ምክንያት የማያልቅበት ሀገር

የሀገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ ጭማሪ ማሳየት ሲጠበቅበት ይልቁንም ከሚገመተው በላይ እየተሸመደመደ መምጣቱን የናንተን ጋዜጣ ጨምሮ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሰሞኑን አጀንዳቸው አድርገውት ሰንብተዋል። አሃዞች እንደሚያመለክቱት ከሆነ በኤክስፖርት ዘርፍ አርኪ እንቅስቃሴ የለም ለማለት ያስደፍራል። ከሁሉም ከሁሉም የሚያስደንቀው ነገር በስምንት አመታት እድሜ ውስጥ ዘርፉ ያሳየው እድገት አንድ ቢሊዮን ዶላር እንኳን የማይሞላ መሆኑ ነው። ይሄ ማለት ሀገሪቱ ምንም አይነት እንቅስቃሴ እያደረገች አይደለችም ማለት ነው። በእርግጠኝነት መናገር የምችለው ነገር ቢኖር በከፍተኛ አለመረጋጋት ውስጥ የሚገኙ ሀገራት እንኳን እንዲህ አይነት ዝቅተኛ ውጤት ማስመዝገብ እንደማያቅታቸው ነው። ሀገራችን ግን በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሆና እንኳን ከሁሉም የመጨረሻ የሆነ አፈፃፀም ነው ያላት።

 

ሀገሪቱ በርካታ ወደ ውጭ ተልከው ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ ምርቶች እያሏት በዚህ ደረጃ ዝቅተኛ አፈፃፀም ማስመዝገቧ መንግስት ምን እየሰራ ነው እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው ያስብላል? ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝ ከሆኑ ነገሮች መካከል አንዱና ዋናው የኤክስፖርት ገቢ እንደመሆኑ መጠን በዘርፉ ጥሩ ስራ መስራት ካልተቻለ ሀገር መንኮታኮቱ አይቀሬ ነው። ዴሞክራሲው ቢስፋፋ፣ ሰላም ቢሰፍን ያለ ኢኮኖሚ እድገት ሀገር ሲያደግ ታይቶ አይታወቅም። የኢኮኖሚ እድገት ሲባል ደግሞ የኤክስፖርት ገቢ ዋናው ነው። ምንም እንኳን ጊዜው ቢረፍድም አሁንም ቢሆን ከዚህ ቀደም የደረሰው አይነት ኪሳራ እንዳይደገም ሰፊ ጥረት ማድረግ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። በተለይ የዘንድሮ የዝናብ ስርጭት አያያዝ ተስፋ ሰጪ በመሆኑ በርትቶ መስራት ያስፈልጋል። ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች፣ ከማከናወን ጎን ለጎን ለኢኮኖሚውም ትኩረት መስጠት ካልተቻለ ውጤቱ ከዚህም የከፋ ሊሆን ይችላል። ያሉትን መልካም አጋጣሚዎች እየተጠቀሙ ማሻሻል እንጂ በየጊዜው የተለያዩ ምክንያቶችን እየዘረዘሩ መቀጠል የሚቻለው እስከ መቼ ድረስ ነው?

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us