news admin

news admin

የስንብት ዜና

Thursday, 09 August 2018 18:25

 

ከነሐሴ 1997 ጀምሮ በየሳምንቱ ረቡዕ እየታተመ የሚወጣው "ሰንደቅ" ጋዜጣ ከህትመት ዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ ከነሐሴ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ እንዲዘጋ የድርጅቱ ባለአክስዮኖች ወስነዋል። ባለፉት ዓመታት መረጃ እና የማስታወቂያ ድጋፍ በማድረግ፣ ገንቢ ሂስ በመስጠት አብራችሁን ለነበራችሁ ሁሉ ምስጋናችን የላቀ ነው። የሰንደቅ ጋዜጣ የኤዲቶሪያል ቦርድ

የስንብት ዜና

Thursday, 09 August 2018 18:25

በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባለፈው ሳምንት የጸደቀውን የምህረት አዋጅ ተከትሎ በወንጀል ሕግ፣ ጸረ ሽብርና አስቸኳይ ጊዜ አዋጆች በተጠቀሱ የተለያዩ አንቀጾች የተጠረጠሩ፣ የተከሰሱና ቅጣት የተላለፈባቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ምሕረት ተደረገላቸው።


በመላ አገሪቱ ተፈጻሚነት የሚኖረው የምሕረት አዋጁ ከግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም በፊት በተፈጸሙ ወንጀሎች ብቻ ተግባራዊ ይሆናል።


የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ከትላንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ፤ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታውን የተሟላ ለማድረግ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት፣ አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል የምህረት አዋጁ አንዱ እርምጃ ነው።


በዚህም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የተለያዩ ወንጀሎችን የተላለፉ ግለሰቦች በአገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በመሳተፍ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ ሐምሌ 13 ቀን 2010 ዓ.ም የምህረት አዋጅ መጽደቁን አውስተዋል፡፡


ምህረትና ይቅርታ በወንጀል ፍትህ ስርዓት ላይ የሚገኙ ጉዳዮች ቢሆኑም የራሳቸው የተለያዩ አካሄድ እንዳላቸው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ጠቅሰዋል።


“ምህረት” የወንጀል ምርመራ ከመጀመሩ በፊት፣ ከተጀመረ በኋላ፣ በክስ ሂደት ያለ፣ የወንጀል ቅጣት ከተሰጠበት በኋላ በሕግ አውጭ አካል የሚሰጥና ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ የሚያደርግ እንደሆነም ገልጸዋል።


“ይቅርታ” ግን በወንጀል ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ፣ በማረሚያ ቤት እየታረመ ያለ፣ በሕግ ጥበቃ ስር ያለ ግለሰብ በአገር ጉዳይ ላይ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን በይቅርታ ቦርድ አማካኝነት በአንድ ጊዜ የሚሰጥ አሰራር መሆኑን ተናግረዋል።


ከዚህ በፊት በይቅርታና በክስ ማቋረጥ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸው፤ ከዚህ ውጭ ያሉትን ተጠርጣሪዎች፣ ተከሳሾችና ፍርደኞች የሕግ አፈጻጸም የምህረት አዋጅ ስነ ስርዓት ተዘጋጅቶ ምህረት መሰጠቱን አስታውሰዋል።


በወንጀል ሕግ፣ በጸረ ሽብርና በአስቸኳይ አዋጆች የተጠቀሱ የተለያዩ አንቀጾችን ጠቅሰው፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ግለሰቦች የምህረት አዋጁን በመጠቀም ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለው የራሳቸውን አገራዊ አስተዋጽኦ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።


በወንጀል ሕጉ ከተጠቀሱት መካከል አንቀጽ 238፣ 239፣ 240፣ 241፣ 247፣ 248፣ 249፣ 252፣ 256፣ 288ና አንቀጽ 438 ይገኙበታል።


በተመሳሳይ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 241 ኢ-ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ የአገሪቱን አንድነት እንዲፈርስ፣ ፌዴሬሸኑ እንዲከፋፈል፣ ሕዝቡ በከፊል እንዲገነጠል በማድረግ፣ በአንቀጽ 247 ደግሞ በወታደራዊ ተቋም በአገር ኢኮኖሚ ጉዳት በማድረስ፣ መከላከያው ኃላፊነቱን በሚገባ እንዳይወጣ በማድርግ በማናቸው መንገድ በማሰናከል፣ ወታደሩ እንቢተኛ እንዲሆን፣ እንዲከዳና መሰል ድርጊቶች እንዲፈጽም በማድርግ ወንጀል የተሳተፉ አካላት ምህረት መደረጉን አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል።


በአንቀጽ 248 እና 249 ላይ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ አደራ የተጣለበት ማንኛውም ሰው መሳሪያ በመያዝ ኢትዮጵያን የተቃወመ፣ የአገርን ምስጢር ሰነድ ለሌላ አካል፣ ድርጅት በማስተላለፍ እንዲሁም በአንቀጽ 252 ለውጭ አገር መንግስትና ድርጅት ሲል በተቋም፣ በድርጅት፣ በዜጎች ላይ ጉዳት በሚያደርስ ሁኔታ በፖለቲካ፣ በዲፖሎማሲ፣ በወታደራዊና ስለላ ስራ በመሳተፍና በመደራጀት ምስጢር በማስተላለፍ ወንጀል ለተሳተፉም ምህረት መደረጉን ገልጸዋል።


የወንጀል ሕግ አንቀጽ 256 በመተላለፍ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማፍረስ፣ የአገሪቷን ግዛት ወይም ሉዓላዊነት በመተላለፍ በመንግስት የውጭ ደህንነትና በመከላከያ ኃይሉ ላይ ወንጀል ለመፈጸም በማሰብ ወታደሮችን፣ የሽምቅ ተዋጊዎችን፣ ሽፍቶችን፣ ቅጥረኞችን በመጠቀም በመመልመል፣ በማቋቋም፣ ወደ አገር ውስጥ በማስገባትና የጦር መሳሪያዎችን በማዘጋጀት ወንጀል የተሳተፉትን ምህረቱ ተመልክቷቸዋል።


በተመሳሳይ አንቀጽ የተጠቀሱ ወንጀሎችን እንዲፈጽሙ በማድረግና በማናቸውም መንገድ በመገፋፋትና ግዙፍ በሆነ መንገድ ተግባር የተሳተፉት ምህርት መደረጉን ገልጸዋል።


በአንቀጽ 288 በመተላለፍ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን በመጠቀም ከወታደራዊ አገልግሎት ለማምለጥ በማሰብ የጦር ክፍሉን ወይም ወታደራዊ ነክ አገልግሎት ተግባሩን በመተው ወይም በፈቃድ ሂዶ ወደ ክፍሉ ሳይመለሱ በኩብለላ ወንጀል የተሳተፉ ምህረቱ ተደርጓል።


“በወንጀል ሕግ 438 ሕዝብ በመንግስት ላይ እንዲያምጽ በማድረግ በመንግስት ወይም በህዝብ ባለስልጣናት የሐሰት ወሬዎችን ሃሜቶችን በማውራት ህዝብን በማነሳሳት ወንጀል ሙከራ የተሳተፋችሁ ምህረት ተደርጎላችኋል” ብለዋል።


የምህረት አዋጁ ከወንጀል ህጉ ባሻገር በ2001 ዓ.ም በጸደቀው የጸረ ሽብር አዋጅና በ2009 እና 2010 ለወራት ታውጀው በነበሩ የአስቸካይ ጊዜ አዋጆች የተጠቀሱ አንቀጾችንም ይጠቅሳል።


በሶስቱም የሕግ ማዕቀፎች የተጠቀሱት አንቀጾች እንዳሉ ሆኖ ግን የሰው ሕይወት ያጠፉ ግለሰቦችን በተመለከተ በልዩ ሁኔታ ምህረት የማይደረግላቸው ወንጀሎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።


በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች አስረኞች ሲለቀቁ ሁሉም እስረኛ እንደሚለቀቅ ማሰብ ህጋዊ አለመሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ፣ ከተጠቀሱት አንቀጾች ውስጥ በሌሎች ወንጀሎች ላይ ምህረት አለመደረጉን ገልጸዋል።


ስለሆነም በተጠቀሱ ወንጀሎች የምህረቱ አዋጅ ተጠቃሚዎች ላይ የወንጀል ምርመራው ያልተጀመረባቸው እንዳይጀመር፣ የተጀመረባቸው እንዲቋረጥ፣ የጥፋት ውሳኔው የተላለፈባቸው ውሳኔው እንዲሻር፣ የተፈረደባቸውም ቅጣቱ እንዳይፈጸምና ጥፋተኛ እንዳይባሉ መታገዱን አስገንዝበዋል።


የምሕረት አዋጁ ለቀጣይ ስድስት ወራት የሚዘልቅ ይሆናል ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ የምህረት አዋጁ ተጠቃሚዎች በአጠቃላይ ዐቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤት ወይም በክልል ፍትህ ቢሮዎች በአካል በመቅረብ፣ በወኪል፣ በስልክ፣ በፖስታና በድረ-ገጽ የተዘጋጀውን ፎርም መሙላት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።


ከኩብለላ ወንጀል ጋር ተያይዞ በርካታ ወንጀሉ የሚመለከታቸው አካላት ስላሉ በመከላከያ ሚኒስቴር በኩል በተዘጋጀው የመመዝገቢያ ቅጽ እንዲመዘገቡ አስታውቀዋል።


ምህረት የተደረገላቸው አካላት ወደ ማህበረሰቡ ገብተው እርቅ የመፈጸም ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።


በስድስት ወራት ውስጥ በተጠቀሱ መንገዶች የመመዝገቢያ ፎርም ያልሞሉ የወንጀል ተሳታፊዎች ግን የምህረት አዋጁን ላለመጠቀም እንደወሰኑ ተቆጥሮ የአዋጁ ተጠቃሚ እንደማይሆኑ መግለጻቸውን ከኢዜአ ያገኘነው ዜና ያስረዳል።

በይርጋ አበበ


ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በመላው ኢትዮጵያ በሚያስብል መልኩ አብዛኛው አገሪቱ ክፍል ድጋፍ ሰጥቷቸዋል። ህዝቡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፉን ለመስጠት የቻለበትን ምክንያት ሲናገርም ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶችን በዋናነት ያስቀምጣል። በመጀመሪያ ደረጃ የሚቀርበው የድጋፋቸው ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከብሔርና ከነገድ የተለየ አመለካከትን ይዘው መቅረባቸው ሲሆን በተከታይነት የሚቀርበው ምክንያት ደግሞ እስረኛን ከማስፈታት ጀምሮ በተለያዩ መስኮች የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋ የሚያስችሉ ተግባራትን መፈጸማቸው ነው ሲሉ ይናገራሉ።


ሆኖም ይህ የዶክተር አብይ አህመድ ከአገር ውስጥ እስከ ጎረቤት አገርና ገልፍ ባህረ ሰላጤ ድረስ የዘለቀው ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶችና የአገር ውስጥም የህዝብ ድጋፍ ዘላቂነቱን የሚጠራጠሩ ምሁራንና ፖለቲከኞች አሉ። ለዚህ ስጋታቸው የሚቀርቡት ቀዳሚ ምክንያት ደግሞ የዶክተር አብይ አካድ ተቋማዊ መልክ አልተላበሰም በማለት ነው። ተቋዊ መልክ ያተላበሰ ለውጥ ደግሞ ውጤቱ ዘላቂነት አይኖረውም ሲሉ የሚሰጉ ሲሆን አያይዘውም በከፍተኛ አመራች የተካሄደው የለውጥ ጅማሮ ወደታችኛው የስልጣን ተዋረድ አልዘለቀም ሲሉ ያቀርባሉ። የምሁራኑንና የፖለቲከኞችን ሃሳብ ከዚህ በታች እናቀርበዋለን።

