መልዕክቶች

መልዕክቶች (330)

 

በአዲስ አበባ ከተማ የእግረኛ መንገዶችን ለፓርኪንግ አገልግሎት ማዋል በእጅጉ እየተለመደ መጥቷል። ይህ ችግር ከእንጭጩ ሊቀጭ ባለመቻሉ ሁሉም የከተማዋ የእግረኛ መንገዶች በሚያስብል ሁኔታ የመኪና ፓርኪንግ ወደመሆን እየተሸጋገሩ ነው። ይህም በመሆኑ እግረኞች እነዚህን መንገዶች በመተው በምትኩ የተሽከርካሪ መንገዶችን ለመጠቀም ተገደዋል።

 

ይህም በዋነኝነት ነዋሪዎችን ለተሽከርካሪ አደጋ እያጋለጠ ከመሆኑም ባሻገር የእግረኛ መንገዶች እድሜም እንዲያጥር በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህም በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ይሄንን ህገ ወጥ ተግባር በየቦታው ተከታትሎ ህጉ የሚፈቅደውን እርምጃ እንዲወስድ ማሳሰብ እፈልጋለሁ።

 

መቅድስ ወርቁ ከሃያ ሁለት

 

የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ በከተማዋ በኮብል ስቶን መንገድ ንጣፍ ምክንያት ለተፈጠረው እንግልት ህዝቡን ይቅርታ ጠይቋል። ቢሮው ያደረገው ነገር የሚያስመሰግነው ብቻም ሳይሆን ሌሎች ተቋማትም ቢሮውን አርአያ እንዲያደርጉ የሚያበረታታ ነው። በአሁኑ ወቅት ጥቂት የማይባሉ ተቋማት በየአቅጣጫው የተጣለባቸውን ኃላፊነት መወጣት እያቃታቸው ኅብረተሰቡን እያማረሩ ነው የሚገኙት። እነዚህ ተቋማት ጥፋታቸውን አምነው ኅብረተሰቡን ይቅርታ ሊጠይቁ ቀርቶ ጥፋታቸው ሲነገራቸው እንኳን አንዱ ወደሌላው ከማላከክ ባለፈ ጥፋታቸውን ለመቀበል ሲዘጋጁ አይታዩም። ቢሮው ግን የህዝቡን እንግልት ተመልክቶ ይቅርታ ለመጠየቅ መነሳቱ የሚያስመሰግነው ነው። ታዲያ ይቅርታ መጠየቅ ብቻም ሳይሆን፤ ከስህተቱ ተምሮ ለወደፊት ይህን ስህተት ላለመድገም መትጋት ይጠበቅበታል። ሌሎች መሰል ችግሮችን በኅብረተሰቡ ላይ እያደረሱ ያሉ ቢሮዎችም ከቢሮው ተሞክሮ በመውሰድ ስህተት ሲፈፀም ወደ ውስጣቸው በመመልከት ኅብረተሰቡን ላጠፉት ጥፋት ይቅርታ መጠየቅ ይልመዱ።

 

በስልክ የተሰጠ አስተያየት - ከመገናኛ¾

 

በየዓመቱ ከሰኔ ወር ጀምሮ በርካታ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከተለያዩ ትምህርት ተቋማት ይመረቃሉ። ዘንድሮም በርካታ ተማሪዎች እየተመረቁ ናቸው፤ ገናም ይመረቃሉ። የተመራቂዎችን ቁጥር ማብዛቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ጥራት ያለው ተመራቂን ማፍራቱ ደግሞ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የሚጠበቅ ቀዳሚው ተግባር ነው። ተቋማቱ በዚህ ጉዳይ በየጊዜው የሚወቀሱ ከመሆኑ አንጻር ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገው ብዙ የተማረ የሰው ሃይልን አስተምረው ማስመረቃቸውን እርግጠኛ መሆን አለባቸው። በተለይ የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየዓመቱ በሚቀርብ የኦዲት ሪፖርት የሀገር እና የህዝብ ሀብትን ያለአግባብ በማባከን ስማቸው ከሚነሳ ተቋማት ቀዳሚዎቹ ናቸው። ይሄንን ችግር መቅረፍ የሚቻለው ብቁ እና ለህዝብ ተቆርቋሪ የሆነ የተማረ ዜጋን በማፍራት መሆኑን አውቀው የበለጠ ሊተጉ ይገባል። ዛሬ ላይ አግበስብሶ ቢያስመርቁት ነገ ሌላ ችግር ፈጣሪ ሆኖ መገኘቱ ስለማይቀር ይሄን ያህል ቁጥር ያለው ተማሪ አስመረቅን ለማለት ከመሮጥ ይልቅ ጥራቱ ላይ ማተኮሩ የተሻለ ይሆናል።

