“በነፃነት ጠንክረን ኦሮሚያ ውስጥ ስንሰራ የሕዝባችንን ችግር መፍታት እንችላለን”

Wednesday, 28 February 2018 12:52


“በነፃነት ጠንክረን ኦሮሚያ ውስጥ ስንሰራ
የሕዝባችንን ችግር መፍታት እንችላለን”

 

አቶ ለማ መገርሳ
የኦሮሚያ ክልለ ፕሬዚደንት

 

የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ የካቲት 15 ቀን 2010 ዓ.ም ባካሄደዉ ስብሰባ አዲስ ሊቀመንበር መምረጡ ይታወሳል። በዚህም መሰረት ዶ/ር አቢይ አህመድ የድርጅቱ ሊቀመንበር፣ አቶ ለማ መገርሳ ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር ሆነዉ እንዲያገለግሉ ወስኗል።


ኦህዴድ አዲስ ሊቀመንበር መምረጥ ለምን እንዳስፈለገው? የኦሮሚያ ክልልን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዴት ማሳካት ይቻላል? የፌዴራል ሥልጣን ኦሕዴድ እንዴት ይመለከተዋል? እና መሰል ርዕሰ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አቶ ለማ መገርሳ ከኦ.ቢ.ኤን ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ቃለምልልስ ምላሽ ሰጥተዋል።


አቶ ለማ መገርሳ ከኦ.ቢ.ኤን ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ የኦሮሚያ የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት ወደ አማርኛ መልሶታል። ይህንኑ ከዚህ በታች አስተናግደነዋል። መልካም ንባብ።

 

*** *** ***

 

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባካሄደው ስብሰባ፤ የድርጅታችን አሰራር መሠረት በማድረግ የአመራሮችን ሁኔታ አስመልክቶ አንዳንድ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።


በአሁኑ ወቅት በሃገራችን ከተፈጠረው ሁኔታ በመነሳት፤ ድርጅታችን የሕዝባችንን ጥያቄ ከመመለስ አንፃር እስካሁን የሄደዉ አካሄድ ምን እንደሚምስል እና ትግሉን ብስለትና ቀጣይነት ባለው መንገድ እንዴት መምራት ይችላል በሚል መንፈስ መልሰን መላልሰን ስንመለከተው ነበር።


በዚህ አካሄድም ግልጽ የሆነ ነገር ተፈጥሯል። ሕዝባችን እንደክልል ራሱን በራሱ ማስተዳደርና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን ከመፈለጉ የተነሳ ጥያቄዎችን ሲያነሳ ነበር። በሌላ መልኩም በፌደራል ደረጃ የሃላፊነት ድርሻ በመወሰድና በወሰደውም ልክ የአመራርነት ድርሻ እንዲኖረው ጥያቄ ነበረው። ይህ ጥያቄ ደግሞ የሕዝባችን ብቻ ሳይሆን የድርጅታችንም ጥያቄ ነበር። በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ የአመራርነት ሚናችንን በተገቢዉ መንገድ በመወጣት ለህዝባቸን ጥያቄ ተገቢዉን ምላሽ መስጠት እንዳለብን እናምናለን። ይህንን ከግብ ማድረስ ይገባናል። ለስኬታማነቱም ከሕዝባችን ጋር በመሆን ረዥም የትግል ጉዞ በማድረግ እዚህ ደርሰናል። ይህ ማለት ግን ትግሉ በዚህ አበቃ ማለት አይደለም። ትልቁ ትግል ከፊታችን ያለው ነው። ከዚህ በመነሳትም በፌዴራል መንግስት ውስጥ የአመራርነት ሚና በብቃት መወጣት አለብን ስንል ክልላችንን በመዘንጋት መሆን የለበትም።