 

የለውጥ ጅማሮውና የህዝብ ጥያቄ

 

ከ1997 ዓ.ም ብሔራዊና አገር አቀፍ ምርጫ ማግስት ኢህአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ደም የተቃባበት ዘመን ነው ሲሉ ፖለቲከኞቹ ይናገራሉ። በአንጻሩ ኢህአዴግ በአገሪቱ ላይ ተጨባጭ የኢኮኖሚና ማህራዊ ስኬቶችን አስመዝግቤያለሁ ሲል ይናገራል። ለዚህ ስኬቱ ጠቋሚ ውጤቶች ብሎ የሚቀርባቸው ደግሞ እንደ ህዳሴ ግድብ፣ የባቡር ሀዲድ ዝርጋታ እና የመሳሰሉትን የኮንስትራክሽኑን ዘርፍ ውጤቶች ነው።


ይህን የልማት ጅማሮና ውጤቶች መቀበል አይከብደንም የሚሉ ምሁራንና ፖለቲከኞች ደግሞ ኢህአዴግ ከዴሞክራሲ ጋር ዐይን እና ናጫ ሆኗል ሲሉ ይወነጅሉታል። ለዚህ መከራከሪያቸው አስተማማኝ አስረጂ አድርገው የሚቀርቧቸው ምስክሮች ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን፣ የጸረ ሽብርተኝነት እና የበጎ አድራጎት አዋጆችን በማንሳት ነው። እነዚህ አዋጆች ህዝብን ለማፈን ተቃውሞን ደግሞ ለማጥፋት የታቀዱ ስልታዊ ማጥቂያዎች ናቸው ብለው ይናገራሉ።


በተለይ በጸረ ሽብርተኝነትና በጋዜጠኝነት ላይ ወጡ አዋጆች በርካቶችን ለእስርና ለስደት የዳረጉ ሲሆን የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መኖራቸውን ደግ መንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። በዚህ በኩል ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ሲወጡ የወሰዷቸው እርምጃዎች ሁሉም በሚያስብል መልኩ የህዝብ ጥያቄዎች ነበሩ ይላሉ አስተያየት ሰጪዎች። ዶክተር ተፈሪ ብዙነህ በዚህ ሃሳብ የሚስማ ምሁር ናቸው። እንደ ምሁሩ አረዳድ ‹‹በርካታ ዜጎች ወላቻቸውና ቤተሰባቸው ለእስር ተዳርጎ በመቆየቱ ህዝብ የታሰሩበት ወገኖቹ እንዲፈታ ሲጠይቅ ቆይቷል›› ሲሉ ንግግራቸውን ይጀምራሉ።


በዚህ የተነሳም ኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረው የአመራር ለውጥ ለህዝብ ይዞ ቀረበው ተስፋም ሆነ ጅማሮ ለህዝብ ጥያቄ መልስ የሰጠ መሆኑን የሚምኑት ምሁሩ፤ ለውጡና የተገኘው ምላሽ ግን ከህዝብ ጥያቄ ጋር ሲነጻጸር ገና መሆኑን ይናገራሉ። በተለይም ለውጡ ወደታችኛውና መካከለኛው የገዥው ፓርቲ አመራር ያልወረደ መሆኑ ህዝብ አሁን በስጋት ውስጥ እደሚገኝ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።


አቶ ቴዎድሮስ መብራቱ የተባሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሲቪክስ መምህር በበኩላቸው የአመራር ለውጡ እና የለውጡ ጅማሮ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ቢጋሩትም ስጋት እንዳሏቸው ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ የሚያቀርቡት ምክንያት ህዝቡ ለለውጥ የተዘጋጀ እና ነጻነትን ለመሸከም ዝግጁ ሆኖ እንዳላገኙት ይናገራሉ። አሁን አሁን በህዝቡ ላይ የሚዩት የመለያየት ስሜትና በየአቅጣጫው እየፈነዳ ያለው ግጭት ለውጡን በእንጭጩ ለማስቀረት ይችላል ብለው እንደሚምኑ ገልጸዋል። ነገር ግን ህዝቡ መተባበር ካሳየና አንድ ከሆነ ይመጣል ብለው የሚስቡት ስጋት እንደማይደርስ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ። ለዚያ ስኬት ደግሞ ዶክተር አብይም ሆኑ ካቢኔያቸው በቅድሚያ ሊያከናውኑት የሚገባቸው የቤት ስራዎች መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ ቴዎድሮስ፤ ተቋማዊ በሆነ መልኩ ለውጡ ሊመራ ይገባ ሲሉ ይናገራሉ።


በአሜሪካን አገር የሚኖሩትን አንጋፋው ምሁርና ፖለቲከኛ ዶክተር አክሎግ ቢራራ “ድርጅታዊ ምርመራ” በሚለው መጽሃፋቸው፤ ኢህአዴግ በብድርና በእርዳታ ሰራኋቸው ከሚላቸው የልማት ስኬቶቹ በተጓዳኝ በአገሪቱ ሙስናን እና የዘር ጥላቻን፣ የአንድ ፓርቲና የአንድ ብሔርን የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነት ያጎናጸፈ ነው›› ሲሉ ይገልጹታል። አያይዘውም አሁን በአገሪቱ የተፈጠረው ለውጥ በኢህአዴግ ውስጥ ከተፈጠረው የአመራር ለውጥ ጋር የተገናኘ መሆኑን ይናገራሉ። በዚህ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚወስዱት ድርሻ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

 

የዴሞክራሲ ለውጥ እና የመንግስት ውሳኔ

 

የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ቀደም በምህረት እና በይቅርታ መልክ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታቱ ይታወሳል። ሆኖም እስካሁን የተደረገው እስረኛን የመፍታት ስራ ግን በህግ እና በስርዓት መልክ ሳይሆን በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ሲባል በመንግስት መልካምነት የተደረጉ ነበሩ ማለት ይቻላል። ከትናንት በስቲያ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ አቶ ብርሀኑ ፀጋዬ ያረጋገጡትም ይህንኑ ነው።


መንግስት ደግሞ በቀጣይ አገሪቱን ወደዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ይመራታል ብሎ ያሰበውን ተቋማዊ አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ “የምህረት አዋጅ” ማውጣቱን የገለጹት ጠቅላይ አቃቢ ህጉ፤ እስከ ግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም የተፈጸሙ ጥፋቶችን መንግስት ምህረት እንደሚደርግ ጨምረው ተናግረዋል። ምህረት የተደረገላቸው ግለሰቦችና ህጋዊ ሰዎች (የፖለቲካ ድርጅቶች) በምህረት አዋጁ ተጠቅመው ከእስር ይፈታሉ፣ ክሳቸው ይቋረጣል እንዲሁም በውጭ አገር የሚኖሩም ወደ አገራቸው እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።


የተቋማዊ ለውጥ ናፍቆት

 

አቶ ቴዎድሮስ መብራቱም ሆኑ የስነ ትምህርት ምሁሩ ዶክተር ተፈሪ ብዙአየሁ የሚናገሩት በአገሪቱ የተፈጠሩ ለውጦች ተስፋ ሰጪ ቢሆኑም ፈጽሞ እንከን አልባ አይደሉም። ለዚህ ደግሞ የመንግስት ውሳኔ በተቋማዊ አደረጃጀትና መዋቅር ሊታገዝ ይገባዋል።


ኢትዮጵያ ከአጼ ቴዎድሮስ እስከ ዶክተር አብይ ድረስ ስትመራ የመሪ ብቃት ችግር የለባትም›› የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ ችግሩ የተቋማት ግንባታ ላይ ስላልተሰራ ለውጦች ቀጣይነት ሳይኖራቸው ይቀርና በእንጭጩ ይቀጫሉ ብለዋል። አሁንም ዶክተር አብይ በአትዮጵያ መሪነት ታሪካቸው ሲወሳ የሚኖረው በፈጠሩት ለውጥ ሳይሆን በሚፈጥሩት ተቋማት ግንባታ ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ። ለዚህ ደግሞ የፍትህ ስርዓቱ፣ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ሁሉንም የዴሞክራሲ ተቋማት በተጠና መልኩ ሊዋቅሩ ይገባል ብለዋል።


ዶክተር ተፈሪ ብዙአየሁ ደግሞ በተቋማት ግንባታ ላይ ከአቶ ቴዎድሮስ ጋር ተመሳሳይ ሃሳብ ቢኖራውም በዋናነት ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡት ተቋማት ግን የደህንነት፣ የመከላከያ እና የፖሊስ ተቋማት ገለልተኛ ሆነው ሊዋቀሩ ይገባል ይላሉ። አያይዘውም በአገሪቱ የተፈጠሩ ለውጦች መልካም ቢሆኑም ከእስር የተፈቱ እና ሰዎቹን ወደ እስር ቤት የላኩት ሰዎች አሁን በአንድ ሜዳ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው በበቀል መልኩ ችግር ሊፈጠር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። በተለይ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል አስተዳዳሪዎች ላይ በላይኞቹ እርከን በኩል ለውጥ መፈጠሩን አስታውሰው ሆኖም በታችኛውና በመካከለኛው አመራር በኩል ግን የተፈጠረ ለውጥ አለመኖሩን በጥንቃቄ ሊታይ ይገባዋል ይላሉ።

አሰፋ አደፍርስ (ከዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ)

 

ይህችን አነስተኛ ጽሑፌን ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚወዷቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚደርስ ከፍተኛ እምነት አለኝ።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ከተረከቡ ከ100 ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ማንም ያላሰበውን ተራራ ያህል ርቆን የነበረን የመከራ ጊዜ የማሳለፍ ጭላንጭል ስላሳዩን እጅግ በጣም በግል ከማመስግናቸው ፈጣሪ አምላካችን ይህንን እኩይ ተግባር አስወግዶ ጭላንጭል ስላሳይየን ምስጋና ይገባዋል፤ ለክቡር ሚኒስትራችን ብርታቱንና የማስተዋል ኃይላቸውን እንዲያጠናክርልን እፀልያለሁ።

አባቶች እንደሚሉት አንድ አይነግሥ አንድ አይነድ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያሻል። ክቡር ጠ/ ሚኒስትሩ ስለፍቅር፤ ስለ ይቅርታ፤ ስለአገር አንድነትና ወሰን የሌለሽ ግንኙነት እንዲፈጠር ራዕያቸው እንደሆነ ደጋግመው ሲናገሩ እንሰማለን፤ እናደንቃለንም፤ ግን እማን ላይ ቆመሽ እግዜርን ታሚያለሽ አይነት ሁኔታ እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ያሻል። በማን ነው የተከበቡት? ይህንንስ እንዴት ነው፣ የሚለዩት? ጥንቃቄ ያሻል!!

