የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ዝግጅት እና አዋጁ

Wednesday, 07 February 2018 13:26

 

የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት እገዳ ባለፈው ሳምንት ተነስቷል። የእገዳውን መነሳት ተከትሎ ሕጋዊ መስፈርቶችን ለሚያሟሉ ዜጎች አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሞኑን አስታውቋል።


አዲሱ አዋጅ ቁጥር 923/2008 በግልጽ እንደደነገገው የሥራ ስምሪቱ የሚከናወነው ኢትዮጵያ በይፋ ስምምነት ከፈጸመችባቸው ሀገሮች ጋር ብቻ ነው። እስካሁን ሀገሪቱ ከሶስት ሀገራት ማለትም ኩዌት፣ ኳታር እና ዮርዳኖስ ጋር ብቻ ስምምነቱን ያደረገች ሲሆን ተጨማሪ ሀገራት ጋር ስምምነት እስኪፈጸም ድረስ ጉዞ የሚደረገው በእነዚህ ሶስት ሀገራት ብቻ ይሆናል። ይህ በራሱ እንደ አንድ ትልቅ ተግዳሮት የሚታይ ነው።

 

የክልከላው መነሻ


የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት በድንገት በ2006 ዓ.ም የታገደው በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ኢትዮጵያዊያን ወገኖች ከሥራ ስምሪት ጀምሮ በድካማቸው ልክ ተገቢውን ክፍያና ጥቅማ ጥቅም ያለማግኘት እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች መጣስ መደጋገሙ አሳሳቢ ደረጃ በመድረሱ ነው። ይህ ሁኔታ በወቅቱ በሥራ ላይ የነበረውን አዋጅ እንዲፈተሸ አስገድዶአል። በእርግጥም አዋጅ ቁጥር 632/2001 ሲፈተሸ መሠረታዊ የሕግ ክፍተቶች እንዳሉበት ማረጋገጥ ተቻለ። በሒደትም አዋጁ እንዲሻሻል ተደርጎ በ2008 ዓ.ም ሊጸድቅ በቅቷል። ይህም ሆኖ የታገደው የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አዋጁን ለማስተግበር በቂ ዝግጅት እንዲደረግ በሚል እገዳው ሳይነሳ ባለበት ጸንቶ ቆይቷል።


ሚኒስቴር መ/ቤቱ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ ላይ በግልጽ እንደተመለከተው የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪትን ለማቀላጠፍ አዋጁ ዝርዝር መመሪያና ደንቦችን በማዘጋጀት ለህጋዊ የሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ፈቃድ ይሰጣል። በዚህ መሠረት እሰካሁን 980 ኤጀንሲዎች ህጋዊ እውቅና እና ፈቃድ ለማግኘት አመልክተዋል።


አንድ ፈቃድ መውሰድ የፈለገ ህጋዊ የስራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ አንድ ሚልየን ብር በዝግ የባንክ ደብተር ማስቀመጥ ይጠበቅበታል።


ይህንና ሌሎችም ህጋዊ መስፈርቶችን ላሟሉ ለ20 ኤጀንሲዎች ብቻ እስከአሁን እውቅና መስጠቱንም ታውቋል።

 

አዲሱ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 ምን ይላል?

፮. ቀጥታ ቅጥር የተከለከለ ስለመሆኑ


፩. ማንኛውም አሠሪ በሚኒስቴሩ ወይም በኤጀንሲ በኩል ካልሆነ በስተቀር በቀጥታ ሠራተኛን መልምሎ ሊቀጥር አይችልም።


፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተደነገገው ቢኖርም ሚኒስቴሩ በሚከተሉት ሁኔታዎች ቀጥታ ቅጥር ሊፈቅድ ይችላል፡-


