የምህረት አዋጁ እነማንን ይመለከታል?

Wednesday, 25 July 2018 13:46

በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባለፈው ሳምንት የጸደቀውን የምህረት አዋጅ ተከትሎ በወንጀል ሕግ፣ ጸረ ሽብርና አስቸኳይ ጊዜ አዋጆች በተጠቀሱ የተለያዩ አንቀጾች የተጠረጠሩ፣ የተከሰሱና ቅጣት የተላለፈባቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ምሕረት ተደረገላቸው።


በመላ አገሪቱ ተፈጻሚነት የሚኖረው የምሕረት አዋጁ ከግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም በፊት በተፈጸሙ ወንጀሎች ብቻ ተግባራዊ ይሆናል።


የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ከትላንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ፤ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታውን የተሟላ ለማድረግ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት፣ አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል የምህረት አዋጁ አንዱ እርምጃ ነው።


በዚህም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የተለያዩ ወንጀሎችን የተላለፉ ግለሰቦች በአገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በመሳተፍ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ ሐምሌ 13 ቀን 2010 ዓ.ም የምህረት አዋጅ መጽደቁን አውስተዋል፡፡


ምህረትና ይቅርታ በወንጀል ፍትህ ስርዓት ላይ የሚገኙ ጉዳዮች ቢሆኑም የራሳቸው የተለያዩ አካሄድ እንዳላቸው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ጠቅሰዋል።


“ምህረት” የወንጀል ምርመራ ከመጀመሩ በፊት፣ ከተጀመረ በኋላ፣ በክስ ሂደት ያለ፣ የወንጀል ቅጣት ከተሰጠበት በኋላ በሕግ አውጭ አካል የሚሰጥና ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ የሚያደርግ እንደሆነም ገልጸዋል።


“ይቅርታ” ግን በወንጀል ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ፣ በማረሚያ ቤት እየታረመ ያለ፣ በሕግ ጥበቃ ስር ያለ ግለሰብ በአገር ጉዳይ ላይ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን በይቅርታ ቦርድ አማካኝነት በአንድ ጊዜ የሚሰጥ አሰራር መሆኑን ተናግረዋል።


ከዚህ በፊት በይቅርታና በክስ ማቋረጥ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸው፤ ከዚህ ውጭ ያሉትን ተጠርጣሪዎች፣ ተከሳሾችና ፍርደኞች የሕግ አፈጻጸም የምህረት አዋጅ ስነ ስርዓት ተዘጋጅቶ ምህረት መሰጠቱን አስታውሰዋል።


በወንጀል ሕግ፣ በጸረ ሽብርና በአስቸኳይ አዋጆች የተጠቀሱ የተለያዩ አንቀጾችን ጠቅሰው፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ግለሰቦች የምህረት አዋጁን በመጠቀም ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለው የራሳቸውን አገራዊ አስተዋጽኦ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።


በወንጀል ሕጉ ከተጠቀሱት መካከል አንቀጽ 238፣ 239፣ 240፣ 241፣ 247፣ 248፣ 249፣ 252፣ 256፣ 288ና አንቀጽ 438 ይገኙበታል።


በተመሳሳይ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 241 ኢ-ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ የአገሪቱን አንድነት እንዲፈርስ፣ ፌዴሬሸኑ እንዲከፋፈል፣ ሕዝቡ በከፊል እንዲገነጠል በማድረግ፣ በአንቀጽ 247 ደግሞ በወታደራዊ ተቋም በአገር ኢኮኖሚ ጉዳት በማድረስ፣ መከላከያው ኃላፊነቱን በሚገባ እንዳይወጣ በማድርግ በማናቸው መንገድ በማሰናከል፣ ወታደሩ እንቢተኛ እንዲሆን፣ እንዲከዳና መሰል ድርጊቶች እንዲፈጽም በማድርግ ወንጀል የተሳተፉ አካላት ምህረት መደረጉን አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል።


በአንቀጽ 248 እና 249 ላይ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ አደራ የተጣለበት ማንኛውም ሰው መሳሪያ በመያዝ ኢትዮጵያን የተቃወመ፣ የአገርን ምስጢር ሰነድ ለሌላ አካል፣ ድርጅት በማስተላለፍ እንዲሁም በአንቀጽ 252 ለውጭ አገር መንግስትና ድርጅት ሲል በተቋም፣ በድርጅት፣ በዜጎች ላይ ጉዳት በሚያደርስ ሁኔታ በፖለቲካ፣ በዲፖሎማሲ፣ በወታደራዊና ስለላ ስራ በመሳተፍና በመደራጀት ምስጢር በማስተላለፍ ወንጀል ለተሳተፉም ምህረት መደረጉን ገልጸዋል።