                             

በስልክ የተሰጠ አስተያየት

ችግር ሲገጥም መረዳዳት ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ኢትዮጵያዊ ባህላችን ነው። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይሄን ባህላችንን የሚሸረሽሩ እና እርስ በርሳችን እንዳንተማመን የሚያደርጉ ክስተቶች እየተስተዋሉ ነው። በተለይ የጤና እክል የገጠማቸው በርካታ ሰዎች ህክምና ለማግኘት ከፍተኛ ገንዘብ ሲጠየቁ እርዳታ መጠየቅ እና ህዝቡም የመተባበር ሁኔታው ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። ያም ሆኖ እውን ለህክምና ተጠየቅን የሚባለው ገንዘብ ይሄንያህል ይደርሳል ወይ የሚለው ብዙዎቻችንን ጥያቄ ያጭሩብን ነበር። አሁን እዚህም እዚያም የምንሰማቸው ነገሮች ደግሞ በተቸገሩ ሰዎች ስም ከህዝበ የሚሰበሰብ ገንዘብ የአንዳንድ ግለሰቦች መጠቀሚያ እየሆነ መምጣቱን ነው። ነገሩ በጣም አሻሚና ለማመንም ላለማመንም የሚከብድ ነው። በዚህ መካከል እውነተኛ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች እገዛውን ሳያገኙ ህይወታቸውን መስዋዕት እስከማድረግ የሚደርሱበት አጋጣሚ ይፈጠራል። እየሰማነው ያለነው ነገር ወደ መጨካከን እና እርስ በርስ እምነት ወደማጣት እየመራን ነው። የሚሰሩት አሻጥሮችም ከሁሉም በላይ በሰው ህይወት ላይ የሚሰሩ አሻጥሮች መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። እንዲህ አይነቱን እኩይ ስራ የምትሰሩ ሰዎች እባካችሁ መጨካከንን አትንዙብን።

                              አስቴር ደገፉ - ከሳሪስ 

ለዓመታት የዘለቀው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዛሬም ድረስ አልተፈታም። በዚህ ችግር ሳቢያ የሚመጣው ችግርም የእያንዳንዳችንን ቤት በማንኳኳት ላይ ይገኛል። በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የመድሐኒት እጥረት እንዳለ እየተነገረ ነው። ንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረት እየተከሰተ ያለው ከውሃ ማጣሪያ እጥረት ጋር በተያያዘ መሆኑን አንዳንድ መረጃዎች ይፋ እያደረጉ ነው። እነዚህ መሠረታዊ ችግሮች ያጋጠሙትም ሀገሪቱ ባለባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ነው። ነገር ግን ህዝቡ ይሄንን መረጃ በአግባቡ እንዲያገኝ እንኳን ማድረግ አልተቻለም። የችግሩ መንስኤ ራሳቸው መሆናቸው የገባቸው አካላትም የተለያዩ ሰበቦችን ከመደርደር ውጪ ትክክለኛውን ምክንያት እየነገሩን አይደለም። በመካከል ግን ማህበረሰቡ በጣም እየተቸገረ ነው። ለውጭ ምንዛሪና እጥረቱ ዋናው ምክንያት በወጪ እና በገቢ ንግዱ መካከል ያለው ክፍተት ከፍተኛ መሆኑ ነው ተብሏል። ይሄ ክፍተት ደግሞ በዘንድሮው ዓመትም እንደቀጠለ ነው። አሁንም አንድ መፍትሄ ካልተፈለገለት የባሰ ችግር እና ቀውስ ውስጥ መግባታችን አይቀርም።

 

