የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ 100 ቀናት!

Wednesday, 11 July 2018 12:57

 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቃለ መሐላ ከፈፀሙ እነሆ በዛሬው ዕለት (ሐምሌ 4 ቀን 2010 ዓ.ም) 100 ቀናትን ደፈኑ። በእነዚህ ቀናት ካከናወኙዋቸው በርካት ተግባራት መካከል የሚከተሉት የሚጠቀሱ ናቸው።

 

1.    ኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮምቴ በወሰነው መሠረት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የነበረው የድንበር ግጭት እልባት እንዲያገኝ አድርገዋል። ከ20 ዓመታት ቁርሾ በኋላ ባለፈው ሳምንት እሁድ ዕለት ጠ/ሚ አብይ አሕመድ በአስመራ ከተማ ሲገኙ ፕሬዚደንት ኢሳያይስ አፈወርቂ ጨምሮ ከፍተኛ የኤርትራ መንግሥት ባለስልጣናት እና የኤርትራ ሕዝብ ደማቅ አቀባባል አድርገውላቸዋል። ሠላሙን ማስቀጠል የሚያስችል የሁለትዮሽ ስምምነትም ሁለቱ መሪዎች ተፈራርመዋል። ይህን ተከትሎ የቴሌኮምኒኬሽን አግልግሎት ተጀመረ ሰሆን የኢትዮጽያ አየር መንገድ መደበኛ በረራውን ከሚቀጥለው ማክሰኞ ዕለት እንደሚጀምር አስታውቋል።

የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮምቴ ውሳኔ ምን ነበር?

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየውን አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር በይፋ ጥሪ አቅርቧል። "ለኢትዮጵያችን እድገትና ለሕዝቦች ተጠቃሚነት ሰላም ከምንም በላይ ትልቅ ዋጋ አለው። ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው። ከግለሰብ የወደፊት የማደግና መለወጥ ህልም ጀምሮ እስከ ሀገር ድረስ ሰላም ከደፈረሰ የቱንም አይነት የልማትና የዲሞክራሲ አላማዎችን ማሳካት አይቻልም።


በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተውን ጦርነት በአፍርካ ከተከሰቱ የድንበር ጦርነቶች ሁሉ ደም አፋሳሹ ሲሆን፣ ከሁለቱም ወገን በርካታ ሺህ የሰው ሕይወት ሊጠፋ ችሏል። ጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከኤርትራ እና ከኢትዮጵያ የድንበር አካባቢ መኖሪያ ቀዬ አፈናቅሏል።


በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገው ጦርነት በሁለቱም አገራት ያሉ ቤተሰቦችን አፍርሷል፣ በድንበር አቅራቢያ የሚኖሩ ዜጎች ሁሌም ያለመረጋጋትና የስጋት ስነ-ልቦና ሰለባ አድርጓቸዋል።


በድንበር አካባቢ በንግድ የሚተዳደሩ ሰዎች ላይ ተፅኖ ፈጥሯል። በድምሩ ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ፈጥሯል። በመሆኑም የሁለቱ ሀገራት የወደፊት ግንኙነት ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው ጥያቄ የአብዛኛው ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን እንዲሁም የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል።


ከጦርነቱ በኋላ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በተባበሩት መንግስታት አደራዳሪነት የአልጀርሱ ስምምነት ቢደረግም ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱ ወንድማማች ሀገሮች መካከል ጦርነትም ሆነ ሠላም የሌለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ወደነበረበት ለመመለስ ላለፉት ሃያ አመታት የተደረጉ ሙከራዎች በሙሉ ውጤት አላመጡም። በዚህም ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በሁለቱ ሀገራት መካከል የዕውነት ሰላም ለማስፈን ከቀድሞው የተለየ አቋምና አካሄድ ያስፈልጋል። ሁለቱም መንግሥታት ለህዝባቸው ምርጫና ፍላጎት ቦታ የማይሰጡ ሊሆኑ አይችሉም።


እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ የሚል ፉክክር ለሁለቱም ህዝቦች የሚፈይደው ነገር አይኖርም። ከዚህም በተጨማሪ ለአፍሪካ ቀንድ ሀገሮችና አካባቢ የፖለቲካ ቀውስ መብረድና መረጋጋት ዘላቂው መፍትሔ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጤናማ ግንኙነት መመሥረት ነው። ይህን ባለማድረጋችን በርካታ ለሁለቱ እህትማማች ሀገሮችም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ትልቅ ፋይዳ ያላቸዉ እድሎች አምልጠዉናል። የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ህዝቦች ቀድሞም ቢሆን ወዳጅ ነን። በደም፣ በባህል፣ በቋንቋ እና በረጅም ጊዜ የጋራ ታሪክ የተሳሰርን ሕዝቦች ነን።

 

በመሆኑም በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ ሀገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል የኢትዮጵያ መንግስት የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነና ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን ለመግለፅ ይፈልጋል።


ይህንኑ በጋራ ተጠቃሚነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተውን የሀገራችን ፖሊሲም አጠናክረን እንደምንቀጥል በዚሁ አጋጣሚ በድጋሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን። የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም በመውሰድ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ የሰላም ጥሪያችንን ተቀብሎ በሁለቱም ወንድማማች ህዝቦች መካከል ከዚህ በፊት የነበረውን አብሮነትና ሰላም ወደነበረበት ለመመለስና በቀጣይም ዘላቂነቱን ለመጠበቅ ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት እንዲሰራ እንጠይቃለን።" ብሏል።

 

