የኢትዮጵያ ቀጣዩ በጀት ምን ይነግረናል?

Wednesday, 04 July 2018 12:52

·        በአጠቃላይ 346 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ተበጅቷል

·        111 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ከውጭና ከአገር ውስጥ ብድርና ዕርዳታ የሚገኝ ነው

·        59 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ታይቷል

 

 

የ2011 የኢትዮጵያ መንግሥት በጀት 346 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር እንዲሆን ለፓርላማው ረቂቅ አዋጅ ቀርቧል፡፡ ፓርላማው ከሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በፊት ያጸድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ በጀት ከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር አጣጥሞ ሲዘጋጅ የሚከተሉት የአጠቃላይ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ታሳቢ መደረጋቸውን ዶ/ር አብርሃም ተከስተ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር በቅርቡ ረቂቅ በጀቱ ለፓርላማ በቀረበበት መድረክ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ታሳቢ ከተደረጉት አበይት ነጥቦች መካከል፡-

 

 •   ባለፉት ዓመታት የታየው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይ እንደሚሆንና በ2011 በጀት ዓመት ኢኮኖሚው በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ በተመለከተው ግብ አንጻር በ11 በመቶ እንደሚያድግ ታሳቢ ተደርጓል፤
 •   የዋጋ ዕድገትም በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተቀመጠው ግብ መሠረት በ2011 የ8 በመቶ አማካይ የዋጋ ዕድገት እንደሚኖር ታሳቢ ተደርጓል፡፡ በያዝነው የ2010 በጀት ዓመት እስካሁን የታየው የዋጋ ዕድገት ለ2011 ከተያዘው ግብ አንጻር በተወሰነ መልኩ ከፍ ያለ ቢሆንም በበጀት ዓመቱ መጨረሻ እየተረጋጋ እንደሚሄድ ተገምቷል፡፡
 •    ከዚህም ጋር ተያይዞ የአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት በጊዜው የገበያ ዋጋ (Nominal GDP) በ2011 በጀት ዓመት የ19 በመቶ ዕድገት እንደሚኖረው ግምት ተወስዷል፡፡
 •    በ2011 በጀት ዓመት የገቢ ዕቃዎች ወጪ (Value of goods import) የ9 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት እንደሚኖረው እና ይህም ከገቢ ዕቃዎች ለሚሰበሰበው የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ መሰረት ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የ2011 የውጭ ምንዛሬ ትንበያ ለበጀቱ ታሳቢ ተወስዷል፡፡

በፊስካል ፖሊሲው ረገድ በጀቱ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ማዕከል ያደረገ እንዲሆንና የፈጣንና ዘላቂ ልማቱን፣ የድህነት ቅንሳን፣ እንዲሁም ትራንስፎርሜሽንን የሚደግፍ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ በሌላ በኩል በ2010 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ ከታቀደው ብር 201 ቢሊዮን የፌዴራል መንግሥት የታክስ ገቢ በጀት ውስጥ ከብር 50 ቢሊዮን በላይ እንደማይሰበሰብ እና ለ2011 የተያዘው የታክስ ገቢ ግምት ከ2010 አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር በጣም የተለጠጠ ዕቅድ እንደመሆኑ መጠን የታክስ አስተዳደሩን በልዩ ሁኔታ ማጠናከር የሚጠይቅ ነው፡፡ እንዲሁም እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት የታክስ ገቢ አቅም እንደሚፈጥርና አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ግምት ውስጥ ገብቷል፡፡ ለታክስ ገቢ አሰባሰቡ መጠናከር የታክስ አስተዳደሩን አቅም በመሠረታዊነት ለመቀየር የሚያስችል የአቅም ግንባታና ሌሎች ድጋፎች የሚደረግ ሲሆን፣ መንግስት የታክስ አጀንዳን ቅድሚያ ትኩረት አድርጎ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡ መላ የኢትዮጵያ ህዝቦችና ግብር ከፋዮችም ለበጀት ዓመቱ የተያዘው የታክሲ ገቢ ተሟልቶ እንዲሰበስብ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