ይቅር ማለት፤ ይቅር መባባል የክርስትናም የእስልምናም እምነት እንደሆነ አልጠራጠርም። ይቅር ማለት ግን ሌባን መልሶ የሰረቀበት ምንጭ ላይ ማስቀመጥ ሳይሆን ባደረገው ተፀፅቶ ወደ ነበረበት መልካም ሕብረተሰብ እንዲመለስ እንጂ ያንን የለመደበትን ሥፍራ ይዞ ድጋሚ ይቅርታ እንዲጠይቅ አይደለምና ይህ ጉዳይ ቢታሰብበት መልካም እንደሚሆን የሁሉም ጥሩ ኢትዮጵያዊያን ምኞትና ፍላጎት እንደሆነ አልጠራጠርም።

ከጉራፈርዳ ሰውን አጋድሎ የሰውን ደም እንደጎርፍ አፋስሶ ከአስገዳይ ጓዶቹ ጋር በከፍተኛ ደረጃ በለመደው ተግባሩ ሌላውንም እንዲያከናውን ተሾሞ ሳለ ከቦታ ቦታ ሲመቻችለትና እንደልቡ ሲቧርቅ ያሁኑ አስተዳደር በመምጣቱ እሰየው አረፍን ሌቦች ጉዳቸው ፈላ ብሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከታች እላይ ድረስ ሲፈነድቅ፤ ወያኔ ያደርግ የነበረው የዘር ሽኩቻ ሊጠፋና ኢዮጵያውያን በዕውቀት በችሎታቸውና በአገልግሎታቸው መሰረት እንጂ በአጎት ልጅነት፤ በአቶ እገሌ ጀሌነት ወይንም የክርስትና ልጅነት የመሿሿሙ ሒደት አለፈ ተገላገልን፣ እግዚአብሔር ይመስገን በምንልበት ጊዜ ከድጥ ወደ ማጡ ይመስል ከላይ እስከታች ድረስ በዘር የተንጠላጠለ ሁኔታ መታየት መጀመሩ እጅግ አስደንጋጭ እየመሰለ ነውና ሳይርቅ በቅርቡ ቢታሰብበት መልካም ነው እላለሁ።

የአዲስ አበባን ታሪክ የማይገነዘብ አለ ብዬ አላምንም፤ የሱሉልታው ከተማ ከንቲባ፤ ሱሉልታን እንኳ በትክክል ማስተዳደርና ከተማዋን ፕላን የለሽ የድንጋይ ዳቦ ዘመን የምትመስለው በግንብና በቆርቆሮ በመሸፈኗ ብቻ ነው፤ ከተማዋን ሸንሽኖ ዳይስፖራ ተብዬዎች በምን ጥቅም እንዳካፈለ ለመግለጽ አልችልም፡፡ ግን የተከፋፈሉትን ቦታዎችና የልማትና የከተማ ፕላንን ሄዶ መመልከት በቂ ይሆናል። ታዲያ ይህ ሰው ነው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የሚሆነው? የቀድሞ ከንቲባ ዲሪባ ኩማ ላደረጉት ስህተት በግል ደብዳቤ ጽፌላቸው ነበር፡፡ ግን መልስ ሳይሰጡኝ ኖረው ከሥልጣን ተነሱ፤ ተሾሙም፤ ይገርማል፡፡ በዘር መደራጀት ከዚህ ሌላ ምን ሊያመጣ ይሆን? ይታሰብበት።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ችግርዎም ይገባናል፤ በማን እንደታጠሩም እናውቃለን፤ ግን ረጋ ብሎ ማሰብ፤ አዋቂ ሰዎችን ማሰባሰብ መልካም ይሆናልና ይታሰብበት፡፡ አዲስ አበባ እኮ በእነ ከንቲባ ታከለ ተክለሐዋሪያት፤ በእነ ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ፤ ከንቲባ ዘውዴ ገብረሕወት በእነዶክተር ኃይለጊዮርጊስ ወርቅነህ ብዙዎችም አሉ። ከንቲባ ኃይለጊዮርጊስ ወርቅነህ በምህንድስና ሳይንስ የዓለም ሣይንቲስቶች ያልፈጠሩትን የውሃ ውስጥ ምህድስናን ለአሜሪካ አሳይተው ከፍተኛ ሥራ ላይ ከዋሉ በኋላ የሰው አገር ለምኔ ብለው ሁሉንም ትተው አገራቸው ገብተው ያገለገሉ ሙሑር ጀግና ነበሩ። ራስ እምሩን ሳነሳ የዘመኑ ሕዝብ ቀደምቱን የሚጠላ ስላለ ራስ እምሩን ከንቲባ ዘውዴን ለምን አነሳህ የሚል ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ። የኔ አጻጻፍ ከልማዳቸውና ከችሎታቸው የተነሳ እንጂ በነበራቸው የመንግሥት ሁኔታን ለመደገፍ ወይንም ለመቃወም ሳይሆን የችሎታቸውን፤ ላገር ያበረከቱትን አስተውጽዖን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው።

ፀሐፊውን ለማግኘት የሚከተለውን አድራሻ ይጠቀሙ፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.


በመኮንን ተሾመ ቶሌራ

(ዘ ገዳም ሰፈር)

ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዐብይ አህመድ ባዕለ-ሲመታቸውን በቀጥታ በቴሌቭዥን መስኮት እየተከታተልኩ ነበር። የቀጥታ ስርጭቱ ባበቃ በአስር ደቂቃዎች ውስጥ “የጠቅላይ ሚኒስትራችን እናት” የሚል ፅሁፍ ለማኀበራዊ ሚዲያ ጽፌ ነበር። ይህን ያደረኩት ከዚህ ቀደም እንደዚህ ሰውን የሚያመሰግን፣ ሰው ሰው የሚልና ለሰዋዊ ስሜት ቅርብ የሆነ መሪ አይቼ ባለማወቄ እንደሆነ በወቅቱ ገልጬ ነበረ። ይህ ፅሁፍ በጋዜጣም ታተሞ በርከት ያሉ አንባቢያን እንደወደዱት ገልጸውልኝ ነበር።

መቼም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሰዋዊ ስሜት ያላቸው አንደበተ ርዕቱ እና የተሳካላቸው የአደባባይ ንግግር አዋቂ መሆናቸውን ሁላችንም አይተናል። በዚሁ ምክንያት ብዙዎች ተማርከውና ተደምመው የሠላም ጥሪያቸውን ተቀብለዋል።

እሳቸውም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በመላ ሃገሪቱ እየዞሩ ሠላምን ሰብከዋል፣ የታሰረ አስፈትተዋል፣ የተጣላ አስታርቀዋል በጐረቤት ሃገርና በወዳጅ ሃገሮችም በሚያስደንቅ ፍጥነት እየተጓዙ አብሮነታቸውን ለማሳመንና አጋር ለመሆን ጠይቀዋል፣ በዚህም ተሳክቶላቸዋል። በተለይ ሰሞኑን ከኤርትራ ጋር ያደረጉት የሠላም ግንኙነትና ግጭትን የመፍታት ሥራ ከፍ ያለ ዋጋ የሚሰጠው ነው። በዚህም እሳቸው ራሳቸው እንዳረጋገጡልን የኢትዮጵያ ተፈላጊነትና የአለም አቀፍ የገበያ ሁኔታ እየተሻሻለ ነዉ።

በኔ አመለካከት ባጠቃላይ የጀመሩት የሠላምና የፍቅር ዘመቻ በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚጠቀሱት የሠላም፣ የእኩልነትና የመብት ተሟጋቾች ከነማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ከነማህተመ ጋንዲ፣ ከነ ማልኮልም ኤክስ፣ ከነቦብ ማርሌ ተርታ እንዲሰለፉ የሚወስዳቸው መንገድ ላይ ያስቀመጣቸው ይመስለኛል። እሳቸውም ቀደም ሲል የሃገራችንን አርቲስቶች ሰብስበው በሚናገሩበት ወቅት እነ ማርቲን ሉተርን፣ እነ ማልኮልምን፣ እነ ቦብ ማርሌን እያነሱ ተምሳሌትነታቸውን ሲናገሩ የእነዚህ ሰዎች ተፅዕኖ ሊኖርባቸው እንደሚችል መገመት ችዬ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትራችን ማንንም ምሳሌ ያድርጉ፣ ከማንም በጐ ነገርን ይማሩ በዚህ ጊዜ እያደረጉ ያሉት ነገር በብዙዎች ተቀባይነትን አግኝቷል። ውጤትም እያፈራ ይገኛል።

ታዲያ ዛሬ ደግሞ ብዕሬን ላነሳ የወደድከት የተሾሙ እለት የተሰማኝን እንደገለፅኩ ሁሉ አሁንም ከዚህ በኋላ ሊያደርጉት ይገባል የምለውን በኔ አመለካከት ለመግለፅ ፈልጌ ነው።

እናም በአሜሪካን ሃገር እ.ኤ.አ. ከ1945 እስከ 1975 የሃገሪቱን የሲቪል መብቶች እንቅስቃሴ (Civil Right Movement) የመሩትን እነ ማርቲን ሉተርና እነ ማልኮልምን እንደመሰሉ ሁሉ ከዚህ በኋላ ከ1960 እስከ 1968 የኢኮኖሚ ሪፎርም እና ታላቅ ማህበረሰብ ‘’ Great Society’’ እውን ለማድግ የለፋትን ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲንና በሳቸው እግር የተተኩትን ሊንደን ጆንሰንን ቢመስሉ ተገቢ ይመስለኛል።

በ1963 ተወዳጁ ማርቲን ሉተር በዋሽንግተኑ ሰልፍ “March on Washington” ላይ “ህልም አለኝ” (I have a dream) የሚለውን ታላቅ ንግግሩን ካደረገ በኋላና የአሜሪካው ኮንግረስ በ1964 የሲቪል መብቶችን ህግ (Civil Rights Act) ካፀደቀ በኋላ እንዲሁም በ1960 ዓ.ም ጆን ኤፍ ኬኔዲ ከሪቻርድ ኒክሰን ጋር ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ ተወዳድረው የኬኔዲን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ በሀገረ አሜሪካ በርካታ ለውጦችና ተስፋዎች መታየት ጀምረው ነበር።

በሰሜን አሜሪካ በዚያን ዘመን የተከሰቱ ነገሮች በሙሉ ከአሁኑ የሃገራችን ሁኔታ ጋር ፍጹም ተመሳሳይነት ነበራቸው ማለት ባይቻልም በተወሰነ መለኩ ልንማርባቸው የምንችላቸው ነገሮች በመኖሩ ባጭሩ መዳሰስ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

በወቅቱ በኢኮኖሚያዊና በማኀበራዊ ጉዳዩች ተሳትፎ ጥቂቶች ተጠቃሚ ሆነው ሌሎች የተገለሉበት፤ ፍትህ የተዛባበት ሁኔታ በስፋት ይታይ ነበር። በተለይም ጥቁር አፍሪካ አሜሪካውያን ከኢኮኖሚያዊና ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች የተገሉበትና ከፍተኛ በደል የሚደርስባቸው አግባብ ይስተዋል ነበር። ጥቂቶች የሰውን ጉልበት በተለይም የጥቁሮችን እየበዘበዙ ይከብሩ ስለነበር ብሶቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። ጾታዊ እኩልነትም ባለመኖሩ ምክንያት ሴቶች የአደባባይ ትግል ጀምረውም ነበር።

በዚያን ጊዜ የነበረው የአሜሪካ የእኩልነትና የፍትህ እጦት በዋነኝነት ከስርዓትና ከሕግ ክፍተቶች ጋር ይያያዝ ስለነበር በአሁኑ ሰዓት ሃገራችን ውስጥ ካለው እኩል ተጠቃሚነትና የዴሞክራሲ እጦት ችግሮች ጋር ፍፁም የሆነ ተመሳሳይነት እንደሌለው እሙን ነው።

በዚያን ዘመን በአሜሪካ ነጮችና ጥቁሮችን፣ ወንዶችና ሴቶችን፣ ሀብታሞችና ደሃዎችን እኩል ለማረግ በ1964 ዓ.ም. የፀደቀው የሲቪል መብቶች ህግ እና ሌሎችን ህጐች አርቅቆ ማፅደቅ ተገቢ ነበር። ከዚህ አንፃር በኛ አገር በአሁኑ ሰዐት ብዙም በህግ ክፍተት ባናሳብብም በዚያን ዘመን በአሜሪካ ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ለማምጣት የተጠቀሙበትን ዘዴች መመልከተ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

