የዶ/ር አብይ የአመራር ጥበብ ፍልስፍና

Wednesday, 18 April 2018 13:14

 

የመጽሐፉ ርዕስ፡-          እርካብና መንበር

የገጽ ብዛት፡-             173

ዋጋ፡-                   ብር 85

የመጽሐፉ ዓይነት፡-        ኢ- ልቦለድ

የታተመበት ጊዜ፡-         ታህሳስ 2009

ጸሐፊ፡-                 ዲራአዝ

ዳሰሳ (Book Review)፡-  ፍሬው አበበ

“እርካብና መንበር” ዶ/ር አብይ አሕመድ ወደጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበር መሳብን ተከትሎ ስሙና ገበያው የናኘ መጽሐፍ ነው። ከታተመ አንድ ዓመት የደፈነው ይህ መጽሐፍ ስሙ በድንገት ሊናኝ የቻለው የመጽሐፉ ጸሐፊ (ደራሲ) አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ናቸው የሚል ወሬ በመነገሩ ነው። በእርግጥም ለጉዳዩ ቅርበት ባላቸው ምንጮቼ መረጃ መሠረት የመጽሐፉ ጸሐፊ ዶ/ር አብይ አሕመድ ናቸው።

መጽሐፉ በአራት ክፍሎችና በሰባት ምዕራፎች የተቀነበበ ነው። የመፅሐፉ ዋንኛ ጭብጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነው። ጸሐፊው የሊደርሺፕ ብቃትና ችሎታን በመላበስ ሥልጣንን ለህብረተሰብ ዕድገትና ብልጽግና እንዴት ማዋል እንደሚቻል ይሰብካሉ። ጀብዳዊ፣ ጭካኔ የነገሰበት የኃይላን የሥልጣን አጠቃቀም ታሪክ እንዳልበጀን ጥሩ ጥሩ ማሳያዎችን በማቅረብ ከውድቀታችን እንድንማር ይወተውታሉ።

ዶክተር አብይ ይህን መጽሐፍ ባሳተሙት ወቅት (በ2009 ዓ.ም) በተለይ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ሕዝባዊ አመጾች ተቀጣጥለው ጫፍ የደረሱበትና ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግም ሁነኛ መፍትሔ ለማስቀመጥ አቅም አጥቶ በከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ ሲዋልል የታየበት ወቅት መሆኑን እናስታውሳለን። ምናልባትም ዶክተሩ ይህን መጽሐፍ የተከሰቱ ችግሮችን መነሻ በማድረግ መፍትሔ ፍለጋ አስበውት ያዘጋጁት ሊሆን እንደሚችል የአንዳንድ ወገኖች መላምት አለ። የሚከተለው የመጽሐፉ ሀሳብም ይህንኑ የሚያጠናክር ይመስላል።

“…እንደተራራ ፊታችን ከተከመረው ፍርስራሽ ስር እየተቀሰቀሰ ያለው የለውጥ ምጥ ምንድነው? ከእነዚህ ለውጦች ጋር እንዴት መናበብና አብሮ መጓዝ ይቻላል?...” ሲሉ እየጠየቁ፣ እያሰላሰሉ፣ እየመለሱ…ይቀጥላሉ።

“መሪ መሆን የሚችሉ ሰዎች ግን የመምራት ሥራቸውን የሚጀምሩት ዛሬውኑ ነው” ሲሉም በአጽንኦት ያሳስባሉ። ምናልባትም ዶ/ር አብይ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰየሙ በኋላ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት በጅግጅጋ፣ በአምቦ፣ በመቐሌ፣ በአዲስአበባ…ያደረጓቸው ተከታታይና ጥድፊያ የበዛባቸው ሕዝባዊ መድረኮች “መሪ ሥራውን የሚጀምረው ዛሬውኑ ነው!” ከሚለው ፍልስፍና አዘል አቋማቸው የተቀዳ መሆኑን ያሳብቃሉ።

“የእውነት ለመምራት…

የስኬት ተምሳሌት- እንዲሆን መምራትህ

ውል እንዲይዝ ሥሩ

መምራት እና መግዛት

አይጥፋህ ድንበሩ።

ለምትመራው ጀማ

ራስህን ካልሰጠህ ስስቱን በመተው

“እኔ” ያለ ቀን ነው፣ መሪ የሚሞተው።

የመምራት ኃይልህን…

በቅንነት ያዘው በጥበብ አጽድለው

ምክንያቱም…..

