ቤቶቹ የት ገቡ?

የመኖሪያ ቤት ጉዳይ መቼም ማለቂያ ያልተገኘለት ጉዳይ ነው። ብዙ ነገር በዚህ ጉዳይ ላይ ቢባልም አንድ ነገር ግን የተዘነጋ ይመስለኛል። የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ለ11ኛ ጊዜ ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ መውጣቱ ይታወሳል። ይህ ዕጣ በሚወጣበት ወቅት አዳዲስ የተሰሩ ቤቶች ለእድለኞች በዕጣ ሲወጡ በዚህ መካከል ግን ከዚህ ቀደም ብሎ ሰዎች በሕገ-ወጥ መንገድ በር ሰብረው ገብተውባቸው ነበር የተባሉ ቤቶች ጉዳይ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቤቶች በሕገ-ወጥ መንገድ ከገቡት ሰዎች ተነጥቀው ለመንግስት ተመልሰው እንደነበረ ቢታወቅም ለተጠቃሚ መድረሳቸው ግን አልተገለፀም። ቤቶቹ ከሕገ-ወጦቹ ከተነጠቁ በዕጣው ውስጥ ተካተው ለተጠቃሚ መተላለፍ ሲገባቸው ምንም የተባለ ነገር የለም። ድሮም ግልፅነት የጐደለው የጋራ መኖሪያ ቤት ጉዳይ ጉዱ እያደር እየወጣ ነው። እነዚህ ቤቶችም ወይ እንደ ብሎኮቹ የገቡበት ጠፍቶም ከሆነ ህዝቡ እንዲያውቀው መደረግ አለበት። የቤቶቹ ብዛት የሚናቅ ካለመሆኑም በላይ ሲኖሩባቸው የነበሩት ሰዎች መሠረተ ልማታቸውን ያሟሉላቸው ናቸው። ስለዚህ እነዚህ ቤቶች ከአዳዲሶቹ ቤቶች ጋር ተደባልቀው ለእድለኛ በዕጣ መቅረብ ነበረባቸው። ነገር ግን እንዲህም እንዲያም ነው ሳይባል ዝም ዝም ተብሎ ተሸፋፍኖ ቀርቷል። ቤቶቹ “ምርጥ ምርጡን ለመንግስት ባለስልጣናት” በሚል መርህ ለመንግስት አካላት ተሰጥተው ከሆነም ከአሳማኝ ምክንያት ጋር ለህዝቡ ግልፅ መደረግ የሚኖርበት ይመስለኛል። ካልሆነ ግን ለቀሪዎቹ ቤቶችስ የሚኖረው መተማመን ምን ያህል ሊሆን ነው? ቤቶቹ ተዘግተው ተቀምጠው ከሆነ አንድም በድጋሚ ለሌላ ሕገ-ወጥ ተግባር ይዳረጋሉ፣ አሊያም የሙሰኞች መፈልፈያ ይሆናሉ የሚል ስጋት አለኝ።

ወ/ሮ ስንታየሁ አለሙ - ከቄራ       

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us