ከጉዳቱ እያገገመ ያለው የንግዱ ዘርፍ

Wednesday, 25 July 2018 13:41

ከጉዳቱ እያገገመ ያለው የንግዱ ዘርፍ 

ከንግድ ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት ክፍል

 

ዶክተር አብይ አህመድ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሰየማቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ካደረጉት የኢትዮጵያዊያንን ቀልብ የሣበ ንግግራቸው ጀምሮ ሀገሪቷን ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ተጉዘው ከህዝብ ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች፣ በተለያዩ ጊዜያት እንደ ሀገር ባስተላለፏቸው ውሳኔዎች፣ በሰጧቸው መንግስታዊ መግለጫዎች እና ባሳዩት የህዝብ አገልጋይነት አቋም የተነሳ ተስፋ ቆርጣ የነበረችው ሀገራችን ተስፋዋ ዳግም ለምልሟል፤ ተደፍተው የነበሩ አንገቶች ቀና ብለዋል፤ ተቆልፈው የነበሩ አንደበቶች ተከፍተዋል።


የጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጥ ንቅናቄዎች ከበዓለ ሲመታቸው ቀን ጀምሮ በነበሩት ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ “የመደመር” እሳቤያቸው በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ የጋራ ዜማ መሆኑ እጅግ አስገራሚ ሆኗል። ኤርትራን ጨምሮ በበርካታ የጎረቤት ሀገራት ባደረጓቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ያነሷቸው የሠላም፣ የፍቅርና የመደመር እሳቤ ውጤቶች ከኢትዮጵያም አልፎ ለአፍሪካ፤ ከአፍሪካም ለአለም ህዝቦች የፍቅርና የመተሳሰብ አዲስ ብርሀን ፈንጥቋል። በኢትዮጵያ የመተሳሰብ ዘር ዘሪነት በአፍሪካ የሠላም ቀጠና በቅሎና አብቦ እንዲያፈራ የሚያስችል የፍቅር፣ የአንድነት፣ የሠላም፣ የይቅር ባይነት ዝናብ በኢትዮጵያ ሰማይ በዶክተር አብይ አሰተምህሮ ዘንበዋል።


በታሪክ አጋጣሚ በተፈጠረ ክስተት የጎሪጥ ይተያዩ የነበሩ ኢትዮጵያና ኤርትራ አስታራቂ ሽማግሌም ሳያስፈልግ ዛሬ ሁለቱ ሀገራት በስስት አይን የሚተያዩ አንድ አምሳል ሆነው በእኛነት መንፈስ በአንድነት ለመልማት፣ በአንድነት ለማደግ አንድ ቀበቶ ታጥቀዋል፤ በፍቅር መቀነት ተሳስረዋል። በእኔ እምነት የሰላምን፣ የልማትን፣ የእድገትን እና የአንድነትን ጠቀሜታ አስፍቶ በማየት የተፈጠረው ይህ የእኛነት አጀንዳ ታዲያ አጥሯን እያጠበቀች አትድረሱብኝ እያለች ለምትቧርቀው አሜሪካም ሆነ ለሰሜን ኮሪያ የተጋረደባቸውን “የእኔ ብቻ” የሚል ግለኛ የአስተሳሰብ ጨለማ የሚገፍ ይመስለኛል።


የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ሲመጡ “አሜሪካንን ለአሜሪካውያን ብቻ” የሚለው እሳቤ አመዝኖባቸው ሀገሪቷ ከዚህ በፊት ታደርጋቸው የነበረውን የንግድና ኢኮኖሚ ግንኙነቶች ከማቋረጥ በተጨማሪ ከውጪ ሀገራት በሚገቡ ምርቶች ላይ በጣም ከፍተኛ ቀረጥ በመጫን አዲስ የንግድ ጦርነት ሲከፍቱ እና የሌላ ሀገር ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ ቢሮክራሲዎችን ሲነድፉ አስተውለናል። በእኔ እምነት አሜሪካ በሯን ዘግታ በራሷ እድገትና በብልጽግና ብቻ እንድታስብ እያደረጓት ያሉት ትራምፕ ከአራቱ የሂሳብ ስሌቶች በመደመር የግለኝነትን ብራኬት/ቅንፍ/ በመስበር ያላቸውን ለሌሎች ለማካፈል ከሀገራችን ተራማጅ እሳቤ ተሞክሮ ቢወስዱ በአሜሪካን መስፈርት መሰረት ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ካበቃቸው የግል ሀብታቸው የበለጠ የእውቀትና የአስተሳሰብ ሀብት ያገኛሉ ባይ ነኝ።