ተመሪ ውስጥ ነው

የመሪ ዕድሜ ያለው።”

ዶ/ር አብይ በመጽሐፋቸው “መሪ በሙሉ ልቡ ሕዝቡን ሊወደውና ሊያምነው ይገባል። እራስን አሳልፎ እስከመስጠት ድረስ ሊፈተን ይችላል። ለሕዝቡ ራሱን የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን ለመርሖዎቹ የሚገዛ መሆን አለበት።… (ገጽ 78፣ 79)” ይሉናል።

ይቀጥሉናም፤ “ፍላጎቱ ስላለን ብቻ የአገር መሪ ለመሆን መጣር ትርፉ ድካም ነው። ችሎታም ብቻ ለመሪነት የሚያበቃ ነገር አይደለም። መሪ የምንሆነው የግል ፍላጎታችንን ለማግኘት አይደለም። መሪ ስንሆን ትልቅ ኃላፊነት እንቀበላለን።….መሪነት ኃላፊነት ለመቀበል የተዘጋጀ ጽኑ ልብን ይጠይቃል። ጽኑ ያልሆነ መሪ ግን ለራሱ ጥቅም ብቻ ከማደሩም ባሻገር የተሰሩ ሥራዎችንም ጭምር ልክ እንደእንቧይ ካብ ይንዳቸዋል።… (ገጽ 93፣94)”

 

ስለሥልጣን እና የሥልጣን ልጓም

…ሥልጣን የሕዝብ ነው ብለው የሚያምኑ መንግሥታት ኃይላቸውን ልጓም አልባ አያደርጉትም። ምክንያቱም ወደላይ ያነሳቸው ሕዝብ የትግዕስቱ ጽዋ የሞላች ቀን ወደታች እንደሚያወርዳቸው ጠንቅቀው ያውቃሉና። ከዚህም ባሻገር ራሳቸውን ሕዝብ አድርገው ስለሚቆጥሩ ኃይላቸውን ያለአግባብ ለመጠቀም ህሊናቸው እሺ አይላቸውም። ለእነዚህ ዓይነት መንግሥታት ሥልጣን የአገር መወከያ፣ ሕዝብን ማገልገያ፣ ልማትን ማቀጣጠያ፣ አገርን ማስከበሪያ፣ ሰንኮፋዎችን ማስወገጃ ወዘተ መሣሪያ ነው።…አንዳንድ መንግሥታት ሥልጣንን ርስት አድርገው ከመመልከታቸውም ባሻገር ሕዝብንም ከመጤፍ የማይቆጠር አድርገው ይወስዱታል።…”

“ፍጹማዊ ሥልጣን ያባልጋል!”

“እውነት ነው፣ ፍጹማዊ ሥልጣን ደግሞ የባለጌ ባለጌ እንደሚያደርግ የሮማ ካቶሊክ ሊቀጳጳስ አቡነ ጎርጎሪያ ሶስተኛ የተናገሩት ሀሳብ ግሩም ምስክር ይሆናል” ይላሉ ጸሐፊው። “…ድሮም ሆነ ዘንድሮ የመንበር ጥማት ያው የመንበር ጥማት ነው። ከብዙዎች ልብ ተፍቆ አልወጣም። ሥልጣን ቢሰሩበትም ባይሰሩበትም እርካቧን የረገጠ፣ ኮርቻዋን የተቆናጠጠ፣ መንበሯ ላይ የተደላደለ ሁሉ (ቢያንስ አብዛኛው) በሞቱ እንጂ በፈቃዱ ሊለያት የማይሻ ጦሰኛ ፍቅሯ ተቀፍድዶ ይኖራል። አፍቃሪዋም ዘመኑን ሁሉ ሲጨነቅና ሲጠበብ ዕድሜውን የሚገብርላት፣ የክብሩ ዘውድ ወይም የመራራ ውርደቱ ጽዋ ትሆናለች።…”

ስለችግር አፈታት የሚነግሩን የአልበርት አንስታይንን ጥቅስ በማስቀደም ነው። “ችግሩን በፈጠረው አስተሳሰብ፣ ችግርን መፍታት አይቻልም።”

“የአበው ውብ ብሂል…

ከችግር አላቆ መፍትሔን ቢጠራም

እሾህን በእሾህ ለችግር አይሰራም።

እናም..

መንገዱን ለውጦ

ሌላ ሀሳብ ለማዝመር

ከልብ ካቆረጠ..ከሆነ ስስታም

በችግር አምጪ ሀሳብ

ችግሩ አይፈታም።” ይሉናል።

እናም ዶ/ር አብይ ችግሮችን ለመፍታት አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ መንገድ… ያስፈልጋል እያሉን ነው። መንገዳቸው የተቃና እንዲሆን ምኞታችን ነው።

ይምረጡ
(7 ሰዎች መርጠዋል)
1012 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1096 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us