የጫት መዘዙ

Wednesday, 21 March 2018 13:28

 

የአማራ ክልል የጤና ጥበቃ ቢሮ የአማራ ክልልን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን የጫት መቃም (ሱስ) ችግር አስመልክቶ ሰሞኑን ያወጣውን ምክረ ሀሳብ መነጋገሪያ ሆኖ ከርሟል። ጤና ቢሮው ለሁሉም የዘርፍ መ/ቤቶች ያሰራጨው ሰርኩላር ደብዳቤ ይዘት ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘነው እንደሚከተለው ቀርቧል።

 

ስለጫት ዳራ

 

ጫት መሠረቱ ምስራቅ አፍሪካ ሲሆን ስርጭቱም እስከ ደቡብ አፍሪካ ከዚያም አልፎ በየመን አፍጋኒስታንና ቱርክ ውስጥ እንደሚበቅል ይታወቃል። ጫት ተራራማና እርጥበታማ በሆኑ ቦታዎች ይበቅላል።


አንዳንድ ታሪክ አዋቂዎች እንደፃፉት ጫት መሠረቱ ኢትዮጵያ በተለይም ሐረርጌ እንደሆነና ከዚህ በመነሳት ወደ ሌሎች አገሮች እየተስፋፋ እንደሄደ ይናገራሉ።


ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ የመንና ማዳጋስካር በጫት አምራችነታቸውና ተጠቃሚነታቸው በዓለም የታወቁ አገሮች ሲሆኑ የሚያመርቱትም ጫት በተለያየ መንገድ ወደ ጎረቤትና ራቅ ወዳሉ አገሮች በሕጋዊም ሆነ በሕገወጥ መንገድ እንደሚዘዋወር ይታወቃል። በተለይም የአብቃይ አገሮች/ ኢትዮጵያና ኬኒያ/ ጎረቤት የሆኑት ሶማሊያና ጅቡቲ ከፍተኛ የጫት ተጠቃሚ ቁጥር መኖሩ በጥናት ተረጋግጧል።


የጫት ተክል ከቅጠሉ ወይም ከሌላ አካሉ የማነቃቃት ኃይል ያላቸው ካቲን (Catine)፣ ካቲናን (Catahinone) እና ሜትካቲኖን (Methcathinone) የተባሉት ንጥረ ነገሮች ሲኖሩት በሚያደርሱት ከፍተኛ የጤና ጉዳት፣ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ችግሮች ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።


በሌላ በኩል የአንዳንድ አገሮች /አሜሪካ፣ ካናዳና የተወሰኑ የአውሮፓ አገሮች/ የጫት ተክል በአገራቸው ውስጥ እንዳይመረት፣ እንዳይዘዋወርና ጥቅም ላይ እንዳይውል የተጠና የመቆጣጠሪያ ሕግ አውጥተዋል።


በጫት ሱስ የተያዙ ሰዎች በጊዜ ሂደት ለሌሎች ሱሶች ማለትን ለአልኮል፣ ለሲጋራ /ትምባሆ/፣ ሀሽሽ ባስ ሲልም አደገኛ እፆችና መድሀኒቶችን እስከመጠቀም የሚያደርስ ሱስ ውስጥ የመግባት እድላቸው ከፍተኛ ነው።


1. የጤና ችግሮች
- የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ጫት የምግብ ፍላጎትን ይቀንሳል። በዚህም የተነሳ ቃሚው ቫይታሚን፣ ፕሮቲን… ወዘተ በሚፈለገው መጠን ስለማያገኝ በሽታን የመቋቋም ኃይሉ ደካማ ይሆናል። በመሆኑም በተለያዩ በሽታዎች በቀላሉ ሊጠቃ ይችላል።


- የሆድ ድርቀት ያመጣል፣


- በዚህም የተነሳ ለአንጀት በሽታዎችና ለኪንታሮች (hemorrhoids) ያጋልጣል፣


· የአዕምሮ ሕመም መንስኤ መሆንና ማባባስ፣


· ከፍተኛ የድካም ስሜት፣

 

   •        -  ለተላላፊ በሽታዎች ይዳርጋል፣

ጫት ብዙውን ጊዜ በቡድን የሚቃም በመሆኑ በትንፋሽ የሚተላለፉ በሽታዎች ከአንዱ ወደ ሌላው በቀላሉ ሊተላለፍ ይቻላል / ለምሳሌ ሣንባ ነቀርሳ/


· የስሜት መረበሽና መነጫነጭ፣ ራስን መጣል


- ስንፈተ ወሲብ ያስከትላል፣


ጫት ቃሚዎች የወሲብ ፍላጎት ቢኖራቸውም ወሲብ የመፈፀም ብቃታቸው ግን የተዳከመ ይሆናል።


በጫት ውስጥ የሚገኙ አነቃቂ ንጥረ ነገሮች ሱስ የማስያዝ ባህሪ ስላላቸው ተጠቃሚዎች ደጋግመው እንዲወስዱ ተፅዕኖ ስለሚያደርጉ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች እየተባባሱ ይሄዳሉ።


2. በኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት፣


በሱሰኝነት ምክንያት በግለሰብም ሆነ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ይደርሳል።

በግለሰብ ደረጃ


-  ሱሰኛው ሱሱን ለማርካት ሲል ከገቢው እየቀነሰ ለመሠረታዊ ፍላጎት ማዋል የሚገባውን ገንዘብ በተሟላ መንገድ ሊያወጣ አይችልም። በተለይም ቤተሰብ ያለው ከሆነ ለቤቱ አስፈላጊውን ወጪ ስለማይሸፍን ቤተሰብ በርሀብና በእርዛት ይሰቃያል።


- ሱሰኛው ጤናው የተናጋ ስለሚሆን በተሰማራበት የሥራ መስክ ምርታማነቱ ዝቅተኛ በመሆኑ ከሥራ ሊረር ይችላል።

በአገር ደረጃ፣


- አምራች ኃይሉ ጊዜውን በመቃም የሚያሳልፍ ከሆነ ለማምረት የሚያውለው ጊዜና አቅም አናሳ ስለሚሆን የተፈለገውን ያህል አያመርትም፣ ምርታማነት ዝቅተኛ ስለሚሆን የአገር ኢኮኖሚ ይወድቃል።


- ሱሰኞች ጤናቸው አስተማማኝ ስለማይሆን መንግስት ለህክምና ተቋማት ማቋቋሚያ፣ ለባለሙያዎች ስልጠናና ደመዎዝ፣ ለመድኃኒት መግዣ… ወዘተ ለከፍተኛ ወጪ ይዳረጋል።
- ለምግብ እህል፣ አዝርዕትና ፍራፍሬዎች.. ወዘተ ማብቀያ ማዋል ያለበት መሬት (ማሳ) ጫት እንዲበቅልበት ከተደረገ በገበያ ላይ የምግብ እህል አቅርቦት እጥረት ይፈጠራል።
-  የሀሰት ሰነዶች ይበራከታሉ፣ ገንዘብ አስመስሎ መስራት የህገወጥ ገንዘብ ዝውውር እንዲኖ በማድረግ ህጋዊ ሰነዶችን አስመስሎ መስራት የባለሥልጣናት ፊርማ አስመስሎ መፈረም ገንዘብና ሌሎች ሰነዶችን በማጭብርበር ኢኮኖሚው ይዳከማል።

 

3. በማህበራዊ ኑሮ ላይ የሚከሰት ችግር፣


በሱሰኛው ላይ የሚደርሱ ችግሮች በግለሰብ ደረጃ ብቻ ተወስነው የሚቀሩ አይደሉም። በቤተሰብና በማህበረሰቡም ላይ ከፍተኛ ችግር ይደርሳሉ። በሱስ ምክንያት የቤተሰብ መፍረስ ይከሰታል የፈረሰው ቤተሰብ አባላትም፣ እናት ለሴተኛ አዳሪነት ልትዳረግ ትችላለች፣ ልጆች ደግሞ ለጎዳና ተዳዳሪነት ይዳረጋሉ። ልጆችም ወደ ጎዳና ወደሱስ ወደ ህገወጥ ተግባራት (ወንጀል)፣ ይሰማራሉ። በዚህ የተነሳ ፀረ ማህበረሰብ (ANTISOCIAL) እርምጃዎች ሊወሰዱ የህብረተሰብ ሰላም ይታወካል።
­­
4. በፖለቲካ መረጋጋት ላይ የሚፈጠር ችግር፣


የአንድ አገር ፖለቲካ የተረጋጋ የሚሆነው ቀደም ብሎ ተጠቀሱት ጤና ነክ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ሲቀረፉ ነው። አለበለዚያ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የአገርን ፖለቲካዊ ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ ችግሮች ናቸው። በሱሰኝነት ሳቢ የተለያዩ የፖለቲካ ችግሮች ይደርሳሉ፣ ከነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹን ለመጥቀስ ያህል፣


· ሙስናና የሥነ-ምግባር ብልሹነት መስፋፋት፣
· የመንግስት ንብረት መመዝበር፣
· የአገር ሉአላዊነት አለመከበር፣
· የወንጀል ድርጅቶች መበራከት፣
· በአገሮች መካከል የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻከር/ገፅታ መበላሸት/ ናቸው።


በአሁኑ ወቅት ጫት በሀገራችን 7 በመቶ የሚሆነውን ማምረት የሚችል መሬት በሚሸፍን ብዛት በመመረት ላይ የሚገኝ ሲሆን በሁሉም የአገራችን ክፍል በሚባል ደረጃ ጫትን በማምረትና በመጠቀም ተንሰራፍቶ ይገኛል።


