የምህረት ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማው ቀረበ

Wednesday, 06 June 2018 13:37

 

የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ትላንት ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ከተመለከታቸው አጀንዳዎች መካከል የምህረት አሰጣጥ እና አፈጻጸም ሥነሥርዓት ረቂቅ አዋጅ አንዱ ነበር። ረቂቅ አዋጁ ምህረት መቼ እና በምን ሁኔታ እንደሚሰጥ ይዘረዝራል። ትላንት ረቂቅ አዋጁ ለም/ቤቱ በቀረበበት ወቅት ጠንከር ያለ ተቃውሞ ሁሉ አስተናግዷል። አንድ የምክርቤት አባል ይህ አዋጅ ኮንትሮባንዲስቶች፣ ሌቦች ለመታገል የተገባውን ቃል ወደጎን በማድረግ በዚህ የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን ከእስር ከፈቱ በኋላ ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት የቀረበ ይመስላል። የፖለቲካ ሙስና ይህ መንግሥት እየፈጸመ ነው ሲሉ ተቃውመውታል። አንድ እስረኛ በምህረት ሲለቀቅ የተጎጂ ቤተሰቦችን ይሁንታ ቢገኝ የበለጠ ጥሩ ነው በሚል አስተያየት የሰጡ ሲኖሩ በረቂቅ አዋጁ እያንዳንዱ ምህረት የሚደረግለት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል ለፓርላማው ቀርቦ የሚፈጸም መሆኑ አሠራሩን የተንዛዛ ስለሚያደርገው አስፈጻሚ አካሉ ዝርዝሩን ቢያስፈጽም በሚል አስተያየት የሰጡ አባል ነበሩ።

ምህረት ሕገ መንግስታዊ ይዘት ያለው በአብዛኛው የፖለቲካ ጥፋቶችን፣ ሀገር መክዳት፣ የአመጽ ወንጀሎን እና በሀገርና በመንግስት ላይ አመፅ ማነሳሳት ወንጀል ለፈጸሙና በሕግ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ሰላማዊ ኑሮአቸው ተመልሰው የመንግስትን ሕግ እና ሥርዓት ለማክበር ግዴታ ለሚገቡ ጥቂት ወይም መላው ወንጀለኞች መንግስት ያለፈውን ጥፋታቸውን ሙሉ በሙሉ ይቅር የሚላቸው ሥርዓት ነው።

ረቂቅ አዋጁ ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮምቴ ተመርቷል።

የረቂቅ አዋጁ ጭብጥ እንደሚከተለው ተስተናግዷል።

የምህረት አሰጣጥና አፈፃፀም አዋጅ አጭር ማብራሪያ

መግቢያ

ምህረት የሀገርን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በተወሰኑ የወንጀል አይነቶችና በአንድ ደረጃ ለሚገኙ ተጠርጣሪዎች ወይም ወንጀለኞች ላይ ምርመራ ወይም የክስ ሒደት ከማስቀጠል ወይም ቅጣትን ከማስፈፀም ይልቅ ምህረት የተሻለ ውጤት ያመጣል ተብሎ ሲታሰብ የሚሰጥ ነው።

አንዳንድ ፀሐፊዎች እንደሚሉት በ404 ምዕተ ዓመት በግሪክ አቴንስ የመጀመሪያው ምህረሰት እንደተሰጠ ያስቀምጣሉ። በአሜሪካ በ1788 ዓ.ም የመጀመሪያው ምህረት በፕሬዘዳንቱ አማካኝነት እንደተሰጠ ይነገራል። በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድን አገዛዝ ማብቃት ተከትሎ በወቅቱ ለተፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶች ምህረት ለማድረግ የእውነትና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን (truth and reconciliation commission) ተቋቁሞ በፕሬዝዳንቱ አማካኝነት ምህረት ተደርጓል። በኡጋንዳም በየጊዜው እንደየጉዳዩ እየታየ የሕግ አውጪው በሕግ ምህረት ይሰጣል።

በብዙ ሀገራት ልምድ ለማየት እንደሚቻለው በአብአዛኛው ምህረት የሚሰጠው መንግስትን በኃይል ለመገልበጥ ከሚደረግ የወንጀል ድርጊት በኋላ፣ ከእርስ በርስና ዓለም አቀፍ ጦርነት በኋላ የሚኖሩ ፖለቲካዊ ብጥብጦችና አለመግባባቶች ለማርገብ፣ በብጥብጡ ምክንያት የተከፋፈለን ማህበረሰብ አንድነት ለመመለስ መጠነኛ የመንግስትንና የሀገር ሰላም የማደፍረስ ድርጊት ለመፈፀሙና ወደ ሰላማዊ አኗኗር ለመመለስ ፍቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ነው።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን የሚያደፈርሱ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ወቅት የማሕበረሰቡን ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በተሻለ መልኩ ለመጠበቅ ምህረት መስጠት የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ምህረት የሚሰጥበትን ሥነ-ሥርዓት በሕግ መደንገግ ስለሚያስፈልግ የምህረት አሰጣጥና አፈፃፀም ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ማውጣት አስፈላጊ ይሆናል። በዚህም መሠረት አዋጁ በአራት ክፍሎና በአስራ ስድስት አንቀፆች ተከፋፍሎ ተዘጋጅቷል።