የምርጫ ህግ፣ የእስረኞች መብትና የፍትህ ስርዓት

በ1960ቹ በአሜሪካን ከተደረጉ ጠቃሚ እርምጃዎች በከፍተኛ ፍርድ ቤቱና በአቃቤ ህጉ የተወሰዱት ዋነኞቹ ናቸው። በወቅቱ ዋና አቃቤ ሕግ በነበሩት በኤርል ዋረን አማካኝነት የሲቪል መብቶችን እና ነፃነቶችን፣ የምርጫ ህጐችን እንዲሁም የግለሰቦችን መብቶች የተመለከቱ የህግ እርምጃዎችና ማቫሻያዎች ተወሰዱ። በወቅቱ በሀገሬው ህዝብ የዋረን ፍርድ ቤት “Warren Court” በመባል የሚታወቀው ተቋም በማኀበራዊ፣ ሀይማኖታዊና ፖለቲካዊ የሆኑና አጨቃጫቂ የነበሩ ጉዳዩችን ባደረገው ሪፎርም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲፈቱ አድርጓል። ምርጫን በተመለከተም በተለይም ፍርድ ቤቱ “አንድ ሰው አንድ ድምፅ” የሚለውን ዐብይ ፍልስፍና አፅድቆ በሀገሪቱ የምርጫ ስርዓት እንዲሰራበት አድርጓል።”

ከዚህ አንፃር በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋትና የፖለቲካ ኃይሎችን በስፋት ማሳተፍ ስለሚያስፈልግ በዚሁ ዘርፍ በተለይ የምርጫ ስርዓቱ አሳታፊና አመቺ እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል።

በአሜሪካን ሃገር በዚያን ዘመን ማለትም በ1963 ዓ.ም. ፕሬዝዳንት ኬኔዲን የተኩት ጆንሰን በቀጣዩ ዓመት በ1964 ዓ.ም. በምርጫ መሳተፍና ማሸነፍ ይጠበቅባቸው ነበር። ጆንሰን ያሰቧቸውን ትላልቅ ዕቅዶች ለማሳካትና ዳር ለማድረስ ይችሉ ዘንድ ወደ ሥልጣን በመጡ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚደረገውን ምርጫ ማሸነፍ ነበረባቸዉ። እናም ተወዳዳሪያቸው የነበሩትን ባሪ ጎልድዋተርን በብልሃት አሸንፈው በድህነት ላይ የጀመሩትን ዘመቻ ለመቀጠል ችለው ነበር።

የጆንሰን መንግስት በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ የሆነውን የእስረኞች ወይም የታራሚዎችና የተከሰሱ ሰዎችን መብት በተመለከተም ወሳኝ የሆኑ የህግ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ በማድረግ የሃገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይበልጥ እንዲጠናከር አስችሏል።

ከዚህ አንፃር በሀገሪቱ የሚከሰስ ማንኛውም ሰው የመክፈል አቅም ቢኖረውም ባይኖረውም ጠበቃ የማግኘት መብት እንዲጠበቅለት የሚለውም ህግ በአሜሪካ ወጥቷል። በመሆኑም ማንኛውም በህግ ጥላ ስር ያለ ሰው ይህ መብቱ ሳይነገረው በፀጥታ ኃይሎች የተሰበሰበበት ማንኛውም ማስረጃ ዋጋ እንደማይኖረውም ታወጀ።

በዚያን ዘመን ከተለያዩ ህዝባዊ አመፆችና የመብት ትግሎች ወጥታ የተረጋጋች አሜሪካን ለመገንባት የተደረገው የፍትህ ስርዓት እና የዳኝነት ነፃነት ማሻሻያ ወሳኝ ሚና እንደነበረው ማስተዋሉ ለሁላችንም እንደ አንድ ትምህርት የሚወሰድ ይመስለኛል።

በተመሳሳይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በአጭር ጊዜ ውስጥ የምርጫ ውድድር የሚጠብቃቸው ከመሆኑም በላይ በአጠቃላይ ለፖለቲካ ኃይሎች አመቺ የፖለቲካ ምህዳር እንዲፈጠር መስራት ይኖርባቸዋል። ለዚህም ከምርጫ ህጉ እስከ ህገ-መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ ሊያስፈልግ ይችል ይሆናል።

“ታላቅ ማኀበረሰብ” የመፍጠር ሥራዎች

በአሜሪካ በ1963 ዓ.ም ኘሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ወደ ዳላስ ቴክሳስ ግዛት በተጓዙበት ወቅት ሊ ሃርቬይ ኦስዋልድ በተባለ ግለሰብ ከተገደሉ በኋላ በእግራቸው የተተኩት ምክትል ኘሬዝዳንታቸው ጆንሰን የህዝቡን ህይወት ለመለወጥ ከፍተኛ ዘመቻ አድርገዋል። ጆንሰን በተለይ “ታላቅ ማኀበረሰብ” መፍጠር የሚል ዘመቻቸው በሃገሪቱ ታሪክ እስካሁን የሚታወስ ታላቅ ተግባር ነበር። ቀደም ሲል በኘሬዝዳንት ኬኔዲ የተጀመሩ የሲቪል መብቶች እንቅስቃሴዎችና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎችን፣ ጠንካራ ሰራዊት የመገንባት እና በቀዝቃዛዉ ጦርነት (Cold War) አሸናፊ የመሆንን ኃላፊነት የወሰዱት ጆንሰን በራሳቸውም በኩል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በድህነት ላይ ጦርነት “war on poverty” አዋጅ አውጥተው እንዲጸድቅ አስደርገው ለሀገራቸው ሕዝብ “It is time to declare an unconditional war on poverty” ሲሉ በድህነት ላይ ከፍተኛ ጦርነት መታወጁን አሰረዱ። ከምንም ነገር በላይ ድህነትን ለመዋጋት ቆርጠው መነሳታቸውን ግልጽ አደረጉ።

ከዚህ ጋር በተያያዘ እ.አ.አ በማርች 15 ቀን 1965 ዓ.ም በሃገራቸው ኮንግረስ ፊት ቀርበው የተናገሩት የሚታወስ ነው።

‘’I do not want to be the president who built empires, or sought grandeur or extended dominion. I want to be the presidentwho educated young children… who helped to feed the hungry… who helped the poor to find their own way….’’

“እኔ ኢምፓየሮችን የሚገነባ፣ ወይም ታላቅና የተስፋፋ ሃገርን የሚያልም ኘሬዝዳንት መሆን አልፈልግም፣ እኔ መሆን የምፈልገው ወጣቶችን የሚያስተምር፣ የተራቡትን የሚያበላ እና ድሆች ከችግር የሚላቀቁበትን መንገድ የሚያሳይ ኘሬዝዳንት መሆን ነው የምፈልገው” በማለት ፍላጐታቸውን ገለጹ።

ፕሬዝዳንት ጆንሰን ፍላጎታቸውን በመግለጽ ብቻ ሳይወሰኑ በርካታ የሪፎርም እርምጃዎችም እንዲካሄዱ አስቻሉ።

በተለይም አሁን በሃገራችን ትኩረት ከተሰጣቸዉ እንደ ኢንዱስትሪና የማምረቻ ተቋማትን ማዘመንና የግብርና ስራን ከማሻሻልን ባሻገር ህብረተሰቡን ለማሳደግና ድህነትን ለማጥፋት የሚጠቅሙ ስራዎች በመላው ሃገሪቱ እንዲሰሩ አደረጉ። ከእነዚህም ዋነኞቹ ስፋት ያለው የአአካባቢ ጥበቃ ማድረግና የሸማቾችን መብት ማረጋገጥ፣ የጤና ኢንሹራንስን መስጠት፣ የትምህርት አገልግሎት እንዲሻሻል፣ የስደተኞች ፖሊሲ እንዲረቅ፣ የበጎ ፈቃደኝነት እንዲስፋፋ መስራት እና ሌሎች ተጀምረው የነበሩ ማኀበራዊ ስራዎች እንዲከናወኑ ማድረግ ነበር።

በጎ ፈቃደኝነት የወጣቶች ሥራ ፈጠራ

በጎፈቃደኝነትሰዎችያለምንምክፍያበሀገርፍቅርስሜትተነሳስተውበአካልናበአእምሮወገኖቻችንን የምያገለግሉበት መንገድነው።

በጎፈቃደኞችበሚሰጡት የነጻ ማህበራዊናኢኮኖሚያዊአገልግሎትእርካታንየሚያጐናፅፉሲሆን፣ህብረተሰቡደግሞከአገልግሎቱየሚያገኛቸውጥቅሞችዘርፈብዙገጽታአላቸው። በኢትዮጵያበጎፈቃደኝነትየረጅምጊዘታሪክያለውናሰዎችለሰዎችባላቸውቀናልቦናየሚያካሂዱትየመደጋገፍሂደትነው።በጎፈቃደኝነት አካባቢንናሀገርንበማሻሻልረገድየራሱአዎንታዊሚናአለው።

በመሆኑም የዩኒቨርሲቲ፣የኮሌጆች፣የቴክኒክናሙያተቋማት፣እንዲሁምየሁለተኛናየመሰናዶትምህርትተማሪዎችን እንዲሁም ሌሎችበገጠርምሆነበከተማየሚገኙበጎፈቃደኛወጣቶችምበሚሳተፉበትመልኩ ቢሰራ ዜጎች በሀገር ግንባታ ሂደት የበኩላቸዉን መወጣትይችላሉ። ጎን ለጎንም የተጀመሩት የወጣቶች ስራ ፈጠራ ተግባራት ተጠናክረዉ እንዲቀጥሉ ቢደረግም ይበልጥ ዉጤታማ መሆን ይችላል

ከዚህ አንጻር አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ወጣቶችን ለማነቃቃትና ሀገራቸዉን ለመገንባት እንዲሁም ለወጣቶች ስራ ፈጠራ የተጠቀሙበትና ዉጤታማ የሆኑበት ስለሆነ እኛም በጎፈቃደኝነትን በስፋት ልንሰራበት ይገባል

የአካባቢ ጥበቃና የሸማቾች መብት

የጆንሰን “ታላቅ ማኀበረሰብ” የመፍጠር መርሃ-ግብር በዋናነት አጠቃላይ የአሜሪካ ህዝብ ኑሮ እንዲሻሻል ያለመ ሲሆን ይህንንም ለማስቻል ከፍተኛ የንቃተ ህሊና ሥራ እንዲሰራ ተደርጓል። በተለይም በዚያ ዘመን (በ1960ቹ) በሀገሪቱ የአካባቢ ጥበቃና የሸማቾች መብትን የተመለከቱ ምርጥ ምርጥ መፅሐፍት ታትመው ለገበያ እንዲቀርቡ መደረጉ የራሱ አስተዋፅኦ እንደነበረው ይነገራል።

ለምሳሌም በወቅቱ በራቼል ካርሰን “Silent spring” (1962) በሚል ርዕስ የወጣው መፅሐፍ የኬሚካል ማዳበሪያና ፀረ-ተባይ እንዴት ሃገሩን እየበከለ እና ሸማቾች ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረ እንዳለ ግልጽ ያደረገበት ሁኔታ እና በራልፍ ናዴር የተጻፈዉና “Unsafe at Any Speed” (1965) የተሰኘው መፅሐፍ የአውቶሞቲቪ ወይም የመኪና መጓጓዣው ኢንዱስትሪ በብክለት እንዴት ህዝቡን እየጐዳው እንዳለ የተገለፀበት ሥራ በሃገሪቱ የህግ ማዕቀፍ ውስጥ ለውጥ ማምጣት ችሎ ነበር።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከሀገሪቱ የንፁህ ውሃ አቅርቦት እና በትራፊክ ስነ ሥርዓት ጋር ዙሪያ “The Water Quality Act (1965)” “The Clean Water Restoration Act (1966)” እንዲሁም “ The National Traffic and Motor Vehicle Safety Act (1966)” የተሰኙ አዋጆች መዉጣታቸዉ በዘርፋ ከፍተኛ እድገት እንዲመዘገብ አግዟል። ከዚህ አንፃር በተለይ በሀገራችን ጥቅም ላይ የዋሉ መኪኖች ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ የሚፈጥሩት ችግርና በጣም ያረጁ መኪኖችና በሥራ ያሉበት ሁኔታ በሰውና በአካባቢ ደህንነት ላይ የሚያመጣው ተፅእኖ በቅጡ ያመላከታል። ለዚህም ተገቢ ምላሽ መስጠት ያሻል።

