የዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ 150ኛ የመታሰቢያ ዓመት

Wednesday, 11 April 2018 14:20

የዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ዕለተ-እረፍት 150 ኛ ዓመት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል። ይህንን አስመልክቶ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የተለያዩ የታሪክ ምሁራንን በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ አሰባስቦ ስለዓፄ ቴዎድሮስ ዘመን አይሽሬ አበርክቶቶች አወያይቶ ነበር።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ፣ በአሜሪካው የቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር እና በአሁኑ ወቅት በባሕር ዳር ዩቨርሲቲ የፉል ብራይት ስኮላር የሆኑት ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲው ዶክተር ፋንታሁን አየለ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ኢብራሂም ዳምጠው፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር ግርማ ታያቸውና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብዕ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ካሳሁን ተገኘ ናቸው። በውይይታቸው ላይ ያነሷቸውን አንኳር አንኳር ጉዳዮች በዚህ ጽሑፍ አቅርበንላችኋል፡፡

 

*         *       *

 

አቶ ግርማ ታያቸው ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ለ17 ዓመታት እንደመሩና አበርክቷቸው ግን ዘመን ተሻጋሪ በመሆኑ የሰማዕትነት ቀናቸውን ማክበር እንዳስፈለገ አስረድተዋል፤ “ዓፄ ቴዎድሮስ ትምህርታቸው ብቻ ሳይሆን አነሳሳቸውም ሆነ አወዳደቃቸው ትምህርት ነው። የእርሳቸውን ታሪክ እየዘከሩ አለማስተማር የታሪክ ተወቃሽ ያደርጋል፤ ለዚህም ነው በሰማዕትነታቸው ቀን አስታከን ከገድላቸው ለመማርና ለማስተማር እየታተርን ያለነው” በማለት።

ዶክተር ካሳሁን በበኩላቸው ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስን እንደ አንድ ብሔራዊ ጀግናና ባለራዕይ መሪ ለመዘከር ከአንድ ዓመት በፊት በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥራ መጀመራቸውንና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለዚህ ፊታውራሪ መሆኑን አብራርተዋል። የአንድነት ምልክት የሆኑትን ጀግናችንን ለመዘከርና ለትውልዱ መምህር እንዲሆኑ ለማድረግ እስከ ፌዴራል ላሉ ተቋማት ደብዳቤ መጻፉንና በርካታ የምክክር መድረኮች መፈጠራቸውን፣ የመወያያ ጥናታዊ ጽሑፎች እንዲዘጋጁ አቅራቢዎች መለየታቸውን በቀጣይነትም ሌሎች ሀገራዊ ጀግኖችን ለመዘከር መታቀዱን ተናግረዋል። በዓሉ ከቋራ-ደንቢያ-መቅደላ ድረስ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ መሆኑንም ገልፀዋል።

 

 

*         *       *

 

በምሁራኑ ውይይት ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ የደጃች ካሳን የንግሥና ስም አመራረጥ ንጉሡ ኢትዮጵያን በሚገባ አውቀው ያደጉና በታሪክ የበሰሉ መሆናቸውን ማሳያ አድርገው አቅርበውታል። ፕሮፈሰር ሹመት እንዳሉት ደጃች ካሳ ኃይሉ ዘመኑ የሚሻውን ተቀባይት ለማግኘት ለትልቁ ሕልማቸው ታሪካዊ ስያሜን ሽተዋል። በፍካሬ ኢየሱስ የተቀመጠን የትንቢት ስም ይዘው ዓፄ “ቴዎድሮስ” ተብለው መንገሳቸው ለደረሱበት ስኬት የራሱን አስተዋፅዖ አበርክቷል። “የሀገራችን ታሪክ በወቅቱ በብዙ የሀገር ሽማግሌዎች አዕምሮ የተቀረጸና ለንግርት (ቃላዊ አስተምህሮ) የቀረበ ነበር። ታዳጊዎች፣ እናቶችና አባቶች መደበኛ ትምህርት ቤት ባይገቡም ከታሪክ አዋቂዎች ዘንድ ቀርበው የተለያዩ ታሪኮችን ያደምጡ ነበር። ወጣቱ ካሳም በባሕል ይነገር የነበረውን ታሪክ እየሰሙ ያደጉ በመሆናቸው በአካል ተበታትና በታሪክ አንድ ሆና የሚያውቋትን ሀገር ለማዋሐድ በፍካሬ-ኢየሱስ የተቀመጠውን ትንቢታዊ ንጉሥ ስም በመውሰድ “ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ተባሉ።