የረቂቅ አዋጁ ዝርዝር ይዘት

ስለ ምህረት ቦርድ

የረቂቅ አዋጁ ክፍል ሁለት ከአንቀጽ 4-8 ሲሆን በአንቀጽ 4 የምህረት ቦርድ ተመስርቷል። በአብዛኛው ምህረት የሚሰጠው የአገርን ሰላምና መረጋጋት አደጋ ላይ ለሚጥሉ የወንጀል ዓይነቶች ስለሆነ የቦርዱ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ተደርጓል። አንቀጽ 5 የምህረት ቦርዱን አባላት ስብጥር የያዘ ነው። ምህረት ከወንጀልና ቅጣት እንዲሁም ከሰላምና ደህንነት ጋር የተቆራኘ በመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የምህረት ቦርዱ ሰብሳቢ እንዲሆን ተደርጓል። በአብዘኛው ምህረት የሚሰጠው የሀገርን ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ውስጥ ከሚጥል የወንጀል ድርጊት በኋላ በመሆኑ ተገቢውን ውሳኔ ለማስተላለፍና የተፈለገውን ውጤት ለማግኘት የተለያዩ የመንግሥት ሥራ አስፈፃሚ አካላትና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማትና ግለሰቦች በሂደቱ እንዲሳተፉ ማድረግ ተገቢ ነው። በዚህም መሰረት የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር፣ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚወክል አንድ ዳኛ፣ መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰየሙ ሁለት ሰዎች የቦርድ አባላት እንዲሆኑ ተደርጓል።

የረቂቅ አዋጁ ከአንቀጽ 6-8 ስለ ምህረት ቦርዱ ሥልጣን እና ተግባር፣ የውሳኔ አሰጣጥ ሥነ -ሥርዓት እና ስለ ቦርዱ ጽህፈት ቤት ይደነግጋል። ቦርዱ የምህረት ጥያቄዎችን ይቀበሀላል፣ ይመረምራል የውሳኔ ሀሳብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀርባል። ውሳኔውንም በአብላጫ ድምጽ ያስተላልፋል። ምህረት በተወሰነ ጊዜ ለሚፈፀሙ ድርጊቶች የሚሰጥና የሙሉ ጊዜ ሥራ የማይፈልግ ከመሆኑ አንጻር እንዲሁም ለቦርዱ አዲስ ጽህፈት ቤት በማደራጀት በመንግሥት ላይ አስተዳደራዊ ወጪ ከማስከተል ይልቅ በቦርዱ ሰብሳቢ መስሪያ ቤት ማለትም በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ውስጥ በተደራጀው የይቅርታ ቦርድ ጽህፈት ቤት የቦርዱ ጽሕፈት ቤት እንዲሆን ማድረግ የተሻለ አማራጭ እንዲሆን ተደርጓል።

ስለምህረት አሰጣጥ እና አፈፃፀም

ይህ ክፍል ከአንቀጽ 9 እስከ 12 የያዘ ሲሆን አንቀጽ 9 ምህረት የሚሰጥባቸውን ጉዳዮች የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሀገርን ሠላምና ደህንነት ማስጠበቅ ካለው ኃላፊነት እንዲሁም ምህረት ከሚያሰጡ የወንጀል ድርጊቶች ጋር ካለው ቅርበት አንጻር በራሱ ተነሳሽነት ወይም ከክልሎች በሚቀርብ ጥያቄ ምህርት የሚሰጥባቸውን ወንጀሎች እና በወንጀል የተጠረጠሩ ወይም የወንጀል ፍርድ የተላለፈባቸው ሰዎች ለይቶ ለቦርዱ እንዲያቀርቡ ያደርጋል።

የአዋጁ አንቀጽ 10 ደግሞ ምህረትን ለመስጠት ከግምት ውስጥ የሚገቡ ሁኔታዎችን የሚያስቀምጥ ሲሆን ምህረት ለመስጠት ምህረት የተጠየቀበት የወንጀል ድርጊት በሀገር ሉአላዊነት ላይ የሚያስከትለው ወይም ያስከተለው ተፅዕኖ፣ ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ ምህረት የተሻለ አማራጭ ስለመሆኑ እና ምህረት የሚደረግላቸው ሰዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ የሚያሳዩት ፍላጎት ከግምት ውስጥ እንደሚገባ በግልፅ ያስቀምጣል።

የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 11 ምሕረት የሚሰጥበትን አግባብ የሚያስቀምጥ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከምህረት ቦርዱ የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ ከተቀበለ በጉዳዩ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ረቂቅ የምህረት አዋጅ እንዲያዘጋጅ ያደርጋል። በመቀጠልም ረቂቅ የምህረት አዋጁ እንደማንኛውም ሕግ ተገቢውን የሕግ አወጣጥ ሂደት ተከትሎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲፀድቅ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ምህረቱን ያስፈፅማል። ምህረቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል እንዲታይ የሚርብበት ምክንያት በኢትዮጵያ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 230(1) ላይ የምህረት አሰጣጥ በሕግ እንደሚወሰን በመደንገጉ ነው። የማውጣት ሥልጣን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመሆኑ ምሕረቱ በሌላ አካል እንዲታይ ማድረግ የሚቻል ባለመሆኑ ነው።

የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 12(1)(ሀ-መ)ምህረት ከወንጀልና ከፍትሐ ብሔር ተጠያቂነት አንፃር የሚያስከትለውን ውጤት ያስቀምጣል። በዚህም መሠረት ምርመራ ወይም ክስ እንዳይጀመር ወይም የተጀመረ ምርመራ ወይም ክስ እንዳይቀጥል ወይም ቅጣት እንዳይፈፀም ያደርጋል፣ እንዲሁም የጥፋተኝነት ውሳኔም እንዳልነበረ ያስቆጥራል። በተጨማሪም የፍትሐ ብሔር ተጠያቂነትን በተመለከተ በምህረት አዋጁ በልዩ ሁኔታ ካልተገለፀ በስተቀር ለመንግስት ሊከፈል የሚገባውና ገና ያልተከፈለ ኪሳራ በምህረት ቀሪ እንደሚሆን በግልፅ ተቀምጧል። ነገር ግን በፍትሐ ብሔር በኩል የጠፋውን እንደነበረ የመመለስና በተበዳዩ ላይ ለደረሰው ጉዳት የሚከፈለውን ካሳና ኪሳራ እንደማያስቀር በዚሁ አንቀጽ 12(2) ላይ ተደንግጓል።

ማጠቃለያ

የአዋጅ ምህረት ሕገ መንግስታዊ ይዘት ያለው በአብዛኛው የፖለቲካ ጥፋቶችን፣ ሀገር መክዳት፣ የአመጽ ወንጀሎን እና በሀገርና በመንግስት ላይ አመፅ ማነሳሳት ወንጀል ለፈጸሙና በሕግ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ሰላማዊ ኑሮአቸው ተመልሰው የመንግስትን ሕግ እና ሥርዓት ለማክበር ግዴታ ለሚገቡ ጥቂት ወይም መላው ወንጀለኞች መንግስት ያለፈውን ጥፋታቸውን ሙሉ በሙሉ ስሪየት የሚያደርግበት ሥርዓት ነው። ምህረት መብት ሳይሆን የሀገርን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በተወሰኑ የወንጀል ዓይነቶችና በአንድ ደረጃ ለሚገኙ ተጠርጣሪዎች ወይም ወንጀለኞች ላይ ምርመራ ወይም የክስ ሒደት ከማስቀጠል ወይም ቅጣትን ከማስፈፀም ይልቅ ምህረት የተሻለ ውጤት ያመጣል ተብሎ ሲታሰብ የሚሰጥ ነው።

ከተለያዩ ሀገራት ልምድ ለማየት እንደሚቻለው በአብዛኛው ምህረት የሚሰጠው መንግስትን በኃይል ለመገልበጥ ከሚደረግ የወንጀል ድርጊት በኋላ፣ ከእርስ በርስና ዓለም አቀፍ ጦርነት በኋላ የሚኖሩ ፖለቲካዊ ብጥብጦችንና አለመግባባቶች ለማርገብ፣ በብጥብጡ ምክንያት የተከፋፈለን ማህበረሰብ አንድነት ለመመለስ መጠነኛ የመንግስትንና የሀገር ሰላም የማደፍረስ ድርጊት ለፈፀሙና ወደ ሰላማዊ አኗኗ ለመመለስ ፍቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ነው።

በመሆኑም በሀገራችን ውስጥ ሠላምና መረጋጋትን የሚያደፈርሱ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ወቅት የማህበረሰቡን ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በተሻለ መልኩ ለመጠበቅ ምህረት መስጠተ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ነው። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገመንግስት አንቀጽ 28 በስብዕና ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች በምህረት እንደማይታለፉ የሚደነግግ ሲሆን፣ በሌሎች የወንጀል ጉዳዮች ምህረትን በህግ መስጠት የሚቻል ስለመሆኑ አመላካች ነው። የ1996 ወንጀል ሕጉ በሕግ ምህረት መስጠት የሚቻልበትን ሁኔታ የሚደነግግ ቢሆንም ምህረትን የሚመለከተው ሥነ-ሥርዓት ሕግ እስከ አሁን በሕግ አውጪው ወጥቶ ሥራ ላይ አልዋለም።

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
2604 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 847 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us