የትምህርት ጥራት

በጆንሰን “ታላቅ ማኀበረሰብ” የመፍጠር ሥራ ውስጥ ሌላ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ለትምህርት ጥራት ነበር። በተለይም በአሜሪካ በዚያን ዘመን ድህነትን ለማስወገድና የማኀበረሰቡን ኑሮ ለማሻሻል ያስችላል የተባለው የ1965ቱ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ድጋፍ አዋጅ መውጣቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደነበረው ይታመናል። ይህ “Elementary and Secondary Education Act” የተባለው የህግ ማዕቀፍ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ዜጐችን ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ አስችሏል። በዚህም ኑሮአቸው እንዲቀየር ተደርጓል። ይህን አዋጅ ተከትሎም የፌደራል መንግስቱ በሀገሪቱ ላሉ በጣም በኑሮ ዝቅተኛ ለነበሩ ማኀበረሰቦች የተሟላ የትምህርት ቤቶች፣ ላይብረሪዎች፣ የቋንቋ ላቦራቶሪዎች እና ሌሎች የትምህርት አገልግሎቶች እንዲያገኙ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲመደብ አስችሎ ነበር። በዚህም ሃገሪቱ የዜጐቿን የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል በር ከፋች የሆነ ተግባር መፈጸም ችላ እንደነበር ይታያል።

የጤና ኢንሹራንስ

ፕሬዝዳንት ጆንሰን የማኀበረሰቡን የጤናና አጠቃላይ ደህንነት ለመጠበቅ ያደረጉት ሌላኛው ነገር ህብረተሰቡ የጤና መድህን ሽፋን እንዲኖረው ማድረግ ነበር። ይህም ጤነኛና ምርታማ ማኀበረሰብ እንዲፈጠርና አጠቃላይ ለውጥ እንዲመጣ በሚል ይህ “ታላቅ ማኀበረሰብ” የመፍጠር ራዕይ አካል የነበረው መርሃ ግብር በተለይ አዛውንቶችንና አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ያደረገ ነበር።

አሁን አሁን በአገራችን የተጀመሩ መሰል የማኀበራዊ ደህንነት ተግባራት በተለይ ሙሉ ጊዜውን ምርታማነት ላይ ሊያውል የሚችለውን የወጣቱን ክፍልም በተዘዋዋሪ ያግዛል ተብሎ ስለሚታይ መጠናከር ይኖርበታል። በኛ ሃገር ማኀበራዊና ቤተሰባዊ ግንኙነቱ ጠንካራ በመሆኑ ብዙ ወጣትና አምራች ሃይል የሆኑ አዛውንትና አካል ጉዳተኞችን በጉልበትም በገንዘብም በመደገፍ ይሳተፋሉ። መንግስት ይህንን ጫና መካፈሉ ፋይዳው ከፍ ያለ ይሆናል።

ከላይ የተጠቀሱት ቁልፍ ተግባርት የጆንሰንን አስተዳደር “ታላቅ ማኀበረሰብ” ለማሳካት እንዳስቻሉ ሁሉ በኛም ሃገር በአሁኑ ወቅት በጠ/ሚ ዐብይ አህመድ ለሚመራው መንግስታችን ሙሉ በሙሉ በወቅቱ በአሜሪካ የተሰሩ ሥራዎች እዚህም ይሰራሉ ባይባልም አቅጣጫዎችን በማመላከትና ምሳሌ በመሆን ያገለግላሉ የሚል እምነት አለኝ።

ከጉዳቱ እያገገመ ያለው የንግዱ ዘርፍ 

ከንግድ ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት ክፍል

 

ዶክተር አብይ አህመድ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሰየማቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ካደረጉት የኢትዮጵያዊያንን ቀልብ የሣበ ንግግራቸው ጀምሮ ሀገሪቷን ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ተጉዘው ከህዝብ ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች፣ በተለያዩ ጊዜያት እንደ ሀገር ባስተላለፏቸው ውሳኔዎች፣ በሰጧቸው መንግስታዊ መግለጫዎች እና ባሳዩት የህዝብ አገልጋይነት አቋም የተነሳ ተስፋ ቆርጣ የነበረችው ሀገራችን ተስፋዋ ዳግም ለምልሟል፤ ተደፍተው የነበሩ አንገቶች ቀና ብለዋል፤ ተቆልፈው የነበሩ አንደበቶች ተከፍተዋል።


የጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጥ ንቅናቄዎች ከበዓለ ሲመታቸው ቀን ጀምሮ በነበሩት ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ “የመደመር” እሳቤያቸው በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ የጋራ ዜማ መሆኑ እጅግ አስገራሚ ሆኗል። ኤርትራን ጨምሮ በበርካታ የጎረቤት ሀገራት ባደረጓቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ያነሷቸው የሠላም፣ የፍቅርና የመደመር እሳቤ ውጤቶች ከኢትዮጵያም አልፎ ለአፍሪካ፤ ከአፍሪካም ለአለም ህዝቦች የፍቅርና የመተሳሰብ አዲስ ብርሀን ፈንጥቋል። በኢትዮጵያ የመተሳሰብ ዘር ዘሪነት በአፍሪካ የሠላም ቀጠና በቅሎና አብቦ እንዲያፈራ የሚያስችል የፍቅር፣ የአንድነት፣ የሠላም፣ የይቅር ባይነት ዝናብ በኢትዮጵያ ሰማይ በዶክተር አብይ አሰተምህሮ ዘንበዋል።


በታሪክ አጋጣሚ በተፈጠረ ክስተት የጎሪጥ ይተያዩ የነበሩ ኢትዮጵያና ኤርትራ አስታራቂ ሽማግሌም ሳያስፈልግ ዛሬ ሁለቱ ሀገራት በስስት አይን የሚተያዩ አንድ አምሳል ሆነው በእኛነት መንፈስ በአንድነት ለመልማት፣ በአንድነት ለማደግ አንድ ቀበቶ ታጥቀዋል፤ በፍቅር መቀነት ተሳስረዋል። በእኔ እምነት የሰላምን፣ የልማትን፣ የእድገትን እና የአንድነትን ጠቀሜታ አስፍቶ በማየት የተፈጠረው ይህ የእኛነት አጀንዳ ታዲያ አጥሯን እያጠበቀች አትድረሱብኝ እያለች ለምትቧርቀው አሜሪካም ሆነ ለሰሜን ኮሪያ የተጋረደባቸውን “የእኔ ብቻ” የሚል ግለኛ የአስተሳሰብ ጨለማ የሚገፍ ይመስለኛል።


የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ሲመጡ “አሜሪካንን ለአሜሪካውያን ብቻ” የሚለው እሳቤ አመዝኖባቸው ሀገሪቷ ከዚህ በፊት ታደርጋቸው የነበረውን የንግድና ኢኮኖሚ ግንኙነቶች ከማቋረጥ በተጨማሪ ከውጪ ሀገራት በሚገቡ ምርቶች ላይ በጣም ከፍተኛ ቀረጥ በመጫን አዲስ የንግድ ጦርነት ሲከፍቱ እና የሌላ ሀገር ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ ቢሮክራሲዎችን ሲነድፉ አስተውለናል። በእኔ እምነት አሜሪካ በሯን ዘግታ በራሷ እድገትና በብልጽግና ብቻ እንድታስብ እያደረጓት ያሉት ትራምፕ ከአራቱ የሂሳብ ስሌቶች በመደመር የግለኝነትን ብራኬት/ቅንፍ/ በመስበር ያላቸውን ለሌሎች ለማካፈል ከሀገራችን ተራማጅ እሳቤ ተሞክሮ ቢወስዱ በአሜሪካን መስፈርት መሰረት ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ካበቃቸው የግል ሀብታቸው የበለጠ የእውቀትና የአስተሳሰብ ሀብት ያገኛሉ ባይ ነኝ።


በሀገራችን ዘላቂ ሰላምን፣ የልማት ተጠቃሚነትንና፣ የህዝቦች አንድነትን በማረጋገጥ ወደ ቀጣይ የልማትና የእድገት ጉዞ ለመዝመት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የሪፎርም ስራዎች እየተሰሩ ነው። በሀገር ውስጥ የህዝብን አንድነት በማስጠበቅ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሰላም በመፍጠር ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መንግሥት እያካሄደ ያለው ሀገራዊ ለውጥና ንቅናቄ በተለይም ለንግዱ ዘርፍ የላቀ ትርጉም አለው።


ንግድ ለሀገራችን ኢኮኖሚ መጎልበት ከግብርናው ያልተናነሰ ሚና አለው። የሀገራችን ኢኮኖሚ ማርሽ በሆነው የንግዱ ዘርፍ ሀገሪቷ የምትፈልገውን ለውጥና እድገት ማምጣት የሚቻለው በሁላችንም ተሳትፎ ዘላቂ ሠላም ሲረጋገጥ ብቻ ነው። ከሀገር ውስጥና ከጎረቤት ሀገራት ጋር የተረጋጋና ቀጣይነት ያለው ዘላቂ ሰላም ሲረጋገጥ ጤናማ የንግድ እንቅስቃሴ ይኖራል። ከክልል ክልል፣ ከአካባቢ አካባቢ ጤናማ የሆነ የንግድ እቃዎችና አገልግሎቶች የሚንቀሳቀሱትና የተረጋጋ ገበያ የሚኖረው በሰላም የበላይ ጠባቂነት ብቻ ነው። ታዲያ የሁሉም ነገር ቁንጮ የሆነውን ዘላቂ ሰላም ለመንከባከብ ከሁላችንም የሚጠበቅብንን ሁሉ ማድረግ የለብንም ትላላችሁ? አለብን እንደምትሉ በማመን መልካም ንባብ ብያችኋለሁ።


አንኳር ወደሆነው ጉዳይ ልመለስና የወጪ ንግድ የሀገራችን ኢኮኖሚ እድገት መሰላል እንደመሆኑ መጠን ምርቶቻችንን ወደ ውጪ በመላክ የወጪ ምንዛሪ ግኝታችንን ለማሳደግ አሁን የተጀመረው ሀገራዊ ንቅናቄ፣ አንድነት እና ሠላም ለሀገር ውስጥም ሆነ ለወጪ ንግዳችን ውጤታማ አፈፃጸም በጣም ወሳኝ ነው። ለዚህም ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በቅዱስ ቁርአን መማል ሳያስፈልግ ምስክር ይሆነኝ ዘንድ ሸገር ታይምስ መጽሄት /shegertimes magazine/ በድረ-ገጹ እ.ኢ.አ ሰኔ 06/2018 ሮይተርስን ጠቅሶ ያወጣውን እንዲህ አቅርቤዋለሁ።


“ሮይተርስ እንደዘገበው የሀገሪቱ የአንድ ቦንድ ዋጋ በ0 ነጥብ 583 ሳንቲም ዶላር ጭማሪ በማሳየት በ100.25 ዶላሮች ለመሸጥ በቅቷል። የሀገሪቱ ቦንድ ካለፈው ሳምንት ረቡእ ወዲህ ብቻ የ 3 ዶላር ጭማሪ ዋጋ አስመዝግቧል ተብሏል።