ሀ/ አሠሪው የኢትዮጵያ ሚሲዮን አባል ከሆነ፤


ለ/ አሠሪው ዓለም አቀፍ ድርጅት ከሆነ፣ ወይም


ሐ. ከየቤት ሰራተኛነት ቅጥር በስተቀር ማንኛውም ሥራ ፈላጊ በራሱ ጥረት የሥራ እድል ሲያገኝ።


፫. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) (ሐ) መሠረት በቀጥታ የሚደረግ ቅጥር በሚኒስቴሩ ሊፈቀድ የሚችለው፡-


ሀ/ ሠራተኛው በሚሄድበት አገር መብቱ፣ ደህንነቱና ክብሩ ሊጠበቅ እንደሚችል በሚመለከተው ሚሲዮን ወይም በተቀባዩ አገር ሚሲዮን ከሌለ አዲስ አበባ በሚገኘው የተቀባዩ አገር ሚሲዮን እና በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተረጋገጠ፣


ለ/ በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፷፪ (፩) መሠረት የተገባ የሕይወትና የአካል ጉዳት ካሳ ኢንሹራንስ ሽፋን ስለመኖሩ፣ እና


ሐ/ ከሥራ ውሉ ጋር ምቹ የሆነ የአየር ወይም የየብስ መጓጓዣ አገልግሎት የሚያገኝ ስለመሆኑ፣ ማስረጃ ሲቀርብ ብቻ ነው። 

 

፬. በዚህ አንቀጽ መሠረት ቀጥታ ቅጥር እንደፊፅም ለተፈቀደ ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ሊወጣ የሚችለው በሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ባለው ባለሥልጣን በኩል ብቻ ነው።

 

ንዑስ ክፍል ሁለት


ትምህርት፣ ሥልጠና እና የጤና ምርመራ

 

፯. ስለትምህርት ደረጃና የሙያ ብቃት ምዘና

 

፩. ለሥራ ወደ ውጭ አገር የሚሄድ ማንኛውም ሠራተኛ፡-


ሀ/ ቢያንስ የስምንተኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቀ፣ እና


ለ/ በሚቀጠርበት የሥራ መስክ አግባብ ካለው የምዘና ማዕከል የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ የያዘ፣ መሆን አለበት።


፪. በዚህ አንቀ ጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት ሠራተኛው የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ እንዲያቀርብ የሚጠየቀው አሠሪው የሚጠይቃቸውን ሌሎች መስፈርቶች ማሟላቱ ሲረጋገጥ ብቻ ነው።

 

፷. ስለ ግንዛቤ ማሳደጊያ ፕሮግራም

 

ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን፡-


፩. ለሥራ ወደ ውጭ አገር ለመሄድ ፍላጎት ላላቸው ዜጎች ስለተቀባይ አገር ሁኔታ፣ በሚሰማሩበት የሥራ መስክ ሊኖራቸው ስለሚገባ ክህሎት፣ ስለመብታቸውና ኃላፊነታቸው እና ስለመሳሰሉት ጉዳዮ የቅድመ ስምሪትና የቅድመ ጉዞ ግንዛቤ ማሳደጊያ ሥልጠና በመደበኛነት ይሰጣል፣


፪. ሕብረተሰቡ ስለውጭ አገር ሥራ ስምሪት ተጨባጭ ሁኔታ ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኝ የመገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ቀጣይነት ያለው አገር አቀፍ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎችን ያከናውናል፣


፫. ለኤጀንሲ የቦርድ አመራሮች፣ ሥራ አሥኪያጆች እና ሠራተኞች ስለውጭ አገር ሥራ ስምሪት ተከተታይነት ያለው የግንዛቤ ማሳደጊያ ፕሮግራሞችን ያካሂዳል፣


፬. ስለ ኢትዮጵያዊያን ሠራተኞች ምልመላና ቅጥር ሁኔታ፣ ስለውጭ አገር ሥራ ስምሪት በሥራ ላይ ስላሉ ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች፣ ቅድመ ሁኔታዎች እና የተለያዩ መስፈርቶች ለውጭ አገር አሠሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለፃ ይሰጣል።