በሀገራችን ዘላቂ ሰላምን፣ የልማት ተጠቃሚነትንና፣ የህዝቦች አንድነትን በማረጋገጥ ወደ ቀጣይ የልማትና የእድገት ጉዞ ለመዝመት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የሪፎርም ስራዎች እየተሰሩ ነው። በሀገር ውስጥ የህዝብን አንድነት በማስጠበቅ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሰላም በመፍጠር ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መንግሥት እያካሄደ ያለው ሀገራዊ ለውጥና ንቅናቄ በተለይም ለንግዱ ዘርፍ የላቀ ትርጉም አለው።


ንግድ ለሀገራችን ኢኮኖሚ መጎልበት ከግብርናው ያልተናነሰ ሚና አለው። የሀገራችን ኢኮኖሚ ማርሽ በሆነው የንግዱ ዘርፍ ሀገሪቷ የምትፈልገውን ለውጥና እድገት ማምጣት የሚቻለው በሁላችንም ተሳትፎ ዘላቂ ሠላም ሲረጋገጥ ብቻ ነው። ከሀገር ውስጥና ከጎረቤት ሀገራት ጋር የተረጋጋና ቀጣይነት ያለው ዘላቂ ሰላም ሲረጋገጥ ጤናማ የንግድ እንቅስቃሴ ይኖራል። ከክልል ክልል፣ ከአካባቢ አካባቢ ጤናማ የሆነ የንግድ እቃዎችና አገልግሎቶች የሚንቀሳቀሱትና የተረጋጋ ገበያ የሚኖረው በሰላም የበላይ ጠባቂነት ብቻ ነው። ታዲያ የሁሉም ነገር ቁንጮ የሆነውን ዘላቂ ሰላም ለመንከባከብ ከሁላችንም የሚጠበቅብንን ሁሉ ማድረግ የለብንም ትላላችሁ? አለብን እንደምትሉ በማመን መልካም ንባብ ብያችኋለሁ።


አንኳር ወደሆነው ጉዳይ ልመለስና የወጪ ንግድ የሀገራችን ኢኮኖሚ እድገት መሰላል እንደመሆኑ መጠን ምርቶቻችንን ወደ ውጪ በመላክ የወጪ ምንዛሪ ግኝታችንን ለማሳደግ አሁን የተጀመረው ሀገራዊ ንቅናቄ፣ አንድነት እና ሠላም ለሀገር ውስጥም ሆነ ለወጪ ንግዳችን ውጤታማ አፈፃጸም በጣም ወሳኝ ነው። ለዚህም ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በቅዱስ ቁርአን መማል ሳያስፈልግ ምስክር ይሆነኝ ዘንድ ሸገር ታይምስ መጽሄት /shegertimes magazine/ በድረ-ገጹ እ.ኢ.አ ሰኔ 06/2018 ሮይተርስን ጠቅሶ ያወጣውን እንዲህ አቅርቤዋለሁ።


“ሮይተርስ እንደዘገበው የሀገሪቱ የአንድ ቦንድ ዋጋ በ0 ነጥብ 583 ሳንቲም ዶላር ጭማሪ በማሳየት በ100.25 ዶላሮች ለመሸጥ በቅቷል። የሀገሪቱ ቦንድ ካለፈው ሳምንት ረቡእ ወዲህ ብቻ የ 3 ዶላር ጭማሪ ዋጋ አስመዝግቧል ተብሏል።


በናይሮቢ ስታንቢክ ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚስቱ ጂብራን ቁሬይሺ ሲናገሩ በሀገሪቱ እየታየ ባለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች የተነሳ አለም አቀፍ ኢንቨስተሮች የኢትዮጵያን ቦንድ ለመጫረት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ይገኛል ብለዋል። የሮይተርሱ ዘገባ አክሎም የኢትዮጵያ ቦንድ በ10 ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ ጭማሪ አስመዝግቧል ይላል። ይህ የሆነው ደግሞ የሀገሪቱ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከኤርትራው ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተገናኝተው የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር ከተስማሙ በኋላ ነው ይላል።