በናይሮቢ ስታንቢክ ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚስቱ ጂብራን ቁሬይሺ ሲናገሩ በሀገሪቱ እየታየ ባለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች የተነሳ አለም አቀፍ ኢንቨስተሮች የኢትዮጵያን ቦንድ ለመጫረት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ይገኛል ብለዋል። የሮይተርሱ ዘገባ አክሎም የኢትዮጵያ ቦንድ በ10 ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ ጭማሪ አስመዝግቧል ይላል። ይህ የሆነው ደግሞ የሀገሪቱ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከኤርትራው ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተገናኝተው የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር ከተስማሙ በኋላ ነው ይላል።


አብይ አህመድ ሀገራቸውን ብቻ ሳይሆን ምስራቅ አፍሪካን ጭምር እለውጣለሁ ብለው መነሳታቸውን የጠቀሰው ዘገባው የወሰዱት የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ለውጥ ደግሞ ከወዲሁ በአለም የቦንድ ገበያ ላይ የሀገሪቱን ተፈላጊነት ከፍ በማድረግ ውጤት እያመጣላቸው ነው ሲል አስቀምጧል።”


ሌላም አለኝ! በኢትዮጵያ መደበኛ ባልሆነው የውጭ ምንዛሬ ገበያ /ጥቁር ገበያ/ 1 የአሜሪካን ዶላር 40 የኢትዮጵያ ብር ገብቶ የነበረው ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ በፍጥነት ወርዶ 27 ብር ከ30 ሣንቲም ከነበረው የመደበኛ ገበያ ምንዛሪ ጋር ተስተካክሏል። ስለዚህ “እኔና አንተ/ቺ ስንደመር እኛ እንሆናለን። እኛ ማለት ደግሞ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን” የተባለው አካላችንን በምግብነት አዕምሯችንን በመልካምነት እየገነባው ይመስለኛል።


ሲጠቃለል፡- ይህንን እጃችን የገባውን እድል ተጠቅመን የሀገራችን የንግድ ስርዓታችን ከህገ-ወጥነት ተላቆ ሸማቹ ማህበረሰብ ለሚከፍለው ገንዘብ ተመጣጣኝ የሆነ ምርት የሚያገኝበት፣ ህጋዊ ነጋዴዎችን የሚያበረታታና ህገ-ወጥነትን የሚያቀጭጭ፣ የውጪ ባለሀብቶችን ሊጋብዝ የሚችል፣ ፍትሀዊ፣ ተደራሽ፣ አገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋ እና ለጤናማ ውድድር ምቹ እንዲሆን ከንግድ ዘርፉ አመራሮችና ሰራተኞች ጀምሮ መንግስት፣ በሸማችነትም ሆነ በነጋዴነት የሚሳተፍ የዚች ሀገር ተዋናይ ሁሉ አበክሮ መስራት ይኖርበታል።


የውጪ ምንዛሪ ግኝታችን ዋና ቋት የሆነው የወጪ ንግድ ካንቀላፋበት ነቅቶ ወደፊት እንዲራመድና የኢትዮጵያና የህዝቧ ኢኮኖሚ ከለጋነት ወደ ጎልማሳነት፣ ከችግኝነት ወደ ዛፍነት ተቀይሮ ፀሐይ ሲሆን ከፀሐይ፣ ዝናብ ሲሆን ከዝናብ ልንጠለልበትና ሊያድነን የሚችል እንዲሆን ለወጪ ንግድ የምናቀርባቸው ምርቶች ጥራት፣ ብዛትና ዋጋቸው በአለም ገበያ ብቁ ተወዳዳሪ በመሆን የውጪ ምንዛሪ ግኝትን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሻሽሉ መሆን አለባቸው። ይህንን ለማድረግ አምራቹ፣ ነጋዴው፣ ላኪው፣ የንግድ ሴክተሩ፣ የህዝብና የመንግስት ክንፍ አካላት ተናበውና ተቀናጅተው መስራት ይኖርባቸዋል።


ላኪዎቻችን የሀገራችንን ምርት ገዝቶ ከመላክ ይልቅ ፊታቸውን ወደ አምራች ኢንዱስትሪው መለስ አድርገው እሴት ጨምሮ መላክን መልመድ አለባቸው። የሀገር ውስጥ ምርቶችን ወደ ኢንዱስትሪ ግብዓትነት ቀይሮ ያለቀለት ምርት ማምረት ጠቀሜታው ወደ ውጪ በመላክ የሚገኘው ጠቀም ያለ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ከውጪ ሀገር የምናስመጣቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጪ ምንዛሪ እጥረትን ለማቃለል ፍቱን አማራጭም ነው። መንግስት የውጪና የሀገር ወስጥ ባለሃብቶች እንዲሁም አስመጪና ላኪ ነጋዴዎች ወደ ኢንዱስትሪው እንዲያመዝኑ ማበረታታት፣ አማራጮችንና ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ ኢትዮጵያን ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚያገናኙ መሠረተ-ልማቶችን መገንባት አለበት እያልኩ መልካም ንባብ እንዲሆንላችሁ ተመኘሁ።

"የድሮዋ በረራ (የአሁኗ አዲስ አበባ) የአምሃራ፤ ጉራጌ እና ጋፋት ክርስትና ተከታዮች ይኖሩባት የነበረች ከተማ ነች"

 

(ዶ/ር ሺመልስ ቦንሣ)

 

በመጀመሪያ

 

የዛሬ አንድ መቶ ሠላሳ አንድ አመት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1878 ንጉሰነገስት ምንሊክ ወደ አርሲ ሰራዊታቸውን ይዘው ይዘምታሉ። ባልተቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ደግሞ እንጦጦ የነበረውን የመንግስት መቀመጫ ወደ አሁኗ አዲስ አበባ ያዛውራሉ። ለጤና ተመራጭ የሆነው ፍልውሃ ፊንፊን ይልበት የነበረው ቦታ ለከተማው መቀየር አንዱ ግብዐት ቢሆንም የአድዋ ድል፣ የመንግስቱ መረጋጋት፣ የእንጦጦ ቀዝቃዛነትና ባካባቢው የነበረው የማገዶ እንጨት እጥረት የአገሪቷን ዋና ከተማ ወደ አዲስ አበባ ለመቀየር ተጨማሪ ምክንያቶች ሆነው አገልግለዋል። ንግስቲቷ የአገሪቷን መናገሻ አዲስ አበባ ብለው ሲሰይሟት ሌላ ፡ ማለትም ስድስተኛ፡ ምክንያት እንድንፈልግ እንድንመረምርም ያደርገናል፣ ታሪክ።


በስም ወይም ስያሜ ውስጥ ምን አለ? አዲስና አበባ አዲስ አበባ የሁለት ቃላት ጥምር ውጤት ነው፣ አዲስ እና አበባ። የቦታውን ልምላሜና ውበት ከሚወክለው አበባ ከሚለው ስያሜ ይልቅ እንደገና መጀመርን፣ መታደስን፣ መነሳትን የሚያሳየው አዲስ የሚለው ቃል የተለቀ ትርጉም የተሸከመ ስም ይመስላል። ባንድ በኩል ስያሜው የውጭ ወራሪ ጠላትን በማሸነፍ ከመጣው መረጋጋትና እርግጠኝነት በተጨማሪ ስለወደፊቱ የነበረውን ብሩህ ተስፋን፣ ወደፊት ማደግን መመንደግን፣ በአለም ማህበረሰብ ውስጥ ተገቢውን ቦታ አግኝቶ መከበርን ሲያመለክት በሌላ በኩል ደግሞ ወደሁዋላ ተመልሶ ማስታወስን፣ የጠፋን መመለስን፣ የፈረሰ መገንባትን፣ እንደገና መታደስን ያሳያል። እስቲ በሁለተኛው ትርጉም ላይ በማተኮር ወደሁዋላ ተመልሰን የከተማዋን ታሪክ መረጃዎቹ በሚሉት መሰረት እንመርምር።

ከተማና ታሪክ፣ ከበራራ እስከ አዲስ አበባ

 

የከተሜነት ታሪክ በኢትዮጵያ ውስጥ ጥንታዊነቱን ለመረዳት በትንሹም ቢሆን የአገሪቷን ታሪክ ማንበብ ከተቻለም የከተሜነት ስልጣኔዋን የሚመሰክሩ የከተሞች ፍርስራሾችን {ለምሳሌም የሃን፣ አዱሊስን፣ ቆሃይቶን}፣ ወይንም እስካሁን ያልጠፉትን፣ ህይወት ያለባቸውን እነአክሱምን፣ ሐረርን፣ ጎንደርን መመልከት ይበቃል። በስነህንጻ፣ በስነጽሁፍ፣ በስነመንግስትና በኪነጥበብ አክሱም የደረሰችበትን የስልጣኔ ከፍታ የተረዳው ማኒ የተባለው ፐርሻዊ ጸሓፊ አክሱማዊት ኢትዮጵያን ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአራተኛው ክፍለዘመን ከነበሩት አራት ታላላቅ ስልጣኔዎች አንዷ ናት ብሎ ምስክርነቱን ሰጥቷል። ሃረርና ጎንደርም የከተማነት ዝናቸው በብዙ ቦታ የናኘ መሆኑ ሰፊው ታሪካቸው ቆመው የሚታዩትም የስነሕንጻ ቅሪቶችም ማረጋገጫዎች ናቸው።


ይህንን ስንመለከት የአሁኗ አዲስ አበባ የዚህ ጥንታዊና ጥልቅ የከተማ ስልጣኔ ወራሽ እንጂ ጀማሪ እንዳይደለች እንረዳለን ማለት ነው። እስቲ ስለአዲስ አበባ ትንሽም ቢሆን ታሪክን ወደኋላ እንበል። የኢትዮጵያ የታሪክ ድርሳናትም፣ ሆነ የውጭ ሀገር ጸሐፍት የሚያረጋግጡት አሁን ሸዋ ተብሎ የሚጠራውና የአገሪቱ መናገሻ አዲስ አበባ የሚገኝበት አካባቢ ከዛሬ 700 አመት በፊት ማለትም የሰለሞናዊው መንግስት ከተመሰረተበት ከ13ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ የአገሪቱ ቁልፍ የፖለቲካ፣ የወታደራዊ፣ የኢኮኖሚና፣ የባህል ማዕከል ሆኖ ያገለግል እንደነበረ ነው። በጊዜው የነበረው ማዕከላዊው መንግስት ከቦታ ቦታ ተዘዋዋሪ ቢሆንም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከተሞችን የመሰረተ ሲሆን ትልቁና በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው ግን በራራ የተሰኘው ከተማ ነበር። ወረብ በራራ የምትገኝበት ቦታ ሲሆን በመሐከለኛው ዘመን ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት እና የነገስታቱ ቤተመንግስት የተሰራበት የነበረ በ16ኛው ክፍለዘመን ደግሞ ብዙ የውጭ ሀገሮችን የጎበኙት ፣ አባ ዳንኤል የተባሉ ኢትዮጵያዊ መነኩሴም ከኢየሩሳሌም ጋር ሁሉ ያመሳሰሉት ሀብታም አካባቢ ነበር። ሺሃብ አድ ዲን {በቅጽል ስሙ አረብ ፋቂህ} የተባለው የመናዊ የፍቱህ አል ሃበሻ {የሃበሻመወረር} መጽሃፍ ጸሐፊ የግራኝ አህመድን ጦር በማጀብ ወረብንና በራራን ያየ ሲሆን ወረብን የሀበሾች ገነት ብሎ ጽፎላታል።


የበራራ ከተማ በአሁኗ አዲስ አበባ አካባቢ በተለይም እንጦጦ ላይ የተመሠረተ ሲሆን የኢትዮጵያ መዲናነት ታሪኩ የሚጀምረው በአጼ ዳዊት ዘመነ መንግስት {እኤአ1380-1413} ሲሆን የሚያበቃውም በአህመድ ኢብን ኢብራሂም አል ጋአዚ {በቅጽል ስሙ ግራኝ አህመድ} ጦር በሚቃጠልበት የአጼ ልብነ ድንግል {እኤአ 1508-1540} ዘመን ነው። እኤአ በ1450 ለመጀመሪያ ጊዜ ከተማው ፍራ ማዉሮ የተባለ ቬኒሲያዊ {ጣልያናዊ} ባዘጋጀው የዘመኑ ፈር ቀዳጅ በሆነው የአለም ካርታ ላይም ለመስፈር በቅቷል።