እዚህ ላይ ማሰብ ያለብን አብይ ጉዳይ ሃላፊነትን መቀበል አለብን ብለን ማሰብ ብቻ ሳይሆን በታሪክ አጋጣሚ ያገኘነውን ዕድል እንዴት አድርገን ልንሰራበት እንደምንችል በማጤን በበሰለ አካሄድ የወደፊቱን ግብ ማየት ነው እንጂ ኃላፊነትን መቀበል ብቻውን በቂ አይሆንም። ጉዳዩን ስትራቴጅያዊ በሆነ መንገድ ማጤን አስፈላጊ ነው። የተሰጠንን ዕድል በአግባቡ ካልተጠቀምንበትም መውደቅ ሊመጣ ይችላል። ይህ ደግሞ በሕዝባችን ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ቀላል አይሆንም፤ በመሆኑም ጉዳዩን በሰከነ መንፈስ በማየት ልንሰራ ይገባል። ሕዝባችን በፌዴራል መንግስት ተገቢዉን የኃላፊነት ድርሻ ማግኘት አለብን ብሎ ሲጠይቅ ጥያቄው የሞራል ጥያቄ ነው። ድርጅቱም በዚህ ጥያቄ ተገቢነት ያምናል። በፌዴራል ደረጃ የሚቀመጠው አመራር ለኦሮሞ ሕዝብ የተለየ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ያመጣል ብለን አናስብም። አንድ ሰው ከመካከላችን በመውጣት ሀገሪቱን መምራት ይችላል ብንል እንኳ፤ የሀገሪቱን ብሔር ብሔረሰቦች በእኩልነት እና በፍትሐዊነት ይመራል። የታገልነውም ለዚህ ነው። የኦሮሞን ሕዝብ ወክሎ እንደመቀመጡ መጠንም የኢትዮጵያን ሕዝብ ክብርና ጥቅም በማስጠበቅ እኩልነት በሀገሪቱ እንዲሰፍን እና ፍትሐዊነት እንዲረጋገጥ መስራት አለበት።


በሌላ በኩል የኦሮሞን ክብር ማስጠበቅ የምንችለው ሰርቀን ለሕዝባችን በማምጣት ሳይሆን ለፍትሐዊነትና ለእውነት የምንስራ መሆናችንን በተሰጠን ዕድል ሰርተን በማሳየት ብቻ ነዉ።


በቀጣይነት የሚነሳው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄ ነው። ይህ የሕዝብ ጥያቄ እንዴት መመለስ እንዳለበት ማዕከላዊ ኮሚቴው በግልጽና በጥልቀት በመወያየትና በመደማመጥ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አንፃር ያለዉ ችግር እንዴት መፈታት እንዳለበት ሲመለከት ቆይቷል። ይህን ችግር ለመፍታት የአመራሩ ድርሻ ቁልፍ መሆኑ ተሰምሮበታል። ከዚህ በመነሳት እንደ አመራር ያለንን ፑል በመጠቀም ከምን ጊዜውም በላይ በአንድ ልብና ሃሳብ ጠንክረን team spirit (collective leadership) ፈጥረን በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን።


ከግብ የምናደርሰው የህዝባችንን ጥያቄ ስለሆነ በክልል ያለውን አመራራችንን እንዴት እናስቀጥል፣ በፌዴራል ደረጃ ያለንን ተልዕኮስ እንዴት ከግብ እናድርስ የሚለውን ሃሳብ አፅንኦት ሰጥተን ተመልክተነዋል። በፌዴራል ደረጃ ያለውን ብቻ በማየት በክልል ያለውን ጉዳይ የምናንጠባጥብ ከሆነ ውድቀት ማስከተሉ አይቀርም። አንድ ሰው አይደለም፤ ሀያ ሰው በፌዴራል ደረጃ ወንበር ቢያገኝ፤ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ መልስ አግኝቷል ማለት አይደለም። ስለሆነም በሁለቱም አቅጣጫ ተመልክተን አንድም ክልላችንና ሕዝባችን ያሉባቸውን ችግሮች ያለማንም ጣልቃ ገብነትና ንክኪ ራስችንን ችለን ማስተዳደር መቻል ትልቅ ድል ነው።