በንግሥናቸውም የተከፋፈለችውን ኢትዮጵያን ወደ አንድ ለማምጣት ከፍተኛ መሰዋዕትነት ከፍለዋል፤ ራዕያቸውን ለማሳካት ግን በቂ የስልጣን ጊዜ አላገኙም። ከቆይታ ዘመናቸው በላይ ግን ሠርተዋል። ለንጉሡ በዚህ ደረጃ መቀረጽ በዘመኑ የነበሩ ታሪክ ነጋሪዎች ሚናም መዘንጋት የለበትም፤ ቴዎድሮስን የመሠለ የአንድነት ገመድ አፍርተዋልና። በነገራችን ላይ በዘመነ መሳፍንቱ ኢትዮጵያ ከዚያም በላይ ልትፈራርስ ትችል ነበር፤ ነገር ግን የነበረው ባሕላዊ የታሪክ ትምህርት እንደ ካሳ ያሉ ምሶሶዎችን ፈጠረና ታደጓት። በነገራችን ላይ ዓፄ ቴዎድሮስ ገና ከልጅነታው ጀምሮ የኢትዮጵያን ትናንት፣ ዛሬና ነገ የተረዱ ስለነበሩም ነው የተለዩ የምናደርቸው” በማለት ፕሮፌሰር ሹመት አብራርተዋል።

ዶክተር ፋንታሁን አየለ ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱ ስያሜያቸውን እውን ለማድረግ በቀደሙት ነገሥታት ያልተጀመሩ ዘመናዊ ሠራዊት የመገንባት፣ ሠራዊቱን በደመወዝ የማስተዳደርና ወታደራዊ ማዕርግ የመስጠት፣ በአጠቃላይ ብሔራዊ ጦር በመገንባት አንዲት ታላቅ ኢትዮጵያን የመፍጠር ተግባርን እንደጀመሩ አውስተዋል። “በዘመነ-መሳፍንት የነበረው እያንዳንዱ መስፍን የየራሱ ጦር ነበረው፤ ዓፄ ቴዎድሮስ ግን ያንን በየመሳፍንቱ የተበተነ ኃይል በማሰባሰብ አንድ ብሔራዊ ጦር እንዲሆን አደረጉት፤ ይህም የአንድ ማዕከላዊ መንግሥት ምሥረታው አካል ነበር። ጦራቸውን ብቻ ሳይሆን የጦር ኃይላቸውን የማደርጀትና ዘመናዊ መሳሪያ የማስታጠቅ ራዕይም ነበራቸው። በመጨረሻም ለሕይወታቸው ፍጻሜ መነሻ የሆነውን ይህን ወታደራቸውን የማዘመንና በራስ አቅም የማደርጀት ሕልማቸውን እውን ለማድረግ በጋፋት የጀመሩት የጦር መሳሪያ የኢንዱስትሪ መንደር ግንባታ ነበር” ብለዋል፤ ዶክተር ፋንታሁን።

ረዳት ፕሮፌሰር ኢብራሂም ዳምጠው ደግሞ፣ “ቴዎድሮስ በሽፍታነት ዘመናቸው ከግብፆቹ ጋር ገጥመው መሸነፋቸው የጋፋት የጦር መሳሪያ ማምረት ፅንሰ ሐሳብን ሳይወልድላቸው አልቀረም። ምክንያቱም ያ ሽንፈታቸው ከፍተኛ እልህና ቁጭት፣ በራስ መሳሪያ ጠላትን ማሸነፍ መቻል፣ ዘመናዊ የጦር መሳሪዎችን መታጠቅ፣ … የሚሉ ሐሳቦችን ወልዷልና። ዕውቀታቸውም በጣም ተራማጅ ነበር፤ ዘመኑም አውሮፓውያን አፍሪካንና ሌላውን ዓለም የሚቀራመቱበት ነበር። ትንንሽ የአውሮፓ ሀገራት በታጠቁት ዘመናዊ ጦር በርካታ ሀገራትን እንዳስገበሩና ቅኝ ግዛታቸው እንዳደረጉ ቴዎድሮስ የተረዱና ራሳቸውን በሚገባ አደራጅተው ለመጠበቅ ያሰቡ ይመስላል።