1.    ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ ባለፉት 100 ቀናት በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር ተጉዘው ከመሪዎችና ከሕዝብ ጋር ስኬታማ ምክክር አድርገዋል። ከተጓዙባቸው የውጭ አገራት መካከል በሱዳን፣ በጅቡቲ፣ በሳዑዲ ዓረቢያ፣ በግብጽ በተለያዩ ምክንያቶች በእስር ላይ የሚገኙ ወገኖች እንዲፈቱ ከአገራቱ መሪዎች ጋር በደረሱት ስምምነት መሠረት በመቶዎች የሚቆተሩ ወገኖች የነጻነት አየር መተንፈስና ወደአገራቸውም መመለስ ችለዋል። ይህ ድንቅ ስራ እጅግ በርካታ ወገኖችን ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል።

2.    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባለፉት 100 ቀናት ከወሰዱት ተጨማሪ እርምጃዎች መካከል የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ማንሳት ይገኝበታል። አዋጁ ባለፉት ጊዜያት ከታየው የሕዝባዊ ተቃውሞ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በመደበኛ ሁኔታ የአገሪቱን ላም ማስጠበቅ አልተቻለም በሚል ወጥቶ ስራ ላይ የዋለ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን አዋጁ ከተነሳ በሃላ አንጻራዊ ሠላም ሰፍኗል።

3.    በክልሎች እና የፌዴራል መንግሥታቱ ሥር የተያዙ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ማድረጋቸው በተለይም የግንቦት ሰባት ሁለተኛ ሰው የሆኑትን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከመፍታት በተጨማሪም በጽ/ ቤታቸው በክብር ማነጋገራቸው ከላ ወዳድ ወገኖች ታላቅ አድናቆትን አትርፎላቸዋል።

4.    በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት "አሸባሪ" ተብለው የተፈረጁትን ግንቦት 7፣ ኦነግ እና ኦብነግ ፍረጃ እንዲነሳ አድርገዋል።

5.    በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎችና የተቀናቃኝ ፓርቲ መሪዎች ወደአገር ውስጥ ገብተው በሠላም እንዲታገሉ በተደጋጋሚ ባደረጉት ጥሪ መሠረት መግባት ጀምረዋል።

6.    የፕረስ ነጻነት እና የሃሳብ ብዝሃነት እንዲከበር በተደጋጋሚ ባነሱት ሃሳብ መሠረት የመንገሥት መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጽያ ቴሌቭዝንን ጨምሮ የሚደነቅ የይዘት ለውጥ (መሻሻል) ማድረግ ችለዋልረታቸውን በውጭ አገር ያደረጉ ሚዲያዎች እንዲከፈቱ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በዚህም በመበረታታት የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ በአዲስአበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ለመክፈት በቅቷል።

7.    የፀረ-ሽብርተኝነት፣ የሲቪል ማኅበራት እና የመገናኝ ብዙሃን የመረጃ ነጻነት አዋጆችን ለማሻሻል ኮምቴ ተዋቅሮ ሥራ መጀመሩ በአዎንታ የሚወሰድ ነው።

8.    በቀጣይም የፍትሕ አካላትን (ማለትም ፍርድ ቤቶችን፣ ፖሊስ፣ ደኅንነት እና መከላከያ)፣ በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ ብዙኃን መገናኛዎችን እንዲሁም ምርጫ ቦርድን ለሕዝብ እና ሕገ መንግሥቱ ወገንተኛ እንዲሆኑ በማድረግ መልሶ ማዋቀር ለማከናወን ዕቅዶች መኖራቸው የሚበረታታ ነው።

9.    የጠ/ሚ አብይ አሕመድ አመራር ለመደገፍና አስካሁን ለተሰሩ ሥራዎች ዕውቅና ለመስጠት አዲስአበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቁ ሰልፎች ተካሂደዋል። በተለይ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስአበባ የተካሄደውን ሰልፍ ለማደናቀፍ ታስቦ የተወረወረ ቦምብ ንጹሐን ወገኖቻችን መጎዳታቸው በአስከፊነቱና ነውረኝነቱ በታሪክ ተመዝግቦ የሚቀመጥ ሆኗል።

10.  ሚኒስቴሮች ብክነትን ለማስወገድ ከሰኞ እሰከ አርብ የሚካሄዱ ስብሰባዎቻቸውን ወደ ቅዳሜና እሁድ እንዲያሽጋግሩ እንዲሁም አላስፈላጊ ተደጋጋሚ የውጪ ጉዞዎችን ከማድረግ እንዲቆጠቡና እነዚህን መተላለፍ ቀይ መስመር ነው በማለት ጥብቅ ማሳሰቢያ የሰጡትም ባሳለፍነው 100 ቀናት ውስጥ ነው። በዚሁ መሠረት ጠ/ሚ የሚመሩት የካቢኔ ስብሰባ ወደቅዳሜ የተዛወረ ሲሆን በአንዳንድ መንግሥታዊ ተቋማት ለስብሰባ ሚጠፋ ስራ ጊዜ እንዲቀንስ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል።

11.  ጠ/ሚኒስትሩ ካቢኔያቸውን እንደአዲስ ከማዋቀራቸው በተጨማሪ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት የነበሩ አመራሮች ሹም ሽር አድርገዋል። አንዳንዶችን በጡረታ አሰናብተዋል። በተለይ በሙስናና ብልሹ አሰራር የሚጠረጠሩ ተቋማት መሪዎች "ከቦታቸው መነሳታቸው ብቻ ለምን፣ ለምን አይከሰሱም" የሚል የሕዝብ ጥያቄ ቢኖርም ሹም ሽሩ በሕዝብ ዘንድ በአዎንታ የተወሰደ ነው።¾

ይምረጡ
(11 ሰዎች መርጠዋል)
180 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 946 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us