 

 

ዶ/ር አብርሃም እንደሚሉት የፌዴራል መንግስት የ2011 በጀት ዓመት ገቢ የውጭ ዕርዳታን ጨምሮ ብር 254 ነጥብ 8 ቢሊዮን እንደሚሆን ታቅዷል፡፡ ይህም በያዝነው በጀት ዓመት የታወጀውን ተጨማሪ በጀት ጨምሮ ይሰበሰባል ተብሎ ከታቀደው ገቢ ጋር ሲነጻጸር የ1 በመቶ ዕድገት እንደሚኖረው የተገመተ ሲሆን በበጀት ዓመቱ ይሰበሰባል ተብሎ ከተገመተው አንጻር ደግሞ የ11 ነጥብ 9 በመቶ ዕድገት እንደሚኖረው ተገምቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ የታክስ ገቢው ብር 211 ነጥብ 1 ቢሊዮን እንደሚሆን የታቀደ ሲሆን፣ ለ2010 በጀት ዓመት ከተያዘው በጀት አንጻር የ5 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ያሳያል፡፡ ሆኖም በ2010 ይሰበሰባል ተብሎ ከሚጠበቀው አንጻር በ2011 የተያዘው የታክስ ገቢ ዕቅድ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል፡፡ በመሆኑም ይህንን በገንዘብ ዕቅዱን ለማሳካት ከአሁኑ የተለየ የአመራር ጥረትን የሚጠይቅ መሆኑን ማስታወስ እወዳለሁ፡፡

ታክስ ያልሆኑ ገቢዎች በአመዛኙ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚገኘው የዘቀጠ ትርፍ፣ ከመንግስት ዕቃዎችና አገልግሎቶች ሽያጭ የሚገኝ ገቢ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ በ2011 በጀት ዓመት ጠቅላላ ብር 24 ነጥብ 6 ቢሊዮን ያህል ገቢ እንደሚገኝ ታቅዷል፡፡ በ2010 በጀት ዓመት የታወጀውን የተጨማሪ በጀት ጨምሮ ከዚህ የገቢ ምንጭ ብር 34 ነጥብ 5 ቢሊዮን እንደሚሰበሰብ የታቀደ ሲሆን፤ በ2011 በጀት ዓመት ይህ መጠን በ28 ነጥብ 6 በመቶ የሚቀንስ ይሆናል፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት በ2010 በጀት ዓመት ለተጨማሪ በጀት ወጪ መሸፈኛ ከመንግሥት ድርጅቶች ሽያጭ (ፕራይቬታይዜሽን) ገቢ ዕቅድ በመያዙና በ2011 ከዚህ የሚጠበቅ ገቢ ባለመኖሩ እንዲሁም ሊገኝ የሚችለው የዘቀጠ ትርፍ ገቢ ሊቀንስ እንደሚችል በመገመቱ ነው፡፡

 

 

ከውጭ ሊገኝ የሚችለው ሀብት ከልማት አጋሮች በሚገኝ መረጃና የፋይናንሱና የፍሰት ታሪክ በማየት የሚሰላ ነው፡፡ የዚህ ገቢ ምንጭ በሁለት መልክ የሚፈስ ነው፡፡ እነዚህም የቀጥታ በጀት ድጋፍ (የመሠረታዊ አገልግሎት ከለላ ድጋፍ) እና የፕሮጀክቶች ዕርዳታ ናቸው፡፡ ከመጀመሪያው የዕርዳታ ምንጭ የሚገኘው ገቢ በቀጥታ ወደ ፌዴራል መንግሥት ግምጃ ቤት የማፈስና መንግሥት የበጀት ድልድል የሚያደርግበት ሲሆን፣ ከዚህ ምንጭ በዕርዳታ መልክ ለ2011 በጀት ዓመት ይገኛል ተብሎ የታቀደው ገቢ ብር 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ነው፡፡ እንዲሁም ከፕሮጀክቶች ጋር ቁርኝት ያለው ዕርዳታ በበጀት ዓመቱ ብር 16 ነጥብ 8 ቢሊዮን እንደሚሆን ታቅዷል፡፡