                        አቶ ታደሰ ሲሳይ - ከሳሪስ

ጠቅላይ ሚኒስትራችን ካከናወኗቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል በተለያዩ ሀገራት ተሰደው የነበሩ ዜጐችን ወደ ሃገራቸው መመለስ አንዱ ነው። ለዚህ ድርጊታቸው ከልብ የመነጨ ምስጋና ይገባቸዋል። ይሄንን ጉዳይ መነካካታቸው ካልቀረ ግን ችግሩ ስደተኞችን በመለስ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን ከመሠረቱ ብዙ ሥራዎችን መስራት እንደሚያስፈልገው አውቀው ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በአንድ በኩል ይሄን ያህል ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ተመለሱ እየተባለ ባለበት ቅፅበት በሌላ አቅጣጫ ደግሞ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጐች እየተሰደዱ እና ህይወታቸውን እየገበሩ መሆኑ እሙን ነው። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን ችግር ከምንጩ ማድረቅ የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ሳያስፈልጋቸው አይቀርም። ካልሆነ ግን በአንድ በኩል ቀዳዳ ሲደፈን በሌላ በኩል ቀዳዳው እያፈሰሰ ከሆነ የተፈለገውን ያህል ውጤት አያመጣም።

 

ወ/ሮ ሀሊማ ሁሴን - ከቤሌ¾

በቅድሚያ ቤት የህልውና ጉዳይ በሆነበት በአሁኑ ወቅት የኮንዶሚኒየም ቤት ለደረሳችሁ ሰዎች እንኳን ደስ ያላችሁ። ነገር ግን ለመንግስት ማንሳት የምፈልጋቸው ጥያቄዎች አለኝ። በመጀመሪያ ደረጃ ከዚህ ቀደም በወጡት እጣዎች በ1997 ዓ.ም ለተመዘገቡ ባለ 3 መኝታ ቤት ፈላጊዎች ሙሉ ለሙሉ ቤት እንደተሰጣቸው ተነግሮናል። ሰሞኑን በወጣ እጣም ድጋሚ ይኸው መረጃ ሲተላለፍ ነበር። ነገሩ እንዴት እንዲህ ሊሆን እንደቻለ አልገባኝም። ይሄ ሁሉ ቤት ፈላጊ አሰፍስፎ እየተጠባበቀ ባለበት ሁኔታ እንዲህ አይነት አወዛጋቢ መረጃን መስጠቱ ከምን የመነጨ ነው? ሌላው ማንሳት የምፈልገው ነገር ደግሞ ወንድ ቤት ፈላጊዎች መቼ ነው የቤት ባለቤት የሚሆኑት? የሚለውን ነው። ለሴቶች ቅድሚያ መስጠቱ ላይ ተቃውሞ ባይኖረኝም ወንዶች ግን በተወሰነ ደረጃ የተጨቆኑ እየመሰለኝ ነው።

 

ይሄን የፈጠረው ደግሞ ለዕጣ የሚቀርቡት ቤቶች ቁጥራቸው አነስተኛ መሆኑን ነው። ከዚህችው ቁጥር ላይ የተወሰኑት ለሴቶች፣ የተወሰኑት ደግሞ ለመንግስት ሰራተኞች እየተባለ ሲቀናነስለት ወንዶችን ተስፋ የሚያስቆርጥ ይመስለኛል። እነዚህን አስተሳሰቦች ባልቃወምም የወንዶችንም ፍላጎት ለማሟላት እና ተጠቃሚ ለማድረግ ለዕጣ የሚቀርቡ ቤቶችን ብዛት መጨመር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ካልሆነ ግን ወንዶችና ቤት ሳይገናኙ መቅረታቸው ይመስለኛል።

                              በስልክ ከሜክሲኮ አካባቢ የተሰጠ አስተያየት

 

በሀገራችን የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ሰሞኑን ጭማሪ መደረጉ ተነግሯል፤ እኛም በተግባር እያየነው ነው። መሰል የታሪፍ ማስተካከያዎች ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ ሲደረጉ ስለነበረ አዲስ አይደለም። የአሁኑ የዋጋ ጭማሪም ከነዳጅ ዋጋ ጋር የማይገናኝ እና በትራንስፖርት ባለንብረቶች ጥያቄ መሠረት የተደረገ እንደሆነ እየሰማን ነው። ጭማሪው ከማንም ይምጣ ከማንም ተገልጋዩ ከመቀበል ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም። ነገር ግን በዚሁ የዋጋ ጭማሪ ላይ ሁለት መሠረታዊ ስህተቶችን አስተውያለሁ። የመጀመሪያው ሁሉም ነገር ዋጋው በናረበትና ኑሮ በተወደደበት ወቅት መሆኑ ተገልጋዮችን የባሰ አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ ነው የሆነው። በተጨማሪ ደግሞ የዋጋ ጭማሪው ከዚሁ በፊት ከተለመደው ጭማሪ በተለየ መልኩ በአንድ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ የተደረገ ጭማሪ ነው። እነዚህ ሁለት ነገሮች ተደማምረው የተጠቃሚውን ችግር ማባባሰ ይመስለኛል። ጭማሪው ተግባራዊ ከመደረጉ አስቀድሞ የማህበረሰቡን ችግር ያገናዘበ መሆን አለመሆኑን ጥናት ማድረግ ያስፈልግ ነበር። ይህን ጭማሪ ማድረግ ያስፈለገው ጥናት ተደርጎ እንደሆነም ተገልጿል። ነገር ግን ጥናቱ ከተደረገ ቆየት ያለ ሆኖ ሳለ እንዲህ ባለው ፈታኝ ጊዜ ላይ ተግባራዊ መደረጉ ህዝቡን ለባሰ ችግር ያጋለጠ ነው።

