የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምንን ያሳካል?

Wednesday, 21 February 2018 11:47

 

የሚኒስትሮች ምክርቤት የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ የአገሪቱን ሠላምና መረጋጋት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስጠበቅና የዜጎችን ሕገመንግሥታዊ መብት ለማስከበር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ወስኗል። በዚሁ መሠረት ለቀጣይ ስድስት ወራት በሥራ ላይ የሚውል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መተግበር ጀምሯል። ይህ አዋጅ ካለፈው ስድስት ወራት ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ በሥራ ላይ እንዲውል የተደረገ ነው።


እንደሚታወሰው የሚኒስትሮች ምክርቤት በተመሳሳይ ሁኔታ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጎ ለ10 ወራት ጊዜ ያህል በሥራ ላይ ቆይቶ በሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም መጨረሻ ፓርላማው ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ እንዲነሳ መደረጉ የሚዘነጋ አይደለም። በወቅቱ አዋጁ ሲደነገግ ታሳቢ ያደረገው ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያጋጠመውን የጸጥታ መደፍረስ በመደበኛ ሁኔታ መቆጣጠር ባለመቻሉ ነው።

 

የአምናው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምን ፈየደ?


አዋጁ ለሠላምና መረጋጋት እንቅፋት ሆነዋል የተባሉ ግሰለቦችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ጠቅሟል። አንጻራዊ በሆነ መልኩ ጊዜያዊ ጸጥታ ለማስፈንም እንዲሁ። ዘላቂ ሠላም ከማምጣት አንጻር ግን አስተዋጽኦው ዝቅተኛ ነበር ብሎ መውሰድ የሚቻልባቸው ተጨባጭ ሁኔታዎች የአዋጁን መነሳት ተከትሎ ተከስተዋል።


በአንጻሩ ግን ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ጥልቅ ተሀድሶ ለማድረግ በገባው ቃል መሠረት መታደስ ችሏል ወይ የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ነው። በራሱ ግምገማ መሠረት የጥልቅ ተሀድሶው ጥልቀት የሚጎድለው ሆኗል። እናም ለሠላምና ጸጥታ መደፍረሱ ዋንኛ ምክንያት የሆነው በተለይ ሥልጣንን ለግል ጥቅም ከማዋል ጋር ተያይዞ የሚታይ የሥልጣን አተያይ ችግር የወለዳቸው ኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካ መገለጫ የሆኑት ትምክህተኝነት፣ ጠባብነት፣ ብልሹ አሠራርና ሙስና…ትርጉም ባለው መልክ ቀርፎ፣ ተጠያቂዎችን ለሕግ ማቅረብ አልቻለም። እናም የአዋጁ በሥራ ላይ መቆየት ከዚህ አንጻር የነበረው ፋይዳ የረባ አለመሆኑን ለመረዳት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ ከሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም መጨረሻ በኋላ የተፈጠሩትን ዘግናኝ የሠላም መደፍረስ ችግሮች ማጤን ብቻ ይበቃል።


«መጪው ዘመን የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን ነው» በተባለበት የ2010 መባቻ ላይ የተሰማው የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች ዘግናኝ ግጭት እንደአንድ አብነት ማንሳት ይቻላል። ግጭቱ አብረው በኖሩ ሕዝቦች መካከል ሞትና ከፍተኛ ቁጥር የያዘ መፈናቀልን አስከትሏል። ይህም ሆኖ ላለፉት ስድስት ወራት በዚህ ግዙፍ የሞትና የመፈናቀል አደጋ ጀርባ ያሉ አካላት በአግባቡ ተለይተው በተሟላ መልኩ ለፍርድ መቅረብ አለመቻላቸው የገዥው ፖርቲ አገር የማስተዳደር፣ የመምራት አቅምና ብቃት ጥያቄ ምልክት ላይ የጣሉ ናቸው። ከግጭቶቹ ጀርባ ከፍተኛ የመንግሥት ሹማምንት አሉ የሚለው የአንዳንድ ወገኖች ጥርጣሬ መንግሥት መመርመር አለመቻሉ አሁን ድረስ በወጉ ያልተመለሰ እንቆቅልሽ ሆኗል።


ከየካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለተኛ ጊዜ በሥራ ላይ የዋለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዓላማ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በቂ ጊዜ አግኝቶ ማሻሻያዎችን ለማድረግ የሚጠቀምበት ነው ወይንስ የተቃወሙትን ሀይላት በሓይል ጸጥ ለማሰኘት ያለመ ብቻ ነው የሚለው አሁንም በተግባር መመለስ የሚኖርበት ጥያቄ ነው።

 

ለመሆኑ ሕገመንግሥቱ ስለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምን ይላል?


አንቀፅ 93 ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
1 ሀ/ የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፣ ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፣ የፌዴራሉ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን አለው።
ለ/ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የክልል መስተዳድሮች በክልላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጁ ይችላሉ። ዝርዝሩ ክልሎች ይህን ሕገ መንግሥት መሠረት በማድረግ በሚያወጧቸው ሕገመንግሥቶች ይወሰናል።

 

2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 /ሀ/ መሰረት የሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣
ሀ/ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባለ ጊዜ የታወጀ ከሆነ በታወጀ በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ አለበት። አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት- ሦስተኛው ድምጽ ተቀባይነት ካላገኘ ወዲያውኑ ይሻራል።
ለ/ ከላይ በንዑስ አንቀጽ /ሀ/ ሥር የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባልሆነበት ወቅት የሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ ያለበት አዋጁ በታወጀ በአሥራ አምሥት ቀናት ውስጥ ነው።

 

3. በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምክር ቤቱ ተቀባይነት ካገኘ በኝላ ሊቆይ የሚችለው እስከ ስድስት ወራት ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ አንድን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በየአራት ወሩ በተደጋጋሚ እንዲታደስ ሊያደርግ ይችላል።

 

4. ሀ/ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣቸው ደንቦች መሰረት የሀገርን ሰላምና ሕልውና፣ የሕዝብን ደህንነት፣ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሥልጣን ይኖረዋል።
ለ/ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን መሰረታዊ የፖለቲካና የዴሞክራሲ መብቶችን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለማስወገድ ተፈላጊ ሆኖ በተገኘውደረጃ፣ እስከ ማገድ ሊደርስ የሚችል ነው።
ሐ/ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥራ የሚያወጣቸው ድንጋጌዎችና የሚወስዳቸው እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ በዚህ ሕገመንግሥት አንቀጽ 1፣ 18፣ 25፣ እና 39 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 የተቀመጡትን መብቶች የሚገድቡ ሊሆኑ አይችሉም።
………………………….

 

…………………………………
5. በሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአባላቱና ከሕግ ባለሙያዎች መርጦ የሚመድባቸው ሰባት አባላት ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ያቋቁማል። ቦርዱ አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚጸድቅበት ጊዜ ይቋቋማል፣

 

6. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ የሚከተሉት ሥልጣንና ኃላፊነቶች አሉት።

ሀ/ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የታሰሩትን ግለሰቦች ስም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይፋ ማድረግና የታሰሩበትን ምክንያት መግለጽ፣
ለ/ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሚወሰዱት እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ ኢሰብዓዊ አለመሆናቸውን መቆጣጠርና መከታተል፣
ሐ/ ማናቸውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃ ኢ- ሰብዓዊ መሆኑን ሲያምንበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የሚኒስሮች ምክር ቤት እርምጃውን እንዲያስተካክል ሐሳብ መስጠት፣
መ/ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃዎች ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጽሙትን ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ፣
ሠ/ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲቀጥል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ሲቀርብ ያለውን አስተያየት ለምክር ቤቱ ማቅረብ የሚሉት ይገኙበታል። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1065 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 981 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us