 

፱. ስለጤና ምርመራ


፩. የሠራተኛ የጤና ምርመራ የሚደረገው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሚመርጠው የጤና ተቋም ብቻ ይሆናል።


፪. ኤጀንሲው ሠራተኛን ለጤና ምርመራ መላክ ያለበት አሠሪው የሚጠይቃቸውን ሌሎች መስፈርቶች ማሟላቱ ሲረጋገጥ ብቻ ይሆናል።


፫. ሠራተኛው ከአንድ ጊዜ በላይ የጤና ምርመራ እንዲያደርግ የሚጠየቅ ከሆነ ወጪውን ኤጀንሲው መሸፈን ይኖርበታል።

 

ንዑስ ክፍል ሦስት


ስለወጪ አሸፋፈንና የአገልግሎት ክፍያ

 

፲. ስለ ወጪ አሸፋፈን

 

፩. የሚከተሉት ወጪዎች በአሠሪው ይሸፈናሉ፡-


ሀ/ የተቀባይ አገር የመግቢያ ቪዛ ክፍያ፤


ለ/ የደርሶ መልስ የመጓጓዣ ክፍያ፤


ሐ/ የሥራ ፈቃድ ክፍያ፤


መ/ የመኖሪያ ፈቃድ ክፍያ፤


ሠ/ የመድህን ዋስትና ሽፋን፤


ረ/ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኝ ለተቀባ አገር ኤምባሲ ወይም ቆንስላ ጽህፈት ቤት የሚከፈል ከቪዛና ከሰነድ ማረጋገጥ ጋር የተያያዘ ማንኛውንም ወጪ፣ እና


ሰ/ የሥራ ውል ማጽደቂያ የአገልግሎት ክፍያ።


፪. የሚከተሉት ወጪዎች በሠራተኛው ይሸፈናሉ፡-


ሀ/ የፓስፖርት ማውጫ ወጪ፤


ለ/ ከውጭ አገር የሚላክ የሥራ ቅጥር ውል ሰነድ እና ከወንጀል ነፃ ማስረጃ ማረጋገጫ ወጪ፤


ሐ/ የሕክምና ምርመራ ወጪ፤


መ/ የክትባት ወጪ፤


ሠ/ የልደት ሰርተፊኬት ማውጫ ወጪ፤ እና


ረ/ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ ወጪ።


፫. በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀጽ (፪) የተመለከቱ ወቺዎችን ሠራተኛው አውጥቶ በራሱ ጉድለት ባልሆነ ምክንያት በሥራ ላይ ካልተሰማራ ኤጀንሲው ወይም አሰሪው የሠራተኛውን ወጪ የመተካት ግዴታ ይኖርበታል።


፬. ለሥራ ወደ ውጭ አገር ለመሄድ አስፈላጊ ሁኔታዎች ተጠናቀው ያለበቂ ምክንያት ሠራተኛው ወደ ሥራው ባይሰማራ ከቅጥሩ ጋር በተያያዘ አሰሪው በዚህ አንቀጽ በንዑስ አንቀጽ (፩) ያወጣውን ወጪ ሠራተኛው እንዲከፍለው ሊጠይቅ ይችላል።


፲፩. ስለ አገልግሎት ክፍያ


ሚኒስቴሩ አሠሪውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ መሠረት የሥራ ውል ማፅደቂያ የአገልግሎት ዋጋ ክፍያ ያስከፍላል።

 

ንዑስ ክፍል አራት


ስለሁለትዮሽ ስምምነት እና አደረጃጀት

 

፲፪. የሁለትዮሽ ስምምነት ስለማስፈለጉ


በዚህ አዋጅ መሠረት ሠራተኛን በውጭ አገር ለሥራ ማሰማራት የሚቻለው በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በተቀባይ አገር መካከል የሁለትዮሽ ስምምነት ሲኖር ብቻ ነው።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
767 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1120 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us