                              አቶ ሲሳይ አማረ- ከ6 ኪሎ   

 

የግል ትምህርት ቤት ክፍያ ጉዳይ ልክ እንደወትሮው ሁሉ ዘንድሮም የሁላችንም አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል። ገና የተጀመረው የትምህርት ዘመን ሳይጠናቀቅ ለመጪው የትምህርት ዘመን የሚከፈለውን ክፍያ በተመለከተ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ማለት በሚያስችል መልኩ የተማሪ ክፍያን መገመት ከሚቻለው በላይ ከፍ አድርገውታል። አንዳንዶች እንደሚሉት ደግሞ በአንድ ተማሪ ክፍያ ላይ የተደረገው ትንሹ ጭማሪ አንድ ሺህ ብር ነው። ይሄ ማለት ሁለት ወይም ሦስት ልጆች ያሉት ሰው ከወርሃዊ ደመወዙ በላይ የሆነ ጭማሪ ሊደረግበት ይችላል። ይሄን ማድረግ የማይችሉ ተማሪዎች ወላጆችም ዝቅተኛ ክፍያ ወዳለበት ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን ለማዛወር እየተገደዱ ናቸው። ይሄ ጉዳይ ባለፈው ዓመትም ሆነ ከዚያ በፊት በነበሩት የትምህርት ዘመናት የበርካታ ወላጆች ፈተና እንደነበረ ግልፅ ነው። ጉዳዩን መንግስት ማስተካከል እና ገደብ ማበጀት ካልቻለ በየዓመቱ ጉድ ጉድ ከማለት ውጪ ምንም አይነት መፍትሄ ማምጣት አይቻልም። ትምህርት ቤቶቹን ቀርቦ በመቃኘት ያለባቸውን ችግር ተረድቶ ሊደረግላቸው የሚገባ እገዛ ካለም ያንን በማድረግ ወላጆችን ከስቃይ እና ከጭንቀት ማላቀቅ፤ ተማሪዎቹም ተረጋግተው ትምህርታቸውን ሊከታተሉ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል።

ወ/ሮ ስንታየሁ ታደሰ - ከቄራ¾

የመብራት ጉዳይ በሀገራችን ህዝብን ከሚያማርሩ ነገሮች አንዱ ከሆነ ውሎ አድሯል። በመካከሉ በተወሰነ ደረጃ መሻሻል አሳይቶ ትንሽ ፋታ አግኝተን ነበር። ነገር ግን ከሳምንታት በፊት ጀምሮ ተመልሶ መጥፋቱን ቀጥሎበታል። እንዲያውም ይባስ ብሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለዚያውም ለረጅም ጊዜ መጥፋት ጀምሯል። ለኃይል መቋረጡ የተለያዩ ምክንያቶች ቢሰጡም ምክንያቶቹ ግን አሳማኝ አልሆኑም። የኃይል መቋረጡ በግለሰብ ቤት ደረጃ ብቻ የሚታይ ሳይሆን፤ የትላልቅ ፋብሪካዎችን ጭምር ስራ የሚያስፈታ ነው። ስለዚህ ያለውን ችግር በግልፅ ተናግሮ በጋራ መፍትሄ ማፈላለጉ ይመረጣል። በዚህ አይነት ግን ስራችንን መስራት አልቻልንም። ይህ ችግር ዞሮ ዞሮ ከግለሰብ እለታዊ ገቢ አልፎ በሀገር ገቢ ላይም ከፍተኛ ኪሳራን የሚያስከትል መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።

                             

አቶ መሐመድ ሁሴን ከመርካቶ      

 

Page 1 of 24

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1082 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us