ አቅም የሚገነባን ታሪካዊ ፕሮጀክት መደገፍ የዜግነት ግዴታችን አይደለምን? ‹‹መደገፍም አለመደገፍም መብቴ ነው።›› ማለትስ ይቻል ይሆን?


አቶ በላይነህ ክንዴ ‹‹የግድቡን ግንባታ በገንዘብ አለመደገፍ ማለት ኢትዮጵያን ሀገሬ አይደለችም እንደማለት ነው።›› ይላሉ። አቶ ታደሰ ጥላሁንም ቢሆኑ ሳይማር ያስተማረንን እና እስካሁን በድህነት ውስጥ የሚኖረውን ህዝባችንን ህይወት የማሻሻል ጉዳይ በመሆኑ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን መደገፍ የውዴታ ግዴታ ነው ብለዋል።


ይሁንና ለግድቡ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ባለሀብቱን የማስተባበር ስራ ከማጠናከር ጎን ለጎን ባለሃብቶቹ ፕሮጀክቱን ሄደው እንዲጎበኙ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና የተለያዩ የውይይት መድረኮችንም ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑንም ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የተናገሩት።


በተለይም ህዝባዊ ተሳትፎውን ለማስተባበር የተቋቋመው የሕዳሴ ግድብ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅ/ቤት በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ቃል የተገባው ገንዘብና ቁሳቁስ ተከታትሎ ገቢ እንዲሆን ከማድረግ አንጻር ያሉበትን ክፍተቶች ማስተካከል ይኖርበታል። በተጨማሪም የግድቡ ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ ወቅታዊ መረጃዎች መስጠትና የሚጠናቀቅበትን ጊዜ በይፋ መግልጽ ቢቻል ተስፋን የሚያጭር በመሆኑ ቢታሰብበት መልካም ነው።


ባለሀብቱ በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ በራሱ ተነሳሽነት ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንጂ ጉትጎና ልምምጥ ሊደረግ አይገባም ነበር። ለመሆኑ ባለፉት አራት እና አምስት ዓመታት ውስጥ በአደባባይ ቃል የገባውን የድጋፍ ገንዘብ ያልከፈለ ባለሀብትስ መቼ ይሆን ቃሉን እውን የሚያደርገው?


መንግስት እስካሁን የገነባቸውና በቀጣይም የሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በዋናነት ታሳቢ የሚያደርጉት የሀገራችንን ባለሀብቶች ሲሆን ለእነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ሆነ በአጠቃላይ ለሀገራችን አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ሀይል ከማቅረብ አንጻር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚኖረው አስተዋፅኦ ወሳኝ መሆኑን በማጤን የድጋፍ እጃቸውን ለመዘርጋት ጊዜው አሁንም አልረፈደም።
በእርሻ፣ ኢንዱስትሪ፣ በኮንስትራክሽንና ሌሎች ዘርፎች የተሰማራው ባለሀብት ከፍተኛ የሀይል ተጠቃሚ እንደመሆኑ መጠን ለሀገሩ ህዳሴ የበኩሉን ሚና መጫወት አለበት። በተለይ በልማት ከፍተኛውን ሚና መውሰድ ያለበት ባለሀብቱ ነው። ስለዚህ የግል ባለሀብቱ እስካሁን ላደረገው ድጋፍ የሚመሰገን ሆኖ ግድቡ በቀጣይ የሚኖረውን ሀገራዊ ጥቅም ከግምት በማስገባት ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል።


በእርግጥ ንግድና ኢንቨስትመንት በውድድር የታጀበ እንደመሆኑ መጠን በውድድሩ ያልተሳካላቸው ባለሀብቶች ሊኖሩ ይችላል፣ ነገር ግን በኢትዮጵያ ህዝብ ፊት ለዚያውም በመገናኛ ብዙሀን ቃል ተገብቶ ምስጋናና ሽልማት ተወስዷልና ቃልን ማክበር፤ ሀገራዊ ሀላፊነትን መወጣት ያስፈልጋል። በሀገራችን ቃሉን የማይጠብቅ ሰው ‹‹ቃል አባይ›› ይባላል። የዚህ ፅሁፍ መልዕክትም ባለሀብቶች የገባችሁትን ቃል አክብሩ፤ የዜግነት ግዴታችሁንም ተወጡ ነው።


በመሆኑም በተለያዩ አጋጣሚዎች የገቡትን ቃል አክብረው ለግድቡ ግንባታ ድጋፋቸውን ቢሰጡ መልካም ነው። ግድቡ ተጋምሷል፤ መጠናቀቁ አይቀሬ ነው። በኤሌክትሪክ ሀይል እጥረትና መቆራረጥ ምክንያት ክፉኛ ሲያማርሩ የምንሰማቸው ባለሀብቶች ግድቡ ሲጠናቀቅ ከሌላው ህብረተሰብ በተለየ መልኩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ግልጽ ነው።


ባለሃብቶቻችን እንደ ማንኛውም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የግድቡን መጠናቀቅ በታላቅ ተስፋና ጉጉት እንደሚጠብቁ እምነት አለኝ። ሆኖም ቃላቸውን ያልጠበቁትም ሆነ አንዳችም ድጋፍ ያልሰጡት ባለሃብቶቻችን በህዝብና በመንግስት ሃብት ግንባታው ሲጠናቀቅ ከበረከቱ ለመቋደስ የሚያስቡ ከሆነ ግን በእርግጥ ከታሪክ ተወቃሽነት እንደማያመልጡ በሚገባ ሊገነዘቡት የሚገባ ሀቅ ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
202 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 807 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us