“ሙስና አምስተኛው መንግስት ነው የሚባለው የተደራጀ መዋቅራዊ ቡድን በመሆኑ ነው”

Wednesday, 20 June 2018 13:08

“ሙስና አምስተኛው መንግስት ነው የሚባለው የተደራጀ መዋቅራዊ ቡድን በመሆኑ ነው”

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ

 

ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት ገዢው ፓርቲ ሶስት የደርጅቱ ሊቀመንበሮችና የመንግስት ጠቅላይ ሚኒስትሮችን አሳይቶናል። የፓርቲውም የመንግስትም ስልጣን የሚወከለው በድርጅቱ ሊቀመንበር መሆኑን እስካሁን ያለው የድርጅቱ ልምድ ያሳያል። እንደአሰራርም ልክ ነው አይደለም የሚል ክርክር ውስጥ መግባት አይቻልም። ባይሆን ጥሩ ነው ብሎ መሞገት ይቻል ይሆናል፤ ለውይይት ክፍት ነው።

እንደተራ የቀበሌ ነዋሪ ያስተዋልነው ግን የድርጅቱ የፓርቲና የመንግስት አሰያየም፣ ፓርቲና መንግስት ጋብቻ እንዲፈጽሙ ነው፤ ያደረገው። ጋብቻውም በሕዝብና በሀገር ላይ ያደረሰው ውድቀት፣ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የፓርቲ መዋቅር በሲቪል ሰርቪሱ በመዘርጋት አንደኛና ሁለተኛ ዜጎችን ፈጥሯል። ፓርቲው በንግድ ሥርዓት ውስጥ አባላቱን እየሰገሰገ የገበያ ውድድር እንዳይኖር ከማድረጉም በላይ የገበያ ሞኖፖሊ ፈጥሯል። የዚህ ሕገወጥ አሰራር ውጤት በዴሞክራሲው ሒደት ላይ ያለውን አሻራ እያሳየን ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ፣ “የኢኮኖሚ አሻጥር እየተሰራብኝ ነው” ሲሉ ለሕዝብ ክስ አሰምተዋል። የትኛው የግሉ ዘርፍ ባለሃብት ነው ለኢኮኖሚ አሻጥር የሚበቃው? የግሉ ባለሃብት በሀገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ላይ ያለው ድርሻ፣ ለአሻጥር የሚበቃ ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት የኢኮኖሚ ባለሙያ ጠበብት መሆን አይጠይቅም።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ላይ የኢኮኖሚ አሻጥር ሊፈጥሩ የሚችሉት ሁለት አካሎች ብቻ ናቸው። አንደኛው ሥርዓቱ እንደአሸን የፈለፈላቸው ለኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነት እየተጉ ያሉ ኃይሎች ናቸው። ሁለተኛው፣ ኢሕአዴግ በመሰረቱ ፓርቲዎች የሚተዳደሩት የንግድ ድርጅቶች ናቸው። ሁለቱም የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጽሙት አካሎች የሥርዓቱ ውጤቶች ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በፓርላማ ቀርበው፣ “መንግስት በመንግስት ሌቦች አንድ እጁን ታስሮ ነው፤ እየሰራ ያለው” ማለታቸው የሚታወስ ነው። እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስተር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ በሲቨል ሰርቪስ በተጠና ጥናት መነሻ ከፍተኛ የፓርቲና የመንግስት ባለስልጣኖች በተገኙበት የስብሰባው ማጠቃለያላይ፣ “ከዚህ ውይይት ስትወጡ ሁላችሁም የኪራይ ሰብሳቢ ኔትዎርካችሁን ከለላ ለመስጠት እንደምጥሯሯጡ አውቃለሁ” ማለታቸውም በጣም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ዛሬ ላይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስር ዐብይ አሕመድ አሁን የተደረሰበትን የሙስና አደጋ አነፃጽረው፤ “ሙስና አምስተኛው መንግስት ነው የሚባለው፤ የተደራጀ መዋቅራዊ ቡድን በመሆኑ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አይይዘውም፤ “መጠኑ ይስፋም ይነስ እንጂ ሌብነት ከጫፍ እስከ ጫፍ አለ። በሃይማኖት ተቋማት፣ በትምህርት ተቋማት፣ በመንግስት ተቋማት አለ” ብለዋ። በዚህ አገላለፃቸው፤ የአንድ ሕብረተሰብ የሞራል ደረጃ ማሳያ መሆን የሚጠበቅባቸው የኃይማኖት እና የትምህርት ተቋመት መዘፈቃቸውን ይፋ ማድረጋቸው በግልባጭ፤ የሕብረተሰቡን የሞራል ደረጃ ዝቅጠት ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ለሙሰኞችም ያስተላለፉት መዕክት፣ “ማሰር የማይችል መንግስት አድርጎ የሚያስበን ሰው አለ፤ ግን ማሰር ከአባቶቻችን ጀምሮ ነበር፤ አዲስ ነገር አይደለም፤ እጃቸውን መሰብሰብ ያለባቸው ግን አሉ” ሲሉ ነጥለው አስጠንቅቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእርግጠኝነትና በድፍረት፣ “ሃብት የዘረፉ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ። ሌቦች አሉ። ሌቦች እንዳልታወቀባቸው ነገር እየሸረቡ ነው። እርምጃ እንወስዳለን። ስርዓቱ እኩል አይን የለውም። አጣርተን እናስራለን እንጂ አስረን አናጣራም” ሲሉ ተናግረዋል። ማስጠንቀቂያም አከል አድርገው፣ “የመንግስት ባለስልጣን በስራ ላይ እያለ ነጋዴ፣ ሀብታም መሆን አይችልም፤ ነጋዴ፣ ሀብታም መሆን ካማረው ቢሮውን ለቆ መሄድ አለበት” ብለዋል። በተመሳሳይ ሁኔታም፣ አቶ መለስ “ጣታቸውን እንቆርጣለን” ሲሉ አቶ ኃ/ማሪያም በበኩላቸው፣ “ሙሰኞችን መታገል የህልውና ጥያቄ ነው”፣ ነበር ያሉት።