ከ3 ሚሊዮን በላይ የሚሆን የሀገራችን ዜጎች ከጫት ምርት በሚገኘው ገቢ ህይወታቸውን በመመምራት ላይ ይገኛሉ። ይህ መሆኑ ደግሞ ችግሩን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ፈታኝ ያደርገዋል፡፤ ለጫት ሱስ ከሚያጋልጡ ምክንያቶች መካከል አንዱና ዋነኛው የጫት አቅርቦት ሲሆን ጫት በሌለባቸውና በማይታወቅባቸው እንደ ደቡብ አሜሪካ አይነት አገሮች ችግሩ አይታይም። የጓደኛ ግፊት፣ ግንዛቤ እጥረት፣ መገለል፣ ሰዎችን ሞዴል/ አርአያ ማድረግ፣ ፍልሰትና ስራ አጥነት ለሱስ አጋላጭ ምክንያቶች ናቸው።


በክልልችን ከጊዜ ወደ ጊዜ የምርቱ መጠንና ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመምጣቱ በርካታ የተለያዩ አዝርዕት ይመረቱባቸው የነበሩ መሬቶች ወደ ጫት ማሳነት በመቀየር ላይ ይገኛሉ።


በመሆኑም የጤና ጥበቃ ቢሮው በጫት ዙሪያ ያለው ችግርና ወደፊት መስራት ያለባቸው ስራዎች ተወያይቷል። በውይይቱ ከታዩት ውስጥ ዋናው ችግር በጫት ዙሪያ እንደ ክልል ለመከላከልም ሆነ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ህጎች አለመኖሩ ነው።


በጫት ዙሪያ ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከት በመሆኑ በተለይም ጤና ጥበቃ ቢሮን፣ ግብርናን፣ ንግድን፣ አካባቢ ጥበቃን፣ ፖሊሰ ኮሚሽን ባልና ቱሪዝም ወዘተ የጉዳዩን አንገብጋቢነት በመረዳት ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት በመስራት ችግሩን ለመቅረፍ መስራት እንዳለብን ጤና ጥበቃ ቢሮው እያሳወቀ ጤና ቢሮ ምክረ ሀሳብም

 

1. የህግ ማዕቀፍ፡- በክልል ምክር ቤት በኩል ቁጥጥርና ክትትል ለማድረግ የሚያስችሉ ህጎች ቢወጡ፤ ምክንያቱም ጉዳዩ በርካታ ሴክተር መስሪያ ቤቶች በቀጥታም ሆነ ተዘዋዋሪ የሚመለከት በመሆኑ፣


2. ክልከላ፡- ለጫት መቃም ዋና መንስኤ የጫት አቅርቦት በመሆኑ የሚወጡ ህጎች ማተኮር ያለባቸው በቀጣይ ጫት በክልላችን ውስጥ እንዳይመረትና ምርቱም ከሌላ አካባቢ እንዳይገባ በሚያስችል መልኩ ቢሆን ወጣቱን ብሎም የቀጣዩን ትውልድ ጫት በመቃም ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ከመከላከልም አልፎ የታለሙት የልማት አጀንዳዎች ለመተግበር የሚያስችል አቅም ይፈጥርልናል።


3. የማገገሚያ ማዕከላት ግንባታ (rehabilitation centers)፡- በጫት ሱስ የስነልቦናም ሆነ አካላዊ (ፊዚዎሎጂካል) የጤና ችግር ውስጥ የገቡ ሰዎች ከሱስ ለመውጣት የሚያስችል የተሟላ ህክምና መስጠት የሚችል የማገገሚያ ማዕከላት ግንባታ (rehabilitation centers) ማዘጋጀት ያስፈልጋል።


በመሆኑም የጤና ጥበቃ ቢሮው ከላይ የተጠቀሱት ምክረ ሀሳቦች ተወስደው እንዲተገበሩ ያልተቆጠበ ጥረት ይደረግ ዘንድ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ በክልል ለሚገኙ ለሁሉም የዘርፍ መ/ቤቶች ባሰራጨው ስርኩላር ደብዳቤ አሳስቧል።

ግልባጭ
- ለም/ል ቢሮ ኃላፊ
- ለጤናና ጤና ነክ አገ/ግ/ቁጥጥር ዋ/የስራ ሂደት
- ለፈውስ ህክምና ዋ/የስራ ሂደት
ጤና ጥበቃ ቢሮ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1841 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

 • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

 • Aaddvrrt5.jpg
 • adverts4.jpg
 • Advertt1.jpg
 • Advertt2.jpg
 • Advrrtt.jpg
 • Advverttt.jpg
 • Advvrt1.jpg
 • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1015 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us