 

 

ዶ/ር አብርሃም ኤይዘውም የፌደራል መንግሥት የ2011 በጀት ዓመት የወጪ በጀት ድልድል የምንከተለውን የፊስካል ፖሊሲ መሰረት ያደረገ ሲሆን፤ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተቀመጡ ቁልፍ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አቅጣጫና ዓላማዎችን እንዲሁም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀውን የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቀፉን መሠረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው ይላሉ፡፡

 

 

በዚህ መሠረት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ከማሳካት አንፃር፣ ከመንግሥት የፋይናንስ አቅም፣ መ/ቤቶች ከተሰጣቸው ተልዕኮና ኃላፊነት አኳያ ለውጤቶች፣ ለዋና ዋና ተግባራትና ለፕሮጀክቶች የሚያስፈልገውን ወጪ በመገምገም በጀቱ እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡ መ/ቤቶች ለፕሮግራም በጀት ዝግጅት እንዲረዳ አመልካች የበጀት ጣሪያ ከዝርዝር መመሪያ ጋር እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ በበጀት ጥሪው መሠረት አስፈፃሚ መ/ቤቶች የበጀት ጥያቄያቸውን አቅርበው በዚሁ ላይ በመመስረት የበጀት ሰሚ ተከናውኗል፡፡

 

 

የወጪ በጀቱ የተዘጋጀው የፕሮግራም በጀት አሠራርን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም በጀቱ ግብዓትን ከውጤት ጋር የሚያዛምድ፣ ውጤትን በመለካት፣ ተጠያቂነትን በማስፈን፣ ፖሊሲና ስትራቴጂን መሰረት በማድረግ እቅድን ከበጀት ጋር ለማስተሳሰር እና የመደበኛና የካፒታል ወጪዎችን ለማቀናጀት በሚያስችል መልኩ ተዘጋጅቷል፡፡

 

 

የ2011 የወጪ በጀት ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፤ ዘላቂ የልማት ግቦችንና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ዓላማና ግቦችን ለመተግበር በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ አስፈፃሚ መ/ቤቶች የበጀት ጥያቄያቸውን በተሰማሩበት መስክ ከላይ የተጠቀሱትን ሰነዶች ዓላማ ለማስፈፀም የሚያስችሉ ተግባራትን እና ፕሮጀክቶችን አካተውና ቅደም ተከተል ሰጥተው እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡

 

 

የ2011 አጠቃላይ በጀት

የፌዴራል መንግሥት የ2011 በጀት ብር 346 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሲሆን፤ ይህም ከ2010 ወጪ በጀት ጋር ሲነጻጸር በብር 12 ነጥብ 1 ቢሊዮን ወይም የ3 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት ያሳያል፡፡ ከዚሁ በጀት ለመደበኛ ወጪ ብር 91 ነጥብ 7 ቢሊዮን፣ ለካፒታል፣ ብር 113 ነጥብ 6 ቢሊዮን እንዲሁም ለክልል መንግሥታት ድጋፍ ብር 135 ነጥብ 7 ቢሊዮን እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ብር 6 ቢሊዮን ተደግፎ ቀርቧል፡፡

 

 