ይህ ሐሳባቸው ጋፋት ላይ ሴባስቶፖል የተሰኘውን መድፍ ወልዷል። ለዚህም ነው የኢትዮጵያ የዘመናዊ ኢንዱስትሪ ፈር ቀዳጅ የምንላቸው። የኢንዱስትሪ አብዮትን በኢትዮጵያ ለመጀመር አቅደው የነበረም ይመስላል፤ ንጉሡ በአሜሪካና አውሮፓ ጥቁሮች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ጭምር ይጠይቁ የነበሩ ተራማጅና ቀደምት ፓን አፍሪካኒስት እንደነበሩ የሚያሳዩ ጽሑፎችም አሉ። ምናልባት የጥቁሮች መመኪያና ጠበቃ የመሆን ሕልም የነበራቸውና ይህንን ለመሆንም በኢትዮጵያ በተመረተ የጦር መሳሪያ የታጠቀ ሠራዊት ለመገንባት ያለሙ ይመስላል” በማለት አብራርተዋል።

ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ደግሞ ስለዓፄ ቴዎድሮስ ወታደራዊ ሕይወት፤ “ቴዎድሮስ በወጣትነታቸው የተሳካላቸው የጦር መሪ ነበሩ። በተለይ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት የየአካባቢውን መስፍን በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበር ድል ያደረጉት። እስከ መጨረሻው የንግሥና ዘመናቸው (ሕይወታቸው) ድረስ የተሸነፉት ሁለት ጊዜ ብቻ ነው፤ የመጀመሪያው የደባርቅ ጦርነት ሲሆን ሁለተኛው የመቅደላው ነው። በመጀመሪያው ጦርነት በጦር መሳሪያ (ትጥቅ) ልዩነት የተነሳ ነበር የተሸነፉት። የጠላት ጦር ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀና የተደራጀ ነበር፤ በአንጻሩ ካሳ ኃይሉ (በኋላ ዓፄ ቴዎድሮስ) ልምድ የሚያንሳቸው ነበሩ፤ አነስተኛ ኃይልና ኋላ ቀር የጦር መሳሪያ ብቻ ይዘው ነበር የገጠሙ። የሆነው ሆኖ ይህ የመጀመሪያ ሽንፈታቸው ቁጭትን ወለደ። ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ለማምረት እስከመዘጋጀት ድረስ አደገ፤ ለቀጣይ ስኬታቸውም ትምህርት ሆኖ አገለገለ።

የመጨረሻው ሽንፈታቸው ግን በመሳሪያ ኃይል ብቻ የመጣ ስለመሆኑ መናገር አይቻልም። ዓፄ ቴዎድሮስ የነበራቸው ሠራዊት እየከዳ አልቆ በጣም ትንሽ ሰዎች ይዘው ነበር እንግሊዞቹን መቅደላ ላይ የጠበቋቸው። በመጨረሻ ኑዛዜያቸው ላይም ሥርዓት ያልያዘ ሠራዊትና ሕዝብ እንደነበራቸውና በዚያ ሁኔታ ድል እንደማይገኝ ገልፀዋል” በማለት ፕሮፌሰር ባሕሩ አስረድተዋል።

