የግል ት/ቤቶች ጉዳይ

 

የግል ትምህርት ቤቶችን በተመለከተ በተደረገ ፍተሻ አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው የተገኙት ሩብ እንኳን እንዳልደረሱ (24 በመቶ ብቻ መሆናቸውን) የአዲስ አበባ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት እና አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ ሰሞኑን አስታውቋል። በግል ትምህርት ቤቶች ላይ ቅሬታ ሲቀርብ ይሄ የመጀመሪያው አይደለም። ከሚያስከፍሉት ክፍያ ውድነት ጋር ተያይዞም ከዚህ ቀደም ስማቸው በተደጋጋሚ ሲነሳ ነበር። ህዝቡም መንግስትም የአንድ ሰሞን አጀንዳ አድርገው ሲረባረቡበት ነበር። ነገር ግን ወዲያው ተዘነጋ። መንግስት እና ሌላው ማህበረሰብ ቢረሳው እንኳን የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆንን ወላጆች አሁንም ድረስ ዋጋ እየከፈልን ነው። ትምህርት ቤቶቹ በላያችን ላይ እንዲቀልዱብን እያደረገ ያለው ደግሞ መንግስት ነው። እነዚህ ትምህርት ቤቶች ሊተዳደሩበት የሚገባ ጥሩ ህግ አውጥቶ ሕጉን የጣሱት ላይ የማያዳግም እርምጃ ቢወስድ ኖሮ እንዲህ ችግሩ ስር ባልሰደደ ነበር። ይሄን ማድረግ ካቃተው ደግሞ በመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው ትምህርት ጥራት የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ነበረበት። ጥራት ያለው ትምህርት በመንግስት ትምህርት ቤት የሚሰጥ ከሆነ ለምን ከግል ትምህርት ቤቶች ጋር እሰጣ አገባ ውስጥ ይገባል? ማንም ሰው ቢሆን ከተገቢው በላይ ወጪ የማውጣት ሱስ የለበትም። ልጁ የተሻለ ትምህርት እንዲያገኝለት ሲል ብቻ ነው መስዋዕትነት የሚከፍለው። ለወላጅ እና ለሀገር በልጅ ትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ማለት ነገን የተሻለ ዜጋ እና አለምን ለመፍጠር መሰረት መጣል ማለት ነው። ስለዚህ እነዚህ የግል ትምህርት ቤቶች የሚፈለግባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ወገቤን የሚሉ ከሆነ መንግስት ሌላ አማራጭ የማዘጋጀት ኃላፊነት አለበት። ይኸውም ተአምር መፍጠር ሳይሆን በመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው ትምህርት የመርሃ ግብር ማሟያ ሳይሆን የተሻለ ዜጋ መፍጠር የሚያስችል ጥራቱ የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ብቻ ነው።

                              አቶ እስማኤል - ከመገናኛ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us