በተለይ የኢኮኖሚ ጥያቄን በመለከተ፤ ድርጅታችንን በማጠናከርና የመንግስት መዋቅርን በመገንባት ላይ አትኩረን ከሰራን ከምን ጊዜውም በላይ ልንጠቀምበት እንችላለን። ዋናው ትኩረት ኦሮሚያ ላይ መስራት ነው። የስልጣናችን ምንጭ ሕዝባችን ስለሆነ ወደፊትም ወደ ፌዴራል ሄደን የምንሰራው ሥራ በግለሰብ የሚሰራ ስላልሆነ ይህ ሕዝብ ዕውቅና እስካልሰጠውና እስካልደገፈው ሁለት ሰውም ይሁን ሀያ ሰው ሄዶ ውጤታማ ሊሆን አይችልም። ይህንን ደግሞ ማምጣት የምንችለው በቤታችን ውስጥ የምንፈልገውን ነገር መስራት ስንችል ነው። በነፃነት ጠንክረን ኦሮሚያ ውስጥ ስንሰራ የሕዝባችንን ችግር መፍታት እንችላለን። በተለያየ መልኩ እንቅፋት እየሆነብን መሮጥ የምንችለውን ያህል እንዳንሮጥ የገደበን ነገር ቢኖርም፤ አሁን ባለን አቅም መሮጥ የሚያስችለን ነገር አለን ብለን እናምናለን። ስለዚህ ጠንካራ አመራር በክልላችን ሊኖረን ይገባል። ብዙ በጅምር ተንጠልጥለው ያሉ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ሕዝባችንን አንድ የማድረግ ስራዎች ይቀሩናል፡


የመንግስትና የድርጅት አደረጃጀት ጠንካራና ለሕዝቡ የሚቆረቆር መሆን አለበት። ይህንን ድርጅት ለማጠናከር የተለያዩ ትግሎችንና እርምጃዎችን እየወሰድን እዚህ ደርሰናል። ነገር ግን አሁንም ጠንካራ ሆኖ የወጣ አይደለም። አሁንም በተለየ መንገድ ማጠንከር ያስፈልጋል። ዝም ብለን በሩን ክፍት አድርገን ሁላችንም የምንሄድ ከሆነ ተያይዘን እንወድቃለን። አሁን ባለበት በአንድ ልብና ሃሳብ ጠንክረን ከሰራን ከላይ የምንሰራው ስራም ዉጤታማ ይሆናል፣ ረዥም መንገድም ይጓዛል፣ በመንገድም አይቀርም። ይሄንን የሚያስተጓጉል የሚሞክር ሊኖር ይችል ይሆናል፤ በሕዝብና በጠንካራ ድርጅት ከተደገፈ ግን ምንም አይሆንም፤ ስለሆነም በኦሮሚያ ላይ የሚሰራው ስራ ወሳኝ ነው።ስለዚህ ጠንካራ የሆነ አመራር ኦሮሚያ ላይ ሊኖረን ይገባል። ልክ እንደ እግር ኳስ ጨዋታ ማን የት ቢጫወት የበለጠ ውጤት ያመጣል እንደሚባለው ማየት አለብን። ከዚህ በመነሳት ካለን የአመራር ፑል ማንን የትና እንዴት ብናዘጋጅ ይሻላል ብለን አንዱን በማንሳትና ሌላውን በመተው ሳይሆን በአንድ ሃሳብና በቡድን ለአንድ ግብ ብንስራ ተያይዘን ረዥም መንገድ መጓዝ እንችላለን። ሕዝባችን ከእኛ የሚጠበቀውንም ነገር ከግብ ማድረስ እንችላለን።


ከዚህም በመነሳት የህዝባችንን ፍላጎት ከግብ ለማድረስ በሚያስችለን መልኩ አንድ አንድ ማስተካከያዎችን አድርገናል። ያደረግነው ማስተካከያ በፌዴራል ደረጃ የኦህዴድ ሚና የጎላ እንደሚሆን ሙሉ እምነት አለን። ድርጅቱ በፌዴራል አመራርነት ዉስጥ በሚገባ ሚናውን እንዲወጣ ስንታገል ነበር፤ እየታገልንም ነው፥ ለወደፊትም እንታገላለን።ይሄም ጥያቄ ዉስጥ አይገባም። የሚሆነዉም ዲሞክራቲክ በሆነ መልክ ነው። እንዲህ ስናደርግ ደግሞ ማን የት ቢተካ የበለጠ ዉጤታማ እንሆናለን በማለት አይተናል። በሌላ በኩል እንደመስፈርት የሚነሱ አንድ አንድ ጉዳዮች ከወዲሁ በተሟላ መልክ እንድናደራጅ ትኩረት ሰጥተን ተወያይተን ወስነናል። አንድ አንድ ለውጥም አድርገናል፤ ለምሳሌ ማናችንም ከማናችን በልጠን አይደለም፤ ነገር ግን ማን የት ቢሆን በይበልጥ ዉጤት ማምጣት ይችላል? እና የድርጅቱን አላማ ከግብ ማድረስ ይችላል በማለት አይተናል።


