እንዲህ ነው ትምህርት!

 

ወደ ምርት መስጠት ገብተው የሀገሪቱን የስኳር ምርት እጥረት ያቃልላሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው የስኳር ልማት የግንባታ ስራዎች የውሃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል። ፕሮጀክቶቹ በተለያዩ ምክንያቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ መጠናቀቅ አለመቻላቸው ብቻም ሳይሆን ጭራሹን አለመሳካታቸውን መገመት አያዳግትም። የሚቀርቡት ምክንያቶች ደግሞ አንዱ ወደ ሌላው የሚያንከባልላቸው እና መውደቂያ ባለቤት ያጡ ናቸው። በየጊዜው አንዱ በሌላው ላይ እያላከከ ቀጥተኛ ተጠያቂው ማን እንደሆነ እንኳን መለየት እያቃተን ሰንብተናል። ህዝብ ሙሉ እና በቂ መረጃ ማግኘት እንዳለበት ብንገነዘብም መልስ የሚሰጠን በማጣታችን በዝምታ የሚሆነውን ነገር መጠበቅ ነበር የመረጥነው። ከጥበቃችን በኋላ ግን ያልጠበቅነውን ነገር ነው የሰማነው። ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን የብሔራዊ ጣቢያው (ኢቢሲ) ብቅ ብለው የተናገሩት ነገር “በህልሜ ነው በእውኔ” አሰኝታኛለች። የስኳር ፕሮጀክቶቹ ባይሳኩም ትምህርት ወስደንባቸዋል፤ ተምረንባቸዋል ሲሉ ጥፋቱን እንደትምህርት ወስደውታል። ለመሆኑ እኛ ማን ሆነን ነው ከደሀ ሕዝብ በበግብር መልክ በተሰበሰበ ቢሊዮን ብሮች የምንማረው? ማን እንዳደረገው ነው ይሄን ሁሉ ገንዘብ እየረጨን ለወደፊት ልምድ የምንቀስመው? ኧረ የትኞቹ ሞልቶ የተረፈን ሀብታሞች ሆነን ነው እንዲህ አይነቱን ከሌሎች ሀገራት የተለየ ትምህርት የምንወስደው? ከዚህም በላይ በርካታ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ አስደናቂ ንግግር ነው። ጠ/ሚኒስትሩ እውነት አስበውበትና አምነውበት አይመስለኝም ይሄንን የተናገሩት። ነገርየው ስህተትን ለመቀበል አለመፈለግ ነው ሊሆን የሚችለው። ይሄም ቢሆን አግባብ ባለው መልኩ መሆን አለበት እንጂ እንዲህ አይነቱን የሚያስተዛዝብ ነገርን መነጋገር ለዚያው ከጠ/ሩ አይጠበቅም ነበር። በዚህ አይነት ሌሎች ፕሮጀክቶቻችንንም እያከሸፍን መማር ሊኖርብን ነው። እኛ ተምረን ስለማይበቃን ገና በበርካታ ፕሮጀክቶች አለመሳካት ስንማር የምንኖር ከሆነ የትውልድ እድሜን ልንፈጅ እንችላለን ማለት ነው።

                        ሲሳይ  ንጉሴ - ከቃሊቲ   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us