ከማዉሮ ካርታ በተጨማሪም በዘመኑ የነበሩ ኢትዮጵያዉያንና የውጭ ሰዎች ስለበራራና አካባቢው ብዙ መረጃዎችን ትተውልን አልፈዋል። አንዳንዶቹን ለመጥቀስ ያህል አሌሳንድሮ ዞርዚ የተባለ የቬኒስ ጣልያናዊ {15ተኛዉና 16ተኛው ክፍለዘመን}፣ የመናዊው ሺሃብ አድ ዲን {16ተኛው ክፍለዘመን}፣ እና አዉሮፓ የነበሩ የኢትዮጵያ መነኮሳት ፡ አባ ዞርጊ፣ አባ ሩፋኤል፣ አባ ቶማስና አባ እንጦንዮስ {15ተኛዉና 16ተኛዉ ክፍለዘመን} ይገኙበታል። እኤአ በ1529 ሽምብራ ኩሬ {በደብረዘይት ወይም ቢሾፍቱና ሞጆ መሃል ያለ ቦታ} በተደረገ ጦርነት ንጉስ ልብነ ድንግል መሸነፉና ወደሰሜን ማፈግፈጉ ወረብንና የአገሪቱ መዲናን በራራን ለጥቃት ያጋለጠ ሲሆን እኤአ በ1530 ቦታዎቹ በግራኝ አህመድ ጦር ለመያዝ ከተማዋም ለመቃጠል በቅተዋል። እንደሺሃብ አድ ዲን ትረካ ከሆነ የግራኝ ሰራዊት በአስር ቀናት ውስጥ ከአዋሽ ወንዝ መነሻ {የአሁኗ ግንጪ} ተነስቶ በራራ በመድረስ አጭር ቆይታ አድርጓል፣ ከበራራም ሆኖ ግራኝ የተወሰኑ ወታደሮቹን የስድስት ቀን የእግር መንገድ ወደሚፈጀው ደብረ ሊባኖስ ልኮ እንዳቃጠለ ይዘረዝራል። የተቃጠለው የኢትዮጵያ መዲና የነበረው በራራ ከተማ የሚገኝበትን የወረብ ግዛት እንዲያስተዳድር ሙጃሂድ የተባለውን ታማኙን መሾሙንም ይጽፋል።


ከዚህ ጊዜ አንስቶ እስከ 19ተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ስለበራራ የሚዘግብ ምንም የጽሁፍ መረጃ አልተገኘም። በ19ተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ግን የጥንቱን በራራ ታሪክ የሚያስታዉሱ ግኝቶች መታየት ይጀምራሉ። እኤአ በ1881 በንጉስ ምኒልክ የሚመራው የሸዋ፣ እኤአ ከ1889 በሁዋላም የኢትዮጵያ መንግስት መዲናውን እንጦጦ ላይ ያደርጋል። እንደዘመኑ ትርክት ከሆነ {ድርሳነ ራጉኤል ላይ እንደተጻፈው} የንጉስ ምንሊክ እንጦጦ ላይ መከተም ከስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ በተጨማሪ ታሪካዊ ትርጉም ነበረዉ፣ እሱም ታሪክ የዘከረዉን የጥንቱን የአጼ ዳዊት ከተማን እንደገና መገንባት፣ ወደአገሪቱ መዲናነትም መመለስ ነበር። ንግርቱም ታሪካዊ መሰረት እንደነበረው የሚያመላክቱ መረጃዎች በእንጦጦ {የጥንቱ በራራ ክፍል} የተገኙ ሲሆን ይህንንም በጊዜው ሀገሪቷን የጎበኙ የውጭ ሀገር ሰዎች {ዲፕሎማቶች፣ ተጓዦችና ወታደራዊ ባለሙያዎች} ዘግበዉታል። ቻርለስ ማይክል፣ ሲልቬይን ቪኘራስ፣ ሻለቃ ፓወል ኮተን፣ አልበርት ግሌይቸን፣ እና ቸዛሬ ኔራዚኒ፣ ጥቂቶቹ ሲሆኑ ሁሉም በቦታው የነበረዉን ጥንታዊ የመከላከያ ቅጽሩን ተመልክተው ስለጥንካሬዉና ግዙፍነቱ አድናቆታቸውን በጽሁፍ አፍረዋል። እንጦጦ ላይ የፔንታገን ቅርጽ {አምስት ጫፎች ያሉት} ያለው በዙርያውም 12 መመልከቻ ማማዎች የያዘ እንደመከላከ የሚያገለግል ቤተመንግስትና ግንብ የተገኘ ሲሆን ርዝመቱም 520 ሜትር ከፍታውም እስከ 5 ሜትር እንደሚደርስ ታውቋል። የስነህንጻና አርኪዎሎጂ ባለሙያዎች {ለምሳሌም ዴቪድ ፊሊፕሰን፣ ማይክል ዎከርና ማርክ ቪጋኖ እንደተነተኑት ግንቡ እኤአ ከ1550 በፊት የነበረዉን የፖርቱጋልና ስፔን የመከላከያ ግንብ አሰራር ዘዴ የተከተል ሲመስል ቢያንስ የ400 አመት ወይም በላይ ዕድሜ ያለዉና በ16ተኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ አጋማሽ ምናልባትም በአጼ ልብነ ድንግል የተገነባ እንደሚሆን ነው።

 

የአዲስ አበባ ምንነት

 

እንግዲህ በጥንቷ በራራና በአሁኗ አዲስ አበባ መሐከል ታሪካዊ ግኑኝነት እንዳለ ካየን አሁን ደግሞ የሁለቱን ከተሞች በተለይም የአዲስ አበባን መልክ ወይንም ዋና መገለጫ ባህርይ ምን እንደሚመስል እንመልከት። የኢትዮጵያ ከተሞችና መዲናዎች {ለምሳሌም አክሱም፣ ጎንደር} ልክ እንደአገሪቷ ህብረብሄራዊ ገጽታ የነበራቸው ሲሆን በውስጣቸው የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ፣ የተለያየ እምነትና ባህል ተከታይ የሆኑና፣ በተለያየ የስራ ዘርፍ የተሰማሩ ኢትዮጵያዉያን እንዲሁም የዉጭ ሀገር ተወላጆች የሚኖሩባቸው ቦታዎች ነበሩ። ጥንታዊቷ አክሱም በሶስት ቋንቋ {ግዕዝ፣ግሪክ፣ ሳባ} የምትጽፍ፣ ከሶስት ቋንቋ በላይ የምትናገር፣ ከኢትዮጵያዉያን በተጨማሪ ግብጻዉያን፣ የመረዌ {ሱዳን} ሰዎች፣ የመናዉያን፣ የምስራቅ ሜድትራንያን {ፊንቄያዉያን፣ ግሪኮች፣ የጥንት ሶሪያዉያን} ተወላጆች እንዲሁም ህንዶችና ቻይናዉያን የኖሩባት ወይም ደግሞ የሰሩባት ታላቅ ከተማ ነበረች። ጎንደርም ብትሆን የክርስትና፣ የእስልምናና የአይሁድ እምነት ተከታዮች አብረው ኖረው {ተለያይተው የሰፈሩ ቢሆንም}፣ በስራና በህይወት ተስተጋብረው መልኳንና ታሪኳን ውብና ዥንጉርጉር አድርገው የቀረጿት ከተማ እንደነበረች ታሪኳ ይመሰክራል። ሀረርም ከአራቱ የእስልምና ቅዱሳን ቦታዎች አንዷ ስትሆን በብዝሀነቷ እና በእምነት ማዕከልነቷ የምትታወቅ፣ በመቻቻል ታሪኳ የተመሰገነች በዚህም እንደ ታዋቂዉ የፈረንሳይ ገጣሚ አርተር ራምቦ እና እንግሊዛዊዉ ሪቻርድ በርተን ያሉ የውጭ ሰዎችን ለመማረክ የቻለች ምስራቃዊ እንቁ ነበረች፣ ነች።


የበራራም ታሪክ ቢሆን በብዝሃነት ያሸበረቀ እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ። በከተማዉም ሆነ በዙሪያው ባሉ እንደ ወረብ ባሉ ግዛቶች ይኖር የነበረው ማህበረሰብ በብዛት ከአምሃራ፣ ከጉራጌ እና ከጋፋት {ሶስቱም ተቀራራቢ ቋንቋዎችን ይናገራሉ } የተዉጣጣ እና የክርስትና እምነት ተከታይ የነበረ ሲሆን በተጨማሪም የሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎችና እምነት ተከታዮች ይገኙ እንደነበረ ይታሰባል። ለዚህም ምክንያቱ ከተማው ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም ከምስራቅ ኢትዮጵያ በዛም በኩል አድርጎ ከአረቡና የህንዱ ስልጣኔ ጋር በንግድ እና በባህል የተገናኘ ስለነበረ ነው። በበራራ የታሪክና የስነህንጻ አሻራ ላይ የተገነቡት ሁለቱ ወራሽ ከተሞችም {እንጦጦና አዲስ አበባ} የነዋሪዎቻቸው ያሰፋፈር ታሪክ ከዚህ በተለየ መንገድ የተቃኘ አልነበረም፣ ይልቁንም የበፊቱን ታሪክ መሰረት አድርጎ ፣ ብዝሃነትን አቅፎና ደግፎ፣ ኢትዮጵያዊነትን ሆኖና ተላብሶ የተፈጠረ ቅኝት፣ ያደገ ማንነት ነው ያላቸው፣ በፊትም አሁንም።


አዲስ አበባ ስትመሰረት የነበራትን ጥልፍልፍና ድርብርብ ታሪክ በ19ኛውና በ20ኛ ክፍለዘመን መባቻ ላይ በሃገርኛና በጎብኝዎች የተጻፉ ስራዎች ዘግበውታል። ነገስታቱ በተለይም አጼ ሀይለ ስላሴ ከተማዋ ዘመናዊ ብቻ ሳይሆን ብሄራዊ ሆና እንድትፈጠር ወይንም እንድታድግ ያቀዱና የሰሩ ስለነበር አዲስ አበባ ከተማም፣ የሀገርም ምልክት ሆና በእሷ ውስጥ ኢትዮጵያን በኢትዮጵያ ውስጥም እሷን እንዲታይ፣ እኛም እንድናይ ሆና ነበር የተቀረጸችው። በእርግጥ በአገሪቱ መሪዎች እና በከተማ ቀራጮች አእምሮ ውስጥ የታለመችው አዲስ አበባ እንደታሰበችው ሁሉ መሬት ላይ ባትሰራም {ለምሳሌ የመሰረታዊ አገልግሎቶች እጥረት፣ የስራ አጥነት፣ የሀብት ልዩነት ቢስፋፋባትም } ከተማዋ የኢትዮጵያውያን ሆና ኢትዮጵያን ከነዥንጉርጉር ውበቷና ከነውስብስብ ችግሯ መስላና፣ ተመስላ እስካሁን አለች፣ ትኖራለች። አዲስ አበባ፣ አዱገነት ሸገራችን ከብዙ የአፍሪካዉያን ከተሞች በተለየ ድሃና ሀብታም ተሰባጥረው የሚኖሩባት፣ ነዋሪዎቿን ከነብዝሃነታቸው ሳትለይ አቅፋ የኖረች፣ ያኖረች፣ የምታኖር የኢትዮጵያ የልብ ትርታ፣ ነርቭ ማዕከል የሆነች ኦ አዲስ አበባ “ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ“ የምንልላት ከተማችን፣ ችግሯም ችግራችን፣ ፍቅራችን እንደገናም ተስፋችን፣ የሆነች ማረፊያችን ሆናለች።

