የጣቢያዎቹ እና የቢራዎቹ ጋብቻ

በዓላት በመጡ ቁጥር የተለያዩ የቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ጣቢያዎች ፕሮግራም እየቀረፁ ማስተላለፍ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለመደ የመጣ ነገር ነው። ከዚህ ልማድ ጐን ለጐን ግን በዚህ ፕሮግራም ዙሪያ ያሉ አካላት ፍላጐታቸው እና ዓላማቸው ምንድን ነው? የሚያስብል ጥያቄ የሚያጭር ነገር እየተፈጠረ ነው። የፕሮግራሞቹ ይዘት የተመልካችን የተለያየ የእውቀት ደረጃ ያላገናዘቡ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ስለ ስፖንሰር አድራጊዎች ጥቂት ነገር ማለት ፈለኩኝ። በተለይ በተከታታይ ሁለት ዓመታት እንደተገነዘብኩት ከሆነ ዋናዎቹ የእነዚህ የበዓላት ስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች የቢራ ፋብሪካዎች ናቸው። እኛ ኢትዮጵያውያን ችግራችን የአልኮል መጠጥ ነው እንዴ? በየደቂቃው የቢራ ማስታወቂያ ለዚያውም እያከታተሉ መልቀቅ ትውልዱን ወዴት የሚመራው ይመስለናል? ለይስሙላ “ከ18 ዓመት በታች ላሉ የተከለከለ” ምናምን የምትለዋ ተቀፅላ ጣል እየተደረገች ቢራ መገባበዝ የጉብዝና መለያ፣ የወዳጅነት ገመድ ማጥበቂያ እና ሌሎች መገለጫዎች እንዲሆን ለትውልዱ ሲሰበክ የየጣቢያዎቹ ኃላፊዎች ዝምታ ከምን የመነጨ ነው? ስንት ትውልዱን ሊያንፁ የሚችሉ ዓላማዎችን የሰነቁ አካላት እያሉ በቴሌቪዥን ጣቢያዎቻችን እና በእነዚህ የቢራ ፋብሪካዎች መካከል እንዲህ የጠነከረ ፍቅር መኖር አልነበረበትም። እኔ እንደተረዳሁት በአጠቃላይ የቢራዎቹ ማስታወቂያዎች 18 ዓመት የሞላቸው ወጣቶች ወደ ጉርምስና እድሜ በመሸጋገራቸው ሳይሆን “ለአቅመ ቢራ” በመድረሳቸው እድለኝነት እንዲሰማቸው፤ ከዚህ በታች ያሉት ደግሞ መቼ ለዚህ “ክብር” በቅቼ እንዲሉ ለማጓጓት ታስበው የተሰሩ ናቸው። ይህን አይነቱን ትውልድ ገዳይ ድርጊት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ሊያወግዘው ይገባል። ካልሆነ ግን በራሳችን የቴሌቪዥን ጣቢያ ልጆቻችንን ማበላሸት ይሆናል።

(አለምሸት ዝናቡ - ከመገናኛ) 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us