ኢትዮ ቴሌኮም በዘጠኝ ወራት ብቻ 20 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አገኘ

Wednesday, 23 May 2018 13:55

 

·        የኢንተርኔትና ዳታ ተጠቃሚዎች ቁጥር 16 ሚሊየን ደርሷል፣

 

ኢትዮ ቴሌኮም በ2010 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቴሌኮም አገልግሎት 27 ነጥብ 79 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ እና ከታክስ በፊት 19 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ትርፍ ማግኘቱን ይፋ አደረገ።

ኢትዮ-ቴሌኮም ለሰንደቅ ጋዜጣ በላከው መግለጫ እንደጠቀሰው በአሁኑ ወቅት በሁሉም የአገልግሎት ዓይነቶች የኩባንያው ደንበኞች ብዛት 66 ነጥብ 2 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር አጠቃላይ የደንበኞች ብዛት በ17 በመቶ እድገት አሳይቷል። የሞባይል ደንበኞች ብዛት 64 ነጥብ 4 ሚሊዮን መድረሱን፣ ይህም ከእቅዱ አንፃር 97 በመቶ እድገት ማሳየቱን አስታውቋል።

በተጨማሪም የኢንተርኔትና ዳታ ተጠቃሚዎች ቁጥር 16 ሚሊዮን የደረሰ መሆኑን ጠቁሞ ይህ አፈፃፀም የዕቅዱን 77 በመቶ ነው ብሏል። የመደበኛ ስልክ ደንበኞች ቁጥር 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በማሳካት ከዕቅዱ ጋር ሲነፃፀር የ75 በመቶ አፈፃፀም አሳይቷል።

ኩባንያው በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የተሻለ የአገልግሎትና የምርት አማራጭ በማቅረብ 29 ነጥብ 95 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ለማስገባት አቅዶ 27 ነጥብ 79 ቢሊዮን ብር በማከናወን የእቅዱን 93 በመቶ ያሳካ ሲሆን፤ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ15 በመቶ እድገት አሳይቷል።

ከሞባይል አገልግሎት የተገኘው ገቢ ከአጠቃላይ ገቢው 75 ነጥብ 3 በመቶውን ሲሸፍን፣ ዲታና ኢንተርኔት 17 ነጥብ 1 በመቶ እንዲሁም ዓለም አቀፍ አገልግሎት 5 ነጥብ 2 በመቶ ድርሻ ይይዛሉ።

የኩባንያው ያልተጣራ የትርፍ መጠን (ከታክስና ሌሎች ተቀናሾች በፊት የተገኘ ጥቅል ገቢ 19 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ አፈፃፀሙ 19 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ጥቅል ገቢ ከታክስና ሌሎች ተቀናሾች በፊት የተገኘ ሲሆን፣ ይህም የእቅዱን 102 በመቶ አፈፃፀም ያሳያል። ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ7 በመቶ ጭማሪ ያሳያል።

በ2010 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 26 አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶችን ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ታቅዶ 19 አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶችን ለገበያ በማቅረብ አፈፃፀሙ 73 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል። የቀረቡ ምርትና አገልግሎቶችም ኢትዮ ሰልፍ ኬር፣ ዳታ ካልኩሌተር፣ የመደበኛ ስልክ ጥቅል፣ ሀይብሪድ ሲም አካውንት፣ M2M offer (የማሽን ቱ ማሽን አገልግሎት)፣ ኦልተርኔቲቭ ቻናል፣ የሞባይል የድምፅ ጥቅል፣ የVIP ጥቅል፤ የድምፅ ትራንዚት ጥሪ፣ ሮሚንግ IOT discount ፍሬምወርክ፣ ለድምፅ ማሳመሪያ አይ. ቪ. አር፣ ZTE 3G ዋይፋይ እና ሞደም፣ ይሙሉ etop up via external distributor፣ የIPDC O&M support እና የዳታ ሴንተር colocation ታሪፍ ናቸው።

በተጨማሪም የደንበኛን እርካታ ማምጣት የሚችሉ አገልግሎቶችን በማሻሻል እንደ ዳታ ሮሚንግ ታሪፍ ማሻሻል፣ የሳተላይት አገልግሎት ታሪፍ ማሻሻል፣ የቀፎ ሽያጭ ፕሮሞሽን፣ የቅዳሜ እና እሁድ የሞባይል ኢንተርኔት ጥቅል አገልግሎት፣ የሞባይል ቀፎ ጥቅል አገልግሎትና ሌሎች አገልግሎቶች ተግባራዊ ተደርገዋል።

በተለይም ባለፉት ዓመታት በዘርፉ የተመዘገበውን አመርቂ ውጤት በማስመልከት ኩባንያው በተከታታይ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ከሚገኙ በዘርፉ ከፍተኛ ዕውቅና ካላቸው ተቋማት ዕውቅና የተቸረው ሲሆን ተቋሙ ብቃቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ የማሳደግ እንቅስቃሴውን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጫው ጠቅሷል።

ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያጋጠሙትንም ተግዳሮቶች ዘርዝሯል። የቴሌኮም ማጭበርበር ዓለም አቀፍ የድምጽ ጥሪዎችን በመቀነስ በኩባንያው ገቢ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ከማሳደሩም ባሻገር ደንበኞች ላይ የተለያዩ የማጭበርበር ድርጊቶች በመፈፀማቸው፤ ኢትዮ ቴሌኮም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ከመሥራቱም ባሻገር ህብረተሰቡን ጨምሮ ከልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሷል።

ከኬብሎች መቆረጥ አንፃር ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ በፋይበርና በኮፐር ኬብሎች ላይ የሚደርሰው አደጋ ተደጋጋሚ መሆንና መሠረተ ልማቱን ለአደጋ የማጋለጥ ተግዳሮት አንዱና ዋነኛው ነው። ችግሩን ለመፍታትም የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ መሆናቸውን የኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዲፓርትመንት የላከልን መግለጫ አትቷል።  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
85 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 896 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us