 

የአዲስ አበባ ማንነት

 

ይህችን ስብጥር የሆነች ከተማ፣ ንብርብር ታሪክ የተሸከመች ምድር፣ ከመሪዎቿ በላይ የብዙሃን ነዋሪዎቿ ድምር ውጤት፣ የእጅ ስራ ነጸብራቅ ሆና የኖረች ግማደ-ኢትዮጵያ የማን ናት? በብዝሃነት ጥልፍልፍ ተጸንሳ ለተወለደች፣ አድጋም ለጎለመሰች አዲስ አበባ ምንነቷና የማንነቷ ምስጢር በአንድነት ተጋምዶ፣ በልዩነት ውበት አሸብርቆ ደምቆ የተፈጠረ የሃገርነት ቋጠሮ ነው። አዲስ አበባ ልክ እንደኢትዮጵያ የነዋሪዎቿ ስብስብ ውጤት ብቻ ሳትሆን፣ ከድምርነትም በላይ እጅግ የጠበቀ፣ የጠለቀ ጥልፍ ስብጥር ናት። ለመሆኑ እዲስ አበባን ለመፍጠር ያልተጋ ኢትዮጵያዊ እጅ የት አለ ኦሮሞው ከአማራው፣ ጉራጌ ከትግሬው፣ ዶርዜ ከሀረሪው፣ ሶማሌ ከወላይታው፣ ምስራቁ ከደቡብ፣ ሰሜኑ ከምዕራብ፣ ወንዱ ሴቱ፣ ልጅ አዋቂዉ፣ አማኙ የማያምነው፣ ነጋዴው ከምሁሩ፣ ሀገሬዉ ከሌላው ተዋዶ፣ ተዋልዶ፣ ተናግዶ፣ ተቀናጅቶ የፈጠራት፣ ከተማ ከሚባል ነገር በላይ የሆነች ምስጢር አይደለችምን? ከቦታነት በላይ የዘለቀች ሁሉም እምነቷን ካመኑ፣ ሕይወቷን ኖረው ትርጉሟን ካወቁ አባል የምታደርግ፣ እጆቿን ዘርግታ የምትቀበል፣ የራሷ የምታደርግ ትልቅ ሃሳብ {Addis Ababa as an Idea} አልሆነችም? አዲስ አበባ አግላይ ከሆነ የኔነት፣ የኔ ናት ከሚል ህሳቤ ወጥታ፣ ርቃ አልፋ ሄዳ፣ የኛነት፣ የእኛ ናት ወደሚል ሰብሳቢ ሃሳብነት ያደገች ከተማ ሆናለች።


ይህ ማለት ግን ሁሉም እኩል ነበር? እኩል ታይቶስ ነበር? ብዙው አዲስ አበቤ አልተገለለም? እስቲ በምሳሌ እናስረዳ። በአጼ ሃይለስላሴ ዘመን በ1960ዎቹ አመታት በቁጥር 1768 የሆኑ ግለሰቦች 58% የሚሆነውን የከተማውን ቦታ ተቆጣጥረው ነበር። 24000 የሚሆኑት የከተማው ነዋሪዎች 7 ነጥብ 4 በመቶ {በግለሰብ 150 ካሬ ሜትር ማለት ነው} የከተማውን ቦታ ሲይዙ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የከተማው ህዝብ መሬትም ሆነ መኖርያም አልነበረውም። በንጉሳዊው ዘመን፣ ከስርዓቱም መውደቅ በሁዋላ ባሉት መንግስታት በተለይ አሁን ጥቂቶችን በጠቀመ ልማትና ዘመናዊነት ስም ከተሜው ከኖረበት ቀዬው እየተነሳ ይፈናቀላል፣ ከኑሮውም ከማህበራዊ ህይወቱም ይቆራረጣል። በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ዙሪያ የሚኖሩት አርሶአደሮችም {ኦሮሞም አማራም ትግሬም ሲዳማም እና ሌሎች ኢትዮያውያን} በአነስተኛ ካሳ መሬታቸውን ይቀማሉ፣ ሰርቶ የመኖር መብታቸውን ይነጠቃሉ። እንግዲህ የአዲስ አበባንና የሌሎች ከተሞቻችንን ታሪክ ስንተርክ እነኝህንና ሌሎች ታሪካዊ በደሎችን፣ ዘመናዊ ነጠቃዎችን የተሸከመ ከተሜነትና ዘመናዊነት ይዘን መሆኑን ሳንዘነጋ ነው።


አዲስ አበባና የዘመኑ ትርክት በአሁኑ ሰዓት፣ እንደ በፊቱ ሁሉ፣ የአገሪቱ መዲና አዲስ አበባ ቅራኔዎች የሚፈጠሩባት፣ እንዲሁም የሚንጸባረቁባት ቦታ ሆናለች። ውጥረቶቹ በመሠረታዊነት መደባዊ ሆነው በብሄር ማንነት መነጽር ይተነተናሉ፣ በዛም ላይ ተንተርሶ ህዝብን ለትግል ማደራጃ ሆነው ያገለግላሉ። በአሁኑ ጊዜ ሁለት ትርክቶች የከተማውንም ሆነ የአገሪቱን ትኩረት ስበው ይገኛሉ። ሁለቱም ታሪክን በተለያየ መንገድ ይመለከታሉ የራሳቸውንም በደሎች ያጣቅሳሉ። አንደኛው ህብርብሄራዊ ሆኖ ረጅም የታሪክ ምልከታ ይዞ አዲስ አበባን፣ ከፍ ሲልም ኢትዮጵያን በህብረብሄራዊ መነጽር እያየ በከተማውም ሆነ በአገሪቱ ያሉ የተንከባለሉ ብሶቶችን በመደብ መነጽር ይተነትናል። ሁለተኛው ብሄርን ማዕከል አድርጎ በቅርቡ የታሪክ እይታ ተመስርቶ ከተማውን፣ በከተማዉና በአገሪቱ ያሉ የተከማቹ በደሎችን በብሄር መነጽር ይሞግታል፣ አማራጮችንም ይጠቁማል።


ሁለቱም እይታዎች እነሱም ላይ የቆሙ ትንተናዎች የየራሳቸው እዉነቶች አሏቸዉ። የከተማዉን ብሎም የአገሪቷን ታሪክ እና ነባራዊ ሁኔታ በራሳቸው መንገድ ይተርካሉ፣ ይሞግታሉ። ነገር ግን አዲስ አበባን በሁለቱ መነጽሮች ብቻ መመልከት የከተማዋን በዛውም የአገሪቷን ንብርብር እና ቁልፍልፍ ታሪክና እውነት አበጥሮ፣ አብጠርጥሮ ለመረዳት የሚያስችል መንገድ አይሆንም። የጎደለ እይታን ይፈጥራልና። በተለይ ደግሞ መጤ እና ነባር የሚለው ትርክት በአንድ አገር ዜጎች መሐከል ደረጃ በማውጣት አንደኛና ሁለተኛ ዜግነትን በመፍጠር የማግለል አንዳንዴም የመንቀል ፖለቲካን ያመጣል። በሰዎች ህይወትም ላይ የሚወስን ነውና አደገኛም ነው። በቅርቡም በመንግስት የቀረበው “የልዩ ጥቅም መብት“ ከፍ ሲልም በአንዳንድ የዘውጌ ልሂቃን የተነሳው “የባለቤትነት“ ጥያቄ በከተማውም ሆነ በአገሪቱ ያለውን ውጥረት ያሳያል። የአዲስ አበባ የልዩ መብትና የባለቤትነት ፖለቲካ በኢትዮጵያ እየጦዘ፣ እንዲጦዝ እየተደረገ ያለው የዜግነት፣ የአገርነትና፣ የአገር ባለቤትነት ትልቅ ጥያቄ መገለጫ ነው። ታዲያ ምን ይሻላል።


የአዲስ አበባ ምሳሌነት አዲስ አበባ በብዙ መንገድ የኢትዮጵያ ተምሳሌት መሆኗ በየቀኑ የሚታይ እውነታ ነው ከተማዋን ማወቅ ማለት አገሪቷን መረዳት ማለት ነው። የአዲስ አበባን ችግሮች ተረድተን መፍታት ከጀመርን የኢትዮጵያን ጥያቄዎች የመሞገት፣ ፈተናዎቿንም የመጋፈጥ ታላቅ ስራ ጀመርን ማለት ይሆናል። ከተማዋን የምንመለከትበት መነጽር ፣ ከፍታዎቿን፣ ዝቅታዎቿንና ተስፋዎቿን የምንተነትንበት መንገድ ለአገሪቷም ይሰራልና ለጊዜው እንደዚህ ብንጀምርስ፣ አንደኛ፣ እይታዎቻችን በብሄር ወይንም በመደብ ምልከታ ከማጥበብ፣ እኛም ከመጥበብ ሰፋ አድርገን፣ ሁለቱንም ተቀብለን ሌሎችም አማራጮች እንዳሉ ግን አጥብቀን ተረድተን፣ እንሱንም ፈልገን፣ ሁሉን አቀፍ አገራዊ እይታ ብንፈጥርስ (avoiding the danger of a single story)


ሁለተኛ፣ ከተማችን እንዲሁም አገራችን የብዙዎች እኛነቶች ጥምር ውጤት መሆኗን አምነን ያንዳችን ችግር ወይም ብሶት እንደራሳችን ወስደን እይታቸውንም ዋጋ ሰጥተን ያጋመዱንን ገመዶች ብናጠብቅስ (having radical empathy for fellow countrymen) ሶስተኛ፣ በእኔነት እና በልዩነት ብቻ የገነገነውን ፖለቲካና ትርክታችንን በእኛነት ላይ፣ ድልድይ በመስራት ፣ ከእኛ ባሻገር ካሉ የኛዎች ጋር ባለን አንድነት ላይ አትኩረን። ብንሰራስ (Bridge building, crossing borders)

 

በአዲስ አበባ ከተማ የእግረኛ መንገዶችን ለፓርኪንግ አገልግሎት ማዋል በእጅጉ እየተለመደ መጥቷል። ይህ ችግር ከእንጭጩ ሊቀጭ ባለመቻሉ ሁሉም የከተማዋ የእግረኛ መንገዶች በሚያስብል ሁኔታ የመኪና ፓርኪንግ ወደመሆን እየተሸጋገሩ ነው። ይህም በመሆኑ እግረኞች እነዚህን መንገዶች በመተው በምትኩ የተሽከርካሪ መንገዶችን ለመጠቀም ተገደዋል።

 

ይህም በዋነኝነት ነዋሪዎችን ለተሽከርካሪ አደጋ እያጋለጠ ከመሆኑም ባሻገር የእግረኛ መንገዶች እድሜም እንዲያጥር በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህም በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ይሄንን ህገ ወጥ ተግባር በየቦታው ተከታትሎ ህጉ የሚፈቅደውን እርምጃ እንዲወስድ ማሳሰብ እፈልጋለሁ።

 

መቅድስ ወርቁ ከሃያ ሁለት

 

ቁጥሮች

Wednesday, 25 July 2018 13:39

 

በኢትዮጵያ

1,509,491                     የመንግሥት ሠራተኞች ብዛት፤

429,836 (30 በመቶ)        በዲግሪ የተመረቁ ሠራተኞች፤

70 በመቶ                        ዲፕሎማና ከዚያ በታች የትምህርት ደረጃ ያላቸው፤

ምንጭ፡- ፎረምፎር ሶሻል ስተዲ ጥናት (ጥቅምት 2010 .)

Page 1 of 229

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 888 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us