ሕገ ወጡ ሕጋዊ እንዳይሆን

መንግሥት በአነስተኛ እና መካከለኛ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ሰዎች የመነገጃ ቦታ እንዲያገኙ ለማድረግ በማሰብ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የኮንቴነር ሱቆች በተለምዶ አርከበ ሱቅ የሚባሉትን ገንብቶ በዝቅተኛ ዋጋ እያከራየ ይገኛል። በዚህም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሰዎች በተለያዩ አነስተኛ እና መካከለኛ ንግድ ላይ መሰማራት ችለዋል። ሱቆቹ መሰጠት ላለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በአግባቡ ተሰጥተዋል፣ አልተሰጡም የሚለው አጠራጣሪ እና ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ በመሆኑ እዚህ ጋር ማንሳቱ አስፈላጊ አይመስለኝም። ነገር ግን ሱቆቹን በአንድም በሌላም መንገድ ተረክበው ንግድ እያከናወኑ ያሉ ሰዎች የእድሉ ተጠቃሚ መሆናቸው የማይካድ እውነታ ነው። እነዚህ ሰዎች ግን የተሰጣቸውን እድል ከመጠቀም ጎን ለጎን አንዳንድ የህግ ጥሰቶችን ሲፈፅሙ ይስተዋላል። ልብ ብሎ ለቃኛቸው ሰው በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙት እነዚህ ሱቆች የሚከናወንባቸው የንግድ አይነት ግራ የሚያጋባ ነው። አንዳንድ ቦታ ከምግብ ቤት ጎን ፀጉር ቤት ይከፈታል። አንዳንዶቹ ደግሞ ከመዋቢያ እቃ መሸጫ ቤት አጠገብ ምግብ ቤት ተከፍቶ ንግድ ሲካሄድ ይስተዋላል። እንዲህ አይነቱ ተግባር በየትኛውም ህግ አንጻር ብንመለከተው ተቀባይነት አይኖረውም።

 

ሌላው በእነዚህ ሱቆች ላይ የሚስተዋለው የህግ ጥሰት ሱቆቹ ለንግድ ተብሎ ከተፈቀደላቸው ቦታ በተጨማሪ በእግረኛ መንገድ ላይ ንግዳቸውን ማከናወናቸው ነው። ብዙዎቹን ስንመለከታቸው ከፊት ለፊታቸው በሚገኙ የእግረኛ መንገዶች ላይ እቃ ከማስቀመጥ እና ስኒና ጀበና ዘርግተው ቡና ከማፍላት አልፈው ከሰል አቀጣጥለው ምግብ ያበስላሉ። በዚህም ሳቢያ እግረኞች የእግረኛ መንገድን በመልቀቅ ከተሽከርካሪ ጋር ለመጋፋት ይገደዳሉ። በተጨማሪም አይነ ስውራን እና ሌሎች አካል ጉዳቶች ለማለፍ ሲቸገሩ ይስተዋላሉ። የሰው ልጅ በባህሪው ራሱን በራሱ አስተምሮ ከመለወጥ ይልቅ የሚያስገድደው ሰው (ህግን) ይፈልጋልና እንዲህ አይነት ተግባር በሚፈጽሙት ላይም ተግባራዊ የሚሆን ሕግ ያስፈልጋል። ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ዞር ብሎ ሊመለከታቸው እና ከጥፋታቸው እንዲታረሙ ሊያደርጋቸው ይገባል። ይሄ ካልሆነ ግን ሕገወጥ ተግባራቸውን ህጋዊ መልክ አስይዘው ላለመቀጠላቸውና ነገም ሌላ የህግ ጥሰት እንደማይፈፅሙ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።

                  ወ/ሮ ሰናይት - ከ6 ኪሎ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us