ከላይ ከሰፈረው የድርጅቱና የመንግስት ጠቅላይ ሚኒስትሮች በሙስና ላይ ያላቸው አመለካከትና ቁርጠኛ የመሆን መንፈሳቸው በጣም ተመሳሳይነት አለው። ከዚህ መረዳት የሚቻለው የሙስናውን ሳይክል ለመበጠስ አደገኛ አደናቃፊ የሆነ መስመር፤ በድርጅቱ ውስጥ መኖሩ ነው። በርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የበለጠ ነገር ሊያሳዩን የሚችሉበት እድል እንዳለ ከግምት መውሰድ ይቻላል። በቀላሉ ግን ይተገበራል ማለት አይደለም። ጊዜ የሚፈልግ ሥራ ነው።

በዚህ ጽሁፍ ማሳየት የተፈለገው፣ ኢሕአዴግ እንደድርጀት እንደመንግስት የሙስና አባት መሆኑን መቀበል ነው። ይህም ሲባል፣ ሙስና በኢትዮጵያ መንግስትና በበገዢው ፓርቲው ውስጥ የተደራጀ መዋቅራዊ ይዘት ይዟል። አንዱ ከሌላው በተለየ መልኩ “ሙሰኛ አይደለሁም” በሚሉበት የፖለቲካ ቁመና ውስጥ አይደሉም። እንደሚታወቀው፣ ከዚህ በፊት የሙስናው መተጋገል በፓርቲው መዋቅራዊ አደረጃጀት ላይ ባላቸው አቅም የሚወሰን ነበር። አሁን የተለየ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ስለሚገኙ፤ ለውጥ ይጠበቃል።

የለውጡ ዋና ተዋናይ ደግሞ ሕዝቡ ነው። አብዛኛው ሕዝብ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ቅቡልነት ሰጥቷል። ይህንን የህዝብ ድጋፍ በትክክል መረዳት የሚችል የመንግስት ኃላፊ፣ የሙስና መዋቅራዊ አደረጃጀቱን ለመበጣጠስ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ብቻ ነው፤ የሚጠበቅበት። ሙሰኞቹ ሕዝቡ ውስጥ ነው፤ ያሉት። ሕዝቡ የሚያምነው የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያለው መሪ ካገኘ፤ ሙስናን ለማጥፋትና የሚጠየፈው ማሕበረሰብም ለመፍጠር በጣም ቀላል ነው።

አቶ መለስና አቶ ኃ/ማሪያም ያልነበራቸውን የህዝብ ድጋፍ የተቸሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ከእሳቸው የሚጠበቀው፤ ውሳኔያቸው ብቻ ነው።¾

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
208 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 920 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us