ዓፄ ቴዎድሮስ ለመጀመሪያ ጊዜ በተዋረድ 10 አለቃ፣ 50 አለቃ፣ የመቶ አለቃ፣ … የሚሉ ማዕረጎችን ሥራ ላይ ያዋሉና ወታደራዊ አደረጃጀትን ያዘመኑ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ንጉሠ ነገሥት እንደነበሩም ፕሮፌሰር ባሕሩ በንጉሡ ትልቅ አስተዋፅዖነት አንስተዋል። ዶክተር ፋንታሁን ከዚህ ላይ ቀበል አድርገው፣ “ዓፄ ቴዎድሮስ ሕልማቸው ወታደራዊ ዘመቻዎቻቸውን በድል መወጣት ብቻ አልነበረም፤ ይልቁንም ወደ ጠረፍ አካባቢ ባሉት የቋራና አካባቢው ቦታዎች ስላደጉና ተደጋጋሚ ጠላትም ወደ ኢትዮጵያ ሲመላለስ ስላዩ የሀገሪቱን ስትራቴጅካዊነትም ተረድተዋል። ይህንን በመረዳትም አይደፈሬ እንድትሆንና የሚመጡባትን ጥቃቶች ሁሉ መመከት የምትችል እንድትሆን በትጥቅ፣ በወታደራዊ ስነ-ምግባርና በመዋጋት አቅም የዳበረ ሠራዊት መፍጠርን ግብ አድርገው ሠርተዋል። ሀገራዊ ባላንጣዎችን እንጅ አካባቢያዊ (የውስጥ) የስልጣን ሽኩቻን የሚናፍቁ ኃይሎችን በዋነኛ ጠላትነት አልፈረጁም ነበር። ለዚህም ነው ገና በአግባቡ ሳይደራጁ ከግብጹ ሙሐመድ አሊ ጋር በደባርቅ የተዋጉት” ብለዋል።

አቶ ግርማ ደግሞ የዓድዋ አባት ቴዎድሮስ መሆናቸውን ሲያብራሩ፤ “በዓድዋ ድልና በዓፄ ቴዎድሮስ መካከል ያለው ዕድሜ 28 ዓመት ነው። ቴዎድሮስ ዘመናዊ ጦርን ማደራጀት ባይጀምሩ ኖሮ፣ ዓድዋ የዛሬ ገጽታው መኖሩ ያጠራጥረኛል። የኢትዮጵያ ዘመናዊነት አባት የሆኑት ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በመንፈስና በአስተሳሰብ የተቀረጹት በቴዎድሮስ ነው። የቴዎድሮስን ዘመናዊ የወታደራዊ አደረጃጀት እየቀሰሙ ለ10 ዓመታት አብረው የቆዩት ዓፄ ምኒልክ ተምረዋል። ለዚህም ነው የዓድዋ አባት ቴዎድሮስ ናቸው የምለው። በተበታተነና ሥርዓት ባልተበጀለት ወታደራዊ ኃይል ጣሊያንን ማሸነፍ ፈጽሞ አይቻልም ነበርና” ብለዋል።

ፕሮፌሰር ባሕሩም፤ “ቴዎድሮስ ዛሬ ያላቸውን ተቀባይነትና ፍቅር ያኔ አግኝተውት ቢሆን ኖሮ የት ደርሰን ነበር?! ይገርማችኋል!... አብሪ ኮከብ እንደነበሩ የታወቀው ከሞቱ ከመቶ ዓመታት በኋላ ነበር ማለት ይቻላል። ቴዎድሮስ ሐሳባቸው ዘመን ተሻጋሪ፣ በጨለማ ውስጥ እንደ ንጋት ኮከብ ብልጭ ያሉ፣ ግን ጉም የሸፈናቸው ነበሩ። ዛሬ ቆጠራ ቢካሄድ በስማቸው የሚጠራ ብቻ ሚሊዮን ቴዎድሮስ እናገኛለን፤ ያኔ ግን ተቀባይነት ሳያገኙ፤ በመጨረሻም አብዛኛው ሠራዊታቸው ከድቷቸው መቅደላ ላይ በክብር ነፍሳቸውን ከጠላት እጅ ነጠቁ። ቴዎድሮስ ከመቶ ዓመት በኋላ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ገብተዋል፤ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች የስበት ማዕከልም ሆነዋል። ዳሩ ኪነ-ጥበቡ ራዕያቸውን ገልፆ ለሕዝቡ አላደረሰም እንጅ” ሲሉ የታላቁን መሪ ውለታና ለዚህ ውለታቸው የተከፈላቸውን ዋጋ ጠቃቅሰዋል።

የአማራ ክልል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅትና ባሕልና ቱሪዝም በጋራ የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስን 150ኛ ዓመት የሙት ዓመት መታሰቢያ ከሚያዝያ 2 እስከ 8 ቀን 2010 ዓ.ም እያከበሩ ነው።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
396 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 942 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us