የወንጀል ሕግ አንቀጽ 256 በመተላለፍ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማፍረስ፣ የአገሪቷን ግዛት ወይም ሉዓላዊነት በመተላለፍ በመንግስት የውጭ ደህንነትና በመከላከያ ኃይሉ ላይ ወንጀል ለመፈጸም በማሰብ ወታደሮችን፣ የሽምቅ ተዋጊዎችን፣ ሽፍቶችን፣ ቅጥረኞችን በመጠቀም በመመልመል፣ በማቋቋም፣ ወደ አገር ውስጥ በማስገባትና የጦር መሳሪያዎችን በማዘጋጀት ወንጀል የተሳተፉትን ምህረቱ ተመልክቷቸዋል።


በተመሳሳይ አንቀጽ የተጠቀሱ ወንጀሎችን እንዲፈጽሙ በማድረግና በማናቸውም መንገድ በመገፋፋትና ግዙፍ በሆነ መንገድ ተግባር የተሳተፉት ምህርት መደረጉን ገልጸዋል።


በአንቀጽ 288 በመተላለፍ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን በመጠቀም ከወታደራዊ አገልግሎት ለማምለጥ በማሰብ የጦር ክፍሉን ወይም ወታደራዊ ነክ አገልግሎት ተግባሩን በመተው ወይም በፈቃድ ሂዶ ወደ ክፍሉ ሳይመለሱ በኩብለላ ወንጀል የተሳተፉ ምህረቱ ተደርጓል።


“በወንጀል ሕግ 438 ሕዝብ በመንግስት ላይ እንዲያምጽ በማድረግ በመንግስት ወይም በህዝብ ባለስልጣናት የሐሰት ወሬዎችን ሃሜቶችን በማውራት ህዝብን በማነሳሳት ወንጀል ሙከራ የተሳተፋችሁ ምህረት ተደርጎላችኋል” ብለዋል።


የምህረት አዋጁ ከወንጀል ህጉ ባሻገር በ2001 ዓ.ም በጸደቀው የጸረ ሽብር አዋጅና በ2009 እና 2010 ለወራት ታውጀው በነበሩ የአስቸካይ ጊዜ አዋጆች የተጠቀሱ አንቀጾችንም ይጠቅሳል።


በሶስቱም የሕግ ማዕቀፎች የተጠቀሱት አንቀጾች እንዳሉ ሆኖ ግን የሰው ሕይወት ያጠፉ ግለሰቦችን በተመለከተ በልዩ ሁኔታ ምህረት የማይደረግላቸው ወንጀሎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።


በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች አስረኞች ሲለቀቁ ሁሉም እስረኛ እንደሚለቀቅ ማሰብ ህጋዊ አለመሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ፣ ከተጠቀሱት አንቀጾች ውስጥ በሌሎች ወንጀሎች ላይ ምህረት አለመደረጉን ገልጸዋል።


ስለሆነም በተጠቀሱ ወንጀሎች የምህረቱ አዋጅ ተጠቃሚዎች ላይ የወንጀል ምርመራው ያልተጀመረባቸው እንዳይጀመር፣ የተጀመረባቸው እንዲቋረጥ፣ የጥፋት ውሳኔው የተላለፈባቸው ውሳኔው እንዲሻር፣ የተፈረደባቸውም ቅጣቱ እንዳይፈጸምና ጥፋተኛ እንዳይባሉ መታገዱን አስገንዝበዋል።


የምሕረት አዋጁ ለቀጣይ ስድስት ወራት የሚዘልቅ ይሆናል ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ የምህረት አዋጁ ተጠቃሚዎች በአጠቃላይ ዐቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤት ወይም በክልል ፍትህ ቢሮዎች በአካል በመቅረብ፣ በወኪል፣ በስልክ፣ በፖስታና በድረ-ገጽ የተዘጋጀውን ፎርም መሙላት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።


ከኩብለላ ወንጀል ጋር ተያይዞ በርካታ ወንጀሉ የሚመለከታቸው አካላት ስላሉ በመከላከያ ሚኒስቴር በኩል በተዘጋጀው የመመዝገቢያ ቅጽ እንዲመዘገቡ አስታውቀዋል።


ምህረት የተደረገላቸው አካላት ወደ ማህበረሰቡ ገብተው እርቅ የመፈጸም ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።


በስድስት ወራት ውስጥ በተጠቀሱ መንገዶች የመመዝገቢያ ፎርም ያልሞሉ የወንጀል ተሳታፊዎች ግን የምህረት አዋጁን ላለመጠቀም እንደወሰኑ ተቆጥሮ የአዋጁ ተጠቃሚ እንደማይሆኑ መግለጻቸውን ከኢዜአ ያገኘነው ዜና ያስረዳል።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
1888 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 910 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us