ተደግፎ ከቀረበው ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ለክልል መንግሥታት የተመደበው የበጀት ድጋፍ ሲሆን፣ ይህም የጠቅላላ በጀቱ 39 ነጥብ 1 በመቶ መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ ይህም የብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት የበጀት ድጋፍ ለ2010 ከተያዘው ጋር ሲነጻጸር 15 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ አለው፡፡ ለ2011 በጀት ዓመት ለፌዴራል መንግስት የካፒታል በጀት የተደለደለው በሁለተኛ ደረጃ ሲገኝ ድርሻው 32 ነጥብ 7 በመቶ ሆኗል፡፡ ለ2011 በጀት የተደለደለው የካፒታል ወጪ በጀት ለ2010 ከተያዘው ጋር ተመጣጣኝ ነው፡፡ የካፒታል በጀት ወጪ አሸፋፈኑም ከአገር ውስጥ ከሚሰበሰብ ገቢና ከውጭ አገር በሚገኝ ዕርዳታና ብድር ሲሆን፤ ከመንግስት ትርዥሪ፣ ከእርዳታ እና ከብድር እንደሚሸፈን የተያዘው የካፒታል ወጪ በጀት በቅደም ተከተል ብር 76 ቢሊዮን (66 ነጥብ 9 በመቶ)፣ ብር 16 ነጥብ 3 ቢሊዮን (16 ነጥብ 4) እና ብር 21 ቢሊዮን (18 ነጥብ 5 በመቶ) ነው፡፡ በሌላ በኩል ለመደበኛ ወጪ የተደለደለው በጀት ከአጠቃላይ ወጪ በጀት ድርሻው 26 ነጥብ 4 በመቶ ሲሆን ለ2010 ከተመደበው የተስተካከለ በጀት አንጻር የ4 ነጥብ 4 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

 

የበጀቱ ከፍተኛ ድርሻ የማን ነው?

ከአጠቃላይ የ2011 መደበኛና ካፒታል በጀት ውስጥ 66 በመቶ ድርሻ ያላቸው ትምህርት፣ መንገድ፣ ግብርና፣ ውሃ፣ ጤና፣ ኢንዱስትሪ፣ ከተማ ልማት፣ የከተማ ምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሞች ናቸው፡፡ በመሆኑም በጀቱ በዘላቂ ልማት፣ በኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን እና በድህነት ተኮር ክፍላተ ኢኮኖሚና የመሠረተ ልማት አውታሮችን በማስፋፋት ላይ ያመዘነ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ከዚህም በላይ የብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት ለሚያካሂዷቸው አጠቃላይ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የልማት እንቅስቃሴዎች የሚያስፈልገውን የወጪ ፍላጎት ለመሸፈን እንዲቻል ከፍተኛ የበጀት ድጋፍ መመደቡን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በጥቅሉ የ2011 በጀት በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተቀመጠውን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽንን አቅጣጫ ለመተግበር የሚያግዝ እንደሆነ ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡

 

 

59 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት በምን ይሸፈናል?

በ2011 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ከሃገር ውስጥ የገቢ ምንጮች እንዲሁም ከውጭ አገር ዕርዳታና ብድር በድምሩ ብር 287 ነጥብ 6 ቢሊዮን ገቢ እንደሚሰበሰብ መታቀዱን ዶ/ር አብርሃም ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም ለመደበኛ፣ ለካፒታል እና ለብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት የበጀት ድጋፍና የዘላቂ ልማት ግቦች ማጠናከሪያ ወጪ ጠቅላላ ብር 346 ነጥብ 9 ቢሊዮን በጀት ተደግፎ ቀርቧል፡፡ በዚህም መሠረት በታቀደው የፌዴራል ገቢና ተደግፎ በቀረበው የወጪ በጀት መካከል የብር 59 ነጥብ 3 ቢሊዮን የበጀት ጉድለት ይታያል፡፡ ይህንንም የበጀት ጉድለት ከሃገር ውስጥ በሚገኝ ብድር ለመሸፈን ታቅዷል፡፡ የሀገር ውስጥ ብድር መጠኑ ከአጠቃላይ የሀገር ምርት አንጻር 2 ነጥብ 3 በመቶ ሲሆን፣ ይህም የማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ተግባራዊ ከሚደረገው የገንዘብ ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ ከመሆኑም በላይ በዋጋ ንረት ላይ የጎላ ተፅዕኖ እንደማያሳድር ግምት ውስጥ ገብቷል፡፡  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
276 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

 • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

 • Aaddvrrt5.jpg
 • adverts4.jpg
 • Advertt1.jpg
 • Advertt2.jpg
 • Advrrtt.jpg
 • Advverttt.jpg
 • Advvrt1.jpg
 • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1080 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us