አብይ አህመድ ሀገራቸውን ብቻ ሳይሆን ምስራቅ አፍሪካን ጭምር እለውጣለሁ ብለው መነሳታቸውን የጠቀሰው ዘገባው የወሰዱት የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ለውጥ ደግሞ ከወዲሁ በአለም የቦንድ ገበያ ላይ የሀገሪቱን ተፈላጊነት ከፍ በማድረግ ውጤት እያመጣላቸው ነው ሲል አስቀምጧል።”


ሌላም አለኝ! በኢትዮጵያ መደበኛ ባልሆነው የውጭ ምንዛሬ ገበያ /ጥቁር ገበያ/ 1 የአሜሪካን ዶላር 40 የኢትዮጵያ ብር ገብቶ የነበረው ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ በፍጥነት ወርዶ 27 ብር ከ30 ሣንቲም ከነበረው የመደበኛ ገበያ ምንዛሪ ጋር ተስተካክሏል። ስለዚህ “እኔና አንተ/ቺ ስንደመር እኛ እንሆናለን። እኛ ማለት ደግሞ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን” የተባለው አካላችንን በምግብነት አዕምሯችንን በመልካምነት እየገነባው ይመስለኛል።


ሲጠቃለል፡- ይህንን እጃችን የገባውን እድል ተጠቅመን የሀገራችን የንግድ ስርዓታችን ከህገ-ወጥነት ተላቆ ሸማቹ ማህበረሰብ ለሚከፍለው ገንዘብ ተመጣጣኝ የሆነ ምርት የሚያገኝበት፣ ህጋዊ ነጋዴዎችን የሚያበረታታና ህገ-ወጥነትን የሚያቀጭጭ፣ የውጪ ባለሀብቶችን ሊጋብዝ የሚችል፣ ፍትሀዊ፣ ተደራሽ፣ አገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋ እና ለጤናማ ውድድር ምቹ እንዲሆን ከንግድ ዘርፉ አመራሮችና ሰራተኞች ጀምሮ መንግስት፣ በሸማችነትም ሆነ በነጋዴነት የሚሳተፍ የዚች ሀገር ተዋናይ ሁሉ አበክሮ መስራት ይኖርበታል።


የውጪ ምንዛሪ ግኝታችን ዋና ቋት የሆነው የወጪ ንግድ ካንቀላፋበት ነቅቶ ወደፊት እንዲራመድና የኢትዮጵያና የህዝቧ ኢኮኖሚ ከለጋነት ወደ ጎልማሳነት፣ ከችግኝነት ወደ ዛፍነት ተቀይሮ ፀሐይ ሲሆን ከፀሐይ፣ ዝናብ ሲሆን ከዝናብ ልንጠለልበትና ሊያድነን የሚችል እንዲሆን ለወጪ ንግድ የምናቀርባቸው ምርቶች ጥራት፣ ብዛትና ዋጋቸው በአለም ገበያ ብቁ ተወዳዳሪ በመሆን የውጪ ምንዛሪ ግኝትን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሻሽሉ መሆን አለባቸው። ይህንን ለማድረግ አምራቹ፣ ነጋዴው፣ ላኪው፣ የንግድ ሴክተሩ፣ የህዝብና የመንግስት ክንፍ አካላት ተናበውና ተቀናጅተው መስራት ይኖርባቸዋል።


ላኪዎቻችን የሀገራችንን ምርት ገዝቶ ከመላክ ይልቅ ፊታቸውን ወደ አምራች ኢንዱስትሪው መለስ አድርገው እሴት ጨምሮ መላክን መልመድ አለባቸው። የሀገር ውስጥ ምርቶችን ወደ ኢንዱስትሪ ግብዓትነት ቀይሮ ያለቀለት ምርት ማምረት ጠቀሜታው ወደ ውጪ በመላክ የሚገኘው ጠቀም ያለ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ከውጪ ሀገር የምናስመጣቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጪ ምንዛሪ እጥረትን ለማቃለል ፍቱን አማራጭም ነው። መንግስት የውጪና የሀገር ወስጥ ባለሃብቶች እንዲሁም አስመጪና ላኪ ነጋዴዎች ወደ ኢንዱስትሪው እንዲያመዝኑ ማበረታታት፣ አማራጮችንና ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ ኢትዮጵያን ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚያገናኙ መሠረተ-ልማቶችን መገንባት አለበት እያልኩ መልካም ንባብ እንዲሆንላችሁ ተመኘሁ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
87 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1017 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us