በዚህም መሰረት ዶ/ር አብይ የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆኖ እንዲሰራ እኔ ደግሞ ምክትል ሆኜ እንድሰራ ወስነናል። ይሄን ስናደርግ ለህዝባችን ግልፅ ሊሆን የሚገባው ምንም ነገር ተፈጥሮ አይደለም። ነገር ግን የህዝባችንን ፍላጎት ከግብ ለማድረስ የተጠቀምንበት ስልት እንጂ። ይሄ የፖለቲካ ጉዳይ ነው፤ እድር አይደለም ወይም ማህበር አይደለም። ፖለቲካ ደግሞ በሁሉ አቅጣጫ መመልከትን ይጠይቃል። የህዝብ ፍላጎትን ያማከለና የድርጅቱን ዓላማ ከግብ ያደርሳል ብለን ያስብነውን ሁሉ አድርገናል። በዚህ ዕይታ ነው ይሄን ማስተካከያ ያደረግነው። እንደዚህ ሲሆን አንድና ሁለት ሰው ማዘጋጀት ሳይሆን ወደ ፌዴራል አመራር የሚሄድ አካል በቡድን እንዲሰራ በማሰብ ጭምር ነው። ለፌዴራል የሚሄድ አካል እንዴት መሰራት እንዳለበት፤ ምን መስራት እንዳለበት ግንዛቤ በመያዝ ይሄን ማስተካከያ አድርገናል። በክልል የሚቀረው አካል ምን መስራት እንዳለበት አንድ ሁለት ብለን አስቀምጠናል። ሁለቱም አካላት ደግሞ በመደማመጥ፤ በመተጋገዝ ይሰራሉ ብሎ ድርጅቱ አምኖበት ማዕከላዊ ኮሚቴው ቀጣዩን ስራ በማጤን ወስኗል።


ይህ ማለት ድርጅቱን ስመራው እንደቆየሁት አሁንም እመራለሁ፤ ሌሎቹም እንዲሁ። በጅምሩ ተንጠልጥሎ ያሉ የቤት ሥራዎች አሉን። ተንጠልጥሎ ያለ ሥራን ትቶ መሄድ ደግሞ የራሱ የሆነ ተፅእኖ ይኖረዋል። ስለዚህ እንደ እኛ ሃሳብ ጅምር ስራዎችን በክልሉ እየገነባን ባለነው ቲም/ቡድን/ በርትተን ብንሰራ ይበልጥ የተሳካ ይሆናል። ወደ ፌዴራል የሚሄደው ቡድን በዚህ ደረጃ የህዝባችን ፍላጎት ያስከብራል። ይሄንን ስናደርግ ለስልጣን ስሌት የምናየዉ ከሆነ፤ አንዱ ወንበር ካንዱ ይበልጣል። ይሄ ደግሞ በታሪክ ሲገጥመን ለመቀበል ማናችንም ትልቅ ጉጉት ይኖረናል። ነገር ግን እንደግለሰብ ወንበር በመመኘት ብቻ ህዝባችን ዋጋ የከፈለበትን ጉዳይ ከግብ እናደርሳለን ብለን ማሰብ አይቻልም። በይበልጥ የት ሆነን ብንሰራ ህዝቤ ዋጋ የከፈለበትን ከግብ አደርሳለሁ ብሎ በማሰብ እንጂ። ለእኔ ትልቁ ስኬት ዋጋ ከፍለን እዚህ ያደረስነዉን ትግልና በኦሮሚያ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ትግል ከግብ ማድረስ ሲቻል ነው። የተለያዩ ጫናዎችና ሙሉ ትኩረታችንን የሚበትኑ ጉዳዮች ከቆሙ በሙሉ ኃይል ዛሬ ላይ ከምናደርገው ሩጫ በሁለትና ሶስት እጥፍ መፍጠን እንችላለን። ሌት ተቀን ሙሉ ኃይላችንን በመጠቀም በኦሮሚያ የጎሉ ለውጦች እናመጣለን ብዬ አምናለሁ።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
2417 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1024 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us